ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደ አዲስ ያደራጁትን ካቢኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡ በአዲሱ አደረጃጀት መሠረት እያንዳንዱ የካቢኔ ሚኒስትር ኃላፊነቱን በውጤታማነት እንዲያከናውን ይጠበቃል፡፡ ለዚህም የተሰጠው ሹመት መመዘኛ ውጤታማነት፣ የሕዝብ ወገንተኝነት፣ እውቀትና ክህሎት፣ ልምድ፣ መልካም ሥነ ምግባር፣ ታታሪነት፣ ወዘተ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡ በአዲሱ ካቢኔ በዚህ መሥፈርት ለሥልጣን የበቁ ተሿሚዎች መገንዘብ ያለባቸው ሕዝብ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚጠብቅ ነው፡፡ የመንግሥት ከፍተኛ ተሿሚዎች በተመደቡባቸው የተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ለዓመታት የተጠራቀሙ ችግሮች እንዳሉ አውቀው፣ እነዚህ ችግሮች የሚፈቱት ደግሞ በተለመደው የማድበስበስና የማለባበስ አካሄድ ሳይሆን በሥር ነቀል ለውጥ ብቻ መሆኑን ይረዳሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡
ከዚህ ቀደም በፍትሕ ሥርዓቱ፣ በንግዱ ዘርፍ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ፣ በመኖሪያ ቤቶች፣ ወዘተ ይሰሙ የነበሩ ቅሬታዎች አቅጣጫቸውን ቀይረው ለሁከት መቀስቀስ፣ ለዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ ለአካል መጉደል፣ ለንብረት ውድመት መንስዔ ከመሆናቸውም በላይ ለአገርና ለሕዝብ ህልውና ሥጋት መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ የቅርብ ጊዜ መሪር ትዝታም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ስህተቶችና አጓጉል ድርጊቶች የፈጠሩትን አደገኛ ሁኔታ ለማስተካከል የሚፈለግ ከሆነ፣ አዲሱ ካቢኔ ለሥር ነቀል ለውጥ መነሳት አለበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሕዝብ ከመንግሥት የሚፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ሕዝብ ያቀረባቸው ጥያቄዎች አሁንም ፈጣን ምላሽ ይሻሉ፡፡
አዲሱ ካቢኔ በአዲስ አደረጃጀት ሲወቃቀር የሰዎች መለዋወጥ ወይም መሸጋሸግ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደም ሕዝብን ሲያስመርሩ የነበሩ ብልሹ አሠራሮች በተሻሉ አሠራሮች የመለወጥ ጉዳይ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ ተሿሚዎች ብቃታቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ሥነ ምግባራቸውንና ታታሪነታቸውን የሚያሳዩት ውጤታማ ተግባራትን በመፈጸም ነው፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የተፈጠረው መበለሻሸት ሥር ነቀል በሆነ መንገድ መስተካከል አለበት፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው እንቅፋት የሆኑ ድርጊቶች ተገትተው የተሻለ ሥርዓት መፈጠር ይኖርበታል፡፡ ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩትና የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት ዓውድ መኖር የግድ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ደግሞ ከተሿሚዎች ቁርጠኝነት ይጠበቃል፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ይጠበቃል፡፡
የመንግሥትን ትልቅ ኃላፊነት መሸከም አደራው የከበደ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቅ ሰብዕና ይጠይቃል፡፡ ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት፣ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መርህ መገዛት፣ ከአድሎአዊና ከቡድንተኝነት አስተሳሰብ ራስን ማራቅ፣ ሙስናን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር መፀየፍ፣ አስመሳይነትንና አድርባይነትን መዋጋት፣ በማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን ቢሆን በራስ መወሰን፣ አገርና ሕዝብን የማገልገል ክብር መጎናፀፍ፣ ከፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት መታቀብ፣ ተቋማትን ጠንካራና ዘለቄታዊ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ሥራን ከባለሙያ ጋር ማገናኘት፣ በአርዓያነት የሚጠቀስ አመራር መስጠት፣ ከአልባሌ ድርጊቶችና ሥፍራዎች ራስን ማራቅና የመሳሰሉት በጣም ተፈላጊ ናቸው፡፡ አገሪቱ አሁን ካለችበት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ወጥታ ሰላማዊው ድባብ ሙሉ በሙሉ እንዲሰፍንና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ተሿሚዎችን ሲያቀርቡ ባደረጉት ንግግር ቀደም ሲል የነበረው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ በክላስተር የማስፈጸም፣ እንዲሁም አማካሪ የሚባሉ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ መቅረታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሿሿም እንዲበቃ መደረጉ ጥሩ ከመሆኑም በላይ የተንዛዙ አሠራሮችን ያስቀራል፡፡ ከዚህ ቀደም ብቃት የሌላቸው ግለሰቦች ከኃላፊነታቸው ሲነሱ የሚወሸቁባቸው የአማካሪነት ቦታዎች መብዛት በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ አንደኛ ተጠያቂነት አለመኖሩን ከማሳየቱም በላይ፣ አማካሪ የሚባለው ሹመት ትርጉም አጥቶ ነበር፡፡ ሁለተኛ በየጊዜው ለሚፈጠሩ ሹመቶች በሚሠራ መዋቅር የሚባክነው ጊዜና የአገር ሀብት ያሳዝን ነበር፡፡ አሁን ግን ወቅቱ የሚፈልገው ውጤታማነትን በመሆኑና ውጤታማነት የሚገኘው ደግሞ በብቃትና በዳበረ ልምድ መሆኑ ግንዛቤ ተይዟል፡፡ ይህ ፍላጎት እንደተለመደው በወሬ እንዳይቀር መደረግ አለበት፡፡ ሕዝብ የሚፈልገው ሥር ነቀል ለውጥ ብቻ ነው፡፡
የካቢኔ አባላቱ ሹመታቸውን ያፀደቀላቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ የሥልጣን ቁንጮ መሆኑ የተረጋገጠ እንዲሆን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው፡፡ ለተወካዮች ምክር ቤት የሚያቀርቡት ሪፖርት ከሐሰት የፀዳ፣ ተጠያቂነት ያለበትና የምክር ቤቱንም ክብር የሚጠብቅ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የምክር ቤቱ አባላት የአስፈጻሚውን የሥራ ክንውንና አፈጻጸም በሚገባ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ሲኖርባቸው፣ በተለይ ቋሚ ኮሚቴዎች ምክር ቤቱ ጥርስ ያለው አንበሳ እንዲሆን መርዳት አለባቸው፡፡ የአዲሱ ካቢኔ አባላትም ራሳቸውን ለሕግ የበላይነት በማስገዛት የምክር ቤቱን ክብር ከመጠበቃቸውም በተጨማሪ፣ ለሕዝብና ለህሊናቸው ታማኝ በመሆን ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ከአሁን በኋላ ሕዝብ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚጠብቅ በማመን፣ ራሳቸውን ለትልቅ የሕዝብና የአገር አደራ ያዘጋጁ፡፡ ከአገርና ከሕዝብ በላይ ምንም ነገር የለም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ሰላም የምትሆነው ጤነኛ አመራር ሲኖራት ነው፡፡ ሕዝብ እርካታ የሚያገኘው በአግባቡ ሲመራ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ መገንባት የሚቻለው በብሔራዊ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ መግባባት ሲቻል ነው፡፡ ዴሞክራሲ ዕውን የሚሆነው የፖለቲካ ምኅዳሩ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሲመራ ነው፡፡ ዕድገት የሚገኘው ኢኮኖሚው ብቃት ባላቸው ዜጎች አመራር ሰጪነት ሲከናወን ነው፡፡ ማኅበራዊ ፍትሕ የሚሰፍነው አመራሩ በብቃትና በቁርጠኝነት አገሩን ማገልገል ሲችል ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት የሚከበረው የሕግ የበላይነት መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡ በምርጫ ሥርዓቱም ሆነ በፌዴራል ሥርዓቱ አወቃቀር ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር የሚቻለው አመራሩ ለሕዝብ ፍላጎት ሲገዛ ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል የሚፈጠረው ለሥር ነቀል ለውጥ የተነሳ አመራር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ ነው፡፡ የአገር ህልውና አስተማማኝ የሚሆነውና የሕዝብ ፍላጎት በሚፈለገው መጠን እርካታ የሚያገኘው፣ ለሥር ነቀል ለውጥ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ሲሰጥ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡ ከአዲሱ ካቢኔ ሥር ነቀል ለውጥ የሚጠብቀው!