Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ይህን ያህል አያሳጣ!

ሰላም! ሰላም! አንዱ መጣና ‹‹መስከረም ብቻ ጠብቶ ቀረ እንዴ?›› አለኝ። እኔ የዘመን እንቆቅልሽ ፈቺ የሆንኩ ይመስል። ‹‹ታዲያ ሌላ ምን አስበህ ኑሯል?›› ስለው፣ ‹‹የለም! ሰውና ኑሮው ግን እንደ አምናው ናቸው፤›› ብሎኝ መልስ ሳይጠብቅ ሄደ። እሱ እንደመጣለት የጠየቀኝን እንደ ሥራ ፈት ቆሜ ከመፍተሌ በፊት ጤንነቱን መጠራጠር ያዝኩ። በአንድ ዕርምጃ የተጀመረ የሺሕ ኪሎ ሜትሮች ሩጫ ለምን በፍጥነት አላለቀም ባዮች ሲበራከቱ ሳይ ጤንነታቸውን ያልተጠራጠርክ ምናቸውን ልትጠረጥር ነው የምትሉኝ? ጉድ እኮ ነው እናንተ? ዘመን በተቀየረ ማግሥት መና ጠባቂው፣ መንግሥት በተለወጠ ቁጥር ተዓምር ናፋቂው፣ አሠልጣኝ በተለወጠ ቅጽበት ውጤት ውለዱ ባዩ እኮ አገር በጠበጠ እናንተ? እኔ በዚህ አያያዛችን አንድ የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ሆስፒታል ብቻውን ስለማይችለን፣ ከመንገድና ከሕንፃ ልማቱ እኩል የአዕምሮ ጤና ላይ የሚሠሩ ሆስፒታሎች ላይ ኢንቨስት መደረግ አለበት ብዬ ደምድሜያለሁ።

‹‹ዳሩ እኛ እንደመድማለን እንጂ በጀት አናፀድቅ?›› የሚለኝ ነገረኛው ጓዴ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው። እሱ እንኳን እንዲህ ‘ፈረሱም ያው ሜዳውም ያው’ ብዬ መንገድ ሰጥቼው ቀርቶ ሰርስሮ መግባት ይችልበታል። ያለመታደል ነገር ሆኖብኝ በነገር ሰንጣቂ ተከብቤ ማንጠግቦሽም እንዲሁ ድምዳሜዬን ሳካፍላት፣ ‹‹እብዱስ አንተ! እንደሚያወሩት አውርተህ፣ እንደሚያስቡት አስበህ፣ እንደሚስቁት ስቀህ የማትኖረው፤›› አትለኝ መሰላችሁ? ኧረ መሄጃ አጣሁ፡፡ እንዲህ ተያይዘን እየተደነባበርን ስንጓዝ እኮ ዓለምን የሚዞራት የለውጥ ባቡር ጥሎን ከነፈ፡፡ እውነቴን ነው! ቆም ብሎ ማሰብ፣ መተራረም፣ በሐሳብ መነቃቀፍና መተማመን መቻል እንደ እንግዴ ልጅ አልወጣልን ብሎ 2009 ይቁጠርብን? ባሻዬን ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ምነው ይኼን ያህል እያደር ባሰብን?›› ስላቸው፣ ‹‹ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም፤›› ብለው ወሽመጤን ቆረጡት። አወይ ቢጤ ማጣት!

ነገሩን ከላይ ከላይ እንደ ስልባቦት አንስቼ ጨዋታ መጀመሬ ጥንስሱ የት መሰላችሁ? ያው የፈረደበት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ነዋ። ጥንት የጋርዮሽ ሥርዓት ሲጀምር እርስ በርስ መጠቃቃት ቆሞ ሰላም ብቻ ይፈልግ የነበረው የሰው ልጅ፣ አሁን በደረሰበት ዘመን የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የኔትወርክ፣ የመብራትና የውኃ ችግር እርስ በርሱ አጠማመደው የሚሉ አሉ፡፡ ሰፋ አድርገው ቢያዩት ደግሞ ዓለም በብጥብጥ እየታመሰች ነው፡፡ እንዴት ያለ ነገር ነው?  አሁን እዚህ ጋ ‹‹አይ የተነሱበትን አለማወቅ?›› አትሉም። ምክንያቱስ ካላችሁ ለተከበረው የሰው ልጅ ሌላ ሌላው ቀርቶ ፍትሕና መልካም አስተዳደር ተፈጥሮውን የሚመጥኑ ስለሆኑ ነው መልሴ። ዳሩ ቆመህ ጠብቀኝ በዛና ተቸገርን። እነዚያ ጥጉን ይዘው እነዚህን መቦጨቅ። እነዚህም እነዚያን በሐሜት መዘንጠል፡፡ ይኼ መገዳደር ተራራውን ሜዳ፣ ሜዳውን ሸለቆ ያደርገዋል ብሎ ማሰብ ገደለን። በአንድ ጽንፍ እያየን እንዳላየን ሆነን የምናልፈው ከንቃት ጉድለት ለሚመጣው የአስተሳሰብና የአመለካከት ወለምታ፣ ጥቂቶች በሌላ ጽንፍ በቻሉት አቅም ከራሳቸው ነጥቀው ለሌሎች የሚቀምሙት መድኃኒት አልሠራ ብሏል።

ይህ እንግዲህ በአጭሩ ‘ዲማንድ ኤንድ ሰፕላይ’ አልተመጣጠነም ማለት ነው። (እንግሊዝኛዬ እንዴት ነው? ምንም ደላላ ብሆን ፀሐይ የሞቃቸውን ቃላት እንኳን እኔ አዋፍት እያወቋቸው መጥተዋል) ‹‹ለዚህ እኮ ነው ከዳር ቆሞ ማሽሟጠጥና ጠጋ ብሎ ለጥቅም ማጨብጨብ የበዛው፤›› የሚሉኝ በዚያ ማራኪ አንደበታቸው አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። አፈር ልብላላቸውና፡፡ መቼም ትልቅ ሰው ትልቅ ነው። ግን የሚያሳዝናችሁ ትልቅ ሰው ለመሆን ከሚመኘው ይልቅ ልማታዊ ባለሀብት ሆኖ ትልቅ ሕንፃ ለመሥራት የሚጓጓው እየበዛ የኩረጃ ትምህርት ቤቶች ተጨናንቀዋል። ወረቀት ይዞ በአቋራጭ ለመክበር፡፡ ታዲያ በዚህ ዓይነት በረከታችን እንደ ዳቦ በአጭር ጊዜ ተጋግሮ ቢበስል ስንካፈል እንዴት ሊሆን ነው? ኧረ ከአሁኑ በደንብ እንጠያየቅ! ተው ግዴለም?!

ፀብ ያለሽ በዳቦ የሆነው የዘመኑ ትዕግሥት የለሽ ሰው (ፀብ ያለሽ በ ‘ኔትወርክ’ ብል ይሻል ነበር መሰል! የምግብ ዋስትናችን ተረጋግጧል በተባለበት በዚህ ጊዜ ዳቦ ዳቦ ስል ዳቦዬን አጥቼው እንዳላርፍ ደግሞ! ሆሆ!) የማይሆነው ነገር የለም። ወጣት ባልና ሚስት ተጣልተው ኖሮ የገዛ መኖሪያቸውን ሸጠው ሊካፈሉ (ሲገኝ መከራ ሲታጣ መከራ) ደልል ተባልኩ። በፍቅር ጊዜ በትዕግሥትና በጥናት የተሠራውን ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ አጣድፌ እንዳሻሽጠው መልዕክት ደረሰኝና ቀልቤን ሳትኩ። በኋላ ለቤቱ ገዥ አግኝቼ ይዤያቸው ቤቱን ለማሳየት ወደ ሥፍራው አቀናሁ። ደንበኛዬ ቤቱን ተዘዋውረው ዓይተው ከጨረሱ በኋላ፣ ‹‹ለመሆኑ ምነው አለ ይኼን የመሰለ ቤት በዚህ ዋጋ የሚሸጠው?›› ብለው ስለሻጩ ጠየቁኝ። የሰማሁትን እኔም ‘አሉ’ እያልኩ አጫወትኳቸው።

እሳቸውም፣ ‹‹እንደ ራሱ የሚወዳት ሚስት የነበረችው ገበሬ ታሪክ ትዝ አለኝ፤›› ብለው ጨዋታ ያዙኝ። ልማዴ ነውና ከሥራ ጎን ለጎን በተረት የታሸ ወሬ ለመለቃቀም ‘እህ’ ብዬ መስማቴን ቀጠልኩ። ‹‹ሚስቱ ድንገት ሳትታመም ሞተችና አረፈች። መኖር በአጠቃላይ አስጠላው። አንድ ቀን መንገድ ሲሄድ ‘ኧረ ምን አባቱ! ባይኬድ ምን ሊኮን?’ ይልና ድንጋይ ላይ አረፍ እንዳለ ዋለ። አመሻሽ ላይ የሚያውቀው የመንደሩ ሰው በዚያ መንገድ ወደቀዬው ሲያዘግም አገኘው። ‘ምነው ወዳጄ ደክሞህ ነው?’ አለው። ‘የለም! ከእግዜር ተጣልቼ ነው’ አለው። ወዳጁ ተገርሞ ‘እና ብትጣላ ተቀምጠህ ምን ትፈይዳለህ?’ ብሎ ጠየቀው። ‘ተጉዤስ ምን አደርጋለሁ? መጨረሻዬ የምወዳት ሚስቴ የሌለችበት ቤት መግባት አይደለም ወይ?’ ሲለው ወዳጁ መልሶ ‘ተቀምጠህስ ምን ትሠራለህ? እግዜር ጨክኖ ቢጨክን ለጅብ አይድርህ?’ ብሎ አሸንፎት እያፅናናው አብረው አዘገሙ ይባላል። የዘመኑ ሰው ትዕግሥት እያጣ የነገን የተሻለ መሆን ማየት ተስኖት ለሌላ ትልቅ ጥፋት ሲፈጥን ይህን ያህል ነው፤›› ብለውኝ ቤቱን እንደሚያስቀሩት መወሰናቸውን አሳወቁኝ። የማትሰሙት የለም እኮ ጆሮ ከሰጣችሁ!

ያን የመሰለ ቤት መቻቻል በመጥፋቱ ፈርሶ ሲሸጥ በእውነት ያገኘሁት ‘ኮሚሽን’ ‘ምን አገባኝ?’ ቢያስብልም አንጀቴ ተላወሰ። የራሴን ጎጆ ዘወር ብሎ መቃኘት ግድ ሆነብኝ። ፍርኃት ተጋብቶኝ ሥጋት ሲገባኝ ማንጠግቦሽን ጠጋ ብዬ ይኼ ነው፣ ይኼ ነው ሳልል አጋጣሚውን እንደ ቀልድ ነገርኳት። ‹‹ይኼውልህ እንዲህ ነው ይህቺን የመሰለችም አገር ቀስ በቀስ የምትፈርሰው፤›› ብትለኝ ድንጋጤዬ እንደ ማዞር አድርጎ ስላንገዳገደኝ ደሜን ለመለካት አቅራቢያዬ የሚገኝ ‘ክሊኒክ’ ጎራ አልኩ። ‹‹ደም ለመለካት ነበር፤›› ብዬ ቀጥሮ ያስያዝኳት ነርስ እስትጠራኝ የጠበቅኩትን ያህል ጊዜ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ይወጣልኝ ነበር ብል ማጋነን አልነበረም።

ወዲያ ጥግ ተቀምጦ የሚንቆራጠጥ ታማሚ ትዕግሥቱ አልቆ፣ ‹‹እናንተ ሰው ናችሁ? የገነት መግቢያ በር አሳላፊ ብትሆኑ ምን ልታደርጉን ነበር?›› ይላል። ‹‹ወንድሜ ክፍለ ከተማ አይደለም ያለኸው! አርፈህ ዶክተሩ እስኪጠራህ መጠበቅ ብቻ ነው!›› ይላል በ‘ኮምፒዩተር እስክሪኑ’ ካርታ የሚጫወት ወጣት የሕክምና ባለሙያ ተብዬ። ‹‹እሺ እኔስ? እኔን እኮ ዶክተር ማየት አይጠበቅበትም፤›› አልኩት ሹመት ሰጥቶ በሚለምናቸው ሕዝብ ላይ ደረታቸው የሚያብጥ አገልጋዮቻችንን ባስለመድንበት የልምምጥ ዘዬ። ‹‹ተከተለኝ አንተ፤›› አለኝ አፍታ ሳይቆይ። ‹‹አይ አንቺ አገር!›› ብዬ ብዙ ልብሰለሰል ስል ለደም ግፊት ስሰጋ ሰኳር ደርቤበት እንዳላርፍ ለራሴ ስላሰብኩ ዝም አልኩ። ሆሆ ደግሞ ለስኳር ‘ቼክ አፕ’ ቢቀጥሩኝ ዓባይ ተገድቦ አልቆ አይመረቅምና ነው?! ደም ግፊቴ ‘ኖርማል’ እንደሆነ ስሰማ ግን እንዳሻኝ እየተበሳጨሁ ወጥቼ ሄድኩ። አይ የአገልጋይና የተገልጋይ ነገር እያልኩ ነዋ! ሌላማ ምን ብዬ እበሳጫለሁ?

በሉ እስኪ እንሰነባበት ደግሞ። ባሻዬ አዘውትረው ‹‹ሁሉም በአገር ያምራል!›› ይላሉ። ሁሉም ሲሉ ታዲያ ሁሉም ነው። ብስጭትንም ጨምሮ። የባሻዬን ልጅ የተለመደችዋ ግሮሠሪያችን ሳገኘው ብስጭቴ ደስታ ወልዷል። ‹‹ምነው ዛሬ ተፍነከነክ?›› ብሎ ሲጠይቀኝ መልሴ ‹‹ስለተበሳጨሁ!›› የሚል ነበር። ግር ብሎታል። ‹‹ሰው ተበሳጭቶ እንዴት በእኩል ሰዓት ይደሰታል?›› አለኝ መልሶ። ‹‹በአገር ነዋ! የተበሳጨሁት በአገሬ ላይ ሆኜ ነዋ! ይኼኔ ሰው አገር ቢሆን ኖሮ ገመድ አልገዛም ነበር?›› አልኩት። አንድ ሁለት እያልን ጨዋታችንን አደራነው። ውሎዬን ሰማ፡፡ ውሎውን አዳመጥኩ። የሁለታችንም ገጠመኝ በአጉል ነገር ተረግዞ ብስጭት ሲወልድ የዋለ ነበር። እኛ ብቻ ሳንሆን ብዙኃኑ ጠጪ ማለት ይቻላል በእሮሮ ተቃኝቶ ነው የመጣው።

አንዱ ኑሮ ያንዘላዘለው’ ተንዘላዝሎ ስለጠፋበት አምስት ሺሕ ብር ይቆጫል። ሌላው ተበልቶ ስለቀረበት ብድር ያማርራል። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ኧረ የኔትወርክ ያለህ? እንጀራችሁን ጣሉ ጣሉ ብለው ‘ኔትወርክ’ ላይ አስጥለውን አሁን የት አባታችን እንድረስ?›› ይላል። ‘ናፈቀኝ ክርክር! ናፈቀኝ በተለያዩ ሐሳቦች ተማምኖ መከባበር’ የሚለው ደጋግሞ ጂኑን ይጋታል። የባሻዬ ልጅ ዘወር ብሎ ወደኔ ሲያፈጥ፣ ‹‹ማንን ታያለህ እስኪ ስለሌላ አገር የሚጮህ?›› አልኩት። ‘ማንንም’ ለማለት ራሱን ነቅንቆ ሲያበቃ፣ ‹‹ሁሉም በአገር ያምራል አቦ! ብስጭትም ቢሆን!›› አለኝ። ይኼን ሲለኝ የሰማ አንድ ሞቅ ያለው ‹‹ታዲያስ! አገር የሞተ እንደሆን. . . .››  ብሎ ሳይጨርሰው ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹ወዴት ይደረሳል?›› ብሎ ጮኸ። ይህን ያህል አያሳጣ ነው የሚባለው። አለበለዚያማ ወዴት ይደረሳል?! ቸር ሰንብቱልኝ እስኪ! መልካም ሰንበት!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት