[ክቡር ሚኒስትሩ በአዲሱ ሹመት ውስጥ ባለመካተታቸው ተበሳጭተው ከባለቤታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ምንድነው ብስጭትጭት ያደረገህ?
- እንዴት አልበሳጭ?
- ካልተሾምክ ምን ታደርገዋለህ ታዲያ?
- የእኔ ውለታ ይኼ ነው?
- የምን ውለታ?
- ለድርጅቴ ብትይ ለመንግሥት ብትይ የሠራሁት ውለታ?
- ድንቄም ውለታ፡፡
- ምን ማለትሽ ነው?
- አንተን ብሎ ባለውለታ?
- አንቺም እንዲህ ትያለሽ?
- አንዳንዴ እውነቱን እንነጋር እንጂ፡፡
- የምን እውነት?
- በሹመትህ ዘመን ምን ሠራህ?
- እኔ?
- እኔ ነኝ ታዲያ?
- እንዴት ምን ሠራህ ትይኛለሽ?
- ከአገልግሎትህ ይልቅ ያጋበስከው ጥቅም የትና የት ነው፡፡
- በምን? በምን?
- በውጭ ጉዞ ብትል ከአፍሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ አሜሪካ ምኑ ቅጡ. . .
- እሺ?
- ከጉዞ አበል እስከ ክብር መጠበቂያ በዩሮ፣ በዶላር. . .
- ሌላስ?
- በመንግሥት ወጪ በውድ ሆቴሎች መንፈላሰስ፡፡
- ከዚያስ?
- ከፕራዶ እስከ ቪኤይት በየዓይነቱ፡፡
- ህም. . .
- የሚዥጎደጎድልህ ሥጦታና ገፀ በረከት በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡
- ሆሆ. . .
- በዚያ ላይ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚገኘው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ኮሚሽን፡፡
- ወይ ጉድ?
- በተለያዩ ዘመዶችህ ስም ሕንፃዎች፣ ሞሎች፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ጂሞች. . .
- ኧረ አንቺ ሴትዮ ዝም በይ፡፡
- እኔማ ዝም ብዬ ነው የኖርኩት፡፡
- አሁን ይኼን ሁሉ የሚያስለፈልፍሽ ምንድነው?
- አንተ ነሃ፡፡
- እኔ ምን ሆንኩ?
- ለምን አልተሾምኩም ብለህ ስትበሳጭ ነዋ?
- ምን ልበል ታዲያ?
- እንኳንም ሹልክ ብዬ ወጣሁ ነው ማለት ያለብህ፡፡
- ለምን?
- አላርፍ ካልክ የሚከተለውን አታውቅም ማለት ነው?
- ምን እንዳይመጣ?
- ተረቱን አታውቀውም?
- ምን የሚባለውን?
- ‹የአንበሳ ትራፊ አይጥ በልታ በልታ፣ አመጣች ነገሯን ጎትታ ጎትታ› የሚባለውን፡፡
- ምን ለማለት ነው?
- ካላረፍክ ዋ!
- ምንድነው እሱ?
- እጅህ ላይ ያጠልቁልሃል፡፡
- የወርቅ ብራስሌት?
- አይይ. . .
- ምንድነው ታዲያ?
- ካቴና!
[ክቡር ሚኒስትሩ እንደተሰባጩ ወደ ቢሯቸው እየሄዱ ከሾፌራቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር?
- አቤት፡፡
- የእኔ ጉዳይ ምን ሊሆን ነው?
- አንተ ደግሞ ምን ሆንክ?
- እርስዎ ከሥልጣንዎ ተነሱ ማለት አይደል?
- ማን ነገረህ እሱን?
- አሁን ባረጋግጥም ቀደም ሲል ሠራተኛው ሁሉ ይኼንን አይደል እንዴ ሲያወራ የከረመው?
- ቀድሞ ከየት ሰማው?
- በዚህ ዘመን ወሬ ከየት መጣ አይባልም እኮ?
- ፌስቡክ በተዘጋበት በዚህ ጊዜ የእኔ መነሳት ወሬ ከየት መጣ?
- ፌስቡክ ቢዘጋም ወሬው ግን በእግሩ መጥቷል፡፡
- አንተ ከየት ሰማህ?
- ሠራተኞች ክበብ ውስጥ ሲወራ፡፡
- ምን ተባለ?
- ክቡር ሚኒስትሩ ተንሳፈፉ፡፡
- የሚያንሳፍፍ ያንሳፋችሁ፡፡
- እኔ ግራ የገባኝ የራሴ ጉዳይ ነው፡፡
- አንተ ምን ትሆናለህ?
- እርስዎ ከተባረሩ ማለቴ ከተነሱ አለቀልኝ፡፡
- እንዴት?
- የሚወራውማ ሌላ ነው፡፡
- ምን ተባለ?
- እርስዎ ከተጫሩ እኔም መውረዴ ነው፡፡
- ከምንድነው የምትወርደው?
- ከቪኤይት ነዋ፡፡
- ከዚያስ?
- ጠቅላላ አገልግሎት ሊወሽቁኝ ነው ተብሏል፡፡
- ወይ ጣጣ?
- ሞተሩ እንደ ወፍጮ የሚጮህ አሮጌ ፒካፕ ላይ መመደቤን ሰምቻለሁ፡፡
- እኔ ሳላውቅ ይኼ ሁሉ ከምኔው ተወሰነ?
- እርስዎ ጥቅም የሚያስገኙ ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ብቻ ሲሯሯጡ ሌላውን እኮ አያውቁትም ነበር፡፡
- ማለት?
- ማለትማ እንደሌሉ ነበር የሚቆጠረው፡፡
- እንዴት?
- ለዚህም እኮ ነው የሚንሳፈፉት፡፡
- አንተ ምን እያልክ ነው?
- እየተባለ ያለውን ነው የደገምኩልዎት፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ የበለጠ እየተናደዱ ቢሮአቸው ገብተው ጸሐፊያቸውን ጠሯት]
- አንቺ ምን እየተከናወነ ነው ያለው፡፡
- ኧረ ጉድ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው ጉዱ?
- ልክ እንደ እግር ኳስ ቡድን ነው የሆነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አዲስ ፎርሜሽን ተሠራ እየተባለ ነው፡፡
- የምን ፎርሜሽን?
- በፊት የነበረው 4-4-2 ፎርሜሽን ተለውጧል፡፡
- እና ምን ሆነ ታዲያ?
- አሁን 3-5-2 ሆኗል ተብሏል፡፡
- ምን ማለት ነው?
- በጥልቀት ማጥቃት የሚያስችል፡፡
- ከጥልቅ ተሃድሶ ጋር ይገናኛል?
- እንዲያ ነው አሉ፡፡
- ይኼንን ከእኔ ጋር ምን ያገናኘዋል?
- እርስዎ ቻው ከተባሉ አሠላለፉ እንዲህ ነው እየተባለ ነው፡፡
- ማን ነው የነገረሽ?
- አማካሪዎ፡፡
- እሱም እየዶለተብኝ ነበር እንዴ?
- አሠላለፍን መቀየር ብቻ ሳይሆን ማሊያ መቀየርም ተጀምሯል፡፡
- እኔን ከዳኝ ማለት ነው?
- መሰለኝ፡፡
- በምን አወቅሽ?
- የሆነ ጥቅስ ሲያነበንብ ነበር፡፡
- ምን የሚሉት ጥቅስ?
- ‹በሚሰጥም ጀልባ ማንም አይሳፈርም› የሚል፡፡
- ምን አልሽ አንቺ?
- እኔ አይደለሁም ያልኩት፡፡
- ያንቺስ አቋም ምንድነው?
- ከተጨባጭ ሁኔታው አንፃር የተቃኘ ነው፡፡
- ምን ማለት ነው?
- እኔ ደግሞ አንድ አባባል ደስ ይለኛል፡፡
- ምንድነው እሱ ደግሞ?
- ‹ሁለት ባላ ትከል አንዱ ሲሰበር ሌላው ላይ ተንጠልጠል› የሚል፡፡
- እና?
- እናማ አሳዘኑኝ፡፡
- አሳዝኜሽስ?
- አማካሪዎት እንዳለው መሆኑ ነው፡፡
- ምንድነው የሚሆነው?
- አዲሱን ፎርሜሽን በአዲሱ ማሊያ መቀላቀል፡፡
- በቃ?
- ምን ይደረግ እንግዲህ?
- ወይ ሰው?
- ቀበሮም እንዲህ ነው ያለችው፡፡
- ምን አለች?
- ‹ለሰው ሞት አነሰው›፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ተናደው በትካዜ ውስጥ እንዳሉ አንድ የሚያውቁት ባለሀብት ደወለላቸው]
- ክቡር ሚኒስትር ምንድነው የምሰማው?
- ምን ሰማህ?
- ተንሳፋፉ መባልን፡፡
- ይኼ ቃል ከየት ነው የተሠራጨው?
- ምኑ?
- መንሳፈፍ የሚባለው?
- መባረር ከሚባለው ይሻላል ተብሎ ነው፡፡
- አንተም እንዲህ አልክ?
- ምን ልበል ታዲያ?
- ትንሽ ኃፍረት የለህም?
- ለምን የሚሆን?
- ይሉኝታ፡፡
- ይሉኝታ ድሮ ቀረ፡፡
- በምን ተተካ?
- በአማራጭ ፍለጋ፡፡
- ምን ዓይነት አማራጭ?
- ከወቅቱ ጋር መራመድ፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አሮጌውን ሸኝቶ አዲሱን ማላመድ፡፡
- በዚህ ነው የተካንከው፡፡
- ይኼንንማ እርስዎ ከእኔ በላይ ያውቁታል፡፡
- እንዴት እባክህ?
- ያኔ ጨረታዎቹን እንደ ካርታ እየፐወዙ ሲጫወቱብን ነዋ፡፡
- አሁን እየተካካድን ነው ማለት ነው?
- አዎን፡፡
- ስለዚህ?
- ያው እንግዲህ እኔም በጨረታው አልገደድም፡፡
- ምን ለመሆን?
- ከእርስዎ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ለማቋረጥ፡፡
- ይዝጋህ!
- እርስዎም እንዳይዘጋብዎት፡፡
- የት ነው የሚዘጋብኝ?
- ቅሊንጦ!
[ክቡር ሚኒስትሩ እንዲሁ ሲጨሱ እንደዋሉ የማታ ማታ ቤታቸው ደርሰው ከልጃቸው ጋር ማውራት ጀመሩ]
- ዳዲ ምን ሆነሃል?
- ምን ሆንኩ?
- ፊትህ?
- ፊቴ ምን ሆነ?
- ጥለኸዋል፡፡
- ምን ማለት ነው?
- አኩርፈሃል፡፡
- የሆነ ነገር አበሳጭቶኝ ነው፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ከሥልጣኔ ተነሳሁ፡፡
- ሶ ዋት?
- አያናድድም?
- ኧረ ዳዲ አትቀልድ፡፡
- ለምን?
- ብዙ ነገር ቀለለልህ፡፡
- ለምሳሌ?
- ስኳር፡፡
- ምን?
- ደም ግፊት፡፡
- እ. . . ?
- ኮሌስትሮል፡፡
- ምንድነው የምትይው?
- ከበሽታ ዓይነቶች ትገላገላለህ፡፡
- በቃ እንዲህ ብቻ ነው የምታስቢው?
- ዋናው ጤና ነው ዳድ፡፡
- አንቺ ምን አለብሽ?
- ኧረ ዳድ አታካብድ፡፡
- ለምንድነው የማላካብደው?
- ከጤናህ በላይ ሌላም ችግር አለ፡፡
- የምን ችግር?
- የአንተ ነገር መጣራት ቢጀመር እኮ ብዙ ችግር ይፈጠራል፡፡
- ምን ስለሆነ?
- ዳድ ታውቀዋለህ፡፡
- ምኑን ነው የማውቀው?
- እስከ ዛሬ የሠራኸውን፡፡
- ምን ሠራሁ?
- ከሠራኸው ይልቅ ያልሠራኸውን ብቆጥር ይቀለኛል፡፡
- በምን አወቅሽ?
- ሁሉንም ነገር አውቃለሁ፡፡
- ለምሳሌ?
- ሥልጣንህን ለምን ተግባር እንደተጠቀምክበት፡፡
- እና ከሥልጣን መነሳቴ ትክክል ነበር?
- ኧረ በእሱ በተገላገልክ?
- ምን እንዳይመጣ?
- የሚመጣውን ለመተንበይ ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡
- እንቺ ልጅ ምን እያልሽ ነው?
- እኔማ የምልህ ሪያሊቲውን አትሽሽ ነው፡፡
- እና?
- እናማ ውጤቱን በፀጋ መቀበል ነው ያለብህ፡፡
- የምኑን ውጤት?
- የመባረሩን፡፡
- ምን አልሽ አንቺ?
- ማለቴ የመንሳፈፉን፡፡
- ምን?
- ገብቶሃል፡፡
- ባይገባኝስ?
- አፉን ከፍቶ ይጠብቅሃል፡፡
- ምንድነው የሚጠብቀኝ?
- ታውቀዋለህ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- ሸቤ!