ያለህበት
የሥልጣኔ መናኸሪያ
የጥበባት መጠለያ
ከጊዜ ሽርሸራ መከለያ
የማይፋለስ ሐቅ ማብሰሪያ
የአሉባልታ መፋለሚያ
የሙያዎች ማለምለሚያ
ካለህበት ቃላት ይናኛሉ
አንዴ ተነግረው የማያልፉ
የማይረሱ የማይጠፉ
ታርመው ተቃንተው የነጠሩ
የማይነጥፉ የማይሻሩ
ወዳጄ ሆይ!
የረገጥከው ስፍራ ክቡር ነው
ያለህበት ማተሚያ ቤት ነው፡፡
- አማረ ማሞ
* * *
የሥራ ጠል ዋልጌዎች ፍልስፍና ምንዛሪው ወሬ ብቻ
‹‹ለመሪህ ዓሳ ምሰል››፣ ‹‹እሺ ይበልጣል ከሺ›› የሚባሉት ቃላት በሙሉ የሰነፎች ቢሮክራቲክ ፍልስፍና ምንጭ ናቸው፡፡ አንዳንድ ሰነፍ ዋልጌ ከሥራ አለቆቹ የሚሰጠውን ትዕዛዝ ሁሉ ‹‹እሺ ጌታዬ ወይም እመቤቴ›› ብሎ እጅ ነስቶ ይቀበላል፡፡ ነገር ግን በተግባር ተፈጽሞ የሚታይ ቁም ነገር የለም፡፡ ወደ አሜሪካ ተሰዶ ሲገባ ግን ባጭር ታጥቆ ለመሥራት ተፍ ተፍ ማለት ይጀምራል፡፡ ለደቂቃ እንኳን ቀና ብሎ ከሰው የሚነጋርበት ጊዜ የለም፡፡ የግል ስልክ ድራሹ አንዲጠፋ ይደረጋል፡፡ ሹክሹከታ እንኳ ክልክል ነው፡፡ ባገራችን ግን ለወሬ ሲባል ብቻ ለማኙ ሁሉ የእጅ ስልክ አለው፡፡ ለወሬ ቀኑ እንኳ አልበቃ ብሎ የዞረ ድምር ሆኖ ወደ ሌሊት ይተላለፋል፡፡ በቢሮ ወሬ በመኪናም ውስጥ ወሬ ብቻ በተለይም በሕዝብ መመላለሻ አውቶብሶችና ሚኒ ባሶች እንደ ጉሊት ገበያ የደራ ወሬ፣ በየፌርማታው በመቆም አውቶብስ ሲጠበቅ ወሬ ብቻ እንጂ አንባቢ በመብራት ቢፈለግ አይገኝም፡፡ ዛዲያማ ፈረንጅ ‹‹ጥቁር ሕዝብ በተለይ ሀበሻ ምስጢርህን እንዳያውቅብህ ከፈለግህ በመጽሐፍ ጽፈህ አኑረው›› የሚልበት ምክንያት ልክ ነዋ! ምናልባት ግን ትንሽ የተሰፋ ጭላንጭል እንዲኖር ከተፈለገ የጋዜጣና የሬዲዮ መገናኛ ብዙኃን ሳያሰልስ ይህን ሁሉ የተበላሸ ሕይወት ለማስተካከል ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡
ሌላውም አስገራሚ ነገር በታላላቅ አውቶቡስና ሚኒባስ ውስጥ የሚጦፈው የደራ ወሬ ብዛት ነው፡፡ ከዚያ ሁሉ ወሬ ጋር ሾፌሮች ሙዚቃውን አለቅጡ ከፍተው ሻይ ቤት በማስመሰል የሕዝቡን የጆሮ ጅማት የሚበጥስ ድምፅ ማሰማት ይወዳሉ፡፡ ‹‹ቀንሱት›› ሲባሉም እሺ አይሉም፡፡ ነገር ግን ሰሚ የላቸውም፡፡ ሕዝቡም ያውካል የእጅ ስልኩ ያቃጭላል፡፡ በውጭ ዓለም በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካና ጃፓን ግን ይህ ዓይነቱ አሠራር በጣም አስነዋሪ ስለሆነ በሕግ ያስቀጣል፡፡ የማኅበረሰባችን ሒደት ከብልጽግና ይልቅ ወደ ባሰ ፍጹም ድህነትና ጉስቁልና የሚመራ ነው፡፡ ወደ ሥልጣኔ ደረጃ መሸጋገሪያው ድልድል ከሰማይ የራቀና እስከ መጨረሻ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆኗል፡፡ ይህን አለመታደል ነው፡፡ ‹‹ለወሬ የለም ፍሬ ላበላ የለው ገለባ›› ይባላልና ነው፡፡ ይህን ሐቅ መናገር እንደ ድፍረት ይቆጠር ይሆን? አንባቢዎች ፍረዱ!
- መጋቤ አዕላፍ መክብብ አጥናው፣ ‹‹ሁለገብ ትምህርት ሰጭ የአዕምሮ ማዝናኛ›› (2005)
******
የወፏ ምክር
አንድ ሰው አንዲት በጣም ቆንጆ ወፍ በመዳፉ ውስጥ ይዞ ጨምቆ ሊገድላት ሲል ከመሞቷ በፊት አንድ ወይም ሁለት ቃላት ትናገር ዘንድ እንዲፈቅድላት ጠየቀችው፡፡
እንዲህም አለች “እባክህ አትግደለኝ፡፡ ሦስት ጠቃሚ ምክሮችን እሰጥሃለሁ፡፡ የመጀመሪያው ምክር፤ በእጅህ ያለውን ነገር አትልቀቅ፡፡ ሁለተኛው ምክር፤ ስለሆነው ነገር ሁሉ አትቆጭ፤” ካለችው በኋላ ዝም አለች፡፡
ሦስተኛውንም ምክር ትነግረው ዘንድ ሲጠይቃት “ሦስተኛው ምክር ለልጆችህና ለልጅ ልጆችህ በጣም ጠቃሚ ስለሆነ ካለቀከኝ አልነግርህም፤” አለችው፡፡
በዚህ ጊዜ ሰውየው ሦስተኛውን ምክር ለመስማት በጣም ጓጉቶ ስለነበረ ወፏን ሲለቃት ከአንድ ዛፍ ላይ በርራ ወጥታ “ምንድን ነበር ያልኩህ? ታስታውሳለህ?” ብላ ጠየቀችው፡፡ እርሱም “በእጅህ ያለውን ነገር አትልቀቅ ነው ያልሺኝ፡፡” አላት፡፡
“ሁለተኛውስ?”
“ስላለፈው ነገር ሁሉ አትቆጭ፡፡”
“አዎ፡፡ ነገር ግን የነገርኩህን ነገር አልተቀበልክም፡፡ ባትለቀኝ ኖሮ ከሆዴ ውስጥ ለልጅ ልጆችህ የሚሆን ወርቅ ታገኝ ነበር፡፡ ይኸው ነው፤” አለችው፡፡
ሰውየው “ሦስተኛውስ ታዲያ?” አላት፡፡
እሷም “ሦስተኛው የሁለተኛው ምክር ድጋሚ ነው፡፡ ስላጣኸው ነገር አትቆጭ፡፡ ይኸው ነው፡፡ ደህና ሁን፡፡ ምክሬንም ባለመቀበልህ በድህነት ትኖራለህ፤” አለችው፡፡
- በወርቁ ወልደማርያም የተተረከ የከፋ ተረት
በሰፈሩት ቁና…
የሰሜናዊ ቻይና ፖሊሶች ከመጠን ያለፈ መብራት ከመኪናቸው በመልቀቅ ከፊት ለፊታቸው ያሉ አሽከርካሪዎችን እንዲሁም መንገደኞችን የሚያውኩ ሾፌሮችን ለመቅጣት ያወጣችው ሕግ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ከመጠን ያለፈ መብራት የለቀቁ አሽከርካሪዎች ሲያዙ፣ ለአንድ ደቂቃ ያህል ወንበር ላይ ተቀምጠው ከፍተኛ መብራት የለቀቀ መኪና እንዲመለከቱ ይደረጋሉ፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ትራፊኮቹ ከ44 ዶላር ቅጣት በተጨማሪ ሾፌሮችን በመኪና መብራት መቅጣት እንደሚጀምሩ ሲያሳውቁ ብዙዎች ደግፈዋቸዋል፡፡ ‹‹በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም›› እንዲሉም የሰሜን ቻይና ትራፊኮች ቅጣቱን ተያይዘውታል፡፡ ተመሳሳይ ቅጣት ከሁለት ዓመት በፊት ተሞክሮ ተቃውሞ ስለገጠመው ቢቀርም፣ አሁን ብዙዎች ቅጣቱን እያበረታቱ ነው፡፡ ሾፌሮች በሌሎች አሽከርካሪዎችና እግረኞች ላይ እያደረሱ ስላሉት ተጽእኖ ሊገነዘቡ የሚችሉበት ብቸኛ መንገድ ነው ያሉ አሉ፡፡ በተቃራኒው ቅጣቱ የሰዎችን የዓይን ጤና የሚጎዳና ሰብዓዊ መብትን የሚጻረር ነው ያሉም አልታጡም፡፡
* * *
ስፔን የውሾች ዲኤንኤ ምዝገባ ልትጀምር ነው
ስፔናውያን ውሾቻቸውን ይዘው ከተማው ውስጥ ሲዘዋወሩ ድንገት ውሾቻቸው ቢፀዳዱ፣ ቆሻሻውን ከማንሳት ይልቅ ጎዳና ላይ ትተውት መሄድ አብዝተዋል፡፡ የስፔን መንግሥትም የአገሪቱን ንጽህና ለማስጠበቅ ሲል የውሾችን ዲኤንኤ መመዝገብ ሊጀምር መሆኑን አሳውቋል፡፡ የውሾቹ ዲኤንኤ ከተመዘገበ በኋላ የባለቤቶቻቸው ስምና አድራሻም ተያይዞ ይመዘገባል፡፡ ውሻው በመንገድ ተፀዳድቶ ሳያነሳ የቀረ ሰውም ይቀጣል፡፡ የጎዳና ፅዳት ሠራተኞች ቆሻሻውን ለአገሪቱ ማዘጋጃ ቤት ያስረክቡና ባለቤቱ እስከ 200 ዩሮ ይቀጣል፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ አሜሪካና እንግሊዝም ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል፡፡