Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሴቶቹ ተሞክሮ

የሴቶቹ ተሞክሮ

ቀን:

አዳራሹ በሆታና በዕልልታ ደምቋል፡፡ ነጋዴ ሴቶችን ለመዘከር በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በተለያዩ የንግድ ሥራዎች የተሰማሩ ሴቶች ተገኝተዋል፡፡ በተለያየ የዕድሜ ክልል ውስጥ ቢገኙም፣ ፕሮግራሙ አንድ ዓይነት ስሜት አሳድሮባቸዋል፡፡

የሕይወት ልምዳቸውን ላካፈሏቸው የነበሩት ስኬታማ ሴቶች በጭብጨባ አድናቆታቸውን ይገልጻሉ፡፡

ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ከተጋበዙት ሴቶች መካከል የሙልሙል ዳቦ ባለቤት ወ/ሮ ስምረት አባተ ንግግራቸውን የጀመሩት ከዛሬ 18 ዓመታት በፊት የነበሩበትን ሁኔታ በማስታወስ ነው፡፡ ወ/ሮ ስምረት የሦስት ልጆች እናት ሲሆኑ፣ ልጆቻቸውን ለብቻቸው ሆነው የማሳደግ ኃላፊነት የወደቀባቸው ሦተኛ ልጃቸው ድክድክ ማለት ባልጀመረችበት ወቅት ነበር፡፡ ‹‹ረጅም ታሪክ ነው እንዴት እንደሆነ አልነግራችሁም፡፡ ነገር ግን በአጋጣሚ ልጆቼን ለብቻዬ ለማሳደግ ተገደድኩ፤›› ሲሉ ሦስት ልጆቻቸውን ለብቻቸው ማሳደግ የጀመሩበትን ወቅት ያስታውሳሉ፡፡

ልጆቻቸውም ሆኑ እሳቸው ከሌሎች የምግብ ዓይነቶች በተለየ ዳቦ ይወዳሉ፡፡ ነገር ግን የሚፈልጉትን ዓይነት ዳቦ ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ይህም ቤታቸው ውስጥ መጋገር እንዲለምዱ አደረጋቸው፡፡ በየጊዜው ይጋግሩ ስለነበርም ባለሙያ ሆነዋል፡፡ ዳቦ ከሙያ ባለፈ መተዳደሪያ ይሆነኛል ብለው አስበውት አያውቁም ነበር፡፡ የሚያውቁት ሙያ ዳቦ መጋገር ነበረና እንደ መተዳደሪያ ሊያደርጉት አሰቡ፡፡ ባይሳካስ በሚል ጥቂት አመነቱ፡፡ ይሁንና ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው ዳቦ ጋግሮ ወደ መሸጡ ሥራ ተሰማሩ፡፡ ‹‹ዝም ብሎ ነገር መሥራት አልፈለኩም፡፡ ስለዚህም ከገብስ፣ ከአጃና ከጤፍ የተመጠነ ዳቦ መጋገር ጀመርኩ፤›› በማለት ‹‹ሙልሙል ዳቦ›› ዛሬ የደረሱበትን ስኬት ጅማሮ ያስታውሳሉ፡፡

በወቅቱ የሚያግዛቸው ሰው አልነበረም፡፡ ሌሊት ዳቦ በሚጋግሩበት ጊዜ ድንገት ከእንቅልፏ እየነቃች ታለቅስ የነበረችው ሕፃን ልጃቸውን አባብሎ ማስተኛትም ድርብ ሥራቸው ነበር፡፡ ነገሮች ተደራርበው ለመሥራት እንቅፋት ፈጥረውባቸዋል፡፡ መንፈሰ ጠንካራዋ ወይዘሮ ግን፣ በፈተና ውስጥ እንዴት ማለፍ እንደሚቻል አስመሰከሩ፡፡ እንጀራዬ ብለው የያዙት ሥራቸው አላሳፈራቸውም፡፡ የሚጋግሩት ዳቦ ተወዳጅ ሆነ፡፡ የሚረከቧቸው ድርጅቶች ቁጥርም እየበዛ ሄደ፡፡ ለአንድ ቤተሰብ መተዳደሪያ ተብሎ የተጀመረው ሥራ ለብዙዎች የገቢ ምንጭ ለመሆንም በቃ፡፡

ዛሬ የወ/ሮ ስምረት ሙልሙል ዳቦ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ ለ350 ዜጐችም የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ እልህ አስጨራሽ የነበረን የሕይወት ትግል ከወይዘሮዋ አንደበት ያደምጡ የነበሩት ታዳሚዎች ንግግራቸው እንደተቋጨ በደስታ አጨበጨቡ፡፡ ማን ያውቃል ከመካከላቸው ሌላ ወ/ሮ ስምረት ይኖር ይሆናል፡፡   

ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ከተጋበዙት ሌላዋ የኔክስት ዲዛይን ባለቤት ወ/ሮ ሣራ መሐመድ ነች፡፡ ‹‹እንደ እናንተ የተለያዩ የቢዝነስ ሥልጠናዎች ወስደን ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት በደረስን ነበር፤›› በማለት በአሁኑ ወቅት ያለውን ዕድል በማድነቅ ነበር ንግግሯን የጀመረችው፡፡ የስኬታማ ሴቶቹ የሕይወት ተሞክሮ ለውድቀታቸው ምክንያት እየሰጡ ወደኋላ የሚቀሩ ሴቶችን የሚያነቃቃ ነበር፡፡ ከምንም በመነሳት ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ እስኪበቁ ያጋጠሟቸውን እንቅፋቶች እንዴት እንዳለፉ፣ የትናንት ትዝታቸውን ሲያወሱ፣ ሰው እችላለሁ ብሎ ራሱን ካሳመነ የሚያቅተው ነገር እንደማይኖር የሚያስገነዝብ ነበር፡፡

ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት ወ/ሮ ሣራ በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራ ነበር፡፡ በወር የምታገኘው ግን እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ከወር እስከ ወርም አያደርሳትም፡፡ ለታክሲ እንኳን ትቸገር ነበር፡፡ ‹‹በጣም ቀጭን ስለነበርኩ አሠሪዬ አዝናልኝ ምግብ ተኮናትራልኝ ነበር፤›› ትላለች፡፡ የዲዛይን ዕውቀት የነበራት ወይዘሮዋ በሙያው በመሰማራት ከተቀጣሪነት ለመውጣት ወሰነች፡፡

ይሁንና ይህ ነው የሚባል ገንዘብ አልነበራትም፡፡ ይህ ግን ውሳኔዋን እንድትቀይር አላደረጋትም፡፡ ቤት አስይዞ መበደር እንደሚቻል አታውቅም፡፡ በሕይወቷ ትልቁን ውሳኔ መወሰን ነበረባት፡፡ ቤቷን መሸጥ፡፡ ‹‹ለእኔ ስኬት አምኖ መሥራት ነው፡፡ ፈጣሪ ለገበሬ ዘርን ለሠሪ ስኬትን አይከለክልም፤›› የምትለው ወ/ሮ ሣራ፣ ጠንክራ በመሥራቷ ውጤታማ መሆኗን ለታዳሚዎቹ አስረድታለች፡፡

በዕለቱ አምባሳደር ገነት ዘውዴና ሴት ነጋዴዎች ማኅበርን ከመሠረቱት አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ናሁሰናይ ግርማ ተገኝተው የማነቃቂያ ንግግርና ምክር ለሴቶቹ ለግሰዋል፡፡ ዶት ዲጂታል ኦፖርቹኒቲ ትረስት ስኬት ለሴት ነጋዴዎች በሚል መርህ በቀድሞው የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ኤጀንሲ ቅጥር ግቢ፣ ዓርብ ጥቅምት 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ባካሄደው ዝግጅት ላይ የተገኙት፣ በድርጅቱ ሲኒየር ውመን ዴቨሎፕመንት ኤንድ ፓርትነርሺፕ ኦፊሰሯ ቤተልሔም መለሰ እንደገለጸችው፣ የፕሮግራሙ ዓላማ ሴት ነጋዴዎችን ማበረታታትና የበለጠ እንዲሠሩ ማነሳሳት ነው፡፡ ከተቋቋመ ዓመታትን ያስቆጠረው ድርጅቱ ለወጣት ሴቶችና ወንዶች ከንግድ ጋር ተያያዥ የሆኑ በተለይም ተቀጥረው የማይሠሩ ዜጐች ሥራ እንዲፈጥሩ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ይሰጣል፡፡ ሠልጣኞችን ከረጂ ተቋማት ጋርም ያገናኛል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...