Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክሕገ መንግሥትን ሕገ መንግሥታዊነት ሲርቀው

ሕገ መንግሥትን ሕገ መንግሥታዊነት ሲርቀው

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ሕገ መንግሥታዊነት በብዙ አገሮች አሁንም አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተቱት ካሉት ምክንያቶች መካከል የቀለም አብዮት፤ ከቱኒዚያ የጀመረው የዓረብ የፀደይ አብዮት፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎችና ለውጦች በሥልጣን ላይ የሚገኙ ፓርቲዎች ከሕገ መንግሥት ይልቅ ለፓርቲያቸው ታማኝ መሆን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከሰሐራ በታች ባሉት የአፍሪካ አገሮች ሦስተኛውና አራተኛው ምክንያቶች ይጎላሉ፡፡ አንዳንዶቹ አድራጎቶች ሕገ መንግሥታዊ ቢሆኑም ቀሪዎቹ ደግሞ አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥታዊ ቢሆኑም ሕገ መንግሥታዊነት የጎደላቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የሚቃረኑም አሉ፡፡ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ባይሆኑም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ብሎም ሕገ መንግሥታዊነታቸው ላይ ቢሆን ብዙም ጥያቄ የማይነሳባቸው አሉ፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓቢይ ትኩረት ሕገ መንግሥታዊነት ምን እንደሆነ መዳሰስ ሲሆን፣ አስቀድሜ ስለ ሕገ መንግሥት ምንነትና ፋይዳ ምጥን ቅኝት በማድረግ የሁለቱን ግንኙነት አሳያለሁ፡፡ በመቀጠልም ሕገ መንግሥት እያለ ተከብሮም ሥራ ላይ እየዋለ ሕገ መንግሥታዊነት የማይኖርበትን ሁኔታዎች አቀርባለሁ፡፡ በተጨማሪም ሕገ መንግሥት ሳይከበር ወይንም ተጥሶም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ የሚሆኑ አድራጎቶችን አሳያለሁ፡፡

ሕገ መንግሥት ምንነት

ሕገ መንግሥት ስንል ምክንያታዊ ከሆኑ መርሆች የሚመነጩ ለሕዝብ ጥቅም የሚበጁ ደንቦች፣ ልማዶችና ተቋማትን ያካተተ የአንድ አገርን ጥቅል ሥርዓት የሚያስቀምጥ ብሎም ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር ትዳሩን በዚሁ መልክ ለማድረግ የተስማማበት ሕግ ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ ድንበሯ በታወቀ አገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ከመንግሥት ጋር የተዋዋሉት ማኅበራዊ ኪዳን ነው፡፡ ተዋዋይ ወገኖቹ በአንድ በኩል መንግሥት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዜጎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ሁለቱም የራሳቸው የሆነ ተነጻጻሪ ግዴታዎች አሉባቸው፡፡ የፖለቲካ ፈላስፎች የሕገ መንግሥትን  ማኅበራዊ ኪዳንነት (ውልነት) ይቀበሉና ልዩነታቸው የሚመጣው የተዋዋይ ወገኖቹ ተነጻጻሪ መብትና ግዴታዎቻቸው ላይ ነው፡፡

ሕገ መንግሥት የአንድን አገር ማንነትም ይወስናል፡፡ ድንበሯን ያስቀምጣል፣ ግቧን ይለያል፣ ሰብዓዊ መብቶችን ያካትታል፣ ሥልጣን እንደምን እንደሚገኝ ይደነግጋል፡፡ ግልጽ ለማድረግ ኢትዮጵያ ሲባል የት እንደምትገኝ ማለትም ማን እንደሚያዋስናት፣ ምን ዓይነት መንግሥት እንዳላት፣ ሕዝቦቿ ያላቸው መብቶችና ከመሳሰሉት ሁኔታዎች ተነጥላ ልትሳል አትችልም፡፡ ስለሆነም የአገሪቷን ማንነት የሚገልጽ ሰነድ ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበረችው ኢትዮጵያ በደርግ ከነበረችው ትለያለች፤ በደርግ የነበረችው ደግሞ ከአሁኗ ትለያለች፡፡ በእነዚህ ዘመናት ኢትዮጵያን እንደ አገር የሚለይዋትም የሚያሳውቋትም ሁኔታዎች ይለያያሉ፡፡ በዋናነት ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተመሥርቶ የመጣ ልዩነት ነው፡፡

 

ሕገ መንግሥት አንድም ከላይ የተገለጹትን መርሆች፣ ድንጋጌዎች፣ መብቶች፣ግዴታዎች ወዘተ. የያዘ ሰነድ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሰነድነቱ የሚያልፉ ማለትም ሰነዱ ባይኖርም እንኳን የማይቀሩ አገራዊ ግቦችንም ይይዛል፡፡ የሕዝቡም የመንግሥትም ጥረትና ጉዞ ያንን ግብ ለማሳካት መሆን አለበት፡፡ ዜጎችም ለዚያ ግብ የሚሰጡት ዋጋ ከፍ ያለ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥታዊ ግብ እንከን የለሽ ኅብረት መፍጠር፣ ፍትሕ ማስፈን፣ አገራዊ ፀጥታን ማስፈን ወዘተ. ናቸው፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዋና ግብ ‹‹አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር›› ሆኖ ይኸንን ግብ ለማሳካት የሚያግዙ ሌሎች ንዑሳን ግቦች አሉት፡፡ በቅድሚያ ሕዝቡ  ይኼንን ግብ የእኔ ነው ብሎ ሊቀበለው ይገባል፡፡ ከተቀበለው በኋላ ስኬቱ የሚገመገመው ግቡን ለማሳካት በሚደረገው ጥረትና ውጤት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሕገ መንግሥታዊ ግባችን ምን ያህል ሕዝባዊ ነው? እሱንስ ለማሳካት የተጓዝንባቸው መንገዶች የት አደረሱን? የሚለው ፍተሻ ያስፈልገዋል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥት ስንል ከሰነድነቱ የዘለሉ ዜጎች ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጧቸው ዕሴቶችን የሚያመለክት ነው፡፡

የሕገ መንግሥት ፋይዳዎች

የሕገ መንግሥት ዓቢይ ፋይዳው የመንግሥትን አመል መግራት፣ ሥልጣኑን መገደብ ብሎም የዜጎችን ፍላጎቶች ዕውቅና በመስጠት ጥበቃ ማድረጊያ ሥልቶችን ማበጀት ነው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ገና ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ጀምስ ማድሰን፣አሌክሳንደር ሐሚልተንና ጆን ጀይ የተባሉ ምሁራን ከጻፏቸው ውስጥ ፌዴራሊስት ቁጥር 52 ላይ አንድ ትልቅ ቁም ነገር ተካቷል፡፡ ይኸውም ሕገ መንግሥት በመጀመሪያ መንግሥት ተገዥዎችን (ሕዝቡን) ሊቆጣጠር የሚያስችለው ሕጋዊ አቅም እንዲኖረው ማስቻል ሲሆን፣ ቀጥሎ የሚመጣው ደግሞ መንግሥት ራሱን የሚቆጣጠርበት ሥልት ማበጀቱና መቻሉ ነው፡፡ ይኸንን ቁም ነገር ለማሳካትም እጅግ አስቸጋሪ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ አሁንም አገሮችን ያስቸገረው መንግሥት ሕዝብን እንዳሻው ሲቆጣጠር፣ ሕዝብ በተራው መንግሥትን የሚቆጣጠርበት ሥርዓት አለመኖር አሊያም መድከምና ውጤታማ አለመሆናቸው ነው፡፡ እንዲህ እንዲሆን የሚሠራው ደግሞ አንዱ ተዋዋይ የሆነው ይኼው መንግሥት ነው፡፡ አሁንም ኢትዮጵያን ያስቸገራት መንግሥትነትን በመዳፉ ያደረገው ገዥው ፓርቲ ራሱን የሚቆጣጠርበት ሥልት አለመሥራቱ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥትን የሥልጣን ሥዕልና ንድፍ ያስቀምጣል፣ ተቋማትንም ያቋቁማል፡፡ ይሄንን አምባገነን መንግሥታትም ያደርጉታል፡፡ በመሆኑም ዴሞክራሲያዊነትን አያሳይም፡፡ ዴሞክራሲያዊነትን ለማስፈን ከመጀመሪያው ፋይዳ ጋር መቀዳጀት አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊነትን ለማምጣት ከሥነ ሥርዓታዊ ይልቅ  መሠረታዊ ለሆኑት እሴቶች ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡ ለምሳሌ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ከማድረግ በዘለለ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመደራጀት መብትን አለማጣበብ፣ የሕግ የበላይነትን ሥር የሰደደ ባህል እንዲሆን መሥራት፣ የፍርድ ቤቶች ነፃነትና ገለልተኛነትን ማረጋገጥና የመሳሰሉት መሠረታዊ የዴሞክራሲ ባህርያት ናቸው፡፡

ሌላው የሕገ መንግሥት ዓላማ የታወቀና የተረጋጋ ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡ አንድ ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደር የዴሞክራሲዊ እሴቶችና የሕዝቡ ፍላጎት ነፀብራቅ ከሆነ፣ ተቀባይነቱ ከጨመረና ሕዝቡ የእኔነት ስሜት ካለው የተረጋጋ ሥርዓት መፍጠር አይገደውም፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት ማለት

ሕገ መንግሥታዊነት በአጭሩ የመንግሥት ሥልጣን ሊገደብ መቻሉን፣ ሊገደብም እንደሚገባው የሚያሳይ ሲሆን፣ ሥልቶቹንም ጭምር የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ስለሆነም ዋናው ነጥቡ ያለው የሥልጣን ገደብ ላይ ነው፡፡

ለላዕላይ ሕጎች የመገዛት ቁርጠኝነት አንዱ የሕገ መንግሥታዊነት ክፍል ነው፡፡ መንበረ ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ሰዎች ከሕግ በታች መሆናቸውን ከልብ በማመን ለወጡት ሕጎች ተግባራዊነት በቁርጠኝነት መሥራትን ይጠይቃል፡፡ እንደ እውቁ አሜሪካዊ የፖለቲካ ፈላስፋ፣ ጆን ራውልስ አመለካከት ‹‹ሕጎች ሲወጡ ሰውንም ድርጅትንም ታሳቢ ያደረጉ መሆን የለባቸውም፡፡ የሕግ አውጭው የመንግሥት አካል ብሔርን፣ ፓርቲን፣ሃይማኖት፣ ጾታን ወዘተ. ከሰው በመነጠል ሁሉንም እኩል አድርጎ በማየት ነው ሕግ መውጣት ያለበት፤›› ይላል፡፡ ይህ ሁኔታ ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥት ሲረቀቅ መተግበር አለበት፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን ወሰን ሲታለም ሕገ መንግሥት አርቃቂዎችና አጽዳቂዎች ሥራ ላይ ሲውል ሊያገኙት የሚችሉት ጥቅም ማሰብ የለባቸውም፡፡ ሥልጣን ሊይዙ የሚችሉ አካላትንም ከግምት ማውጣት አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት በዚህ ሁኔታ አስቀድሞ የተተለመ የሥልጣን ወሰንና ሥርዓት እንዲኖር ታሳቢ ያደርጋል፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት የሚያመለክተው በሕግ አውጭው፣ በሕግ አስፈጻሚውና በሕግ ተርጓሚው መካከል የሥልጣን ክፍፍል መኖርን፣ የሕግ ተርጓሚ ነፃነት፣ በወንጀል የተከሰሱ ሰዎችን በተመለከተ ፍትሐዊና ሕጋዊ ሥርዓትን መከተል፣ የግለሰቦች መብት መከበርና የመሳሰሉት ሕገ መንግሥታዊ ሒደቶችና ሥነ ሥርዓቶችን ማስፈኛ ሥልትን መሆኑን ነው፡፡

የሕገ መንግሥታዊነት አላባውያን

ሕገ መንግሥታዊነት እንደ ጽንሰ ሐሳብም ይሁን እንደ ፖለቲካዊ ንድፈ ሐሳብ የሚያሟላቸው አላባውያን አሉት፡፡ ከእነዚህ መካከል አራቱን ብቻ በአጭሩ እናያለን፡፡

በአንዲት አገር ውስጥ ሕገ መንግሥታዊነት አለ ወይንም የለም ለማለት የመጀመሪያው ነጥብ የሕግ የበላይነት መሥፈኑን ወይንም ያለበትን ደረጃ የሚመለከት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ባልሰፈነበት ወይንም የገዥዎች ፍላጎት በነገሠበት ሥርዓት አልበኝነት በሰረፀበት ሁኔታ ሕገ መንግሥታዊነት አይኖርም፡፡

ሁለተኛው ነጥብ ሕገ መንግሥት፣ ከሁሉም ሕጎች የላቀ ቦታ መያዝን፣ በውስጡ የተካተቱት ጉዳዮችም እንዲሁ የላቀ ዋጋ ያላቸው መሆኑን ይመለከታል፡፡ ሌሎች ደግሞ ከዚያ በታች እንደሆኑ መረዳትና ዋና ግባቸውን ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱትን ለማሳካት እንደሆነ አመኔታ መኖርንና በተግባር የሚፈጸመውም ይኼው መሆንን ይጠይቃል፡፡

ሦስተኛው ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ግቦችንና ድንጋጌዎችን የሚያስፈጽሙ ተቋማት የመኖራቸው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም የሥልጣንን ክፍፍል ያለው መንግሥት ነፃ የዳኝነት ተቋም የሰብዓዊ መብትን ለማስጠበቅ የሚረዱ እንደ ፖሊስና ዓቃቤ ሕግ ያሉ አካላት መኖራቸውን ታሳቢ ያደርጋል፡፡

የመጨረሻው ነጥብ ለሰብዓዊ መብት ከሚሰጠው ዕውቅናና ጥበቃ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እነዚህ መብቶች በማይከበሩባቸው አገሮች ሕገ መንግሥታዊነት ሰፍኗል ማለት አይቻልም፡፡ እነዚህ ከላይ የተገለጹት አራቱ ጉዳዮች የሕገ መንግሥታዊነትን ህልውና ከሚያሳዩት መሥፈርቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የአሜሪካ ሕገ መንግሥታዊ አባት ከሚባሉት አንዱ የሆነው ሐሚልተን ደግሞ በዋናነት ሕገ መንግሥታዊነት ስንል ‹‹ሥርዓት ያለውና ሥርዓቱን ብቻ ጠብቆ በመጓዝ የሚያስተዳድር መንግሥት ማቆምን፣ የሥልጣን ዱካውን ለይቶ ማስፈርንና ይኸን ሥርዓት ለሕዝብ ታማኝ ማድረግ ነው፤›› ይላል፡፡

የሕገ መንግሥታዊነት ዓይነቶች

በዓለማችን ላይ አንድ ዓይነት ሕገ መንግሥታት የሉም፡፡ እንደ አገሮቹ ብዛት ይለያያሉ፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት ግን የሕገ መንግሥትን ያኸል ብዛት የለውም፡፡ ይሁን እንጂ እሱም ቢሆን የራሱ የሆኑ ልዩነቶች አሉት፡፡ ለአብነት የሚከተሉትን እንይ፡፡ አንዳንድ አገሮች ሕገ መንግሥታዊነትን የሚመዝኑት በዚያች አገር ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች ባላቸው እሴት ላይ ተመሥርተው ነው፡፡ ሲወርድ ሲዋረድ ይዘውት የመጡት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ባህላዊ እሴቶችን መነሻ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የተለዩ መለኪያዎች ሊኖሩት ይችላል፡፡

ሌላው ደግሞ በርካታ አገሮች የሚያስተሳስር የሕገ መንግሥታዊነት እሳቤም አለ፡፡ ለምሳሌ ኮንትኔታል (ከታላቋ ብርቴን ውጭ ያሉ የአውሮፓ አገሮች) በዚህ ረገድ ብዙ ነገር ይጋራሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ሁሉንም ሰው ልጆች የሚያስተሳስሩ በሕገ ልቦና የሚታወቁ መርሆችም ስላሉ ሁሉን አቀፍ ባህርያትም አሉት፡፡ ይኸ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ በሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች አማካይነት የሚለኩም አሉ፡፡ በርካታ የዓረብ አገሮች ለዚህ አስረጂ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በተለየ ሁኔታ ደግሞ በአመክንዮ ላይ የተመሠረቱ መሥፈርቶችንም ሲወሰድ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይኼ ርእዮተ ዓለማዊም ሊሆን ይችላል፡፡ ሶሻሊዝም፣ ካፒታሊዝም ወዘተ. ሕገ መንግሥታዊነት ላይ ያላቸው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ከላይ የተገለጹት ሁኔታዎች ዓይነቱን ይወስኑታል፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት የሕገ መንግሥት ቅርጹ፣ ይዘቱም፣ ቅቡልነቱም ይፈተሽበታል፣ ይገመገምበታል፡፡ ወይንም መፈተሻና መገምገሚያ መሥፈርትም በመሆን ያገለግላል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ዓይነት ያሳያል፡፡   

ሕገ መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ቅቡል መሆንን ይሻል፡፡ ይኸንን የቅቡልነት ምርኩዝ ካጣ ወይንም ቀድሞውንም ከሌለው በመንግሥት (በገዥው) እና በሕዝብ (በተገዥው) መካከል ቅራኔ መኖሩ ስለማይቀር ሕገ መንግሥቱ የይስሙላ ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ በውስጡ የተካተቱት መርሆች፣ ድንጋጌዎች፣ አስተዳደራዊ መዋቅሮችና ሌሎችም ጉዳዮች ተፈጻሚ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ ውሎ አድሮም በገቢር እየተዘነጉ ስለሚሄዱ የመንግሥትም ይሁን የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ተቀባይነት ተንኖ ያልቃል፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ በየአገሮቹ የወጡ ሕገ መንግሥቶች ማክበር ወይንም ማስፈጸም ብቻ የሕገ መንግሥታዊነትን መኖርን አያሳይም፡፡ አሁን አሁን ሉላዊ (ግሎባል) ሕገ መንግሥታዊነት የሚለው ጽንሰ ሐሳብም በዓለም አቀፍ ሕግ እየዳበረ መጥቷል፡፡ እንግዲህ ዓለም አቀፋዊ ሕገ መንግሥት የሚባል ሰነድም ሳይኖር ሉላዊ ሕገ መንግሥታዊነት ያደገበት፣ ከሕገ መንግሥት የዘለለ፣ በዋናነትም ጽንሰ ሐሳብ ስለሆነ ነው ማለት ነው፡፡

ሕገ መንግሥታዊነት በኢትዮጵያ

ይኸ ጽሑፍ በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥታዊነትን ታሪክ በጥልቀት የመዳሰስ ዓላማ የለውም፡፡ ይልቁንም የመንግሥትን የሥልጣን ገደብ በተመለከተ የመጀመሪያው ጨምሮ ባሉት አራት ሕገ መንግሥት ውስጥ ምን እንደሚመስል ጥቂት ነጥቦችን የማንሳት ዓላማ ነው ያለው፡፡ ከ1923 ዓ.ም. በፊት የሥልጣን ምንጩ በዋናነት ይወሰን የነበረው ባልተጻፈው የመሳፍንት ዘር ሀረግን በመከተልና ክብረ ነገሥት ላይ ባለው የሰለሞናዊ ሥርዓት መሠረት ነበር፡፡ በዚህ ዓመት የወጣው ሕገ መንግሥት የባላባቱን ሥልጣን የገፈፈ ነው፡፡ ባላባቱ በግዛቱ ውስጥ ለሚኖረው ጉዳይ ሕግ አውጪ ነው፡፡ አስተዳዳሪ ነው፡፡ ዳኛም ነው፡፡ የራሱ ወታደርም አለው፡፡ እርሱም በተራው ለንጉሠ ነገሥቱ ይገብራል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ያመጣው ትልቅ ለውጥ ቢኖር ሕግ ማውጣትን፣ ዳኝነትንና ወታደርን በአገር ደረጃ እንዲቋቋም ማስቻሉ ነው፡፡

ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ በመሳፍንቱ (በዘር ባላባት የነበሩት እነ ራስ ካሳ ኃይሉ) እና በመኳንንቱ (በሹመት እንጂ በዘር ባላባት ያልሆኑት እንደ በጅሮንድ ተክለሃዋርያት ያሉት) መካከል የነበረው ክርክር የሚያሳየው በመሳፍንቱ ሥር የሚገኙና የሚተዳደሩ ማንም ጭሰኛ ወይንም ተራ ሰው ሁሉ በምርጫ የሕግ መመርያ አባል በመሆን መሳፍንቱንም ጭምር የሚገዛ ሕግ የማውጣት ሥልጣን መሰጠታቸውን አምርረው መቃወማቸውን ነው፡፡ የላይኛው ምክር ቤት ማለትም የሕግ መወሰኛው የመሳፍንቱ ብቻ በመሆኑ፣ የሕግ መምርያው የሚያወጣቸው ሕጎችም በንጉሠ ነገሥቱ መጽደቅ ስለሚገባቸው የመሳፍንቱን ጥቅም የሚጎዳ ነገር ፈጽሞ እንደማይደረግ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር በመስማማታቸው ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ ሕገ መንግሥት ዋና ግቡ የባላባቱን ሥልጣን መገደብ ነበር፡፡ ከባላባቱ የተነጠቀውን ሥልጣን አስቀድሞ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ከዚያም ቀስ በቀስ ወደ ሕዝቡ ማምጣት ነበር፡፡ የ1948ቱ ሕገ መንግሥትና በ1966 የነበረው ረቂቅ የሚያሳየው ይኼንኑ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የሕግ የበላይነት፣ የሥልጣን ክፍፍል፣ የሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም ነፃ ዳኝነት እያደጉ  በመምጣታቸው ሕገ መንግሥታዊነትም በትይዩ እየተሻሻለ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ ይህም ቢሆን ከነባራዊው ሁኔታ አኳያ እንጂ በሕገ መንግሥታዊነት አላባውያን ከለካነው የሚቀሩት ነገሮች ብዙ ናቸው፡፡ በለውጡ ዘገምተኛነት የሥርዓቱ ቅቡልነት በማለቁ አብዮት ተከናወነ፡፡

የደርግ ዘመንን ስንመለከት እስከ 1979 ዓ.ም. በጠቅላላው የወታደራዊ አመራርና የወታደር የበላይነት የሰፈነበት ስለነበር ለወግም አይመች፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከጸደቀም በኋላ ሕገ መንግሥታዊነት ለመለካት በሥራ ላይ የቆየበት ጊዜ አጭር ስለነበር በተግባር እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ አልነበረም፡፡

ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ዓመታት በቻርተር ከዚያም በሕገ መንግሥት መተዳደራችንን ቀጥለናል፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት የማስፈን ሒደቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለማወቅ አንድ ምሳሌ ማየቱ በቂ ይመስለኛል፡፡ የኢሕአዴግ አመራሮች ሕዝቡን ስለበደልን ራሳችን ጥልቅ ተሃድሶ ማድረግ አለብን ማለታቸው አንድ ማሳያ ነው፡፡ የችግሮቹ ሁሉ ምንጮች የኢሕአዴግ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ አለመሆንና ብሎም ሕገ መንግሥታዊነትን ማስፈን አለመቻሉ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ሕገ መንግሥትን አላግባብ መጠቀምና የተዘወተሩ ሥልቶቹ

በሕገ መንግሥታዊ ንድፈ ሐሳብ ውስጥ ጎላ ብለው ከሚታዩት ጥያቄዎች አንዱ ሕገ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከሥጋትና ከአደጋ እንዴት ሊታደግ ይችላል? የሚለው ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተለያዩ ምክንያቶችና አጋጣሚዎች ሥጋትና አደጋ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ሕገ መንግሥት ደግሞ እንደ አንድ ጥሩ ዕቅድ አስቀድሞ ሥጋቶችን በመገመት መፍትሔዎችን ሊዘረጋ ይገባል፡፡ የጀርመንና የቱርክ ሕገ መንግሥቶች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ሒትለርና ፓርቲው በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን ያዙ፡፡ ከዚያም የሆነውን ሁሉ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ ጀርመን ከናዚ አረመኔያዊ ድርጊት በመማር በሕገ መንግሥቷ የተለያዩ መፍትሔ አስቀመጠች፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን አደጋ ላይ የሚጥል ፓርቲ ሥልጣን መያዝ እንዳይችል የሚያደርጉ አንቀጾች በሕገ መንግሥቱ ተካተቱ፡፡ እነዚህ አንቀጾች ደግሞ ዝንተ ዓለማዊ እንዲሆኑ በማሰብ መቼም ቢሆን መሻሻል እንዳይችሉ ወሰነች፡፡ ይኸንን የሚያስፈጽም ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤትም አቋቋመች፡፡

ለሕገ መንግሥታዊነት ታላቅ እንቅፋት በመሆን ካስቸገሩት አድራጎት መካከል  ሕገ መንግሥትን ማሻሻልና መለወጥ ዋናዎቹ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ መንግሥታዊ ሥርዓታቸው ፕሬዚዳንታዊ በሆኑ አገሮች የበለጠ ተለምዷል፡፡ በፕሬዚዳንት የሚተዳደሩ አገሮች የሥልጣን ዘመናቸውን አስቀድመው በሕገ መንግሥት ይወስናሉ፡፡ ይሁን እንጂ የመንበረ ፕሬዚዳንት ዘመኑ ሊያልቅ ሲል ሕገ መንግሥት ማሻሻል ትዝ ይላቸዋል፡፡ በተለይ ከሰሐራ በታች ያሉ አፍሪካ አገሮችና በላቲን አሜሪካ ልማድነቱ አልቀረም፡፡ በቅርቡ እንኳን በቡሩንዲ የሆነው ይኼው ነው፡፡ ሩዋንዳም ተመሳሳይ ጥያቄ መነሳቱ ይታወቃል፡፡ ሕገ መንግሥትን ለግል ጥቅም በማዋል ለሕገ መንግሥታዊነትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዳተኛ ከመሆን የሚመነጭ ነው፡፡

በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጠውን አሠራር ተከትሎ የሚከናወን ማሻሻያና ለውጥ ሕገ መንግሥታዊ ነው ብንልም በዋናነት ዴሞክራሲን ማዳከሚያ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ተግባር ሕገ መንግሥታዊ ቢሆንም ፀረ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ስለሆነም ሕገ መንግሥታዊ የሆነ ሁሉ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑን ያጤንዋል፡፡

በተወሰኑ አገሮች የሚገኙ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንታዊ የሥልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ሕገ መንግሥትን ማሻሻል ኢ ሕገ መንግሥታዊ አድራጎት እንደሆነ በመቁጠር እንዳይሻሻል ወስነዋል፡፡

አፍሪካንና ሌሎች ታዳጊ ዴሞክራሲዎችን ሕገ መንግሥታዊነት በመገዳደር ላይ የሚገኘው የፓርቲዎች አምባገነንነት ነው፡፡ ገዥ ፓርቲዎች ምርጫ ከመከናወኑ በፊት ሕግ በማውጣትና የመንግሥት ተቋማትን በመጠቀም ተቃዋሚ ፓርዎችን ያሳድዳሉ፣ ይከፋፍላሉ፣ በተለያዩ ወንጀሎች ይከስሳሉ፣ መራጩም ተቃዋሚን እንዳይመርጡ ያስፈራራሉ፡፡ አዝማሚያውን በመመልከት የምርጫ ውጤቱንም ሊያጭበረብሩ ይችላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በፓርቲ ደረጃ የሚፈጸም ሕገ ወጥ ድርጊት ብሎም ሕገ መንግሥታዊነትን እንዳይሠርጽ የሚያደርግ እንቅፋት ነው፡፡ ለፓርቲ አምባገነንነት ምቹ ከመሆናቸው ባለፈው የዳኝነትና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን ፓርቲው እንዳሻው ስለሚያዛቸው መላው ሥርዓቱ ይነቅዛል፡፡ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና በፓርቲው መካከል ልዩነት እንዳይኖርም ያደርጋል፡፡ ውሎ አድሮም ሕዝባዊ አመጽ እንዲነሳ ማበረታቻ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ መፍትሔው ሕገ መንግሥታዊነትን በማስፈን ፓርቲውንና የፓርቲው አይነኬ ሰዎችን ከሕገ መንግሥት በታች እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡ 

የእኛው አገርም ችግርም  ይኼው ነው፡፡ ለአብነት ፓርላማው የባለሥልጣናት ሀብት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን የሚያስገድድ ሕግ ቢያወጣም ባለሥልጣናቱን ከሕግ በታች ማድረግ ስላልተቻለ ይኼው እስካሁን ድረስ ‘ወፍ የለም’፡፡ ተቃዋሚዎችንና ግለሰቦችን የሚመለከት ሕግ ቢሆን ኖሮ ግን በማግሥቱ ወይንም እንዳስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕዝቡ ስለመታወጁ ከመስማቱ በፊትም ጀምሮ ቢሆን ሥራ ላይ ይውል ነበር፡፡ በጥልቀት መታደስ ከሕግ በታች መሆንንም ይጨምርና የባለሥልጣኖቻችንን ሀብትም እንወቀው፡፡ ወይንም ሕጉ ይሻር!!! ምክንያቱም ሕግን ማክበር ከዜጎችም በላይ የሚመለከተው መሪዎችን ስለሆነ፡፡ ሕገ መንግሥታዊነት ትመጣልን ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡ የሕገ መንግሥት መኖር ብቻውን ሕገ መንግሥታዊነት ለመኖሩ ምስክር አይደለምና!   

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...