Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአንበሳ ባንክ ያምና ክንውንና አዲስ የቦርድ አባላት ምርጫ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከ140 ሺሕ በላይ ባለ አክሲዮኖችን የያዙት የግል የፋይናንስ ተቋማት የየዓመቱ የሥራ ክንውናቸውን ሰሞኑን በይፋ ማሳወቅ ጀምረዋል፡፡ በአክሲዮን ኩባንያነት የተቋቋሙት 17 ባንኮችና 16 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ባለአክሲዮኖቻቸውን ጠርተው በተጠናቀቀው 2008 በጀት ዓመት የነበራቸውን ትርፍና ኪሳራቸውን የሚነግሩበት፣ ሥራዎቻቸውን የሚገመግሙት ወቅት ነው፡፡

ጠቅላላ ጉባዔ የየኩባንያዎቹ የበላይ ውሳኔ ሰጪ አካል እንደመሆኑ፣ ወደፊት ምን መደረግና መሠራት እንዳለበት የሚወሰንበት ወቅት ይኸው ጊዜ ነው፡፡ የ2008 በጀት ዓመት ክንውኖቻቸውን ለባለአክሲዮኖቻቸው ይፋ በማድረግ ከሰሞኑ ቅድሚያ የመወሰዱት ዳሸንና አምበሳ ኢንተርናሽናል ባንኮች ናቸው፡፡

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ካካሄደው አምበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ሪፖርት መረዳት እንደሚቻለው፣ በ2008 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 378.11 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ይህ ትርፍ ከቀድሞው ዓመት የ37 በመቶ ዕድገት የታየበት እንደነበርም ባንኩ አስታውቋል፡፡

የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ በባንኮች መካከል የነበረው ውድድር ፈታኝ በነበረበት ወቅት የተገኘው ውጤት የሚነቀፍ አልሆነም፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ ፈተናውን ተቋቁሞ የተገኘው የትርፍ መጠንና ዕድገት ባንኩን ከአገሪቱ የግል ባንኮች አንጻር የ5.95 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዲይዝ እንዳስቻለውና ከግል ባንኮች ተርታም በሰባተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ያስቻለው ነው፡፡

ባንኩ በበጀት ዓመቱ 923.3 ሚሊዮን ብር ገቢ አግኝቷል፡፡ ጠቅላላ ሀብቱ ደግሞ በ2.9 ቢሊዮን ብር ጨምሮ 8.1 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተቀማጭ ገንዘቡም 6.3 ቢሊዮን ብር እንደሆነ የባንኩ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል በነሐሴ ወር መጨረሻ 824.2 ሚሊዮን ብር እንደደረሰም ተገልጿል፡፡

የተከፈለ ካፒታሉ ይህንን ያህል የደረሰው 231.6 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አዳዲስ አክሲዮኖችን መሸጥ በመቻሉ ነው፡፡ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን በመተግበር ረገድም በሞባይልና በኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት 1,200 ወኪሎች በመመልመል በመላ አገሪቱ ያሠማራና በዚህ አገልግሎት ዘርፍም 35 ሺሕ ደንበኞች እየተጠቀሙ እንደሚገኙ፣ 35 ሚሊዮን ብርም በዚህ መንገድ ማንቀሳቀሱ ተገልጿል፡፡ 

ብድር አሰጣጥና የማኔጅመንት ኃላፊነት

በ2008 በጀት ዓመት ባንኩ የ2.3 ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥቷል፡፡ አጠቃላይ የብድር ክምችቱን ወደ 4.3 ቢሊዮን ብር ከፍ ሊል እንደቻለ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ የ1.85 ቢሊዮን ብር የብድር ዕዳ ያስመለሰበት ዓመት እንደነበርም ተጠቅሷል፡፡

ከሪፖርቱ መረዳት እንደተቻለው የባንኩ የብድር አፈቃቀድ ሥርዓት የተለየ መንገድ የሚከተል ይመስላል፡፡ ፕሮፌሰር ጣሰው ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ የብድር አስተዳደር ሥርዓቱ ፈጣንና በሙያዊ ትንተና ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ለማስቻል ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ጥያቄዎች ሲቀርቡ በማዕከል የሚፈቀድበት አሠራር ባነኩ ተዘርግቷል፡፡ በመሆኑም ይህ አሠራር የተፈለገውን ውጤት በማስገኘቱ ቀደም ሲል በቦርድ ደረጃ ታይተው ይፈቀዱ የነበሩ ብድሮች መጠን ደረጃ በደረጃ ለማኔጅመንቱ በመልቀቅ የማኔጅመንቱ ብድር የመፍቀድ አቅም በየወቅቱ ከፍ እንዲል ሲደረግ መቆየቱን ተናግራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በማኔጅመንቱ ላይ ያለው መተማመን የላቀ ደረጃ ላይ በመድረሱ ብድር የመፍቀዱን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ለማኔጅመንት በመተው፣ ቦርዱ መላ ትኩረቱን በተቋማዊ አቅም ግንባታና የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት ላይ ማዋሉን ገልጸዋል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው የብድር አስተዳደር ለመፍጠርም ማኔጅመንቱ የሚፈቅዳቸውን ዋና ዋና ብድሮች በየወሩ ለቦርዱ ሪፖርት የሚያቀርብበት አሠራር በመዘርጋት የብድር አሰጣጡን እንደሚቆጣጠር ገልጸዋል፡፡      

የሕንፃ መገንቢያ ቦታ የማግኘት ፈተና

ከባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሪፖርት መረዳት እንደቻለው፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ባንኩን አጋጥመውት ከነበሩት ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ ከተማ ለዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ የሚውል ቦታ ማግኘት አለመቻሉ ነው፡፡

በተለምዶ የፋይናንስ ተቋማት መንደም ጎዳናም እየሆነ በመጣው ሰንጋተራ አካባቢ የግንባታ ቦታ ለማግኘት ብዙ ቢጥርም ሊሳካለት እንዳለቻለ የገለጹት ፕሮፌሰር ጣሰው፣ ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል የነበረው አስተዳደሩ በተወሰኑ አካባቢዎች ለባንኮችና ለፋይናንስ ተቋማት ብቻ በውሱን ጨረታ መሬት ለማስተላለፍ ያሳየው ጅምር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ሆኖም በዚሁ አካባቢ በቅርቡ በባንኮች መካከል በተደረገ ጨረታ የተሰጠው ዋጋ አስደንጋጭ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

የተጋነነ ዋጋ ቀርቦበታል ቢሉም፣ ባንካቸው በተሳተፈበት ጨረታ ተሸንፎ መሬት ማግኘት ሳይችል እንደቀረ፣ የተጋነነ ዋጋ ቀርቦበታል ካሉት የጨረታ ውጤት መገንዘብ የቻሉትም ከዚህ በኋላ በአካባቢው የሚደረጉ ጨረታዎች የመነሻ ዋጋዎች በዚሁ ጨረታ ዋጋ መነሻነት የሚካሄዱ በመሆኑ አስቸጋሪ እንደሚሆንም ጠቁመዋል፡፡

ከአሁን በኋላም ቢሆን በጨረታ ቢሳተፍም ለሕንፃ ግንባታ የሚሆኑ ክፍት ቦታዎችን ከመንግሥት፣ ከድርጅቶች ወይም ከግለሰቦች በድርድር ገዝቶ መሥራት ወይም አዋጭ የሆነ ሕንፃ ከተገኘ መግዛት የተሻለ አማራጭ ይሆናል ወደ ሚለው ድምዳሜ ወስዷቸዋል፡፡

የምርጫው ውጤትና አዳዲስ ገጽታዎች  

የሰሞኑ የፋይናንስ ተቋማት ጠቅላላ ጉባዔ የኢትዮጵያ ብሔሪዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ያወጣው መመርያ የሚተገበርበት ሆኗል፡፡ አንበሳ ባንክ በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት አዲሱን መመርያ ተከትሎ የቦርድ አባላት ምርጫ አካሂዷል፡፡ ቀድሞ ሲሠራበት ከነበረው የምርጫ ሒደት በተለየ ከአንድ ዓመት በፊት የተመረጡ የምርጫ ዓመቻች ኮሚቴዎች ከወራት በፊት በተደረገ ጥቆማ መሠረት የታጩትን ተወዳዳሪዎች ለጠቅላላ ጉባዔው በማቅረብም ድምፅ አሰጥተዋል፡፡

የአንበሳ ባንክ የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴም ባለአክሲዮኖች ዕጩዎችን እንዲጠቁሙ ጥሪ ካቀረበ በኋላ በጠቅላላው 27 ተጠቋሚዎች ቀርበውለታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት መሥፈርቱን የሚያሟሉ 22 ዕጩዎችን በመለየት ከቅዳሜው ምርጫ በፊት አሳውቋል፡፡ በቅዳሜው ምርጫም ከሃያ ሁለቱ ዕጩዎች ከፍተኛ ድምፅ ያገኙት አሥራ አንዱ ለባንኩ ዳይሬክቶሮች ቦርድ ተመርጠዋል፡፡

የምርጫው ውጤት እንደሚያመለክተውም ከቀድሞው ቦርድ በድጋሚ መመረጥ ከሚችሉትና በዚህም ምርጫ ዕጩ ከሆኑት ውስጥ አራቱ በድጋሚ ተመርጠዋል፡፡ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ፕሮፌሰር ጣሰው በከፍተኛ ድምፅ ተመርጠዋል፡፡

በዕለቱ ከፕሬዚዳንቱ ቀጥሎ ሁለተኛውን ከፍተኛ ድምፅ በማግኘት የተመረጡት፣ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤትን በማደራጀትና ውጤታማ በማድረግ የሚታወቁት የቀድሞ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ይርጋ ታደሰ ናቸው፡፡

በቀድሞው ቦርድ ሲያገለግሉ ቆይተው በድጋሚ ከተመረጡት ውስጥ፣ የቀድሞ የመንግሥት ቃል አቀባይና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አምባሳደር ኃይሌ ኪሮስ ይገኙበታል፡፡ ከአንባሳደር ኃይሌ በተጨማሪ በቦርዱ አባልነታቸው እንዲቆዩ የተመረጡት ቀሪዎቹ ሁለቱ አቶ ረዘነ ኃይሉ እና አቶ በየነ በላይ የተባሉ አባላት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች