Saturday, June 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በባህር ዳር እየተገነባ ያለው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ማኔጅመንት ለሒልተን ኢንተርናሽናል ተሰጠ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተለያዩ ንግድና ኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይ የተሰማራው በላይነህ ክንዴ አስመጭና ላኪ ድርጅት፣ በባህር ዳር ከተማ እየገነባ የሚገኘውን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ማኔጅመንት ለሒልተን ኢንተርናሽናል ሰጠ፡፡

ባለፈው ሳምንት የንግድና ኢንቨስትመንት ኩባንያ የሆነው በላይነህ ክንዴ ከሒልተን ኢንተርናሽናል ጋር ተፈራርሟል፡፡

ኩባንያው ቀደም ሲል ከሚታወቅባቸው የአስመጪና ላኪ ንግድ ሥራዎች በተጨማሪ በሆቴል አንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግና በእርሻ ሥራዎች ዘርፍ በጥልቀት ገብቷል፡፡

ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ሦስተኛውን ባለኮከብ ሆቴል ከአዲስ አበባ በ549 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባህር ዳር ከተማ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለበላይነህ ክንዴ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ፕሮጀክት የሚሆን ዓባይ ወንዝ ከጣና ሐይቅ በሚወጣበት መስመር፣ ከአማራ ክልል ምክር ቤት አጠገብ 47 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ሰጥቷል፡፡ ኩባንያው በዚህ ቦታ ላይ በ9,400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ የሆቴል ግንባታ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታው ሥራ አፈጻጸም 60 በመቶ መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡    

የኩባንያው ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ በላይነህ ክንዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እየተገነባ ያለው ሆቴል አንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል የሚይዛቸውን አገልግሎቶች በሙሉ ያካተተ ነው፡፡ ሆቴሉ 200 የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት የባህር ዳር ከተማ በዓባይ ዳር እስከ ጢስ ዓባይ ድረስ ለመገንባት ካቀደው ናይል ማራቶን የመሮጫ ትራክ ጋር የተጣጣመ ነው፡፡

‹‹እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የሆቴል ግንባታው ተጠናቆ ወደ ማጠናቀቂያ ሥራ ይገባል፤›› በማለት ሆቴሉ ያለበትን ደረጃ አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡

ሆቴሉ በአጠቃላይ 800 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ዲዛይኑን አባ አርክቴክት ኩባንያ ነው የሠራው፡፡ ሒልተን ኢንተርናሽናል በዲዛይኑ ላይ ያቀረባቸው ሐሳቦች እንደተካተቱ አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡ ግንባታውን የሆቴሉ ባለቤት እህት ኩባንያ በላይነህ ክንዴ ኮንስትራክሽን እያካሄደው መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ግዙፍ ሆቴል በተጨማሪ በላይነህ ክንዴ በአዲስ አበባ ከተማና በአዳማ ከተማ የሁለት ሆቴሎች ባለቤት ነው፡፡

የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ንብረቶች የነበሩት አዳማ ራስ ሆቴልን በ41 ሚሊዮን ብር፣ አዲስ አበባ የሚገኘውን ኢትዮጵያ ሆቴል በ94 ሚሊዮን ብር በመግዛት የሁለት ሆቴሎች ባለቤት በመሆን ወደ ሥራ የገባው በላይነህ ክንዴ፣ በሁለቱም ሆቴሎች አዳዲስ ፕሮጀክቶች ቀርጿል፡፡

አዳማ ራስ ሆቴልንና ኢትዮጵያ ሆቴልን ከመንግሥት እንደተረከበ 30 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ተጨማሪ እድሳት በማድረግ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በአዳማ ራስ ሆቴል ላይ ተጨማሪ 175 ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ እየተገነቡ ያሉት ሁለት ባለስድስትና ባለሰባት ፎቅ ሕንፃዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አቶ በላይነህ ገልጸዋል፡፡

‹‹ግንባታው ሲጠናቀቅ አዳማ ራስ ተጨማሪ መቶ መኝታ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡ ደረጃውም አራት ኮከብ ሆቴል ይሆናል፤›› ሲሉ የድርጅታቸውን ዕቅድ አስረድተዋል፡፡

አቶ በላይነህ ክንዴ በያዙት ዕቅድ ይዞታቸው የሆነውን ኢትዮጵያ ሆቴልና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሊዝ ድርድር ያገኙት በአሁኑ ወቅት በጎ አድራጎት እየተባለ የሚጠራውን ሕንፃ በማፍረስ፣ 63 ፎቅ ከፍታ ያለውን ግዙፍ ሆቴል መገንባት ነው፡፡ ይህ ዕቅድ ግን ከበጎ አድራጎት ሕንፃ ነዋሪዎች ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ የከተማው አስተዳደር ከበላይነህ ክንዴ የቀረበለትን ግዙፍ ፕሮጀክትና የበጎ አድራጎት ሕንፃን ጠቀሜታ በማነፃፀር ተቃውሞውን ውድቅ በማድረግ፣ በቅርቡ ሕንፃው ፈርሶ ቦታውን ለሆቴሉ ግንባታ ለማስረከብ በድጋሚ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

አቶ በላይነህ እንደገለጹት የአዋጭነት ጥናቱ ተጠናቋል፡፡ ሆቴሉን የሚያስተዳድር ዓለም አቀፍ ኩባንያ ለመምረጥም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሆቴል 300 ሠራተኞችን ወደ ባህር ዳርና አዳማ ሆቴሎች የማዛወር ዕቅድ ተይዟል፡፡ ‹‹ወደ እነዚህ ከተሞች መሄድ ያልፈለገ ሠራተኛ ካለ ደግሞ የአገልግሎት ክፍያ ተሰጥቶት ይሸኛል፤›› ብለዋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች