Thursday, February 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ በፓርላማው ፀደቀ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሱ ካቢኔ በፓርላማው ፀደቀ

ቀን:

– በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የተሰባሰቡት አማካሪዎችና ክላስተሮች ተበተኑ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በድጋሚ ያቋቋሙትን ካቢኔ ከአንድ ዓመት ጊዜ ቆይታ በኋላ አፍርሰው፣ እንደ አዲስ ያደራጁትን አዲስ ካቢኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. አፀደቀው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ2009 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን ሲመጡ በድጋሚ ካቋቋሙት 30 አባላትን የያዘ ካቢኔ ውስጥ ዘጠኝ አባላትን ብቻ በማስቀረት፣ ሌሎች አምስት የቀድሞ ካቢኔ አባላትን በማሸጋሸግና 13 አዲስ የካቢኔ አባላትን በመመልመል አዲሱን ካቢኔያቸውን በፓርላማው አፀድቀዋል፡፡

አዲሱ የካቢኔ አወቃቀር መነሻ የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ኑሮ ማመቻቻ ሳይሆን ለኅብረተሰብ ለውጥ መሣሪያ አድርገው ለመጠቀም የአመራር ጥራት ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡ ከቀድሞው ካቢኔ አባላት ውስጥ ባስመዘገቡት ውጤት በዚያው እንዲቀጥሉ የተደረጉት ዘጠኝ የካቢኔ አባላት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

እነዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ፣ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ፣ የብሔራዊ ፕላኒንግ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሣ ተክለ ብርሃንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ ናቸው፡፡

በቀድሞው ካቢኔ ውስጥ አባል የነበሩና አሁንም ወደ ሌላ ቦታ ተሸጋግረው በካቢኔ አባልነት እንዲቀጥሉ የተደረጉት ደግሞ አምስት የቀድሞ ሚኒስትሮች ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል የትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አንዱ ሲሆኑ፣ በአዲሱ የካቢኔ አደረጃጀት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ በሕዝብ ዘንድ በስፋት የሚታወቁት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነርነታቸው ቢሆንም፣ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ከመምጣታቸው አስቀድሞ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በመቀጠልም በኦሮሚያ ፍትሕ ቢሮ አገልግለዋል፡፡ ለአዲሱ ሥልጣን ከመሾማቸው አስቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ በሕወሓት አባል ብቻ ሲመራ የቆየው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመጀመሪያ ጊዜ ለአጭር ዓመታት በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ተመርቶ የነበረ ሲሆን፣ ከሕወሓት ውጪ ሁለተኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት የኦሕዴድ ተወካዩ ዶ/ር ወርቅነህ ናቸው፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ድረስ በፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ድረስ የትምህርት ዝግጅት አካብተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለቦታው ይመጥናሉ ብለዋቸዋል፡፡

ሌላው በሌላ የሚኒስትርነት ሹመት የካቢኔ አባል ሆነው እንዲቀጥሉ የተደረጉት ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም ናቸው፡፡

ዶ/ር ሽፈራው በቀድሞው ካቢኔ የአካባቢ ደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ ዶ/ር ሽፈራው የደኢሕዴን ፓርቲ አባል ሲሆኑ በአዲሱ ሹመት የትምህርት ሚኒስትር ሆነው በአዲሱ ካቢኔ እንዲቀጥሉ ተደርገዋል፡፡

ዶ/ር ሽፈራው ቀደም ሲል የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በትምህርት ዝግጅታቸው የሕክምና ዶክተር ናቸው፡፡ በ2008 ዓ.ም. የጠቅላይ ሚኒስትሩን ካቢኔ የተቀላቀሉት የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ሌላኛው በአዲሱ ካቢኔ እንዲቀጥሉ የተደረጉ ናቸው፡፡ አቶ ሞቱማ በአዲሱ ካቢኔ እንዲቀጥሉ የተደረጉት የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር በመሆን ነው፡፡

አቶ ሞቱማ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የሠሩት በስታስቲክስ ሲሆን፣ በውኃ አስተዳደር የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ሌላው በአዲሱ ካቢኔ እንዲቀጥሉ የተደረጉት የቀድሞው የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዶ/ር አምባቸው መኮንን ናቸው፡፡

ዶ/ር አምባቸው በአዲሱ የካቢኔ አወቃቀር ውስጥ እንዲቀጥሉ የተደረጉት በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርነት ነው፡፡ ዶ/ር አምባቸው የአማራ መልሶ ማቋቋም ድርጅት ሥራ አስኪያጅና የአማራ ክልል የኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ካገለገሉባቸው የቀድሞ ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በትምህርት ዝግጅቶቻቸውም በኢኮኖሚክስ የትምህርት መስክ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የተማሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢንጂነር አይሻ አህመድ በአዲሱ ካቢኔ እንዲቀጥሉ የተደረጉ ሌላዋ የቀድሞ ካቢኔ አባል ናቸው፡፡ ኢንጂነር አይሻ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትርነታቸው ተነስተው የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነው ተመድበዋል፡፡

ኢንጂነር አይሻ የአፋር ብሔራዊ ክልል ገዥ ፓርቲ አፍዴፓ ተወካይ ሲሆኑ፣ በክልሉ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉና በትምሀርት ዝግጅታቸው ሲቪል መሐንዲስ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ሌላዋ ሴት የቀድሞ ካቢኔ አባል የነበሩትና በአዲሱ አደጃጀትም በሌላ ኃላፊነት እንዲቀጥሉ የተደረጉት ወይዘሮ ደሚቱ ሐምቢስ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ደሚቱ ከቀድሞ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትርነት ተነስተው የሕፃናትና ሴቶች ሚኒስትር ሆነው አዲሱን ካቢኔ ተቀላቅለዋል፡፡

ወይዘሮ ደሚቱ የኦሕዴድ አባል ሲሆኑ በትምህርት ዝግጅታቸው የሕግ ምሩቅ ናቸው፡፡ የቀድሞ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር፣ በመቀጠልም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር፣ እንዲሁም ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ኃላፊነቶች፣ በኋላም የጨፌ ኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ነበሩ፡፡

በሌላ በኩል አዲሱን ካቢኔ እንዲቀላቀሉ የተደረጉና በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ በመቆየት ከሚታወቁት መካከል የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ ይገኙበታል፡፡

አቶ አህመድ ለበርካታ ዓመታት በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ እንዲሁም በአሁኑ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር በሚኒስቴር ዴኤታነት ያገለገሉ ሲሆን፣ አዲሱን ካቢኔ የተቀላቀሉት በትራንስፖርት ሚኒስትርነት ተሹመው ነው፡፡ አቶ አህመድ በትምህርት ዝግጅታቸው ከእንግሊዝ አገር በቢዝነስ ማኔጅመንት የተመረቁ የሶማሌ ብሔር ተወላጅና የክልሉ ፓርቲ ሶዴፓ አባል ናቸው፡፡

ሌላው አቶ ታገሰ ጫፎ ሲሆኑ፣ በአዲሱ ካቢኔ በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት አስተዳደር ሚኒስትርነት ተሹመዋል፡፡ አቶ ታገሰ ለረዥም ዓመታት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፡፡

ሌላው አቶ ከበደ ጫኔ ሲሆኑ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት የንግድ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ በኋላም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በአዲስ ካቢኔ ውስጥ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙ የብአዴን አባል ናቸው፡፡

ቀጣዮቹ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት የተገኙ ናቸው፡፡ እነዚህም ዶ/ር በቀለ ቡላዶ የንግድ ሚኒስትር ሆነው ካቢኔውን የተቀላቀሉ የሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጅ ሲሆኑ፣ በቢዝነስ ሳይንስና ስትራቴጂክ ቢዝነስ ፖሊሲ በዶክትሬት የተመረቁ ናቸው፡፡ በሞሐ ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ ያገለገሉ፣ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የነበሩ፣ የእህል ንግድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በቅርብ መሾማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡

ሌላው አዲሱን ካቢኔ የተቀላቀሉት ደግሞ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ሲሆኑ፣ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ፕሮፌሰር ፍቃዱ ብሔራቸው ኦሮሞ ሲሆን፣ በእንስሳት ሳይንስና በእንስሳት እርባታ፣ እንዲሁም በወተት ልማት መስኮች የተማሩ ናቸው፡፡ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ፣ እንዲሁም የአካዴሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት፣ እስከ አዲሱ ሹመታቸው ድረስ ደግሞ የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኑስትር ሆነው በመሾም ካቢኔውን የተቀላቀሉት ደግሞ ዶ/ር እያሱ አብረሃ ናቸው፡፡ ዶ/ር እያሱ በብሔራቸው ትግራይ ሲሆኑ፣ በዕፅዋት ሳይንስ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙና በትግራይ ክልል በእርሻና በግብርና ዘርፎች ያገለገሉ ናቸው፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ካቢኔውን የተቀላቀሉት ደግሞ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ናቸው፡፡ ዶ/ር ጌታሁን በብሔራቸው ኦሮሞ ሲሆኑ፣ በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ መምህርና ተመራማሪ ሆነው ረዥም ጊዜያቸውን ያሳለፉና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩ ናቸው፡፡

የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ሆነው ካቢኔውን የተቀላቀሉት ዶ/ር ስለሺ በቀለ ሲሆኑ፣ በኃይድሮሊክስ ምህንድስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን የመሠረቱ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የውኃና የአየር ንብረት ባለሙያ፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢኮኖሚና ልማት አማካሪ በመሆን በማገልገል ላይ የነበሩ ናቸው፡፡ የናይል ተፋሰስ ላይ የሠሩ፣ እንዲሁም የግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን ሰብሳቢ ነበሩ፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሆነው ካቢኔውን ለመጀመሪያ ጊዜ የተቀላቀሉት ደግሞ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብሔራቸው አማራ ሲሆን፣ የሕክምና በተለይም የማሕፀን ፅንስ ስፔሻሊስት ናቸው፡፡ በሚኒስትርነት እስኪሾሙ ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲንና የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ በመሆን ሲያገለግሉ ነበር፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር በመሆን ካቢኔውን የተቀላቀሉት ሌላው አዲስ ተሿሚ ደግሞ ዶ/ር ግርማ አመንቴ ናቸው፡፡ ዶ/ር ግርማ ብሔራቸው ኦሮሞ ሲሆን፣ በደን ልማት ዘርፍ በዶክትሬት የተመረቁ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ክልል ደን ቢሮ ኃላፊ የነበሩ፣ የኦሮሚያ የደን ልማት ኢንተርፕራይዝና የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል፡፡

ዶ/ር ሒሩት ወልደ ማርያም ደግሞ ሌላዋ ካቢኔውን በአዲስነት የተቀላቀሉ ሴት አመራር ናቸው፡፡ ዶ/ር ሒሩት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ በብሔራቸው ከምባታ ሲሆኑ በሥነ ልሳንና ቋንቋ ጥናት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በማግኘት በዘርፉ ያስተማሩና የተመራመሩ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን እስከ ሹመታቸው ድረስ ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳው ደግሞ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሆነው ካቢኔውን ተቀላቅለዋል፡፡ አቶ ርስቱ በብሔራቸው ጉራጌ ሲሆኑ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ቢሮ ኃላፊ የነበሩ፣ እንዲሁም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና በክልሎች በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡

ሌላው አዲሱን ካቢኔ የተቀላቀሉት ደግሞ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ሲሆኑ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ዶ/ር ነገሪ በጋዜጠኝነት እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት የትምህርት ክፍል ዲን በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ የትምህርት ዝግጅታቸውም በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና አስተባባሪ፣ አቶ አቡዱልአዚዝ መሐመድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማኅበራት ጉዳዮች አስተባባሪ፣ አቶ ተፈራ ደርበው በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሹመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከመንግሥት የሥልጣን አደረጃጀት ውስጥ ያስወገዱት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪነት ኃላፊቶችን ነው፡፡ በሌላ በኩልም የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሚኒስትርነት አደረጃጀቶችንም አስቀርተዋል፡፡

አሁን የሚፈለገው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በአንድ ጉዳይ የሚያማክር ሳይሆን፣ የፖሊሲና የስትራቴጂክ ጉዳዮች አፈጻጸምን የሚከታተልና የሚያቀናጅ አደረጃጀት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአደራጁት አዲሱ ካቢኔ ውስጥ 18 የሚሆኑት የትምህርት ዝግጅታቸው ዶክትሬት ዲግሪ ሲሆን፣ በርካቶቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪ የነበሩ ናቸው፡፡

ይህንን አስመልክቶም ጠቀላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ፣ ‹‹አገሪቱ አሁን እየገጠሟት ያሉ የመበስበስ ፈተናዎችን ለመፍታት የሙያ ብቃትና ክህሎት ይጠይቃል፤›› ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል፣ እንዲሁም የአመራር ማሠልጠኛ አካዴሚ እንደሚመሠረት ተናግረዋል፡፡

በአዲሱ ካቢኔ የተሾሙ ተሿሚዎች የየትኛውም ብሔር አባል ቢሆኑም፣ ከሹመታቸው ቀን አንስቶ የሚወክሉት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን እንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...