Thursday, June 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትሚዲያው ከዚህ ወቅት የበለጠ ግዳጅ የለውም

ሚዲያው ከዚህ ወቅት የበለጠ ግዳጅ የለውም

ቀን:

በገነት አለሙ

አገራችን ኢትዮጵያ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ናት፡፡ የምንገኝበት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በመሠረቱ ፀንቶ የሚቆየው ለስድስት ወርሃት ሲሆን፣ ይኼ የስድስት ወርሃት የጊዚ ገደብ ከዚያም በፊት ቀሪ ሊደረግ ሊያጥር ወይም ከስድስት ወርሃት በኋላ የጊዜ ገደቡ በየአራት ወሩ እንደገና እየታደሰ ሊቀጥል ይችላል፡፡ አንድ አገር ወይም የአገር ክፍል አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚባለው በዚያ አገር ወይም የአገር ክፍል ውስጥ ልዩና አፋጣኝ፣ አጣዳፊ፣ አስቸኳይ ምላሽና መፍትሔ የሚያስፈልገው ድንገተኛና አስገዳጅ ሁኔታ ሲፈጠር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግ ተደንግጓል ወይም ታውጇል ማለት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚያ ሕግ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ የአስገዳጅ ጊዜ ሁኔታ፣ የአደጋ ጊዜ ሁኔታ መኖሩ ታውጇል፡፡ ታውቋል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የተፈጠረው የአስቸኳይ ወይም የአደጋ ጊዜ ሁኔታ የሚፈልገውና የግድ የሚያደርገው፣ ተጨማሪና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ግዳጅና ሥልጣን ለመንግሥት ተሰጥቷል ማለት ነው፡፡

አገራችን ለአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አስተዳደርና ሕግ በጭራሽ እንግዳ አይደለችም፡፡ አሁን በ2009 ዓ.ም መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ተፈጻሚነቱን የጀመረው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግ ያልተጠበቀና ከ28 ዓመታት በኋላ የተወሰደ የመጀመሪያው ዕርምጃ ቢሆንም፣ እንዲሁም የሕጉ ተፈጻሚነት መላውን ኢትዮጵያን ቢሸፍንም ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜዎች የተወሰዱ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃዎች ታውቃለች፡፡ በ1956 ዓ.ም በሶማሊያ መንግሥት አዋሳኝ በሚገኙት በኢትዮጵያ ክፍለ አገሮች ውስጥ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግና አስተዳደር ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት አንዳንድ ሥፍራዎች ከ1963 ዓ.ም. ጀምሮ በየጊዜው በ1969 ዓ.ም ጭምር እየታደሰ ለረዥም ጊዜ የቆየ ተመሳሳይ ሕግና አስተዳደር ውስጥ ነበር፡፡ በ1980 ዓ.ም በኤርትራና በትግራይ ላይ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር እስከነ ጦርነቱ በሕግ የቀጠለው ኢሕአዴግ በአሸናፊነት አዲስ አበባ እስከገባ 1983 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡ በ1968 ዓ.ም. ውስጥም ከመስከረም እስከ ኅዳር 1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማና በአካባቢው ላይ የፀና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ወጥቶ ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕጎች ሁሉ የተከለከሉና ሕገወጥ የተደረጉ ተግባሮችን የተከለከሉ ሥፍዎችን፣ በተከለከሉ ሥፍራዎችና ጊዜ መዘዋወርን ስለሚወስኑ የሕግ አስከባሪ ወይም የጦርና የፖሊስ ሠራዊት ባልደረቦች በኃይል ለመጠቀም ስለሚችሉበት ሁኔታ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመፈተሽ፣ ለማሰር ይዞ ለማቆየት ስላላቸው ሥልጣን ስለሚደነግጉ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ተፈጻሚነታቸው የታገዱ ሕጎችን ስለሚወስኑ አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መኖር ድርብ ድርብርብ ሥጋት አለው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥቶች ሁሉ የመንግሥትን አስቸኳይ  ጊዜ ሁኔታ አስተዳደር ግዳጅና ሥልጣን ማወቃቸውና መደንገጋቸው እውነት ቢሆንም፣ አሁን ሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት የመሰለ የተፍታታና ስፋት ያለው መጠበቂያም የተበጀለት አልነበረንም፡፡

ይኼ ሕገ መንግሥት አገር አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አስተዳደር ውስጥ የምትገባው የውጭ ወረራ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ወይም የሕዝብን ጤና አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲኖር ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥምና ይኼንንም በተለምዶው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መግባታችንም ለመንግሥት የሚሰጠው ሥልጣን ለዚህ ‹‹….ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘው ደረጃ›› በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉትን መሠረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችልም ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 13 ውስጥ ተጨማሪ መጠበቂያና ዋስትና አለው፡፡ በመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ውስጥ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የአስቸኳይ መብቶች ሕግጋት…. ስምምነቶችና… ሰነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ ይለናል፡፡

ስለዚህም በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ሆነን በሕገ መንግሥቱ ውስጥም መሽገን ኢትዮጵያን ያጋጠማትና ለአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው መታወጅ ምክንያት የሆነው ችግር እውን ይኼንን አስገዳጅ ድንገተኛና የአደጋ ጊዜ ሁኔታ ፈጥሯል ወይ? እውን በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል አደጋ አጋጥሞናል ወይ? ማለት ድረስ የ ‹‹ደፋር›› ጥያቄ ማንሳት መብታችን ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕገ ለመንግሥት ለመንግሥት የሥልጣን አካላት፣ ለሕግና ለፀጥታ አስከባሪ አባላት የሰጠው የአስገዳጅ ድንገተኛ የአደጋ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣንስ ከመሠረታዊ መብቶችና ነፃነታችን ጋር ያጣጥማል ወይ? እነሱን አያጋጭም ወይ? ብሎ መጠየቅም በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ያለ መብታችን ነው፡፡

አሁንም እዚያው በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ውስጥ ሆነን በዋናው ሕግ ተፈጻሚነታቸው ስለታገዱ ሕጎች (አንቀጽ 4) በዋናው ሕግ ሥር በወጣው መመርያ ውስጥ ስለተዘረዘሩት በማናቸውም የአገሪቱ ክፍሎች የተከለከሉ ተግባራት መጠየቅና መጠያየቅን፤ መናገርና መነጋገርን እርም ወይም ነውር የሚያደርግ ምንም ነገር የለብንም ነበር፡፡ ይኼ በተጻፈ ሕግ መሠረት ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ግን ፍርኃት  የረበበት ነው፡፡ ፍርኃት፣ ጥርጣሬና አለማወቃችን ደግሞ ይበልጥ ሕገወጥነትን የሚታገስና የሚያለማ ይሆናል፡፡ በሕግ ለማይገዛ  ለቢሻኝ ውሳኔ ሁኔታ ይሰግዳል፡፡ ለሕጋዊነት ወግ አለመጨነቅን ባህል ያደርጋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጣሉና የሚነሱበትን፣ የባለሥልጣናትም ሆነ የማንኛውንም ሰው ተግባር እንኳንስ መዋጋት አቤት ማለትና መናገርም በራሱ ችግር ነው፡፡

አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ መግባት ድርብ ድርብርብ ሥጋት እንዳለው ከላይ ገልጫለሁ፡፡ ይኼ አገራችን ውስጥ አሁንም እውነት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአገራችን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ መሠረታዊ ሕግ ይበልጥ የተፍታታና የተሻለ፣ እንደሁም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ምሽግ ያበጀ መጠበቂያ እንዳለው አስፍሬአለሁ፡፡ የእነዚህን የሁለቱን ጉዳዮች ትርጉምና አንድም በጥቂቱ ላብራራ፡፡ የአገራችን መንግሥት ሁልጊዜም በበዳይነትና በጨቋኝነት እንጂ በምንም ሌላና ቀና ነገር የማይታወቅበት አገር ሆና ኖራለች፡፡ ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲገዛ የቆየው የወታደራዊ አምባገነን መንግሥት መገርሰስ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና መንግሥቱን በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንደ አዲስ ለመገንባት የሚችልበትን ዕድል የከፈተ ታሪካዊ ወቅት መሆኑን ገልጸን፡፡ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት የቀድሞዎቹ መንግሥታት ተቀጥያ እንደሆነና ውድቀቱም የጭቆናና የአፈና ዘመን ማክተም አመላክቷል፡፡ ነፃነት የእኩልነት መብቶችና የሁሉም ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መርሆዎች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ የማኅበራዊ ሕይወት ምሰሶዎች የሚሆኑበትን አዲስ ምእራፍ ከፍቷል ብለን (የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር) ‹‹ሀ›› ብለን ብንጀምርም፣ ዛሬም ከ25 ዓመታት በኋላ ያንን የደፍ ኬላ ስለመሻገራችን መተማመኛ አላገኘንም፡፡ ማስረጃም የለንም፡፡ እንዲያውም ያለን ማስረጃ መንግሥት በአገራችን ዛሬም ከበዳይነትና ከጨቋኝነት ውጪ በሌላ ቀና ነገር የማይታወቅ መሆኑ ነው፡፡

የዚህ ማስረጃ ሕዝብ ኢሕአዴግን በምርጫ መንግሥት አድርጎ መቶ በመቶ ሾመ፣ ሸለመ በተባለው ወር ሳይሞላ ጀምሮ አገሪቷ በተቃውሞ መላውን የ2008 ዓመት መታመሷ ነው፡፡ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የፀናውንም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ በውጤትነት ያስከተለው ሁለተኛው የሕዝብ ብሶትና ቅሬታ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ‹‹በጥልቀት ለመታደስ›› ቃል የገባው መንግሥት ከመታደስና የማሻሻያ ዕርምጃዎችን ከመውሰድ ጎን ለጎን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ወይም የድንገተኛ ወይም የአጣዳፊ ጊዜ ሥልጣን ጭምር ይዟል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ሁኔታ ተከስቷል ብለን ነው፡፡ ለመንግሥት ተጨማሪ የድንገተኛ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን የተሰጠው በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል አደጋ ነው ተብሎ ነው፡፡ ድርብ ሥጋት ውስጥ የገባነው ደግሞ በአንድ በኩል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ያንዣበበውን አደጋ መቀልበስ የሚያስችል መላና ብልኃት ጨብጠናል ከሚለው አሳሳቢ ጥያቄ ማዕዘን ነው፡፡ ለመንግሥት የተሰጠው ወይም እሱ ራሱ ይገባኛል ያለው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን አጠቃቀምም ያሳስበናል፡፡

የቀደሙት መንግሥታት ሁሉ በሕገ መንግሥቶቹ የተደነገገ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ የ1948 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ንጉሥ ነገሥቱ ‹‹የጦር ጊዜ አስተዳደርን የጦር ሕግን ወይም አገር የሚጠቀምበትን አስቸኳዩን ነገር ያውጃል›› ይል ነበር፡፡ በ1980 ዓ.ም. ሕገ መንግሥትም አስደዳጅ ሁኔታ ሲፈጠርና የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን፣ ጦርነትን፣ የጦር ጊዜ አስተዳደርን ከተትን የማወጅ ሥልጣን ለመንግሥት ምክር ቤት ይሰጥ ነበር፡፡ ከዚህ በላይ ዝርዝርና የተፍታታ ነገር አልነበራቸውም፡፡

የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ግን ከዚህ በላይ የተስፋፉና የተዘረዘረ ነው፡፡ እንቀጽ 93ን የመሰለ በስድስት ንዑሳን አንቀጾችና በሌሎች በርካታ የንዑስ ንዑስ አንቀጾች የተብራራ ድንጋጌ ይዟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለሕገ መንግሥቱም ለዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብቶች ንቅናቄም ምሥጋና ይግባቸውና የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9 እና 13 አማካይነት ከዓለም አቀፉ አሠራርና አተገባበር፣ እንዲሁም አተረጓጎም ጋር ተቆራኝተዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን እንኳንስ የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳደር በተጣለበት መንግሥትም የአስገዳጅ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን በያዘበት ወቅት በመደበኛውና በተረጋጋ ሕይወትም ውስጥ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሥልጣን በያዘው መንግሥት መልካም ፈቃድና ፍላጎቶች ላይ ብቻ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የአንድን መንግሥት መልካም ፈቃድና ‹‹ቁርጠኝነት›› የማይለወጥና የማይናወጥ አድርገን ብንወስድ እንኳን፣ መብታችን በእያንዳንዱ ባለሥልጣንና የመንግሥት ሠራተኛ አተያይና አተረጓጎም ላይ የተንጠለጠለ፣ እንደ ሰው ባህርይ ድንገተኛ መለዋወጥ የተለያየ ነው፡፡ ዛሬም ችግራችን ሕግ አለመኖሩን ሳይሆን ሕግ አስፈጻሚዎች ከሕግ በላይ መሆናቸውና አለመጠየቃቸው ነው፡፡ የሕግ የበላይነትና የተቋም ግንባታ ከአፍና ከተውኔት ይልቅ በተግባር መከበራቸውን ማረጋገጥ አለመቻላችን ነው፡

በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አስተዳደር ውስጥ ሆነን አሁንም ሁለት ነገሮች ያስፈሩናል፡፡ አንደኛውም በሥርዓቱ ላይ ያንዣበበው አደጋ ምንነት፣ የበሽታው ዓይነት መንስዔና ምክንያት በሚገባ ተመርምሮ ተጣርቶና ተረጋግጧል ወይ? መድኃኒቱን ሁሉ አግኝቷል ወይ? ከሕመማችን ለመዳንና ከአገር ሕመም ለመገላገል ሁሉንም ዓይነት የሕክምና መሣሪያ ታጥቀናል ወይ? ሁለተኛው ሥጋት የታዘዘልን መድኃኒት ዓይነትና መጠን ልክነትና ትክክለኛነት ያሳስበናል፡፡ ሥርዓታችንን ከበሽታው ይልቅ መድኃኒቱና አወሳሰዱ የተፈራውን አደጋ እውን እንዳያደርገው እንሰጋለን፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሕግ በወጣበት ወቅት ከ‹‹ትናንት›› ጀምሮ የፀናው ሕግ ዝርዝር ዛሬ በመግለጫ መልክ ሲነገረን፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው የመንግሥት ሥልጣን በተለይ በተለይ ሁለት ጉዳዮችን በፍጹም እንደማያመለክት በማብራሪያው ተረጋግጦልን ነበር፡፡ አንደኛው የቪየና ኮንቬንሽን የዲፕሎማቶች መብት ተባልን፣ ሁለተኛው በደፈናው ‹‹ሰብዓዊ መብቶች›› ሲባል ሰማን፡፡ የሚኒስትሮች ምከር ቤት ያወጣው ‹‹አዋጅ›› ሲነበብ በመግለጫና በማብራሪያ ‹‹ሰብዓዊ መብት›› የተባለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 18 የተደነገገው የኢሰብዓዊ አያያዝ ክልከላ ጉዳይ መሆኑ ገባን፡፡ ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው የኮማንድ ፖስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአፈጻጸም መመርያ መሠረት ደግሞ ዲፕሎማቶች የራሳቸው ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውጪ የኮማንድ ፖስቱን ዕውቅና ሳያገኙ እንዳይንቀሳቀሱ መከልከሉን አወቅን፡፡ በዚህ ግንባር ወይም ዘርፍ የተወሰደው የክልከላ ዕርምጃ መነሳት የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ፣ ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በተሰማው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ማብራሪያ ላይ ተገልጾልናል፡፡

      ከመስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ወዲህ ባለው የአንድ ወር የአፈጻጸም ጊዜ ውስጥ ከምንጊዜም በላይ አረጋግጠን የተማርነውና የተረዳነው አንድ ለእኛም ለሌላም የሚሆን ትልቅ ትምህርት አለ፡፡ ይኼም ዴሞክራሲንና ሥነ ምግባርን በከፊል ትምህርት፣ ከመጽሐፍ፣ ከሕገ መንግሥትና ከአስተማሪ አፍ እየሰሙና እየጻፉ በማጥናት እንደማይማሩት ነው፡፡ ዴሞክራሲንም፣ ሥነ ምግባርንም፣ የዴሞክራሲን ሰናይና እኩይ ነገሮች፣ የፕሬስና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ዳር ድንበሮች መማር የምንችለውና መማር የሚዋጣልን ስንኖረው ብቻ ነው፡፡ ይህን አለማድረጋችንና አለመሆናችን ዛሬ በ‹‹ቀውጢ›› ጊዜ ይፋ ወጣ፡፡

      ዋናው ሕግ በአስቸኳይ ጊዜ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በሚል ርዕስ ሥር ኮማንድ ፖስቱ ሊከላከላቸው የሚችላቸውን በርካታ ጉዳዮች ዝርዝር አወጣ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ‹‹ማንኛውም ሁከት፣ ብጥብጥና በሕዝቦች መካከል መጠራጠርና መቃቃር የሚፈጥር ይፋዊ ሆነ የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ማተምና ማሰራጨት፣ ትዕይንት ማሳየት፣ በምልክት መግለጽ ወይም መልዕክትን በማናቸውም ሌላ መንገድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አንዱ ነው፤›› አለ፡፡ ያልተፈቀደ ሠልፍና ስብሰባ ሌላው ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኮማንድ ፖስቱ ሁከትና ብጥብጥ የሚያስነሳ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ጽሑፍ ማዘጋጀት፣ ወዘተ እንዲሁም ለምሳሌ ያልተፈቀደ ሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ ክልክል ነው ሲል የአፈጻጸም መመርያ አወጣ፡፡

      ኮማንድ ፖስቱ እንዲህ ያለ በተከለከሉ ተግባሮች ውስጥ የሚወድቅ ጽሑፍ ያዝኩ ወይም የተከለከለ ስብሰባ አገኘሁ ሳይል፣ ማተሚያ ቤቶች በመብታችንና በግዴታችን ክልክል ነው ብለው ሳይሆን ፈራን ብለው መጽሔቶችን አናትምም አሉ፡፡ አሳታሚዎችና የግል ማተሚያ ቤቶች የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታውን ሕጎች ምክንያት አድርገው አናትምም ማለታቸውን ገልጸው፣ ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤትና ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት አቤት አሉ፡፡ አቤት የተባለባቸው መሥሪያ ቤቶችም በአዲስ አድማስ የ15 ቀን በፊት ዜና መሠረት የማተሚያ ቤቶቹ ድርጊት ከሕግ መንፈስ ጋር የሚቃረን ነው ቢሉም፣ መንግሥት በአሳታሚዎችና በማተሚያ ቤቶች መካከል ባለ የንግድ ሥራ ግንኙነት ውስጥ መግባት እንደማይችል ገልጸው፣ የጉዳዩ ፋይል በዚሁ ተዘጋ፡፡

በመደበኛው ሕግም ሆነ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀንቶ በሚቆይበት ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚው ይዘትን የሚመለከተው ሕጋችን የፕሬስ ይዘት ሕጋዊነትን የማረጋገጥ ግዴታ የሚጥለው በዋነኛነት በአሳታሚው ወይም በዋና አዘጋጁ ላይ ነው፡፡ ማተሚያ ቤቱ ወይም አታሚው ኃላፊ የሚሆነው (በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 43/1/መ) የፕሬስ ውጤቱ በተሰራጨበት ወቅት አሳታሚውን ለማወቅ ካልተቻለ ብቻ ነው፡፡ ይህ ራሱ አወዛጋቢና ጥያቄ የተነሳበት ድንጋጌ ነው፡፡ በዚህ ሕግ መሠረትም ቢሆን ማተሚያ ቤቶች ቢፈሩ የሚያምርባቸው በአሳታሚው የማይታወቅ ጋዜጣ ወይም መጽሔት ቢያትሙ ብቻ ነው፡፡ ፍርኃትና ‹‹ብዥታ›› ግን ብዙ ድምፆች አላግባብና ያለ አባት (ያለሕግ ማለት ነው) ከአደባባይ እየወጡ ነው፡፡ እስካሁን ይኼንን አደጋ የሚከላከል አላየንም፡፡ ማተሚያ ቤቶችን በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጁ መሠረትም ባይሆን በመደበኛው ሕግና በመደበኛው አሠራር ‹‹ለሕዝብ አገልግሎት አለመስጠት›› ብሎ ነውር ነው ያላቸው የለም፡፡

እስከዛሬ ያጠናነው፣ የሸመደድነውና በቃል ያነበነብነው ዴሞክራሲና የዴሞክራሲ ወግና ባህል በልቦናችን ሊያድር በውስጣችን ሊጣባን ያለመቻሉ ሌላው ምሳሌ ‹‹ያልተፈቀደ ሠልፍንና የአደባባይ ስብሳባ›› ድንጋጌ አፈጻጸም ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው የኮማንድ ፖስቱ የአፈጻጸም መመርያ ‹‹የሕዝብና የዜጎች ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ሲባል ከኮማንድ ፖስቱ ፈቃድ ውጭ ማናቸውም ሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ ማድረግ የተከለከለ ነው፤›› ይላል፡፡ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታርየት ኃላፊ ባለፈው እሑድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳረጋገጡት፣ ‹‹በርካታ የመንግሥት ተቋማት መደበኛ የመንግሥት ሥራዎቻቸውን ለመሥራት፣ ስብሰባ ለመሰብሰብ ለኮማንድ ፖስቱ ጥያቄ እያቀረቡ ነው ያው ያሉት በርካታ ባንኮች ጉባዔያቸውን ለማካሄድ ኮማንድ ፖስቱን. . .›› ጠይቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ጥያቄውን ሲመልሱና ጉዳዩን ሲያብራሩም፣ ‹‹መደበኛ ሥራዎች፣ ለልማት የሚደረጉ መደበኛ ሥራዎች፣ ለማኅበራዊ አገልግሎት የሚደረጉ መደበኛ ሥራዎች፣ በየተቋሙ የሚሠሩ ሥራዎችና እነዚህ ስብሳባዎች አልተገቱም፣ አልተከለከሉም፤›› ስለዚህም የኮማንድ ፖስቱን የቅድሚያ ፈቃድ አይፈልጉም በማለት ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችንና የፋይናንስ ድርጅቶችን እንዲህ ግራ ያጋባ የሕግ መመርያና አፈጻጸም በዴሞክራሲ ሥነ ምግባርና ባህል፣ ወግና እሴት ውስጥ አለመኖራችንና እየኖርንም አለመማራችን ነው የሚያሳዩት፡፡ ከፍ ብለን ያነሳው የሚዲያው ጉዳይም ለኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታርየት ኃላፊ (ለመከላከያ ሚኒስትሩ) ቀርቦ ነበር፡፡ ጋዜጠኛው፣ ‹‹ከግልጽነት ጋር የተያያዙ አሁንም የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፣ ከኅትመት [ከሚዲያ ኅትመቶችና ከሌሎች ኅትመቶች] ውጤቶች ዕገዳ ጋር ተያይዞ አዋጁ በግልጽ ያስቀመጠው ምንድነው?›› ብሎ መጠየቅ፡፡

በሚዲያ መሸፈን ያለባቸው በርካታ የልማት፣ የሰላምና የዴሞከራሲ ሥራዎች መኖራቸውንና የኅብረተሰቡን የዕውቀት ደረጃ የሚገነቡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ሕጉ እነዚህን አለመከልከሉንና ሕጉ የከለከለው ሁከትና ብጥብጥ፣ መጠራጠርንና መቃቃርን የሚፈጥር የሪፖርትና የሚዲያ ሥራዎችን መሆኑን ጠቅሰው፣ ‹‹እነዚህ በርካታ በሚዲያ የሚሠሩ ሥራዎች እያሉ የእኔ ዋነኛ ሥራ ሁከትና ብጥብጥ ነው. . . ይኼንን ከተከለከልኩ ሥራ የለኝም የሚል ሚዲያ/የኅትመት ተቋም ካለ ተከልክሎ ሥራ ማቆም ነው ያለው አማራጭ፤ ሌሎች መደበኛ ሥራዎች አልተከለከሉም፤›› በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

እንዲህ ባለ ሁኔታ በፕሬስ ውጤቶች አማካይነት ጥፋት ቢሠራ ተጠያቂው ማነው? ማለትም የሚያሠራጨው የፕሬስ ውጤት በሕግ የሚያስጠይቅ ይዘት የሌለው መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ ያለበት አሳታሚው ነው? አታሚው? (ማተሚያ ቤቱ) የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ይህንንም ኃላፊነትና ተጠያቂነት የለወጠ የሁሉም ያደረገ ሕግም አልወጣም፡፡

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው የኢትዮጵያ የዛሬው ሕገ መንግሥት ከቀድሞዎቹ ሕገ መንግሥታት በጣም የተሻለና የላቀ መጠበቂያ ያበጀ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ዝርዝሩ ሰፋ ያለ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻችውን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎች አፈጻጸምንና አተረጓጎማቸውን መሠረትም ያደርጋል፡፡

ከሞላ ጎደል በተመሳሳይ ጊዜ የወጣው የአዲሲቷ የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥትም የአንቀጽ 93 አቻ የሆነ አንቀጽ 37 የሚባል ይበልጥ የተፍታታና የተዘረዘረ ‹‹ሀ›› ብሎ ሲጀምር፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ የሚፀናው ከታወጀ በኋላ ነው የሚል የአስቸኳይ ጊዜ ሕጉን በሕጉ፣ መሠረት የሚወጡትን ደንቦች፣ የሚወሰዱትን ዕርምጃዎች ሕጋዊነትና ፅኑነት ለፍርድ ቤት ዳኝነት የዳረገ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታው ምክንያት የሚነኩበትን ዳር ድንበር በነቂስ የሚወሰን፣ በአጠቃላይ ከታች እንዳያፈስ ከላይ እንዳይተነፍስ አድርጎ የሚወስን ሰፊ ድንጋጌ አለው፡፡ በዚህ ብቻ ሳይወሰን ደቡብ አፍሪካ የሕገ መንግሥቱን የአስቸኳይ ጊዜ  ሁኔታ ድንጋጌ ይበልጥ አፍታትቶ የሚደነግግ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ማወጃ የተለየ ሕግ አላት፡፡ ይኼ የተለየ ሕግ በአገሪቱ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ መኖሩን ከሚያሳውቀውና በአስፈላጊው ጊዜ ከመወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተለየ ነው፡፡

ዞሮ ዞሮ የኢትዮጵያንና የደቡብ አፍሪካን ሕገ መንግሥታት አንድ የሚያደርጋቸው በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ድንጋጌዎቻቸውን የሚያመሳስላቸው ሁለቱም ዓለም አቀፋዊ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የገዛ ራሳቸው ሕግ አካል ማድረጋቸውና የሰብዓዊ መብት መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ድንጋጌዎቻቸውን አተረጓጎም በእነሱ ማስገዛታቸው ነው፡፡ ይህ መርህና ሕግ አገር ሲወረር መልካው ሲነጋም ጭምር ይሠራል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ወቅትም ያገለግላል፡፡ አገር ሲወረር መልካው ሲነጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅና መንግሥትም የድንገተኛ ጊዜ ሥልጣን ሲይዝ ሊነኩና ሊገደቡ ከሚችሉት መብቶችና ነፃነቶች መካከል አንዱ የንግግርና የፕሬስ ነፃነት ቢሆንም፣ ያን ጊዜም ቢሆን ሚዲያው ‹‹እረፍት›› አይወጣም፡፡ ብዕሩንና ማይኩን አይሰቀልም፡፡ ይልቁንም በደቡብ አፍሪካ ከተማ ‹‹ችዋኔ መርሆዎች›› ተብሎ በሚጠራው በ “THE TSHWANE PRINCIPLES” መሠረት የሚዲያው ግዳጅ በዚህ ወቅት ይከብዳል፡፡

የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶችና የሰብዓዊነት ሕጎች መጣሳቸው፣ የነፃነትና የደኅንነት መብትና የኢሰብዓዊ አያያዝ ጉዳይ የመንግሥት አወቃቀርና ሥልጣንና ተግባር ያን በመሰለ ቀውጢ ጊዜ እንኳን ገደብ የማይደረግባቸው የኢንፎርሜሽን ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ራሱ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ርዕስ የሚደርጋቸው ዜናዎችና መረጃዎች የሚዲያው የወቅቱ ግዴታ ናቸው፡፡ የልማትም የዴሞክራሲም ቅድመ ሁኔታዎች እነዚሀ ናቸው፡፡ የሰው ሁሉ ይልቁንም የሰው ልጆች ሰብዓዊ ፍጡሮች ሁሉ የጥበብ መጀመርያ የእነዚህ መብቶች መጠበቅ ነው፡፡ እኛም ስለሚዲያ ነፃነት ይገባናል የምንለውና የምንሟገተው በዚህ ምክንያት ነው፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡.

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን...