Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ችግሮች መፍትሔ ይሰጥ ዘንድ የተጠራው ጉባዔ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰኞ ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. የአገሪቱን የንግድ ኅብረተሰብ እንደሚወክሉ የታመነባቸውና የሁሉም የአገሪቱ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች መሪዎችና ተወካዮች ለአስቸኳይ ስብሰባ በሒልተን ሆቴል ተገኝተዋል፡፡ ተወካዮቹ በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን የሚያዋቅሩ ወይም ያዋቀሩ የ18ቱ የንግድና የዘርፍ ምክር ቤቶችን ወክለው የተገኙ ናቸው፡፡ ባልተለመደ ሁኔታ ሁሉም በአንድነት ታድመው የተሰባሰቡበት ዋነኛ ምክንያትም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ይቻል ዘንድ ምክረ ሐሳብና ውሳኔያቸው ተፈልጎ ነው፡፡

ወትሮም ምርጫ በደረሰ ቁጥር ትርምስ የማያጣው ንግድ ምክር ቤቱ፣ ገጠሞታል የተባለው ችግር አሁንም ከምርጫ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይኸውም ወቅቱን ጠብቆ መካሄድ የነበረበትን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ለማካሄድ ያላስቻለ በመሆኑ መሥራች ንግድ ምክር ቤቶቹ ለስብሰባ መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም ከአራቱም የአገሪቱ ክፍሎች ተሰባስበው መጥተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአመራር ቦታ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ የሥልጣን ዘመኑ ያበቃ መሆኑም፣ ቀጣዩ ጉዞ ምን ይሁን የሚለው ጥያቄ መፍትሔ የሚሻ በመሆኑ ተሰብሳቢዎቹ ይህንን ጉዳይም ይመለከታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን እንዳካሂድ እንቅፋት ተፈጥሯል በማለት የዕለቱ ስብሰባ እንዲጠራ ካስገደዱ ጉዳዮች መካከል የተወሰኑ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ መወከል በሚችሉበት ደረጃ የሥር ምርጫ ሳያካሂዱ መገኘታቸው አንዱ ነው፡፡ ሌሎች ምክር ቤቶች፣ ባለፈው ዓመት በጠቅላላ ጉባዔ የፀደቀውን ገዥ መተዳደርያ ደንብ በመጣስ፣ የምርጫ ሒደትና ውጤቱን ያጸደቁበት መንገድም ሕግና ደንብን የጣሰ ነው የሚል አቤቱታና ክስም ቀርቦባቸዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ ሕጋዊ ሊሆን አለመቻሉ መፍትሔ ያስፈልገዋል በመባሉ ጠቅላላ ጉባዔው ተጠርቷል፡፡

ሌሎች የንግድ ምክር ቤቶች መሪዎች የሥራ ዘመኑ የተጠናቀቀው ቦርድ ባለፈው ዓመት ያፀደቀው ደንብ በተገቢው መንገድ ምክክር ስላልተደረገበት አንቀበለውም ማለታቸውም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነበር፡፡ ‹‹በራሳችን መንገድ ምርጫ አካሂደናል፤›› በማለታቸውም ልዩነት ተፈጥሯል፡፡ ይህ ልዩነት እየሰፋ በመሄዱም 18ቱ ንግድ ምክር ቤቶች ጉዳያቸውን ወደ ንግድ ሚኒስቴር ይዘው በመሄድ መፍትሔ ይሰጠን እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ከሕግና ከደንብ ውጭ ምርጫ ያካሄዱ ካሉ የማጣራቱን ሥራ እንደሚሠራ ያስታወቀው ንግድ ሚኒስቴር ቢሆንም፣ በንግድ ምክር ቤቶቹ መካከል የተፈጠረውን ልዩነት ለመመልከት መንግሥት ጣልቃ ከመግባት ተቆጥቦ በመጀመሪያ 18ቱ አባል ምክር ቤቶች ችግራቸውን በራሳቸው መንገድ እንዲፈቱ ማሳሰቡ ይታወሳል፡፡ ሰኞ፣ ጥቅምት 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ስብሰባ እንዲጠራና ለመፍትሔ ፍለጋ ምክክር እንዲደረግ ያስገደደው ሌላው ምክንያት ይኼው የሚኒስቴሩ ማሳሰቢያ እንደሆነም ይታመናል፡፡

የሒልተኑ ስብሰባና የፕሬዚዳንቱ ገለጻ

ለንግድ ምክር ቤቱ ቀጣይ ጉዞ መፍትሔ እንዲሰጥ የተጠራውን የሰኞውን ስብሰባ የመሩት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ያላስቻሉ ችግሮች በማጋጠማቸው ሳይካሄድ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ እርሳቸው የሚመሩት ቦርድ ጥቅምት 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ጥሪ አስተላልፎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም ጥሪው ከመደረጉ በፊት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ 18ቱ አባል ምክር ቤቶች በአዋጁና በሕገ ደንቡ መሠረት አስፈላጊውን መሥፈርት አሟልታችሁ ለጽሕፈት ቤቱ አቅርቡ በማለት ጤናማና ሕጉን የተከተለ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲካሄድ ደብዳቤዎች ቢጽፉም፣ ከአንዳንድ አባል ንግድ ምክር ቤቶች የተላኩት መረጃዎች ግን ክፍተት እንደታየባቸው ተናግረዋል፡፡

ከተወሰኑ ንግድ ምክር ቤቶች የተላከውን መረጃ መሠረት በማድረግ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ከሚያስፈልገው መሥፈርት ዝቅተኛው ተሟልቷል ወይ? ተብሎ ሲጠየቅም ግድፈቶችና ጉድለቶች በመታየታቸው፣ ይህ በሆነበት አኳኋን ጠቅላላ ጉባዔውን ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውም አብራሩ፡፡ ሕጉን ያልተከተሉ ጉዳዮች እያሉ ጠቅላላ ጉባዔውን መጥራት በሕግ ተጠያቂ ያደርጋል፣ ጥሰት ታይቷል እየተባለ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ አግባብ ስላልሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ መፍትሔ ለመፈለግ የዕለቱ ስብሰባ እንደተጠራ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደርያ ደንብም ሆነ በአዋጁ መሠረት አግባብነት የላቸውም የተባሉ የአፈጻጸም ችግሮች ስለነበሩ፣ አቶ ሰሎሞን የሚመሩት ቦርድም የሥልጣን ዘመኑ ስላለቀ እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ መስጠት አስቸግሮት ቆይቷል፡፡ ‹‹እኛ የኃላፊነት ዘመናችን መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አብቅቷል፤›› ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ የሥልጣን ጊዜው ያበቃው ቦርድ እንዴት ነው የሚቀጥለው? ኃላፊነቱን የሚያስረክበውስ እንዴት ነው በሚለው ነጥብ ላይ ተወያይተው የዕለቱ ተሰብሳቢዎች ውሳኔ ያስተላልፉ በማለት በስብሰባው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጉባዔቶቹ ጉራማይሌ ምላሽ

የስብሰባው ዓላማ ከተገለጸ በኋላ ተሳታፊዎች አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በዕለቱ የተሰበሰቡት 18ቱ ምክር ቤቶች የሚሳልፉት ውሳኔ ሕጋዊ ነው አይደለም የሚሉት ሐሳቦችም አከራክረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ንግድ ምክር ቤቱን በሕጋዊ መንገድ ለማስጓዝና ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ እንቅፋት የሆኑት ችግሮች ተጣርተው እንዲወጡ መወሰን ግዴታቸው መሆኑ ስምምነት ተደርስበታል፡፡

18ቱ ምክር ቤቶች መሰባሰባቸው የጠቅላላ ጉባዔውን ኃላፊነት ይወስዳሉ ማለት እንዳልሆነ የገለጹት የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ለመጥራት የሚያስገድዱ ችግሮች በመፈጠራቸው ለዚህ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

‹‹ምርጫን በተመለከተ የቀረቡትን እክሎችና አሉ የተባሉትን ችግሮች ተሸክሞ መጓዝ ምክር ቤቱን እንደማፍረስ  የሚቆጠር ስለሆነ የተጠቀሱትን ችግሮች ፈትሾ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፤›› በማለት ያቀረቡት ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ከክልልና ከዘርፍ ምክር ቤቶች ጋር መክሮ እንደማያውቅ፣ ነገር ግን አሁን ያጋጠመውን ችግር እንዲፈቱለት መጥራቱን በመንቀፍ አስተያየታቸውን የሰጡት የትግራይ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ‹‹ሲቸግራችሁ ስለጠራችሁን እናመሰግናለን፤›› በማለት ኢትዮጵያ ቻምበርን ወቅሰዋል፡፡ ነገር ግን ያሉበትን ችግሮች መፍታት ግድ በመሆኑ ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት መፍትሔ ማፈላለጉ ላይ መሠራት አለበት በማለት ተሰብሳቢዎች መፍትሔ ፍለጋው ላይ እንዲረባረቡ አቶ አሰፋ አሳስበዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ሕግና ደንብን በተከተለ መንገድ ጠቅላላ ጉባዔውን ከማካሄድ አኳያ የገጠመውን ችግር ለመፍታት መፍትሔ ማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ በአንዳንድ ወገኖች ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ያልተፈለገው በሥልጣን ለመቆየት ስለታሰበ ነው በማለት ያሰሙትን ትችት ነቅፈዋል፡፡ ‹‹ዛሬውኑ ኃላፊነቴን ብለቅ ደስ ይለኝ ነበር፤›› ቢሉም አሁን ባለው ሁኔታ መልቀቅ ግን ንግድ ምክር ቤቱን ለአደጋ ማጋለጥ በመሆኑ ሕጋዊ መፍትሔ በማሰጠት ኃላፊነቱን ማስረከቡ ተገቢ በመሆኑ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ወደ አመራር ቦታ ለመምጣት የሚደረግ ፉክቻ የንግድ ምክር ቤቱን ስም ማጉደፉን የገለጹት አቶ ፋሲል ይህንን ስም ማደስ ተገቢ እንደሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በዕለቱ የሚተላለፉ ውሳኔዎች በክልል ደረጃ የተሰጠንን መብት የሚጋፉ ከሆነ ራሳችንን እንገነጥላለን በማለት ማስጠንቀቂያ የሰጡም ነበሩ፡፡ ሌሎች ክርክሮችም  ተስተዋል፡፡ ይሁንና መፍትሔው ላይ ትኩረት ይሰጥ በመባሉ መፍትሔውን ለማምጣት ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ይመሥረት የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት ሊያገኝ ችሏል፡፡ የዚህ ኮሚቴ መዋቀር ጊዜው ያበቃውን ቦርድ ለተጨማሪ ሁለት ወራት በኃላፊነቱ እንዲቆይ መተማመኛ አስገኝቶለታል፡፡ የሚቋቋመው አጣሪ ኮሚቴ የሚያስተላልፈው ውሳኔ በሁሉም አባል ምክር ቤቶች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ተሰብሳቢዎቹ ተስማሙ፡፡

ከብዙ ክርክርና የሐሳብ ፍጭት በኋላ አጣሪ ኮሚቴው እንዲቋቋም ሲወሰን፣ ኮሚቴው ችግሮችን አጣርቶ ለ18ቱ ንግድ ምክር ቤቶች የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በዚያ መሠረትምት ቀመር ተሠልቶ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲጠራ የማድረግ ኃላፊነት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ አጣሪ ኮሚቴውን የሚመሩ ሰባት አባላት ተመርጠዋል፡፡ የኮሚቴ አባላቱ ምርጫ ግን ከክርክር የራቀ አልነበረም፡፡ በተለይ በአጣሪ ኮሚቴው ውስጥ በአባልነት የሚካተቱት ግለሰቦች በየምክር ቤቶቻቸው በተካሄደ ምርጫ ላይ ችግር አለባቸው የተባሉ ስለነበሩበት እነዚህ ይካተቱ ወይም ይውጡ የሚለው አንደኛው የመከራከሪያ ነጠብ ነበር፡፡ የምርጫ ግድፈት ታይቶባቸዋል የተባሉ የምክር ቤት አመራሮች ክስ የቀረበባቸው በመሆኑ በኮሚቴ ውስጥ መካተት የለባቸውም ቢባልም፣ ቢገቡም ለውጥ አያመጡም በመባላቸው ግን አንድ አባል ገብተዋል፡፡ በሌላ በኩል የምርጫ ሒደታቸው ችግር ነበረበት የተባሉ ምክር ቤቶች ተወካዮች ቢካተቱም በማጣራቱ ሥራ ወቅት የእነርሱ ጉዳይ ሲመረመር ከውሳኔ ሰጭነት እንዱወጡ፣ እንዳይገቡ ይደረጋል ተብለው ታልፈዋል፡፡ ጉዳዩን እንዲያጣሩ የኮሚቴ አባላት ሆነው የተመረጡት የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ፣ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ፣ የአዲስ አበባ በንግድና ዘርፍ ማኅበራት ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቴ፣ የጋምቤላ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሸዋዬ ኃይሉ፣ የኦሮሚያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ገና፣ የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔርና፣ ከጥራጥሬ፣ ቅመማ ቅመምና ቅባት እህሎች ዘርፍ አቶ ኃይሌ በርኼ ሲመረጡ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ ደግሞ አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ሆነዋል፡፡

ይሁንና የማጣራቱ ሥራ የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችን መብት የሚነካ ከሆነ፣ አጣሪው ከሚቴ የክልላቸውን ጉዳይ እንዲያጣራ ፈቃደኛ እንደማይሆኑ የገለጹ ምክር ቤቶችም ታይተዋል፡፡ የማጣራቱን ሥራ በገለልተኛ መንገድ ለማከናወንና ውጤቱንም በማቅረብ ቀጣዩ ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ የሚካሄድበትን አግባብና የመፍትሔ ሐሳብ እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡ ተደጋግሞ ወደ አመራር ለመምጣት የሚደረግ ጥረትን ለማስቀረት የሚያስችል መፍትሔ እንዲመጣም ኮሚቴው ኃላፊነት ወስዶ ይሥራ ተብሏል፡፡

አጣሪ ኮሚቴው ለወቅታዊ ችግሮች ብቻም ሳይሆን ለዘለቄታው መፍትሔ የሚሰጥ ሐሳብ ይዞ እንዲቀርብ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ በኋላ በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚረዳ መፍትሔ ይዞ ይቀርባል ተብሏል፡፡ ኮሚቴው ሌሎችም የተጣሉበትን ኃላፊነቶች እንደሚወጣ አቶ አሰፋ ለሪፖርተር የገለጹ ሲሆን፣ የንግድ ምክር ቤቱን የጐደፈ ስም የሚያጠሩ ሥራዎች ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች