Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየሒላሪ ክሊንተንን የምርጫ ዘመቻ የተፈታተነው የኢሜይል ድብብቆሽ

የሒላሪ ክሊንተንን የምርጫ ዘመቻ የተፈታተነው የኢሜይል ድብብቆሽ

ቀን:

የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሊደረግ አንድ ሳምንት ሲቀረው የአሜሪካ ፌዴራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ)፣ ከዕጩዋ ሒላሪ ክሊንተን የኢሜይል ድብብቆሽ አዲስ መረጃ አግኝታችሁ ማለቱ መራጮችንም ሆነ ፖለቲከኞችን ግራ አጋብቷል፡፡ በሰሞኑ የምርጫ ዘመቻም ዳግም አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡

ላለፉት ሦስት ሳምንታት ያህል የሪፐብሊካኑ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ሴቶችን ጐነታትለዋል ተብለው የሚዲያው መነጋገሪያ ሆነው የሰነበቱ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ የሒላሪ ክሊንተን ኢሜይል ጉዳይ አዲስ ክስተት ሆኗል፡፡

ሒላሪ ክሊንተን የኢሜይል ልውውጥ ድብብቆሽ ውስጥ መግባታቸውና ከአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና ባለሥልጣናት የኢሜይል አጠቃቀም መርህ ማፈንገጣቸው የተነገረው እ.ኤ.አ. በመጋቢት 2015 ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እ.ኤ.አ. ከ2009 እስከ 2013 ሲያገለግሉ የአገሪቱን የፌዴራል ሕግ በመጣስ በግል ሰርቨራቸው ኢሜይል ተጠቅመዋል ተብለው የተብጠለጠሉት ክሊንተን፣ በግል ሰርቨራቸው ከተለዋወጧቸው 65 ሺሕ ያህል መልዕክቶች መካከል 33 ሺሕ ያህሉ እንዲጠፉ ማድረጋቸው ሲያስወቅሳቸው ከርሟል፡፡

ክሊንተንም ሆኑ ጠበቃቸው ከአገሪቱ ሥራ ጋር የተያያዙትን 30 ሺሕ የሥራ የኢሜይል መልዕክቶች ለምርመራ በማስፈለጋቸው ለኤፍቢአይ ያስረከቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን ግን ግላዊ ናቸው በማለት እንዳጠፏቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲዘገቡ ቆይተዋል፡፡ የኢሜይል ድብብቆሹ በፓርቲያቸው ለዕጩ ፕሬዚዳንትነት እስከሚመረጡ ድረስ መነጋገሪያ ሆኖ የከረመ ቢሆንም፣ ዕጩ ሆነው ብቅ ካሉ በኋላ እንደ አንድ ውድቀት በትራምፕ እየተመዘዘ ይነገር እንጂ፣ ሚዲያዎች በአብዛኛው ያተኮሩት ዕጩዎቹ ይዘው ብቅ ባሉዋቸው የስደተኞች፣ የታክስ፣ የሴቶች፣ ሌሎች ክርክሮችና በትራምፕ አወዛጋቢ አቋሞች ላይ ነበር፡፡ የክሊንተን ኢሜይል ጉዳይ አለፍ ገደም እያለ ቢነሳምና በኤፍቢአይ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሆነ ቢታወቅም፣ እንደ አሁኑ በወሳኝ ጊዜ ላይ ብቅ ብሎ የሒላሪን የምርጫ ዘመቻ በማቃወስ አላስቆጣም ነበር፡፡ ምርጫው ሊካሄድ 11 ቀናት ሲቀሩት የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሚ የክሊንተንን አዳዲስ፣ ምናልባትም ከዚህ ቀደም አንስተዋቸው ለነበሩ ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጡና ምርመራቸውን የሚያጠናክሩ መልዕክቶች ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ እየገባችና ኢሜይሎችንም እየጠለፈች መሆኑን ኮሚ ተናግረው፣ ያገኟቸውን መረጃዎች ለመልቀቅ ግን የምርጫው ቀን መቃረቡ እክል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከሳምንት በኋላ ከሚደረገው ምርጫ በፊት ያገኟቸውን አዳዲስ መረጃዎች እንደማይለቁ ያስታወቁት ኮሚ፣ ‹‹የአሜሪካ የደኅንነት አካላት ሩሲያ በአሜሪካ የግለሰቦችን፣ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትን ኢሜይል እየጠለፈች መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ ይህ የኢሜይል ዘረፋና መረጃውን ግልጽ የማውጣት አካሄድ ሩሲያ በአሜሪካ የምርጫ ሒደት እጇን እያስገባች መሆኑን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ ቢቢሲ እንዳሰፈረውም ሩሲያ የዶናልድ ትራምፕን መመረጥ ትደግፋለች፡፡ ስለሆነም ትራምፕ እንዲመረጡ የዴሞክራቶችን የመልዕክት ልውውጥ ትጠልፋለች ተብላ ስትወነጀል ከርማለች፡፡

ሚስተር ኮሚ ባለፈው ሰኔ ክሊንተን በኢሜይል አያያዝ ግዴለሽ መሆናቸውን በመግለጽ ለክስ የሚያበቃቸው ነገር እንዳላገኙባቸው አሳውቀው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን አዲስ በመረመሯቸው ኢሜይሎች ስለግል ሰርቨራቸውና ጠፍተዋል ስለተባሉ ኢሜይሎች መረጃ ሊያመላክት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

አዲስ ተገኘ የተባለው ኢሜይል የቀድሞ የኮንግረስ አባል አንቶኒ ዊነር በሰሜን ካሮላይና ለምትኖረው የ15 ዓመት ታዳጊ የላኩት ያልተገባ መልዕክት ይገኝበታል፡፡ የሒላሪ ክሊንተን ከፍተኛ ረዳት በሆነችው የሚስተር ዊነር ባለቤት ሁማ አብዲን ላፕቶፕ የተላኩና የመጡ የተለያዩ የኢሜይል ልውውጦች በቢሮው እየተመረመሩ ነው፡፡ 

650,000 ያህል በላፕቶፕ የተላላኩና የመጡ ኢሜይሎች ላይ ምርመራ እየተደረገ ቢሆንም፣ ማን ላከው? ማን ተቀበለ? የሚለውን ጀምስ ኮሚ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ግልጽ አላደረጉም፡፡

ከሒላሪ ክሊንተን ጋር በቅድመ ምርጫ ትንበያ አንገት ላንገት የተያያዙት ዶናልድ ትራምፕ ግን፣ ኤፍቢአይ የጠፉትን 33 ሺሕ የኢሜይል መልዕክቶች እንደሚያገኝ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ክሊንተን ደግሞ ከሕዝብ የምደብቀው ጉዳይ የለኝም ሲሉ በቅስቀሳ ወቅት ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ኮሚ አዲስ አገኘኋቸው የሚሏቸውን መረጃዎች ምርጫው 11 ቀን ሲቀረው ማንሳታቸው በድብቅ ሒላሪ ክሊንተንን ከፕሬዚዳንትነቱ ሥልጣን ለማጨናገፍ አስልተው ነው የሚል ሙግትም አስነስቷል፡፡ ዋይት ሐውስ በኤፍቢአይ ላይ ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ ባያሰማም በአሜሪካ ሴኔት የዴሞክራቶቹ መሪ ሃሪ ሬይድ ጀምስ ኮሚ የምርመራ ቢሮ ኃላፊ ሆነው በምርጫ ሕግ አንዱን ከአንዱ የሚያበላልጡ መንግሥታዊ መረጃዎችን ማውጣት ያልተገባ ቢሆንም፣ ከሒላሪ ክሊንተን ጋር የተያያዙ መረጃዎች አሉኝ በማለት የምርጫ ሥርዓትን ተላልፈዋል ሲሉ ኮንነዋቸዋል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ቃል አቀባይ ጆሽ ኧርነስት ደግሞ ጀምስ ኮሚ በሚስጥር ምርጫውን ለመጋፋት ብሎ መረጃ ያወጣል ብለው እንደማይገምቱ ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ኮሚ አግኝተናል የሚሉትን አዲስ መረጃ ግልጽ ያድርጉትና እንወቀው በማለት የጠየቁ ዴሞክራቶችም አሉ፡፡

ቢሮው የሒላሪን የኢሜይል ምርመራ ከምርጫው በፊት አጠናቆ ቢያሳውቅስ ምን ይከተላል? የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ ቢሮው በሒላሪ ኢሜይሎች ላይ የጀመረውን ምርመራ በሳምንት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ይፋ ለማድረግ አይችልም የሚሉ ግምቶች ቢኖሩም፣ መራጩ ምርመራው ተጠናቅቆ መረጃውን እንዲያገኝና ለቀጣይ የሚሆነውን ፕሬዚዳንት እንዲመርጥ ይፋ ማድረግ ያስፈልጋል የሚል አስተያየትም እየተሰነዘረ መሆኑን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ በምርጫው ዋዜማ የተፈጠረውን ከሒላሪ ኢሜይል ጋር የተያያዘ ውዝግብ አሁን ካለው በላይ ማጥራትና ሁኔታውን ማረጋጋት ያስፈልጋል በማለት የቢሮው ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ ዳይሬክተሩ ኮሚ ከምርጫው በፊት መረጃዎችን አልለቅም ቢሉም፣ አዳዲስ መረጃ አግኝተናል ማለታቸው ፖለቲከኞችን ብቻ ሳይሆን መራጮችንም አደናግሯል፡፡

የኮሚ መግለጫ ከኢሜይሎቹ ጋር በተያያዘ ብዙ ያልመለሳቸው ጥያቄዎች አሉ፡፡ በተለይ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የፖለቲካው ትኩሳት በፋመበት ሰዓት በዕጩዎችና በአገሪቱ ህልውና ላይ የሚያጠነጥኑ ጉዳዮች ከመንግሥት አካል መነሳቱ ግርታን ፈጥሯል፡፡

ሪፐብሊካኑ የቀድሞው የአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አልቤርቶ ጐንዛሌዝ የኮሚ አካሄድ ችግር አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹በምርመራ ላይ ያለ ጉዳይ አስተያየት አይሰጥበትም፡፡ የሚሰጥ አስተያየትም የምርመራውን ሒደት የበለጠ አደጋ ውስጥ ይከተዋል፡፡ ኮሚም ራሱን የበለጠ አደጋ ውስጥ ከቷል፡፡ ሕዝቡ ካገኘው ጥቂት መረጃ በመነሳት ሁሉንም ማወቅ ፈልጓል፡፡ የኢሜይሎቹ ዝርዝር ይዘት እንዲነገረውም እየጠየቀ ነው፡፡ ኢሜይሎቹ በግልጽ እንዲለቀቁ ጠይቋል፤›› ብለዋል፡፡

ሚስተር ጐንዛሌዝ እንደሚሉት፣ ኮሚም ኢሜይሎቹን አፍኖ በመያዝ መራጩን ሕዝብ ማሳሳት የለበትም፡፡ መራጩ ቀድሞውንም ምንም መረጃ ባይኖረው ያመነበትንና የፈለገውን ይመርጥ ነበር፡፡ አሁን ግን መረጃ ወጥቷል፡፡ ምሉዕ ግን አይደለም፡፡ ይህም ብዥታን ፈጥሯል፡፡ ሒላሪ የምደብቀው ነገር የለኝም፣ ኢሜይሎቹ ይፋ ይሁኑ ቢሉም፣ በቢሮው በኩል የተለቀቀ መረጃ የለም፡፡ ይህም ቢሮው በድብቅ ሒላሪን ከፕሬዚዳንትነት ለማግለል እየሠራ ነው አስብሎታል፡፡ ምርጫው የሳምንት ዕድሜ በቀረበው ወቅት፣ ሕዝቡ ትክክለኛ መሪውን እንዳይመርጥ የተነካኩ ግን ግልጽ ያልሆኑ መረጃዎች ብቅ ብለዋል፡፡ የሒላሪ ደጋፊዎችም ኢሜይሎቹን ማወቅ እንፈልጋለን እያሉ ነው፡፡ ኮሚ ከምርጫው በኋላ መረጃውን እለቃለሁ ማለታቸው ምርጫውንና ከምርጫው በኋላ በሚኖረው የሕዝብ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ ያመጣ ይሆን? ለጊዜው ግን ሒላሪ ክሊንተን በሕዝብ አስተያየት መለኪያ የነበራቸው ብልጫ ጠቦ ከመሄዱም በላይ፣ ዶናልድ ትራምፕ ከታች አንሰራርተው ብልጫ እያገኙ ነው እየተባለ ነው፡፡

     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...