አቶ ታደሰ ኃይሌ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ ማግሥት ጀምሮ በልዩ ልዩ የመንግሥት ኃላፈነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ታደሰ፣ በተለይ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነርነት፣ ከዚያም በቀድሞው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታነት ያገለገሉባቸው ከሚጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ መካከል ይገኙበታል፡፡ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከንግድ ሚኒስቴር ተለይቶ በመውጣት ራሱን ችሎ ሲቋቋም ጀምሮ በማኑፋክቸሪንግ መስክ በተለይም በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ መስክ ያሉትን ሥራዎች በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግሥት በማኑፋክቸሪንግ መስክ የማክሮ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ደረጃ የሚደግፍ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የሚገልጹት አቶ ታደሰ፣ በተለይ በኤስክፖርት መስክ ሲታቀድ ከቆየውም በላይ ውጤት መመዝገብ እንደሚጀመር ዋቢ የሚያደርጉት በአገሪቱ ቅድሚያ ለተሰጣቸው ዘርፎች እየዋለ ያለው ካፒታልና እየተገነቡ ያሉ መሠረተ ልማቶችን ነው፡፡ የሐዋሳው ኤኮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻውን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የወጪ ንግድ ገቢ ከአልባሳት ምርቶችና ከጨርቃ ጨርቅ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከ60 ሺሕ ላላነሱ ዜጎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ከሐዋሳ በተጨማሪ ግንባታቸው በዘጠኝ ወራት ውስጥ ተጠናቀው ሥራ የሚጀምሩ አምስት ያህል የኢንዱስትሪ ፓርኮችም እንደ ሐዋሳው ሁሉ ተስፋ የሚደረጉ መሆናቸውን አቶ ታደሰ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ለበርካታ ዓመታት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ የሚቀመጥለትን ግብ ማሳካት ሲሳነው ቆይቷል፡፡ ይህንን የሚቀበሉት አቶ ታደሰ፣ ዘርፉ በርካታ ለውጦችን ለማለፍ በመገደዱ የመጡ ፈተናዎችንም አውስተዋል፡፡ አሥራት ሥዩም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ስላሉ ችግሮች፣ ዘርፉ ስለሚከናውናቸው እንቅስቃሴዎች፣ ለዘርፉ ድጋፍ ሰጪ ስለሆኑ ተቋማት፣ እንዲሁም በፖለቲካ ቀውሱ ምክንያት ጉዳት ስለደረሰባቸው ፋብሪካዎችና መንግሥት የሚሰጣቸውን ድጋፎች በማስመልከት ከሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ ጋር ያደረገው ቆይታ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ሁለት የተለያዩ ገጽታዎች አሉት፡፡ አንደኛው ዕድገት እያሳየ መምጣቱ ነው፡፡ ባለፉት ሰባት ወይም ስምንት ዓመታት ውስጥ ሳያቋርጥ አድጓል፡፡ እስከ 20 ከመቶ ያደገባቸው ጊዜያትም ነበሩ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ግን የኤክስፖርት ግቡን ማሳካት ተስኖታል፡፡ ይህ ተቃርኖ እንዴት ይታያል?
አቶ ታደሰ፡- የኢንዱስትሪ ወይም ደግሞ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለአገራችን ዕድገትና ለኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ወሳኝ ሚና አለው፡፡ የተሻለ ማምረት እየቻልን ነው፡፡ ቀደም ሲል ቆዳ በጥሬነቱ እንዲሁም ያላለቀ ቆዳ እንልክ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ያለቀለት ቆዳ መላክ ችለናል፡፡ ቆዳ በመላክ ብቻ ግን የተሻለ ገቢ ማግኘት አይቻልም፡፡ እሴት መጨመር ያስፈልጋል፡፡ ጫማ ማምረት አሁን ደግሞ ጓንትም መላክ ተጀምሯል፡፡ ድሮ ፒክል ዌት ብሉ ይባል የነበረውና ወደ ውጭ ይላክ የነበረው ቆዳ አሁን ወዳለቀለት ቆዳ ተቀይሮ መላክ ተችሏል፡፡ ይሁንና ለውጭ ገበያ የሚፈለገው ምርት በሚፈለገው ጊዜና ወቅት ተመርቶ መዘጋጀት አለበት፡፡ የአገር ውስጥ ገበያ በዚህ ረገድ ችግር የለበትም፡፡ በዋጋም ቢሆን አንዳንድ ጊዜ ከውጭ ገበያ ይልቅ የአገር ውስጥ ጥሩ ይከፍላል፡፡ አንዳንዶች ያመረቱትን ጫማ በአሥር ዶላር ወይም በ220 ብር ይልካሉ፡፡ እዚህ ግን ጥሩ የአገር ውስጥ 600 እና 700 ከዚያም በላይ ያወጣል፡፡ ትልቁ ነገር ግን በውጭ ገበያ ላይ ማተኮር የሚያስፈልገው የአገር ውስጥ ገበያ ውሱን በመሆኑ ነው፡፡ ለአገር ውስጥ ገበያ ለማምረት ትልቅ ፋብሪካ ቢከፈት በአንድ ጊዜ ገበያውን ይይዘዋል፡፡ ምንም እንኳ ዋጋው አነስ ቢልም በብዛት አምርቶ በመሸጥ መወዳደር ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፍ ገበያው ነው ዋናውና ዘላቂው ገበያ፡፡ የአንድ ቀን ምርት በአንድ ወርም ተመርቶ ላያልቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ኩባንያው በቀረው ጊዜ ውስጥ ምርት ማምረት ተስኖት ሊቆም ነው ማለት ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን የውጭ ገበያን መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ የውጭ ገበያ ላይ ከማተኮር ጎን ለጎን የአገር ውስጥ ገበያውን መመልከት ይቻላል፡፡ የአገር ውስጥ ገበያ ትንሽ ከመሆኑ ባሻገር የመግዛት አቅሙም ከዓለም ገበያ አኳያ ሲታይ አነስተኛ ስለሆነ የውጭ ገበያ ላይ የምናተኩረው ለዚህ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢንዱስትሪ ክላስተር ወይም የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ስትራቴጂው እንዴት እየተጓዘ ነው?
አቶ ታደሰ፡- አሁን የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ስትራቴጂ ይህንን አካሄድ ይቀይረዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እንደ ምሳሌ ሊነሳ የሚችለው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለመንግሥት የመጀመሪያው ተሞክሮ ነው፡፡ በፓርኩ በዓለም የሚታወቁ አምራቾች ገብተውበታል፡፡ እንደ ጆርጅ ሹ፣ እንደ ሺንትስ የሚባሉ የእስያ ኩባንያዎች ገብተዋል፡፡ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡና በውስብስብ ሒደት የሚመረቱ አልባሳት በእነዚህ ኩባንያዎች እየተመረቱ ለውጭ ገበያ እየቀረቡ ነው፡፡ ጄጄ የተባለው የሕፃናት አልባሳት አምራችም እየላከ ነው፡፡ ሌሎችም የሚጠቀሱ አሉ፡፡ እነዚህ ጀማምረዋል፡፡ በሙሉ አቅማቸው ማምረት በሚጀምሩበት ወቅት የኤክስፖርት ሒደቱና አፈጻጸሙ ይለወጣል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት በተወሰኑ የኤክስፖርት ኩባንያዎች ላይ ብቻ ተመሥርተን ስንሠራ ስለነበር አንዳንዶቹ እንዲያውም እየደከሙ መጥተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከመጡበትም አካባቢ ውጤታማ ያልነበሩ እዚህም መጥተው መቀጠል እያቃታቸው መዘጋት የጀመሩ አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የውጭ ገበያ ስትራቴጂው ላይ ከኢንዱስትሪ ዘርፉ አኳያ በጣም የሚከነክን ነገር ሊጠቀስ የሚችለው ዓለም አቀፍ ገበያው ውስጥ መግባት መፈለጋችን ለዘለቄታው ካለው ጠቀሜታ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስለአፍሪካ ገበያ ብዙም አይባልም፡፡ ቆዳና ጨርቃ ጨርቅ ትልቅ ፍላጎት አለው፡፡ ምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ያለው ፍላጎትም ትልቅ እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ ለአፍሪካ ገበያ ስትራቴጂው ትኩረት አድርጓል ማለት ይቻላል?
አቶ ታደሰ፡- የአፍሪካ ገበያ ትልቅ አቅም ያለው ገበያ ነው፡፡ መታየት አለበት፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ በሚደረግበት ጊዜ ተሰብሳቢዎች ለራሳቸውና ለዘመዶቻቸው ይገዛሉ፡፡ ኢትዮጵያ ሲመጡ ጫማና የቆዳ ውጤቶች ገዝተው ይኼዳሉ፡፡ ይኼ ጥሩ የገበያ አቅም እንዳለው የሚያሳይ ነው፡፡ በቅርቡ በተደረገው መጠነኛ ጥረት አፍሪካ በአንድ ወቅት ኬንያ ሄጄ እንደተረዳሁት በኮንትሮባንድ የሚሄድ ብዙ ምርት አለ፡፡ በኮንትሮባንድም ቢሆን የኢትዮጵያን ምርት የሚገዙትን ሰዎች አግኝቼ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ሲገዙ ጉዳት እንዳለው ገልጬላቸው ነበር፡፡ አቀባዩ ነው ዋናው ተዋናይ፡፡ በዚህ መንገድ የሚሠራው ሥራ ብዙ ጉቦና ሌሎች አላስፈላጊ ወጪዎች ስለሚታከሉበት ጫማው እዚያ ገበያ ሲደርስ ውድ ሊሆን ይችላል፡፡ በመደበኛውና በሕጋዊው መንገድ ቢሆን ግን በቀላሉና በአነስተኛ ዋጋ ሊገዙት እንደሚችሉ ገልጬላቸዋለሁ፡፡ አዲስ አበባ ከመጣችሁ ፋብሪካዎችን እናስጎብኛችሁና ተገናኝታችሁ ግዥ ብትፈጽሙ ይሻላል ብዬ አስረዳኋቸው፡፡ አንዳንዶቹ እኔ ከኬንያ ሳልመለስ ቀድመውኝ አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ቢያንስ በወር እስከ 200 ሺሕ ዶላር የሚያወጡ ልዩ ልዩ ኮንቴይነሮች ይላካል፡፡ በክላስተር ያደራጀናቸውም አሉ፡፡ የካ አካባቢ በክላስተር የሚያመርቱትንም አገናኝተናቸው ነበር፡፡ ከኬንያ፣ ሩዋንዳ ከዚያም አልፎ እስከ ኮንጎ ድረስ በኮንትሮባንድ ምርቱን እያሸጋገሩ ነው፡፡ ገበያው አለ፡፡ ችግሩ ግን በርካታ እንቅፋቶች መኖራቸው ነው፡፡
ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃ ገበያ ስምምነትን ከኮሜሳ አገሮች ውስጥ ፈራሚ አይደለችም፡፡ ስምምነቱን አልፈረመችም፡፡ ይህ በመሆኑ ምርቱ ሲላክ ታክስ ይከፈልበታል ማለት ነው፡፡ እርግጥ የኮሜሳ አባል በመሆናችን ክፍያው ይቀንሳል እንጂ ታክስ እንከፍላለን፡፡ አሁን ትልቁ ገበያ ለእኛ አውሮፓ ነው፡፡ በጣም ተለቅ የሚለው ገበያ ደግሞ የአሜሪካ ገበያ ነው፡፡ እስያም መካከለኛው ምሥራቅም መታየት ያለበት ገበያ ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁን ገበያ ማየት ይጠቅማል፡፡ አፍሪካ እርግጥ ትልቅ የገበያ ዕድልም ቢኖረው ከትራንስፖርትም አኳያ ስታየው ትልቅ እንቅፋት ነው፡፡ ወደ ኬንያ በኮንቴይነር ለመላክ መንገዱ ገና አልተመቻቸም፡፡ ስለዚህ በጂቡቲ ዞሮ መግባት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የምርቱ ዋጋ ከፍተኛ ይሆንና አዋጭነቱን ያሳጣዋል፡፡ ስለዚህ መሠረተ ልማቱ መሟላት አለበት፡፡ በጨርቃ ጨርቅ መስክ የጀመሩ ነበሩ፡፡ በዚህ አኳኃን እየላኩ ነው፡፡ ይህ ግን ሥጋት አለው፡፡ በኬንያ በኩል መንገዱ አልተገባደደም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለመላክም ቢሆን አመቺ ሁኔታ የለም፡፡ ለዚህ የአፍሪካ ትስስርና የአፍሪካ አኅጉራዊ የነፃ ገበያ ስምምነት ተግባራዊ ሲደረግ ለውጦች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በጨርቃ ጨርቅ መስክ ከፍተኛ ዕድል እንዳለን ታይቷል፡፡ ከፍተኛ አምራቾች እኛ ጋ ገብተዋል፡፡ እነዚህ አምራቾች የአፍሪካን ገበያ ይፈልጉታል፡፡ በመሠረተ ልማቱ ምክንያት ግን እንደ ልብ መላክ አልቻሉም፡፡
ሪፖርተር፡- የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በየጊዜው በሚያወጣው ዕቅድ ውስጥ የተለዩ ግቦችን ያስቀምጣል፡፡ በየዓመቱም በየአምስት ዓመቱም ለየት ያሉ ግቦችን ቢያስቀምጥም ብዙውን ጊዜ ግን ማሳካት ሳይችል ቀርቷል፡፡ እነዚህ ግቦች ግን በትክክል ታምኖባቸው ነው የሚወጡት? ወይስ እንዲሁ ፍላጎትን ለመግለጽ የሚወጡ ናቸው? ይህንን ማንሳት ያስፈለገው በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ ከዕቅድ በታች ሲሠራ መታየቱ ጥያቄ ስለሚያጭር ነው፡፡ በዓመታት ውስጥ እንዲህ ያሉ ያለመናበብ ችግሮች የታዩበት ምክንያት ምንድነው?
አቶ ታደሰ፡- እርግጥ ታሳቢ ሲደረግ የነበረው አንደኛው የውጭ ኢንቨስትመንት በስፋት ይገባሉ፡፡ የገቡትም በፍጥነት ወደ ማምረት ሒደት ይሸጋገራሉ በሚል ታሳቢ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግብ ስታስቀምጥ ከሚታሰበው ዓላማ ጋር መያያዝ አለበት፡፡ አሁን የወጪ ንግድ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳካት የማምረት አቅማችንን መጨመር፣ የወጪ ግባችንን ማሳካትም ግድ ይለናል፡፡ እነዚህ ሲሟሉ ነው ማክሮ ኢኮኖሚው ተረጋግቶ ሊጓዝ የሚችለው፡፡ መነሻችን አጠቃላይ በዕድገታችን ዕቅድ ውስጥ ያስቀመጥነው ግብ ነው፡፡ ይህም ሲባል ግን በርካታ የውጭ የሚል ታሳቢ በመያዝ ነበር፡፡ በነበሩት ብቻ ብንሄድ ምንም ምርታማ ብናደርጋቸውና የማምረት ብቃታቸውን ብናሻሽለው እንኳ ምንም ያህል ለውጥ አያመጣም፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ውጤት ሊመጣ የሚችለው በአዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ነው፡፡ እነዚህን ለማስገባትና በቶሎ ወደ ምርት እንዲገቡ ለማድረግ ችግር ነበር፡፡ አሁን ግን መፍትሔው ተገኝቷል፡፡ መፍትሔውም የኢንዱስትሪ ፓርክ ሆኗል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማልማት ብቃትና ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውን የውጭ ገበያ ላይ የሚያተኩሩትን በማስገባትና የተሟላ መሠረተ ልማት በማቅረብ ግቡን ለማሳካት ይቻላል በማለት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይኼ ብርሃን ማሳየት ጀምሯል፡፡ ለምሳሌ የሐዋሳ ፓርክን ብንወስድ ዓለም ካቀረባቸው የተሟላ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቢባል ሐዋሳ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ኤኮ ፓርክ በመሆኑም ተመራጭ ሆኗል፡፡
ከሐዋሳ ፓርክ ባሻገር በመሠራት ላይ ያሉ ከአምስት ያላነሱ ፓርኮች አሉ፡፡ አዳማ፣ ኮምቦልቻ፣ መቀሌ፣ ድሬዳዋ፣ አረርቲ የመሳሰሉት አሉ፡፡ አሥራ አምስት ያህል መንገድ ላይ ያሉ ፓርኮች አሉ፡፡ በአዲስ አበባ የዓለም ባንክ ፋይናንስ የሚያደርገውም አለ፡፡ በመንግሥት የሚገነቡት ፓርኮች በሚቀጥለው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ተጠናቀው ለሥራ ይዘጋጃሉ፡፡ ግንባታቸው ልክ እንደ ሐዋሳው በተመሳሳይ ደረጃ ይሆናል፡፡ ከዚህም በላይ ግን በግሉ ዘርፍ ተነሳሽነት አማካይነት የሚሠሩ አሉ፡፡ ለምሳሌ የቻይናው ኋጂዬን ጫማ አምራች ኩባንያ አዲስ የሚገነባው አለ፡፡ ከሌሎች ቻይናውያን መካከል ሰንሻይን የሚባለውና በሱፍ ልብስ የሚታወቀው ኩባንያ አዳማ አካባቢ የሚገነባው ይጠበቃል፡፡ ሌሎች የቻይና ኩባንያዎችም በድሬዳዋ የግል ኢንዱስትሪ ፓርክ ይገነባሉ፡፡ ጆርጅ ሹ ደብረ ዘይት አካባቢ ይገነባል፡፡ እንዲህ በማድረግ ዕቅዳችንንና አፈጻጸማችንን ለማስተካከል እናስባለን፡፡ ምናልባትም ከዕቅዳችንም በላይ ልናገኝ እንችላለን፡፡ አሁን ካለፈው ሁኔታችን ተነስተን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ያሟላና ለአካባቢ ተስማሚ ኤኮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብተናል፡፡ በርካታ ባለሀብቶችን ሊስብ የሚችል ከመሆኑም በላይ ከሌሎች አገሮች ደካማና ጠንካራ ጎኖች ልምድ ተወስዶበት የተገነባ ነው፡፡ በዚህ አኳኋን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ግብ ለማሳካትና በኢኮኖሚው ውስጥ ብሎም በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ የሚኖረውን ትክክለኛ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል የሚረዱ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሳልጠቅስ የማላልፈው የተቀናጀ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ዕቅድ ነው፡፡ በቅርቡ በተደረገ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኮንፈረንስ የፋይናንስ ጉዳይ ትኩረት አግኝቷል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በብዛት የሚገቡበት በመሆኑም እንዲህ በመሳሰለው እንቅስቃሴ ካቀድነውም በላይ ለመጓዝ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ ዘርፍ ድጋፍ የሚሰጡ ኢንስቲትዩቶችን አቋቁሞ ለዘርፎቹ ትኩረት መስጠቱን አሳይቷል፡፡ እነዚህ ተቋማት ግን ውጤታማነታቸውን በሚመለከት እንዴት ነው የሚገመገሙት? ከተቋቋሙ ረጅም ጊዜ ሆኗቸው እየሠሩ ነው፡፡ ውጤታማ ናቸው አይደሉም ለማለት የሚያስችል መመዘኛ አለ ወይ? የተነሱለትን ዓላማስ እያሳኩ ናቸው ማለት ይቻላል?
አቶ ታደሰ፡- የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ከሌሎች የኢንዱስትሪ መዋቅሮች ለየት የሚያደርገው፣ በተለይ ቅድሚያ ለተሰጣቸው ዘርፎች ድጋፍ የሚሰጡ ኢንስቲትዩቶችን ማቋቋሙ ነው፡፡ ይኼ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሚታይ አይደለም፡፡ ከኮሪያ የወሰድነው ጥሩ ልምድ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው የሚመራው በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሥር ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ ዘርፎቹን ለመምራት እንደ ኢንስቲትዩቶቹ ያሉ ተቋማት አሉት፡፡ ሚኒስቴሩ እነዚህን ተቋማት ተጠቅሞ በኢንዱስትሪው መስክ ዕድገት ለማምጣት እየሞከረ ነው፡፡ ኢንስቲትዩቶቹ ድጋፍ እንዲሰጡ ነው የተቋቋሙት፡፡ በመጀመሪያ የራሳቸውን አቅም መገንባት አለባቸው፡፡ አንዳንዶቹን ለማቋቋም እርግጥ ጊዜ ወስዷል፡፡ የሚፈለግባቸውን ተልዕኮ ለመፈጸም አቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ መንግሥት ለዚህ ብዙ ጥሪት እያፈሰሰ ነው፡፡ አንደኛው ለዘርፉ የሚፈለገውን አቅምና ብቃት እንዲያገኙ ከሌሎች በዓለም ላይ ልምዱና ብቃቱ ካላቸው የውጭ ተቋማት ጋር እናጣምራቸዋለን፡፡ ለምሳሌ በቆዳ ዘርፍ ሴንትራል ሌዘር ሪሰርች ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንዲያ የሚባለው የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው የምርምር ኢንስቲትዩት ከእኛ ጋር አብሮ እንዲሠራ ተጣምሯል፡፡ በጫማ መስክ ፉትዌር ዲዛይን ኤንድ ዴቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ኦፍ ኢንዲያ ከሚባለውም ጋር ተጣምረዋል፡፡ እንዲህ እንዲሆን ያደረግንበት ምክንያት የራሳቸውን ዕድገት ጠብቀው ይደጉ ብንል ውጤታማ ድጋፍ መስጠት እስኪጀምሩ ድረስ ሃምሳ ዓመታት ሊፈጅባቸው ይችላል ብለን ስለሠጋን ነው፡፡ ከሃምሳ ዓመታት በላይ የቆዩ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ እየወደቁና እየተነሱ ያካበቱትን ልምድ በቀላሉ እንዲያስተላልፉ ለማድረግ ነው ከእኛ ተቋማት ጋር እንዲጣመሩ ያደረግነው፡፡ ይህ ሲሆን ለትምህርት የሚጠፋው ጊዜ አጭር እንዲሆን ያግዛል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቃት ፈጥረው ለሌሎች ብቃት እንዲያስገኙ፣ በተለይም የአገር ውስጥ ባለሀብትን ለማቀፍ እንዲያስችሉ የተመሠረቱ ተቋማት ናቸው፡፡
የውጭው ባለ ሀብት የራሱን ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና የማኔጅመንት ልምድ ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከድጋፍ ሰጪ ኢንስቲትዩቶች የፋሲሊቴሽንና የአገልግሎት ድጋፍ ካልሆነ በስተቀር የአቅም ግንባታ ሥራ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ይሆናል፡፡ ኢንስቲትዩቶቹ በአሁኑ ወቅት አቅማቸው እየተገነባና እየሠሩ ነው፡፡ ጥሩ ውጤትም እያሳዩ ነው፡፡ ዋናው ተልዕኳቸውም ከሌሎች ኢንስቲትዩቶች ጋር በመሆን ሥልጠና መስጠት አንዱ ሥራቸው ነው፡፡ ምንም እንኳ ሥልጠና መስጠት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚናም ቢሆን፣ እነዚህ ግን ከዘርፉ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ መስኮች ላይ ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር ምርምርና ሥርፀት እንዲሁም የማማከር ሥራ መሥራት ዓላማቸው ነው፡፡ ሌላው ደግሞ የምርት ጥራት፣ የምርት ጠባይና የምርት አካላዊና ኬሚካላዊ መፈተሻ ወይም መመርያ አገልግሎቶችንም ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ሒደት ኢንስቲትዩቶቹ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ የአገራችን የቆዳ ቴክኖሎጂ ዕድገት ከፒክል፣ ከዌት ብሉ፣ ከክረስት ወዳለቀት ምርት እስኪደርስ ባለው ሒደት ላይ የምክር አገልግሎት በመስጠት የቆዳ ኢንዱስትሪዎችን የሚደግፉትና እዚህ ያደረሱት የእኛ ኢንስቲትዩቶች ናቸው፡፡ ይህ በመጣመር ወይም በቲዊኒንግ አሠራር የመጣ ነው፡፡ ሌላው የዓለም አቀፍ ምርት ተሞክሮ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከውጭ አማካሪዎች ጋር በመሆን ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ የሥልጠና ድጋፍ ይሰጣሉ፡፡ ሲጀመር በሰርቲፊኬት ቀጥሎም በዲፕሎማ ደረጃ ይሰጡት የነበረው ሥልጠና በአሁኑ ወቅት በቆዳ ቴክኖሎጂ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት መስጠት ተጀምሯል፡፡ ሥርዓተ ትምህርቱና ሌላውም የተሰናዳውና ሥልጠናውም ሲሰጥ መደበኛ ኮርሶች በአዲስ አበባ ይሰጣሉ፡፡
በቆዳ ነክ ላይ ያተኮሩ ትምህርቶች ግን በኢንስቲትዩቶቹና አብረዋቸው በሚሠሩት የውጭ ተቋማት አማካይነት የሚደገፍ ነው፡፡ ተማሪዎቹም በቆዳ ቴክኖሎጂ ሳይንስ ይመረቃሉ ማለት ነው፡፡ በጫማ ሳይንስ ቴክሎጂ መስክም ትምህርት መስጠት ተጀምሯል፡፡ ይህም ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ሲሆን፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም ከሥርዓተ ትምህርት ዝግጅት ጀምሮ በቆዳ ምርቶች፣ በዲዛይንና በጫማ ቴክኖሎጂ መስክ ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል፡፡ ይህ ሁሉ ሥራ በኢንስቲትዩቶቹ የሚሠራ ነው፡፡ ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው፡፡ የምርምርና የልማት ሥራም ጀምረዋል፡፡ የቆላ በጎችና ፍየሎች ቆዳ ወይም በከል እየተባሉ የሚጠሩት ቆዳቸው ይጣል ነበር፡፡ አሁን ግን በጥናት ተመራምረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከራክረው በምርምር ውጤታቸው የአእምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት አግኝተዋል፡፡ ይህ ቆዳ አሁን ወደ ምርት ገብቷል፡፡ ይህ እንግዲህ በተቋማቱ የመጣ ነው፡፡ ድሮ ቆዳ ፋቂ ብለን የምናጣጥለው ሙያ በማስትሬትና በዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ የሚሠለጥኑበት ትልቅ ዕውቅና ያለው ነው፡፡ በየፋብሪካው እየሄዱ የሚሰጡት ድጋፍ ቀላል አይደለም፡፡ የተቋማቱ ሥራ በዝርዝር ቢታይ ውጤታማ ናቸው፡፡ የቆዳ ዘርፍ ውጤታማ ነው፡፡ ጨርቅም በፍጥነት እየተጓዘ ነው፡፡ በጨርቅ ዘርፍ በርካታ ባለሙያዎች እየገቡ፣ የድጋፍ አቅም እየፈጠረና የተሻሻለ የአገልግሎት አቅርቦት እየሰጠ የሚገኝ ኢንስቲትዩት አለ፡፡ ጥሩ ጅማሮዎች አሉ፡፡ ሌሎች ኢንስቲትዩቶቻችን ግን ጀማሪዎች ስለሆኑ የራሳቸው ሕንፃ፣ የራሳቸው ላቦራቶሪ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የምርምር ፋሲሊቲ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አሁን በኪራይ እየሠሩ ነው፡፡ ስትራቴጂው በጠቅላላው ሲታይ ትክክለኛ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተቋማት የደረሰባቸው ጉዳት በሚዲያም፣ በመንግሥትም፣ በኩባንያዎቹ መግለጫዎችም ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በእናንተ ሥር በሚገኙ የውጭ ኩባንያዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት በገንዘብ ወይም በዓይነት የሚገልጹ መረጃዎች አሏችሁ?
አቶ ታደሰ፡- የዳሰሳ ጥናት አካሂደናል፡፡ የተጎዱትንም ለማየት ሞክረናል፡፡ በተለይ ጥቃት የደረሰባቸው አብዛኞቹ የውጭ ኩባንያዎች፣ እንዲሁም በሰበታ አካባቢ አንዳንዶቹም በሞጆ አካባቢ የሚገኙ ኩባንያዎች ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡ እርግጥ እንደ አበባ ያሉት እኛን ባይመለከቱም ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አሁን እንዲያውም በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍም የሚያሳዝነው ነገር አንድ ኢትዮጵያዊ ቶቶት የሚባል፣ ቢኤምቲ ከተባለው የቱርክ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም ኬብሎች አምራች ፋብሪካ ፊት ለፊት የሚገኝ ኩባንያ ላይ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ እኛ በአብዛኛው በውጮቹ ላይ ጉዳት እንደደረሰ ነበር የሰማነው፡፡ እሱም ላይ ጉዳት መድረሱን ስናውቅ ጎብኝተነዋል፡፡ ጉዳት ላድርስ ብለህ ተነስተህ ጠላትህ ላይ እንኳ ለማድረስ ብትቃጣ ቶቶት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመገመት የሚከብድ ነው፡፡ የከፋ ሙሉ ለሙሉ ውድመት ደርሶበታል፡፡ ከመርካቶ አካባቢ ወደ ጨርቃ ጨርቅ ሥራ እንግባ ብለው በአገር ውስጥ ጀምረን ወደ ውጭ ቀስ በቀስ እንልካለን ብለው ሥራውን የጀመሩ ወጣቶች ነበሩ ያቋቋሙት፡፡ ሆኖም ማሽኖቻቸውን እንዳለ አውድመውባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢሬቻ በዓል ወቅት በተፈጠረው ችግር የተከሰተ ነገር ነበር?
አቶ ታደሰ፡- ከኢሬቻ በዓል ጋር በተገናኘ በግርግሩ ወቅት በተፈጠረው ችግር ዜጎች በመሞታቸው ለሦስት ቀናት የታወጀውን የሐዘን ቀን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ ሠራተኞች ከሥራ በመቅረታቸውና እሱንም ተከትሎ በመጣው የማቃጠልና መሰል ተግባር አንዳንድ ቦታ ላይ የሠራተኞች አለመረጋጋት ታይቷል፡፡ ስለዚህ አሁን የሆነውን ምንድነው ብለን ስናይ፣ በእርግጥ አደጋ ደርሷል፡፡ እኔ እንዲያው ደምሬ ብገልጸው ከሳይገን ዲማ በቀር ይኼውም ወደ ኮሜርሽያል ኖሚኒስ የተዛወረ የቱርክ ኩባንያ ነው፣ ይህ ኩባንያ የተወሰኑ የፊኒሺንግና የሽመና ማሽነሪዎች ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ሌሎች ግን እንዳሉ ተጎድተዋል፡፡ የሳይገን ዲማ 80 በመቶ የፊኒሺንግ እንዲሁም የተወሰኑ የአልባሳት መስፊያ ክፍሎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ቢሮው እንዳለ ወድሟል፡፡ ይኼ እርግጥ የደረሰውን ጉዳት ለማሳነስ አይደለም፡፡ ይሁንና ቢሮው እንዳለ ወድሟል፡፡ የኩባንያው ሲስተሞች በጠቅላላ ወድመዋል፡፡ ሌሎችን ብንመለከት ለምሳሌ ቢኤምቲ የተባለው ኩባንያ ላይ የደረሰው ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ ቢሮው ላይ ነው፡፡ የቢሮ ዕቃዎች፣ የቢሮ ጽሕፈት መሣሪያዎችና ሌሎችም ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ ፋብሪካው አልተነካም፡፡
ሌላው አርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ሆኖ ሰበታ ላይ የሚገኝ ሚና የሚባል አርባ ምንጭ ሰበታም እየተባለ ይጠራል፡፡ በፊኒሺንግ ሥራ በጣም ውስብስብ የአውሮፓና የጃፓን ማሽኖችን ተክሎ የሚሠራ በኢትዮጵውያንና በቻይናውያን ባለሀብቶች የተገነባ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነበር፡፡ አብዛኛው ምርቱ ከጥጥ ውጭ ባሉት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በጣም አስገራሚ ግንባታ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በሙከራ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ወደ ማምረቱ ሒደት ለመግባት እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነው ጉዳት የደረሰበት፡፡ የደረሰው አደጋ ምንድነው ብለን ብናይ የሕንፃው መስታወቶች መርገፋቸው ነው፡፡ ይኼ እንኳ ብዙም ችግር አልነበረም፡፡ ይሁንና ግን ጨርቅ ከተሠራ በኋላ ጨርቁ የሚጠቀለልበትን ዕቃ የሚያመርት ማሽን በሙሉ አውድመውታል፡፡ ሦስት ያህል ማሽን ከነጥሬ ዕቃው አቃጥለዋል፡፡ ሌላው የተጠቃው የቻይናውያን መኖሪያ ሠፈር ነው፡፡ ፋብሪካውን የሚሠሩ ቻይናውያን የሚኖሩባቸው ቤቶች፣ አልባሳት፣ መጠቀሚያ ዕቃዎቻቸውና ሌሎችም ንብረቶቻቸው ተሠርቀዋል፣ ተቃጥለዋል፡፡ አይካ አዲስ ጉዳት እንዳይደርስበት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ ሊተርፍ ችሏል፡፡ ሠራተኞችም ለተወሰነ ጊዜ ሥራ በማቆማቸው ምርት ተቋርጦ ነበር፡፡ የውኃ ማከማቻ ታንከሮች ማምረቻ ተቃጥሏል፡፡ መጋዘኑና ጥሬ ዕቃዎቹ ተቃጥለውበታል፡፡ ፋብሪካው ግን ተርፏል፡፡ ሌላው ጉዳት የደረሰበት ሞጆ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆዳ አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡ ክሊኒኩና መኪኖች ተቃጥለውበታል፡፡ ወደ ዋናው ፋብሪካ ቦታ አልገቡም፡፡ የአርባ ምንጭ ማስፋፊያ የሆነው ሚና መኪኖችም ግቢው ውስጥ እንዳሉ በሙሉ ተቃጥለውበታል፡፡ የቢኤምቲ መኪኖችና እዚያው የነበሩ የሌሎች ድርጅቶች መኪኖችም ተቃጥለዋል፡፡ የሜታ ቢራ ፋብሪካ መኪኖችና የሌሎች ምርት ለመጫን የመጡ መኪኖችም ተቃጥለዋል፡፡ አሁን የደረሰውን ጉዳት በትክክለኛ ዋጋ ተምኖ ለማውጣት እየሠራን ነው፡፡ እርግጥ የቀረበ ዋጋ አለ፡፡ አንዳንዱ ያቀረበው ትክክለኛ ሲሆን፣ ትንሽ ለመቀበል ከበድ የሚልም አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ጉዳቱን እንዲያጠና የተቋቋመ ኮሚቴ እንዳለና መንግሥት ለደረሰው ጉዳት ካሳ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የእኔ ጥያቄ ግን ከካሳ ክፍያው በተጓዳኝ ያለው ነገር ነው፡፡ መንግሥት ካሳውን መክፈል ብቻም ሳይሆን ከቀረጥ ነፃ ዕድል በመስጠት እንደገና እንዲያንሰራሩ የሚያስችሏቸው ሌሎች ድጋፎችንም መስጠት አለበት የሚሉ ሐሳቦች ስለሚነሱ በዚህ በኩል ምን ታስቧል?
አቶ ታደሰ፡- ይህ የመንግሥት አቅጣጫ ነው፡፡ ውሳኔው ይጠበቃል፡፡ ካሳ ይከፈላል እየተባለ ቢነገርም የመንግሥትን አቅጣጫ እየጠበቅን ነው፡፡ ዝርዝር ጉዳዩን በሚመለከት እርግጥ የደረሰኝ ነገር ባይኖርም መንግሥት ግን እንዲያንሰራሩ እያበረታታ ነው፡፡ ቶሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ ሠራተኛውም ተረጋግቶ ወደ ሥራ ገበታው እንዲገባ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ የድጋፍ ፓኬጅ እየተቀረፀ በመሆኑ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መንግሥት አይቶ የሚወስነው በመሆኑ፣ ያንን የሚወስነውን አካል ተክቶ መናገር ያስቸግራል፡፡