Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ሁለገብ አገልግሎት

ትኩስ ፅሁፎች

ይድረስ ለሁሉም ልቡና

ሰዎች እንሰብሰብ እንበል መላ መላ

ከሰላም በስተቀር ምንም የለም ሌላ፡፡

ማቀድ በሰላም ነው መነሳት ለሥራ

ሰላም ከሌለማ ቀኙ ይሆናል ግራ፡፡

አርሶ ፍሬ ማፈስ ነግዶ ማትረፍ

ተምሮ ለመካን በጥበብ ምዕራፍ፣

መፍትሔው ሰላም ነው ጎበዝ ልብ በሉ

እንኳን በእኛ አገር በዓለም በሙሉ፡፡

አግብቶ ለመውለድ ወልዶ ማሳደግ

ዋስትና ሲኖር ነው ለሰላም መንገድ፡፡

ፍቅርና ሰላም አብረው ካልተጓዙ

የሚመጣው ፍዳ ብዙ ነው መዘዙ፡፡

ይህች ድንቅ አገር በነፃነት ደምቃ

ስንኳን በአፍሪካ ባለም ሁሉ ታውቃ፣

ልትኖር የቻለችው ያላንዳች ጥርጥር

ገንዘብ አድርጋ ነው ሰላምና ፍቅር፡፡

ስለዚህ መራርነት ይቅር፣ እናስብ መልካም

ክፋት ጥፋት እንጂ ውጤት የለውም፡፡

ለወጣቱ ይሰጥ የሰላም ትምህርት

ይዘራ በልቡ ግብረገብነት፡፡

ፍትሕ ባገር ይስፈን ይወገድ ማድላት

ጤና አይሆንምና ሚዛን ማዛባት፣

ሙስናም ይወገዝ የዕድገት ጠር ነውና

በፍጹም አይበጅም ላገር ሕልውና፡፡

እርምት የሌለበት የምቀኛ ትችት

ከሕዝቦች መካከል መወገድ አለበት፡፡

ስንፍናን እንጥላ እንሥራ ለፍሬ

ትጋታችን ይሁን ልክ እንደ ገበሬ፡፡

ድህነት እንዲወገድ ከዚህች ምድር

ሁሉም በየፊናው ይሥራ ይታትር፡፡

መንግሥትም ሕዝብ ነው፣ ሕዝብም ነው መንግሥት

ችግርን እንፍታ በመወያየት፡፡

በአንዳንድ አገሮች ሰላም ስለጠፋ

ቂም በቀል ሰፈነ ጦርነት ተስፋፋ፣

ይህ ፍዳ እንዳይመጣ በኢትዮጵያችን

ሽማግሌ አይጥፋ የሚያስታርቀን፡፡

ስለዚህ ወገኔ እናስብ በጥልቀት

ወዳንድነት እንምጣ ቢኖርም ልዩነት፣

በተገኘው ልማት በመጣው ዕድገት

የተንኮል ማዕበል እንዳይነፍስበት፣

በጥበብ በብልሃት እንንከባከበው

በመሆኑ አለኝታ ነቅተን እንጠብቀው፡፡

  • ከኃይሉ ልመንህ

* * *

የዋይፋይ መዘዞች

ዋይፋይ ምቹ ቢሆንም የሚያስከትላቸውን የጤና ጠንቆች በሚመለከትም በርካታ ጥናቶች ተሠርተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 1997 ላይ ዋይፋይ ለተጠቃሚዎች ከተዋወቀ በኋላ ከተሠሩ በርካታ ጥናቶች መካከል እ.ኤ.አ. 2008 ላይ በሳይንቲፊክ አሜሪካን ህትመት ላይ ‹‹የአእምሮ በስልክ ቁጥጥር ሥር መውደቅ›› በሚል ርዕስ የወጣው ጥናት ይገኝበታል፡፡ ይህ ጽሑፍ ዋይፋይ በሰው ልጆች አእምሮ ላይ ስለሚያስከትላቸው የጤና ጠንቆች ይዘረዝራል፡፡ በቅርቡ የወጣ ሌላ ጥናት እንደሚያመለክተው ደግሞ በተደጋጋሚ ዋይፋይ መጠቀም የስፐርም እንቅስቃሴን ሲቀንስ የዲኤንኤ መነጣጠልንም ያስከትላል፡፡ ጥናቱ እንደሚያሳየው ዋይፋይ በጥቅሉ ጤና ላይ እንዲሁም አእምሮ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ተጽእኖው ደግሞ በሕፃናት ላይ የበረታ ይሆናል፡፡ በጥናቶች መደበኛ የዋይፋይ ተጠቃሚነት ያስከትላቸዋል ከተባሉ የጤና ችግሮች መካከል እንቅልፍ ማጣት፣ የሕፃናት እድገት መገደብ፣ የህዋስ እድገት ችግር፣ የአእምሮ በአግባቡ መሥራት አለመቻልና ምናልባትም መካንነት ይገኙበታል፡፡

* * *

አዲሱ የእንግሊዝ አንድ ፓውንድ ሳንቲም ግርግር አስከተለ

ባለ 12 ጐኑ አዲስ የእንግሊዝ አንድ ፓውንድ ሳንቲም መውጣትን ተከትሎ ነጋዴዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ውዥንብር ውስጥ መግባታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡ ይህንን የአንድ ፓውንድ ሳንቲም ለማስተናገድ ቸርቻሪዎች የገንዘብ መቀበያ ማሽኖቻቸውን ምቹ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምግብና መጠጥ መሸጫ እንዲሁም የፓርኪንግ ማሽኖች መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 1983 ላይ ለዜጐች ይፋ የሆነው የቀድሞው የአንድ ፓውንድ ሳንቲምና አዲሱ ለስድስት ወር ጐን ለጐን አብረው የሚያገለግሉ በመሆኑ የገንዘብ መቀበያ ማሽኖችን የማስተካከል ሒደቱን ችግር ውስጥ ይከትተዋል ተብሎ ተፈርቷል፡፡ 40 በመቶ የሚሆኑት ገንዘብ መቀበያ ማሽኖች አዲሱን አንድ ፓውንድ ሳንቲም ለማስተናገድ ሙሉ በሙሉ ለውጥ ማድረግ ይኖርባቸዋልም ተብሏል፡፡

* * *

‹‹የምርኮ አገር እውነት››

በአርክቴክትና ደራሲ ሚካኤል ሽፈራው የተጻፈው ‹‹የምርኮ አገር እውነት›› የተሰኘ መጽሐፍ ጥቅምት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ከ11፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ይመረቃል፡፡

* * *

‹‹የመናፍስቱ መንደር››

በታደሰ ጸጋ ወልደ ሥላሴ የተጻፈው ‹‹የመናፍስቱ መንደር›› ላይ ጥቅምት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ በትራኮን ሕንፃ ውይይት ይደረግበታል፡፡ የመነሻ ሐሳብ የሚቀርበው በመምህር ሰለሞን ተሾመ ባዬ ሲሆን፣ መርሐ ግብሩን ያዘጋጁት ሊትማን፣ እነሆና ክብሩ የመጻሕፍት መደብሮች የመጻሕፍት ሽያጭም ያካሂዳሉ፡፡

* * *

‹‹መረቅ››

በአዳም ረታ ‹‹መረቅ›› መጽሐፍ ላይ ውይይት ይደረጋል፡፡ የመነሻ ሐሳብ የሚቀርበው በኢየሩሳሌም ዳኜ ሲሆን፣ ጥቅምት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ከ8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ይካሄዳል፡፡ መርሐ ግብሩ በእናት ማስታወቂያና ጐተ ኢንስቲትዩት ጥምረት የተዘጋጀ ነው፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች