Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር እየፈጠረ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብ ዝግጅት ዘርፍ ከውጭ ያስገባቸው የነበሩ የእርሻ ምርቶችን በመተው ከአገር ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች በመግዛት፣ ለአምራቾች ማኅበራት ገበያ መፍጠሩና የውጭ ምንዛሪም በማዳን ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

አየር መንገዱ በ20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ የበረራ ምግብ ማደራጃ ማዕከል ጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ባስመረቀበት ወቅት ንግግር ያደረጉት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የምግብ ማዘጋጃ ማዕከሉ አትክልትና ፍራፍሬ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኘው ከመቂ ባቱ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች የኅብረት ሥራ ዩኒየን ጋር አብሮ መሥራት መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበሩ ለአየር መንገዱ ትኩስ አትክልትና ፍራፍሬ በማቅረብ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ተወልደ፣ አዲስ የተገነባው ግዙፍ የምግብ ማደራጃ ማዕከል በቀን ከ100,000 በላይ ማዕዶች የማዘጋጀት አቅም ያለው በመሆኑ ለኅብረት ሥራ ማኅበሩ ትልቅ ገበያ መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓላማችን ግን ከዚህም ያለፈ ነው፡፡ ለአርሶ አደሮቹ ሥልጠና በመስጠት ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የግብርና ውጤቶችን እያመረቱ ወደ ውጭ እንዲልኩ አስፈላጊውን እገዛ እናደርግላቸዋለን፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ አርሶ አደሮቹ በጎረቤት አገሮችና በመካከለኛው ምሥራቅ ገበያ በማፈላለግ አየር መንገዱ እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡

ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር በኢትዮጵያና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ትልቅ ፈተና እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ አየር መንገዱ በዚህ ረገድ የበኩሉን ለመወጣት ከአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን አካዳሚ በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በመገንባት በየዓመቱ አንድ ሺሕ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የመቂ ባቱ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች የኅብረት ሥራ ዩኒየን 150 መሠረታዊ ማኅበራትና 8,360 አርሶ አደር አባላትን ያቀፈ ነው፡፡ የማኅበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጫላ ጉሬና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቱሬ ቃሲም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ከሰኔ 2007 ዓ.ም. አብሮ መሥራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከፍተኛ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ እንደ ኃላፊዎቹ ገለጻ አየር መንገዱ የማኅበሩ አባላት ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የማምረት ሒደት ላይ ሥልጠና እንዲያገኙ አድርጓል፡፡

በአሁኑ ወቅት ማኅበሩ ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ፎሶሊያ፣ ጥቅል ጐመን፣ ደበርጃንና ፓፓዬ ለአየር መንገዱ ምግብ ዝግጅት ክፍል በቀጥታ በማቅረብ ላይ መሆኑን፣ በሳምንት 200 ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬ ለአየር መንገዱ በማቅረብ በወር ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሽያጭ ገቢ በማግኘት ላይ መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በመካከላችን ነጋዴዎችና ደላሎች ሳይገቡ በቀጥታ ለአየር መንገዱ ማቅረብ በመቻላችን በከፍተኛ መጠን ተጠቃሚ ሆነናል፤›› ብለዋል፡፡

ማኅበሩ ሁለት የአትክልትና ፍራፍሬ ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው መጋዘኖች ያሉት ሲሆን፣ በቀጣይ ለአየር መንገዱ የሚያቀርበውን ምርቶች ለመጨመር በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዎቹ፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን ምርቶች በማምረት ወደ ኤክስፖርት ገበያ ለመግባት የኤክስፖርት ፈቃድ አውጥተው በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ ከሆርቲካልቸር ላኪዎች ማኅበር ጋር የሚሠራ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ገበያ ምርቶችን ለኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት፣ ለአዳማና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ያቀርባል፡፡

በኦሮሚያ ክልል አርሲና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች በስድስት ወረዳዎች የሚንቀሳቀሰው መቂ ባቱ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራሪቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን፣ በ1994 ዓ.ም. በ12 መሠረታዊ ማኅበራት 500 አርሶ አደሮችን በአባልነት በመያዝ በ500,000 ብር የመነሻ ካፒታል ሥራውን ጀምሮ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ወደ 64 ሚሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ የመሠረታዊ ማኅበራት ቁጥር 150፣ የአርሶ አደሮች ቁጥር 8,360 ደርሷል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብ ዝግጅት ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሀብቱ አየር መንገዱ ከመቂ ባቱ የአትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ጋር አብሮ በመሥራቱ ትኩስና ኦርጋኒክ ምግቦችን ለመንገደኞቹ ማቅረብ እንዳስቻለው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አየር መንገዱ በተቻለ መጠን የአገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀም እንደሚፈልግ የገለጹት አቶ አክሊሉ፣ የአገር ውስጥ አምራቾች በሚፈለገው ጥራትና ብዛት የማምረት የአቅም ውስንነት እንዳለባቸው ጠቅሰው በቀጣይ አየር መንገዱ ተከታታይ ሥልጠናዎች በመስጠት አቅማቸውን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር የብድር አገልግሎት የሚያገኙበትን መንገድ ለመፈለግ መታሰቡን ገልጸው፣ የውጭ ገበያ በማፈላለግ ረገድም አየር መንገዱ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ ወቅት ለሚያቀርባቸው ምግቦች ግብዓት አትክልትና ፍራፍሬ ከኬንያና ደቡብ አፍሪካ፣ የተበለተ ዶሮ ሥጋና ዓሳ ከደቡብ አፍሪካና ከአውሮፓ አገሮች ያስገባል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብ ማደራጃ ዘርፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት ጣሊያናዊው ሚስተር ጋታኖ ክርስቲያኖ፣ ከአገር ውስጥ በሚቀርቡ የግብርና ውጤቶች ደስተኛ መሆናቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከኦሮሚያ ክልል በሚቀርበው ትኩስና ኦርጋኒክ አትክልትና ፍራፍሬ ጥራት ደረጃ እረክቻለሁ፡፡ የተበለተ ዶሮም ከአገር ውስጥ መግዛት ጀምረናል፡፡ የአገር ውስጥ አምራቾች የሚያቀርቡትን ምርቶች መጠን መጨመር ይኖርባቸዋል፡፡ የጥራት ደረጃው እንደተጠበቀ ሆኖ፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የምግብ ዝግጅት ዘርፍ 700 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በመጪው ጥቂት ዓመታት ተጨማሪ 200 የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ‹‹ይህ በቀጥታ የፈጠርነው የሥራ ዕድል ነው፡፡ በአቅራቢዎቻችን በኩል በሺዎች የሚቆጠሩ የሥራ ዕድሎች ፈጥረናል፤›› ብለዋል አቶ አክሊሉ ሀብቱ፡፡

የኢትዮጵያ የቪየሽን አካዳሚ የምግብ ዝግጅት ማሠልጠኛ ማዕከል ያቋቋመ ሲሆን፣ ለጀማሪ የምግብ ዝገጅት ሠራተኞች ሥልጠና ከመስጠቱም በላይ ለነባር ሠራተኞችም የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ20 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስገነባው ዘመናዊ የምግብ ማደራጃ የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች፣ የቻይና፣ ጣሊያን፣ ሀላልና ሌሎች ዓለም አቀፍ ማዕዶችን ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የማዘጋጀት ብቃት እንዳለው ተገልጿል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ የተገነባው ነባሩ የምግብ ማደራጃ በቀን 36,000 ማዕዶች የማዘጋጀት አቅም የነበረው ሲሆን ዘመናዊ የማብሰያ፣ ማቀዝቀዣና ማጠቢያ ማሽኖች የተገጠሙለት አዲሱ የምግብ ማደራጃ በቀን 100,000 ማዕዶችን የማዘጋጀት አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በቀን ለአየር መንገዱ ለ240 በላይ በረራዎች 40,000 ማዕዶች ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም ለቱርክና ለቻይና አየር መንገዶች ምግቦች የሚያቀርብ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ለሚበሩ ቻርተርና ቪአይፒ በረራዎች ምግብና መጠጦች ያቀርባል፡፡ በቀጣይ ለሌሎች ወደ አዲስ አበባ ለሚበሩ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ምግብ ለማቅረብ በጨረታ ሒደት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በነደፈው የራዕይ 2025 የዕድገት መርሐ ግብር ከምግብ ዝግጅት 50 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ ለማግኘት አቅዷል፡፡

  

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች