በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው መሠረት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲን በአባልነት ብትቀላቀልም፣ ለፖለቲካ ሥጋቶች ሽፋን የሚሰጠውን የመድን አረቦን ባለመግዛቷ ምክንያት በሰሞኑ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ለደረሰው የንብረት ውድመት ካሳ ማግኘት አለመቻሏ ታወቀ፡፡
ሪፖርተር ባደረገው ማጣራት መሠረት አገሪቱ ምንም እንኳ አባል ለመሆን የሚያስችላትን ቅድመ ሁኔታ ብታሟላም፣ በኢንቨስትመንቶች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለማካካስ የሚሰጡ የመድን ሽፋኖችን አለመግዛቷ ተረጋግጧል፡፡ በአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ ከፍተኛ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ሼሪ ኬኔዲ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ምንም እንኳ ኤጀንሲው ለአገሪቱ የመድን ሽፋን ለመስጠት ዝግጁ ቢሆንም በአገሪቱ የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስና ያስከተለው ጉዳትን ለመሸፈን የሚያስችል አረቦን ባለመግዛቷ ምንም ዓይነት ሽፋን አይሰጥም፡፡
ይሁንና በአሁኑ ወቅት ድርድር ላይ ያሉ የአረቦን ግዥዎች በመኖራቸው፣ እ.ኤ.አ. በዚህ ዓመት ማብቂያ ወይም በሚቀጥለው ዓመት መጀመርያ አካባቢ ተጠናቀው ለአገሪቱ የመድን ሽፋን መስጠት እንደሚጀመር ሚስተር ኬኔዲ አስረድተዋል፡፡ ይሁንና የመድን ሽፋን የሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ወደፊት የሚፈጸሙት እንጂ፣ ወደኋላ በመሄድ ጉዳት የደረሰባቸውን ኤጀንሲው እንደማይሸፍን አረጋግጠዋል፡፡
በአገሪቱ የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት መጠን እንዲያጠና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መመርያ ተሰጥቶታል፡፡ ኤጀንሲው ከልማት ባንክ ጋርም ሆነ ከሌሎች ባንኮች ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ በአራት ዋና ዋና መስኮች ላይ የመድን ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን፣ የፖለቲካ ሥጋት መድን ወይም የኢንቨስትመንት ኢንሹራንስ የሚለው ይገኝበታል፡፡ የንግድ መድን ሽፋን በአብዛኛው ለግል ዘርፍ ተበዳሪዎች የተሰጡ ብድሮች አመላለስ ላይ ሥጋት ሲያጋጥም የሚሰጥ የመድን ሽፋን ነው፡፡ በፖለቲካ ግጭት ወቅት፣ በሽብር ጥቃት፣ እንዲሁም በአሻጥር ምክንያት የሚደርሱ ጉዳቶች ላይ የመድን ሽፋን ይሰጣል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ ለባንኮችና ለመድን ድርጅቶችም የቦንድ ሽፋን የሚሰጥበት አሠራር ሲኖረው፣ በአብዛኛው በጠለፋ ዋስትና አማካይነት ድጋፍ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ባገኘችው 7.5 ሚሊዮን ዶላር ብድር አማካይነት ከአፍሪካ ኢንሹራንስ 75 አክሲዮኖችን በመግዛት አባል መሆኗ ይታወሳል፡፡ ቤኒን፣ ቡሩንዲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ዛምቢያ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የኤጀንሲው አባል አገሮች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2003 ጀምሮ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኤጀንሲው 17 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የንግድና የኢንቨስትመንት የመድን ሽፋኖችን መፈጸሙ ታውቋል፡፡