Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጃካራንዳ አክሲዮን ከሐራጅና ከዕዳ ክሶች ፋታ በማግኘቱ እያንሰራራሁ ነው አለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

 በዘመናዊ የግብርና ሥራዎች ላይ በማተኮር ትርፋማ የአክሲዮን ኩባንያ ሆኖ ለመሥራት በ2001 ዓ.ም. የተቋቋመው ጃካራንዳ ኢንተግሬትድ አግሮ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር፣ ‹‹የገዥው ፓርቲ አባልነታቸውን ተገን በማድረግ ለገዛ ጥቅማቸው የሚያስቡ ኃይሎች ሊያፈርሱት ቢሞክሩም፤›› በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ መትረፉን፣ ከሐራጅና ከዕዳ ፋታ በማግኘቱም እያንሠራራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

የጃካራንዳ አክሲዮን ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምመላሽ ወጋየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣ የሕዝበ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እንዲሁም የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አባላት የሆኑ፣ በጃካራንዳ አክሲዮን ማኅበር በአባልነትና በቦርድ አመራርነት የተመዘገቡ ሰዎች የፖለቲካ ሥልጣናቸውን በመጠቀም ድርጅቱን ሊያፈርሱት ነበር፡፡ አንዳንዶቹም ገንዘብ እንዲሰጣቸው በይፋ እስከመጠየቅ ደርሰው ለኩባንያው ህልውና ሳንካ ፈጥረው ነበር ያሉት አቶ ደምመላሽ፣ በዚህም ሳቢያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በተደጋጋሚ በቀረበው አቤቱታ መነሻነት፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ችግሮች በጥር ወር 2008 ዓ.ም. እልባት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የፓርቲ አባልነታቸውን ተገን በማድረግ በአክሲዮን ማኅበሩ ህልውና ላይ ጉዳት አድርሰዋል በተባሉት የቀድሞ ቦርድ አመራር አባላት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቋቋሙት ኮሚቴ ባደረገው ማጣራት የሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መወሰኑን የጠቀሱት አቶ ደምመላሽ፣ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ የተደረጉ፣ ከነበራቸው ሹመት ዝቅ የተደረጉና ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ የተደረጉ እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ ለሚዲያ ባሠራጨው ደብዳቤም ‹‹ኩባንያውን እንዲመሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው የሥራ ኃላፊዎች፣ ከሕግና ከመመርያ ውጪ በመሥራት መንግሥትና ሕዝብ የሰጣቸውን የፖለቲከ ሥልጣንና የሥራ ኃላፊነት ለግል ጥቅማቸው ማስከበሪያ በማድረግ በኩባንያውና በአገር ላይ ይህ ነው የማይባል በደል ፈጽመው ኩባንያውን ችግር ውስጥ እንዲወቅድ አድርገውታል፤›› ብሏል፡፡  ይህ ሁሉ ችግር ተፈቶ አሁን ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በኋላም ኩባንያውን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ደምመላሽ አስታውሰው፣ የኩባንያው መሬቶች፣ የተወሰዱና የተዘረፉበት ንብረቶችም መመለሳቸውና የወጡበት ሐራጆችም መነሳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ለሠራተኞች እስከ አሥር ወራት ያልተከፈለ ውዝፍ የደመወዝ ዕዳ መክፈሉንና ከተፈናቀሉ፣ 360 ሠራተኞች ውስጥ 54ቱ ተመልሰው ሥራ መጀመራቸውም ተገልጿል፡፡

አሁን ላይ እንዲህ ቢባልም አክሲዮን ማኅበሩ ከምሥረታው ማግሥት ጀምሮ በፍጥጫዎች ውስጥ ለማለፍ ተገዶ ቆይቷል፡፡ በአክሲዮን ማኅበሩ አባላትና በቦርድ አመራሮች መካከል እየተካረረ የመጣው አለመግባባት፣ ከ2004 ዓ.ም. በፊትም ይታይና ሲከሰት የከረመ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ውሎ ሳያድር ‹‹አክሲዮን ማኅበሩ ፈርሷል፣ የተዋጣው የሕዝብ ገንዘብ ተበልቷል፤›› የሚሉ ጥያቄዎችም ሲስተጋቡበት ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎ የጃካራንዳ የወቅቱ የቦርድ አመራር በ2005 ዓ.ም. 150 የአክሲዮን ባለድርሻዎች ተሳትፈውበታል ያለውን ጉብኝት አሰናድቶ፣ ከአዲስ አበባ በ240 ኪሎ ሜትር ርቃ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በምትገኘው ባኮ ቲቤ ወረዳ፣ በ300 ሔክታር መሬት ላይ የእርሻ ሥራውን አስጎብኝቶ ነበር፡፡ በዚህ ጉብኝት ሳቢያም ኩባንያው ላይ የሚነሱ ትችቶችን ለማርገብ ታቅዶ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገር የባኮ ወረዳ አስተዳደር ተጨማሪ 250 ሔክታር መሬት ሊያስረክበው ይሁንታ ሰጥቶት እንደነበር የወቅቱ የኩባንያው አመራሮች ገልጸው ነበር፡፡

ለባኮ እርሻ ትልቅ ትኩረት መስጠቱን በ2005 ዓ.ም. አስታውቆ የነበረው አክሲዮን ማኅበሩ፣ በአዋሽ ቢሾላ፣ ዶዶታ ወረዳ ላይም 17 ሔክታር የሚጠጋ የመሬት ይዞታ ነበረው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ የከብት እርባታ በማካሄድና፣ አዋሽ ወንዝን በመጥለፍ አትክልት በመስኖ የማልማት ዕቅድም ነበረው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ጀምሮም ነበር፡፡ ሌላኛው በደቡብ ክልል ሶዶ ወረዳ ውስጥ በምትገኘው ቡኢ ላይ በ2.5 ሔክታር መሬት ላይ ዘመናዊ የወተት ማቀነባበሪያ ለመገንባት የጀመረው ሥራም ይጠቀሳል፡፡ ይህ ሁሉ ቢባልም ሦስቱም ይዞታዎቹ ላይ የሕግና የዕዳ ጥያቄዎች ሲነሱበትና የፍርድ ቤት ዕግድና ሐራጅ ሲቀርቡበት ቆይቷል፡፡ ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ተጠርቶ፣ በንግድ ሚኒስቴር አዳራሽ በተካሄደው የባለአክሲዮኖች ስብሰባ ላይ በወቅቱ የነበሩት ቦርድ አመራሮች ይህ ችግር ብቻም ሳይሆን፣ ኩባንያው 16 ክሶች ተመሥርተውበት፣ ፍርድ ቤት በመመላለስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ነበር፡፡ በንግድ ሚኒስቴር ሸምጋይነትና አማካሪነት የተካሄደው ይህ ስብሰባ በሁለት ወገን በተከፈሉ ባላንጣዎች መካከል የሚደረግ ሽኩቻ እስኪመስል ድረስ ባለአክሲዮኖችን ያሳዘነና ማኅበሩንም ወደ ማፍረሱ የተቃረበ አዝማሚያ ይዞ ማለፉም አይዘነጋም፡፡

ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ የቦርድ አመራርነት ቦታውን ተረክቦ ኃላፊነቱን የወሰደው አካልና ከዚያ ቀድሞ ይመራ በነበረው መካከል ከፍተኛ ፍትጊያዎች ታይተዋል፡፡ በተለይ አክሲዮን ማኅበሩን በጠነሰሱትና በኋላም እስከ 2004 ዓ.ም. ድረስ በአክሲዮን ማኅበሩ ፕሬዚዳንትነት፣ ቀጥሎም በሥራ አስኪያጅነት ሲሠሩ በቆዩት አቶ ደምመላሽ ላይ ከፍተኛ ነቀፋ በመሰንዘር በ2007 ዓ.ም. ኩባንያውን ለመምራት ፍላጎት እንደሌለው በመግለጽ ራሱን ከአመራርነት ማሰናበቱን የገለጸው ቦርድም አይዘነጋም፡፡

በዚህ ወቅት ኩባንያው ከተመሠረተ ጀምሮ በኪሳራ ላይ ይገኝ እንደነበር ሲገልጹ የነበሩ የቦርድ አመራሮች፣ በይዞታዎቹ ላይ የሐራጅ ማስታወቂያ መውጣቱንና ለዚህ የሚሆን ክፍያ እንደሌለው ሲገልጹ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ሪፖርተር በወቅቱ ስለዚህ ጉዳይ ሲዘግብ የ3.9 ሚሊዮን ብር የግብር ዕዳ ቀርቦበት እንደነበር ከቦርድ አመራሮቹ መገለጹን ጠቅሷል፡፡ አቶ ደምመላሽ ይህ ዕዳ በድጋሚ እንዲታይ መባሉን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር፣ ክፍያቸው አልተፈጸመም ለተባሉ የ300 ሺሕ ብር የከብቶች ግዥዎች፣ የትራክተር አገልግሎት ዕዳ ክፍያዎች አፍጠውበት እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ሦስቱም እርሻዎቹ በዕዳ ተይዘውበት የነበረው ጃካራንዳ፣ የሥራ ማስኬጃ ገንዘብ አጥቶ ችግር ውስጥ መግባቱንም የቦርድ አመራሮቹ አስታውቀው ነበር፡፡

ለዚህ ሁሉ ምክንያት ሲደረጉ የነበሩት የኩባንያው መሥራች አቶ ደምመላሽ ነበሩ፡፡ አቶ ደምመላሽ በበኩላቸው የወቅቱን ቦርድ አመራሮች በተጠያቂነት ፈርጀው ፍርድ ቤት ከማቆም ባሻገር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ድረስ አቤቱታቸውን በማቅረብ ጭምር መፍትሔ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለአክሲዮን ማኅበሩ መክሰርም ሆነ በዕዳ መጠየቅ ጣት ሲቀሰርባቸው የቆዩት አቶ ደምመላሽ፣ ከሥራ ገበታቸው አለአግባብ መታገዳቸውን በመግለጽ ክስ መጀመራቸውን፣ ይልቁንም በስማቸው በተከፈተ የኩባንያው የባንክ ሒሳብ ውስጥ ይገኝ የነበረ ገንዘብ ወጪ ተደርጎ፣ ደብተሩም ደብረ ብርሃን ላይ ተጥሎ መገኘቱንና በፖሊስ ተጠርተው እንዲረከቡ መደረጉን በወቅቱ ለጉባዔው ተናግረዋል፡፡

‹‹ገንዘባችን የት ደረሰ? እናንተ ቦታውን ስትረከቡ በጥሬና በዓይነት ስንት ገንዘብ ተረከባችሁ?›› የሚሉ አፋጣጭ ጥያቄዎች ለቀደመው ቦርድ አመራሮች ሲያቀርቡ የነበሩ የባለአክሲዮኖች ጥያቄዎች ናቸው፡፡ የቀደሙት አመራሮች ሥልጣን በአግባቡ እንዳልተረከቡና አመራሩን በያዙበት ወቅት ገንዘብ የሚባል ነገር የሌለበት፣ ባዶ ካዝና መረከባቸውን ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ በሌላኛው ጽንፍ ግን በታኅሳስ ወር 2006 ዓ.ም. በአንድ የባንክ ሒሳብ ውስጥ ብቻ 2.5 ሚሊዮን ብር እንደነበር፣ ሆኖም የኩባንያው ገንዘብ እንደተመዘበረ በመግለጽ አቶ ደምመላሽም ሆኑ በእሳቸው ወገን ሆነው የሚከራከሩ ሰዎች የሚያራምዱት ሐሳብ ነው፡፡

በዚህ ዓይነት የሁለት ወገን ንትርክ ውስጥ የቆየው ጉባዔ፣ ኩባንያው በእስካሁኑ ጉዞው የኪሳራ ቁልቁለት ውስጥ መግባቱ እየታየ መሆኑና ወደፊት ይቀጥል ቢባል እንኳ ሕልውና እንደማይኖረው እየታየ በመሆኑ ሊፈርስ ይገባዋል የሚሉ አስተያየቶች ከባለድርሻዎች ተነስተውበታል፡፡ በዚህ ሐሳብ የመስማማት አዝማሚያ ላይ የነበረው ባለአክሲዮኖን፣ ወደ ኋላ ላይ ግን አይፍረስ በሚለው አስታራቂ ሐሳብ ተስማምቷል፡፡

ተሰናባቹ ቦርድ የኦዲት ሪፖርት ሳያቀርብ በአዲስ አመራር መተካት የለበትም፣ ምርጫ ማካሄድ አይገባም የሚሉ ተቃውሞዎች የአክሲዮን ባለድርሻዎች ጉባዔ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት ሲደመጡ የነበሩ ነበሩ፡፡ ምርጫው መካሄድ እንዳለበት፣ አለበለዚያ ግን ራሳቸውን ከአመራርነት ባሰናበቱት የቦርድ አባላት ሳቢያ ኩባንያው የሚመራው አጥቶ ዕጣው መፍረስ ነው በማለት የንግድ ሚኒስቴር ኃላፊዎች በወቅቱ በማስጠንቀቃቸው ሳቢያ፣ ተንጠባጥበው በቀሩት ባለአክሲዮኖች አማካይነት ምርጫ ተካሂዷል፡፡ የኩባንያው ህልውናም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ተንጠልጥሎ ቆይቷል፡፡

በተመዘገበ 100 ሚሊዮን፣ በተከፈለ 28 ሚሊዮን ብር እንዲሁም በተፈረመ 21 ሚሊዮን ብር መቋቋሙ የሚነገርለት ጃካራንዳ አክሲዮን ማኅበር፣ ከ2,500 ባለአክሲዮኖች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ከዚህ ቀደም አስታውቋል፡፡ ይህም ባይሆን የባንክ ብድርን ተስፋ አድርጓል፡፡ በውጭ የሚኖሩ 200 ያህል ባለአክሲዮኖች በኩባንያው አመራሮች፣ መንግሥት ባለበት አገር ገንዘባችንን ተበላን በማለት በተለያዩ መድረኮች ሲናገሩ መደመጣቸውን አቶ ደምመላሽ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በሁለት ጎራ ተሰልፈው ሲናቆሩ የከረሙት የቀድሞ የቦርድ አመራር አባላት፣ ስለኩባንያው ትርፍና ኪሳራ፣ ዕዳና ሀብት ከአክሲዮን ባለድርሻዎች ሲጠየቁ፣ ወደፊት በሚካሄድ ማጣራት ላይ ‹‹እንገናኛለን፤ እንተያያለን›› ይሉ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር ስለኩባንያው የኦዲትና የማጣራት ሒደት ወደፊት እንደሚካሄድና ከመጀመሪያው ጀምሮ ጃካራንዳን የመራ የቦርድ አመራር ሁሉ የኃላፊነት ጥያቄዎች እንደሚጠብቁት አስታውቋል፡፡

አቶ ደምመላሽ እንደገለጹት ከሆነ ደግሞ ከግለሰቦች፣ ከባንክ፣ ከባለአክሲዮኖችና ከሌሎችም ብድር እያሰባሰቡ ኩባንያውን እየታደጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ሁሉ መፍትሔ አለው እያሉ ይገኛሉ፡፡ አብሮ የሚሠራ ኩባንያ ሥራ መጀመሩንም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ኩባንያውን የመሠረትኩት በነበረኝ ራዕይ ተመሥርቼ፣ ከሐሳብ ወደ ወረቀት፣ ከወረቀትም ወደ ተግባር ለመለወጥ ተግቼ ነው እንጂ እንደ ሌሎቹ ኩባንያው ችግር ውስጥ በገባ ጊዜ ጥሎ በመሄድ አይደለም፤›› በማለት እንዴት እንደሚታደጉትና ወደ አትራፊ ድርጅትነት እንደሚያስገቡት እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በታኅሳስ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. የኩባንያው ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚጠራና ባለአክሲዮኖች ስለኩባንያው ወቅታዊ ሁኔታ እንዲነጋገሩ ቀጠሮ መያዙን አቶ ደምመላሽ ጠቅሰዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች