Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሥነ ጥበብ ባህር እንዲሻገር

ሥነ ጥበብ ባህር እንዲሻገር

ቀን:

ክሪኤት ሀብ ጋለሪ ዱባይ የሚገኝ ጋለሪ ሲሆን፣ ትኩረቱን በአፍሪካ ሥነ ጥበብ አድርጎ የአፍሪካውያን ሠዓሊያን ሥራዎችን ለዕይታ ያበቃል፡፡ የሠዓሊያኑ ሥራዎች እንዲሸጡም መንገድም ያመቻቻል፡፡ የአፍሪካን ሥነ ጥበብ፣ በተለይም የምሥራቅ አፍሪካን ሥነ ጥበብ ለዓለም የማስተዋወቅ ዓላማ አንግበው የሚሠሩት የጋለሪው ባለቤቶች ጥንዶቹ ሊዲያ ካችቶሪያንና ክሪስቲያን ካችቶሪያን ናቸው፡፡

የጋለሪው ቢዝነስ አማካሪ በመሆን ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በማቅናት የሥነ ጥበብ ሥራዎችን የሚገመግመው ክሪስቲያን ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ተገኝቶ ነበር፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ሥነ ጥበብ ባተኮረው የጋለሪያቸው ስብስብ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ሠዓሊያንን የማካተት ዕቅድ ይዞም የሠዓሊያኑን ወርቅነህ በዙና ናሁሰናይ ንጉሤ ሥራዎችን መርጧል፡፡

ክሪስቲያን ከሪፖርተር ጋር ባደረገው አጭር ቆይታ፣ ሁለቱ የኮንቴምፕረሪ አርት (ዘመንኛ ሥነ ጥበብ) ባለሙያዎች ሥራዎቻቸው ኦሪጅናልና መነሻቸውን የማኅበረሰቡ ነባራዊ ሁኔታ ያደረጉ በመሆናቸው እንደተመረጡ ገልጿል፡፡ ‹‹በዋነኛነት የምናተኩረው በአፍሪካ ሥነ ጥበብ እንደመሆኑ ሥራዎቻቸው አፍሪካዊ ይዘት ያላቸውን እንመርጣለን፡፡ ሠዓሊያኑ ለተመልካቾች ስለመጡበት ማኅበረሰብም ያንፀባርቃሉ፡፡ በዚህ ረገድ ወርቅነህ ለዓይነ ሥውራን የሚሆኑ ሥዕሎች ያዘጋጃል፤›› ይላል፡፡ ወርቅነህ ዓይነ ሥውራን በመዳሰስ ሊገነዘቧቸው የሚችሉ ሥዕሎችን በመሥራት ይታወቃል፡፡

ላለፉት አራት ዓመታት በጋለሪያቸው ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ሠዓሊያን ሥራዎችን አሳይተዋል፡፡ በዚህም ሠዓሊያኑ ከአገራቸው ውጪ ዕውቅናቸው እንዲጨምር መደረጉን ክሪስቲያን ያምናል፡፡ አብዛኞቹ ሠዓሊዎች ከአገራቸው በዘለለ ባህር ተሻግረው ሥራዎቻቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ አናሳ ነው፡፡ ከአገራቸው ወጥተው ዐውደ ርዕይ ለማሳየት ወይም ሥራዎቻቸውን ለገበያ ለማቅረብ የሚያቀኑትም ወደ አውሮፓ ብቻ ነው፡፡

‹‹ሥራዎቻቸው ወደ ዓረቡ ዓለምም መግባት አለባቸው፡፡ ዱባይ ለተለያዩ ክንውኖች ተመራጭና መአከል እየሆነች እንደመምጣቷ ጥሩ አማራጭ ነው፤›› ሲል ይናገራል፡፡ እሱና ባለቤቱ የሚኖሩት ዱባይ ከመሆኑ አንፃር ለሥነ ጥበብ ያለውን ፍላጎትና ገበያውን እንደሚያውቁትም ያክላል፡፡ በርግጥ ስለ አፍሪካ ሥነ ጥበብ ያለው ግንዛቤ ውስን መሆኑን ሳይገልጽ አላለፈም፡፡ የአፍሪካ ሥነ ጥበብ ከትራዲሽናል አፍሪካን አርት (ባህላዊ የአፍሪካ ሥነ ጥበብ) ጋር ብቻ አያይዞ የማሰብ ነገርም አለ፡፡

‹‹ስለ አፍሪካ ሥነ ጥበብ በቂ ግንዛቤ የለም፡፡ ብዙዎች የአፍሪካ ሥነ ጥበብ የማስክ (ጭንብል) ሥራ ብቻ ይመስላቸዋል፡፡ የአፍሪካውያን አርቲስቶች ሥራዎችን ከአህጉሪቷ ውጪ በማሳየት ይህንን የተዛባ አመለካከት መለወጥ ይቻላል፤›› ይላል፡፡ በቀዳሚነት በኮንቴምፕረሪ አርት ላይ የሚሠሩም ስለ ዘርፉ ያለው ግንዛቤ እንዲሰፋ በማሰብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ኮንቴምፕረሪ አርት በዓረብ አገሮች ብዙ አለመታወቁ፣ የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎች ስለ ዘርፉ ለማወቅ ጉዳት እንዲያድርባቸውም አድርጓል ብሎ ያምናል፡፡

ዐውደ ርዕይ አሳይተው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ሥራዎቻቸው በጋለሪው ለሽያጭ ክፍት ይሆናሉ፡፡ ይኽም ሠዓሊያኑን በገንዘብ ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር እንደሚታይ ይናገራል፡፡ ‹‹ሠዓሊያኑ በሥራዎቻቸው ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፡፡ ግብይቱ ከሥነ ጥበብ ዐውድ ወጥቶ ንግድ ተኮር እንዳይሆን እንሞክራለን፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

ከዚህ ቀደም በክሪኤት ሀብ ጋለሪ የኬንያ፣ የኮንጎ፣ የናይጄሪያ፣ የሞዛምቢክና የሌሎችም አፍሪካ አገሮች ሠዓሊያን ሥራዎች ተሽጠዋል፡፡ ክሪስቲያን በየአገሩ እየተዘዋወረ ከአርቲስቶቹ ጋር በመገናኘት ሥራቸውን ይመለከታል፡፡ ባወጣቸው መሥፈርቶች መሠረት መዝኖም ለጋለሪው የሚሆኑትን ሥራዎች ይወስዳል፡፡ እነዚህን ሥራዎች ወደ ዱባይ ማጓጓዝ ግን አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ አንዳንድ የሥነ ጥበብ ሥራዎችን ለማጓጓዝ አስቸጋሪ ከመሆኑ በተጨማሪ ሥራዎቹ የተዘጋጁበትን ቅርፅ ሳይለቁ በጋሪው ማቅረብም ፈታኝ ይሆናል፡፡

‹‹የሞዛምቢኩ አርቲስት ጎንዛሎ ማቡንዳ ሥራዎች የሚዘጋጁት ከጦር መሣሪያ ልዩ ልዩ ክፍሎች ነው፡፡ ከምላጭ፣ ቃታ፣ ጥይትና ሌሎችም ቁሳቁሶች የሚሠራቸውን ቅርፆች በአውሮፕላን ለማጓጓዝ ከባድ ነበር፤›› ይላል፡፡ ሌሎች ሥራዎችን ወደ ዱባይ ለመውሰድም ይቸገራሉ፡፡ ሥራዎቹ ወደ ጋለሪው ከተወሰዱ በኋላ ደግሞ የተመልካቾችን ቀልብ ወደ አፍሪካ ሥነ ጥበብ የመሳብ ጉዳይ አለ፡፡ ብዙዎች ስለ ዘርፉ ያላቸውን ዕውቀት እንዲያዳብሩ ማነሳሳት ያሻል ይላል፡፡

ክሪስቲያን እንደሚገልጸው፣ እስካሁን በጋለሪው ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ 15 አርቲስቶች መካከል፣ እንኳንስ ከአህጉሪቱ ውጪ በአገራቸውም ሰፊ ዕውቅና ያላገኙ ይገኙበታል፡፡ የእነዚህ አርቲስቶች ሥራዎች ጥሩ ቢሆኑም፣ ተደራሽነታቸው አለመስፋቱን ይናገራል፡፡ በየአገራቸው መገናኛ ብዙኃንና በጋለሪው ድረ ገጽም ስለ ሠዓሊያኑና ሥራዎቻቸው ለማስተዋወቅም ይሞክራሉ፡፡ ‹‹ሥራዎቻቸው ጥሩ የሆኑ አርቲስቶች በአገራቸው እንዲሁም በዓለምም መታወቅ አለባቸው፡፡ ሰዎች ስለሥራዎቻቸው ይዘት እንዲገነዘቡም መድረኩ ሊመቻችላቸው ይገባል፤›› ይላል፡፡

ከሠዓሊያኑ አንዱ ወርቅነህ በዙ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ብዙ ሠዓሊያን አስተዋዋቂ በማጣት ሥራዎቻቸው አገር ውስጥ ይቀራሉ፡፡ ‹‹ስቱዲዮዋችን ድረስ መጥተው ሥራዎቻቸውን በማየት ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እንድናገኝ የሚሠሩት ሥራ ለኛ ሠዓሊያን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ዕውቅናም ያግዛል፤›› ይላል፡፡ ከኢትዮጵያ ባለፈ በመላው ዓለም ዕውቅና ማግኘትና ስለ ሥራዎቻቸው ቴክኒክና ይዘት ግብረ መልስ ማግኘት ያለውን በጎ አስተዋጽኦም ይናገራል፡፡

ሠዓሊው የአፍሪካ ሥነ ጥበብ ብዙም ቦታ እንዳልተጠሰው ገልጾ፣ የአፍሪካውያንን የሥነ ጥበብ ሥራዎች ከጋለሪና ከሙዚየም በተጨማሪ ሕዝብ ጋር ያላቸው ተደራሽነት መስፋት እንዳለበት ይናገራል፡፡ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው የሥነ ጥበብ ሥራዎች በልብስ ወይም በተለያየ በቁሳቁስ ላይ ታትመው ለሕዝቡ ቢደርሱ መልካም ነው ይላል፡፡ ‹‹ጊዜው የአፍሪካ ሥነ ጥበብ ነው፡፡ ዱባይ የብዙ ክንውኖች መካከል በመሆኗም የሥራዎቻችን ተደራሽነት ይሰፋል፤›› ሲልም ይገልጻል፡፡

ሠዓሊ ናሁሰናይ ንጉሤም በወርቅነህ ሐሳብ ይስማማል፡፡ ሠዓሊው የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የቅርብ ጊዜ ተመራቂ በመሆኑ መሰል ዓለም አቀፍ ዐውደ ርዕዮች ማቅረብ እንደሚያበረታታው ይገልጻል፡፡ ‹‹ሌላ አገር ያሉ ተመልካቾች ሥራዎቼን አይተው በሚሰጡኝ አስተያየት ምልከታዬ ይሰፋል፤›› ይላል፡፡ የአፍሪካ ሥነ ጥበብ በተለይም የኢትዮጵያ በቴክኒክና በግብዓት አጠቃቀም የተለየ በመሆኑ የሥነ ጥበቡ ተመልካቾች ፊታቸውን ወደ አፍሪካ እንዲያዞሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ያክላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...