Monday, February 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮምፒውተር ወንጀሎች

የኮምፒውተር ወንጀሎች

ቀን:

ከአንድ ወር በፊት የሆነ ነው፡፡ መስሪያ ቤቷ ያለውን የኢንተርኔት መስመር ተጠቅማ ከሥራዋ ጋር የተያያዙ ድረ ገጾችን ትጎበኛለች፡፡ ጠቃሚ ሆነው ያገኘቻቸውን መረጃዎች ወደ ላፕቶፕ ዳውንሎድ ታደርጋለች፡፡ ዘና ለማለት ደግሞ አንድ የአማርኛ ሙዚቃ በዮቲዩብ ታዳምጣለች፡፡  የከፈተቻቸው ድረ ገጾች በርካታ ነበሩና ከአንዱ ወደሌላው እየተሸጋገረች ታነባለች፡፡ የኢሜል መልዕክት የምትከታተልበት የያሆ ሜል ገጿንም አልፎ አልፎ ትመለከታለች፡፡

በዚህ መሀከል አንድ መልዕክት የያዘ ሳጥን በኮምፒውተር ስክሪኗ ታየ፡፡ ሳጥኑ ኤክስና ኖ (አልፈለገም) የሚሉ አማራጮች ነበረው፡፡ ፅሁፉ ምን እንደሚል ሳታነበው የኤክስ ምልክቱን ተጫነች፡፡ ብዙ ጊዜ ከአንድ ድረ ገጽ መረጃ በነጻ እንድታወርድ ወይም ለመረጃ ሰብስክራይብ (ምዝገባ) እንድታደርግ የሚጠይቁ የመልዕክት ሳጥኖች ስለሚመጡ፣ በዕለቱ የመጣላት ሳጥንም ተመሳሳይ ጥያቄ የያዘ መስሏት ነበር፡፡ የመልዕክት ሳጥኑ በድጋሚ ሲመጣ አሁንም ሳታነበው ኖ ላይ ተጫነች፡፡

ከመቅፅበት የላፕቶፑ ስክሪን ተለወጠ፡፡ የከፈተቻቸው ድረ ገጾች ጠፍተው በምትኩ ኮምፒውተሩ ውስጥ ያሉ ፋይሎቿ ባጠቃላይ ኢንክሪፕት (በኮድ መቆለፋቸውን) የሚገልጽ መልዕክት ታየ፡፡ መልዕክቱ የኮምፒውተሩ ባክግራውንድ ፒክቸር (በስክሪን የሚታይ ምስል) ሆነ፡፡ ሀሊማ አሊ (ስሟ ተቀይሯል) እንደምትለው፣ በኮምፒውተሯ ውስጥ ያሉ ፋይሎች እንደተቆለፈባትና 500 ዶላር ካልከፈለች እንደማይከፈትላት በመልዕክት ሳጥኑ ተገልጿል፡፡

‹‹ሁኔታው ግራ ስለገባኝ መስሪያ ቤቴ ያሉ የአይቲ ባለሙያዎችን ጠራሁ፡፡ እነሱም ግራ ተጋብተው እርስ በርስ ሲተያዩ ሁኔታው የበለጠ አደናገረኝ፡፡ የኮምፒውተሬ ስክሪን ሴቨር በሆነው የመልዕክት ሳጥን የሚነበበው ፅሁፍ ማብቂያ ላይ ዶላሩን የምልክበት አድራሻ ተቀምጦ ነበር፡፡ የአይቲ ባለሙያዎቹ አንቲቫይረስ (ቫይረስ የሚከላከል ሶፍትዌር) ጫኑልኝ፡፡ ነገር ግን ምንም ለውጥ አላመጣም፤›› ትላለች፡፡ የፅሁፍ፣ የፎቶግራፍ፣ የድምፅና የቪዲዮ ፋይሎቿን ለመክፈት ብትሞክርም አልቻለችም፡፡ በኮምፒውተሯ የኢንተርኔት አገልግሎት ከማግኘት በዘለለ የግል መረጃዎቿን መጠቀምም አልሆነላትም፡፡ በነጋታው ሁኔታው ተቀይሮ በጽሑፍ የመጣላት መልዕክት በድምፅ ተቀየረ፡፡ 500 ዶላር በአፋጣኝ ከፍላ ፋይሎቿ ዲክሪፕት (የተቆለፉ ፋይሎችን መክፈት) እንዲደረግላት በእንግሊዘኛ የሚጠየቅ ድምፅ ያለማቋረጥ ከኮምፒውተሯ ስፒከር ይደመጥ ጀመር፡፡

‹‹ገንዘቡን ልላክላቸው ብል እንኳን እኛ ሀገር የክሬዲት ካርድ ሲስተም የለም፡፡ የተጠየቅኩት ገንዘብ ኮምፒውተሬን ከገዛሁበት ገንዘብም ይበልጣል፡፡ የመጀመሪያ እርምጃዬ ፋይሎቼን ባጠቃላይ ማጥፋት ነበር፡፡ ለጥቂት ቀናት መልስ ሳልሰጣቸው ስቀር ይተውኛል ብዬ ነበር፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡ ኮምፒውተሯን ፎርማት (ፋይሎችን ባጠቃላይ መሰረዝ) ማድረጓ ግን ሁኔታዎችን አልቀየረም፡፡ የመልዕክት ሳጥኑና ድምጹ ለአንድ ሳምንት ቢጠፋም፤ መልዕክቱ በድጋሚ ተላከላት፡፡

‹‹የቀረኝ ፋይል ባይኖርም በድጋሚ ኢንክሪፕት የተደረገውን ፋይል ዲክሪፕት ለማስደረግ ገንዘብ ክፈይ የሚል መልዕክት በድጋሚ ሳገኝ አዲስ ላፕቶፕ ለመግዛት ወሰንኩ፡፡ የመስሪያ ቤቴ አይቲ ባለሙያዎች መጀመሪያ ከጫኑልኝ አንቲማልዌሮች የጠነከሩ ሶፍትዌሮች ጫኑልኝና ኮምፒውተሩ በድጋሚ ፎርማት ሲደረግ መልዕክቱ ጠፋ፤›› ትላለች፡፡

ሀሊማ እንደምትናገረው፣ ለረዥም ጊዜ የሰበሰበቻቸው ፎቶዎች፣ ሰነዶችና ሙዚቃዎች መጥፋታቸው አበሳጭቷታል፡፡ ስለ ሳይበር ክራይም (ከኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ወንጀል) በዜና ከሰማቸውና በፊልም ካየችው የዘለለ ጥልቅ መረጃ አልነበራም፡፡ ከሷ ውጪ ለማንኛውም ሰው ሊጠቅም የሚችል መረጃ በኮምፒውተሯ ባለመኖሩ ጥቃቱ ይደርስብኛል ብላም አትገምትም፡፡ ስለዚህ የኮምፒውተሯን ፋይሎች ለመጠበቅ ምንም ዓይነት ጥረት አድርጋ አታውቅም፡፡ አንቲማልዌር ሶፍትዌርም የላትም፡፡ የምትጎበኛቸውን ድረ ገጾች ትክክለኛነት አትፈትሽም፡፡ ኢሜል አካውንቷ የወጣው በስሟ ሲሆን፣ ፓስዋርዱ (የይለፍ ቃል) ቀላል ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ሀሊማ ብቻ ሳትሆን ብዙዎች ከግምት አያስገቡም፡፡ ስለ ደኅንነት ሲነሳ ከአካላዊው ባለፈ በተለይ በቴክኖሎጂው ባልበለፀጉ አገሮች ኮምፒውተር ላይ ስላሉ መረጃዎቻቸው ደኅንነት የሚያስቡ ጥቂቶች ናቸው፡፡ የመረጃ ዘመን በሚባለው በዚህ ወቅት የበርካቶች ሕይወት ከኤሌክትሮኒክስ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ ከመሆኑ ባሻገር ጠቃሚ መረጃዎች የሚመዘገቡትም በኤሌክትሮኒክስ ነው፡፡ በእጅጉ ከህይወት ጋር ከተሳሰሩ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች አንዱ ኮምፒውተር፣ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ መዝገብ እንደመሆኑ ስንቶች ለደህንነቱ ጥንቃቄ ያደርጋሉ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ ስንቶችስ መረጃዎቻቸውን ከጥቃት የሚከላከሉባቸውን መንገዶች ያውቃሉ?

የኮምፒውተር ጥቃት የሚደርስባቸው መንገዶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ ስለመጡ፣ ራስን መከላከል ከባድ ቢሆንም ምንጊዜም ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ያፈልጋል፡፡ ሀሊማ እስከ አሁን ጥያቄዋ ያልነበረው የኮምፒውተር ጥቃት ከደረሰባት በኃላ ግን ጥንቃቄ ከምትወስድባቸው ጉዳዮች አንዱ ሆኗል፡፡ የመረጃዎቿን ደኅንት ለመጠበቅ አስቀድማ ዕርምጃ ወስዳ ቢሆን ላታጣቸው ትችል ነበር፡፡

ኤሌክትሮኒክስን ያማከለው ዘመናዊ አኗኗር፣ ነገሮችን ቀላል ቢያርግም የሰዎች የግል መረጃዎች ደኅንነት ስጋት ውስጥ መውደቁ አልቀረም፡፡ ከኮምፒውተር ጋር የተያያዙ ጥቃቶች የግለሰቦች፣ የተቋሞችና በሀገር ደረጃም የራስ ምታት ከሆኑ ሰነባብተዋል፡፡ በየጊዜው መንገዱን እየለዋወጠ የሚመጣው ኮምፒውተርን ያማከለ ወንጀል አገሮችንን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያሳጣም ነው፡፡

እ.አ.አ በ2014 መገባደጃ በተሰራ አንድ ጥናት መሠረት፣ በዓመት ከዓለም ኢኮኖሚ 400 ቢሊዮን ዶላር የሚጠፋው በዚህ ወንጀል ሳቢያ ነው፡፡ ጥቃቱን የሚያደሱት ግለሰቦች አንድ ሀገር ውስጥ ሆነው ሌላ ሀገር ያሉ ግለሰቦች ወይም ተቋሞችን ኢላማ ስለሚያርጉ በሕግ ተጠያቂ ሳይሆኑ የሚያመልጡበት ጊዜም አለ፡፡ በአንፃሩ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሱ የነበሩና እጅ ከፍንጅ ተይዘው የታሰሩ ግለሰቦች አልያም ቡድኖችም ብዙ ናቸው፡፡

 ኢትዮጵያም ጊዜና ቦታ የማይገድበው የኮምፒውተር ጥቃት ሰለባ መሆኗ አልቀረም፡፡ የኮምፒውተር ፋይላቸው ኢንክሪፕት ተደርጎባቸው ማስለቀቂያ ገንዘብ የተጠየቁ ገጥመውናል፡፡ ኢሜላቸው ውስጥ ከማያውቋቸው ሰዎች አንዳንዴም የሚያውቋቸው ሰዎችን በማስመሰል የተላከ የእርዳታ ጥያቄ የደረሳቸውም አሉ፡፡ ኢሜል አድራሻቸውን በመጠቀም በአካውንታቸው ውስጥ ላሉ ሰዎች ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ የተላከባቸውም ብዙ ናቸው፡፡

ግሩም ስዩም የያሆ ሜል አካውንቱን በመጠቀም ስለሱ የተሳሳተ መረጃ እንደተላከ ያወቀው ዘግይቶ ነበር፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከዓመት በፊት የሱን ኢሜል አድራሻ በመጠቀም አካውንቱ ላይ አድራሻቸው ላሉ ሰዎች የተላከው መልዕክት፣ ሞሮኮ ውስጥ የመኪና አደጋ እንደገጠመው ይገልጻል፡፡ ሰዎች በአፋጣኝ ገንዘብ እንዲልኩለት በመጠየቅ ሞሮኮ የሚገኝ ባንክ ሒሳብ ቁጥርም ሰፍሯል፡፡

‹‹ኢሜሉ የደረሳቸው ሰዎች አደጋ ውስጥ ያለሁ ስለመስላቸው ተደናገጡ፡፡ ማለዳ ላይ ሀገር ውስጥና ውጪ ያሉ ዘመዶቼና ጓደኞቼ እየደወሉ ስልኬን አጨናነቁት፡፡ ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር አልነበረምና ግራ ተጋባሁ፤›› ይላል ግሩም፡፡ ኢሜል አካውንቱን ስካመሮች (በሀሰተኛ መረጃ ልኮ በማጭበርበር ገንዘብ የሚያካብቱ) እንደተቆጣጠሩት ተገነዘበ፡፡ ወዳጆቹ ጉዳዩን ሳያጣሩ እሱን ለመርዳት ገንዘብ ልከው እንዳይጨበረበሩም የአይቲ ባለሙያ ማማከር ጀመረ፡፡

ኢሜል አካውንቱን ለመክፈት የይለፍ ቁጥሩን ሲያስገባ አልከፈት አለው፡፡ ከይለፍ ቁጥሩ ውጪ ያሉ እንደ ስልክ ቁጥሩ ያሉ አማራጮችን በመጠቀም ሲሞክር ተከፈተለት፡፡ ኮንታክት አድራሻዎቹ ባጠቃላይ ግን ጠፍተው ነበር፡፡ ወዲያው በፌስቡክና ቫይበር ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለና ምንም ዓይነት አደጋ እንዳልደረሰበት አሳወቀ፡፡ አዲስ ኢሜል አድራሻ ማውጣቱን ገልጾም ተለዋጭ አድራሻ አስቀመጠ፡፡

ብዙ ሰዎች ስለ ኢንተርኔት አጠቃቀም ያላቸው ግንዛቤ አናሳ መሆኑን ግሩም ይገልጻል፡፡ ‹‹ብዙዎች ኢሜል አድራሻቸውንና የይለፍ ቁርሩን እንዲያገቡ ለሚጠይቁ የመልዕክት ሳጥኖች ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ በኢሜላችን አንድ የምናውቀው ሰው አደጋ ውሰጥ እንዳለ የሚገልጽ መልዕክት ሲደርሰን ማጣራት ሳይሆን ለመርዳት መሞከርን እናስቀድማለን፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛዬ መሰል ኢሜል ደርሶት ከአሜሪካ 500 ዶላር በባንክ ልኳል፣›› ይላል፡፡ እጣ ወጥቶላችኋል ወይም ሎተሪ ደርሷችኋል የሚል መልዕክቶችን የሚያምኑ ሰዎች እንዳሉም ያክላል፡፡

ጉዳቱ ሳይደረስበት በፊት ብዙም የሚጠነቀቅ ሰው ባይሆንም፣ አሁን እያንዳንዱ እንቅስቃሴው የታሰበበት ነው፡፡ ‹‹ለዓመታት የተሰበሰቡ ኢሜል አድራሻዎቼ ስለጠፉ ከዜሮ መጀመር ነበረብኝ፡፡ ሁኔታው ብዙ ነገሮች ስላመሰቃቀልብኝ አሁን ጠንቃቃ ነኝ፤›› ሲል ይናገራል፡፡

አቶ ፀጋዬ በለጠም ተመሳሳይ ተሞክሯቸውን አካፍለውናል፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በጎረቤታቸው ኢሜል አድራሻ አንድ መልዕክት ደረሳቸው፡፡ ኢሜሉ በጎረቤታቸው እንደተጻፈ መስሎ፣ ጎረቤታቸው እንግሊዝ ውስጥ እንደተዘረፉ ይገልጻል፡፡ ‹‹ጎረቤቴ እንግሊዝ እንዳልሄደ አውቃለሁ፡፡ ከዛ በፊትም ተመሳሳይ ተሞክሮ ስለነበረኝ ስካም መሆኑን አወቅኩ፡፡ ኢሜሉን ለላከልኝ ሰውዬ ገንዘብ ልልክለት ብፈልግም የክሬዲት ካርድ ሲስተም ስለሌለ እንዳልቻልኩ ጻፍኩላት፤›› ይላሉ፡፡ በስካመሩ ድርጊት ተበሳጭተው ስለነበረ ከጎረቤታቸው ጋር ተመካክረው የቻሉትን ያህል ለማስለፋት ወሰኑ፡፡

ወደ እንግሊዝ የሚሄድ ጓደኛ ስላላቸው ገንዘቡን እንደሚልኩለት ለስካመሩ ኢሜል አደረጉለት፡፡ ማንነቱን የሚገልጽ መታወቂያ ይዞ አየር መንገድ ሄዶ ገንዘቡን እንዲቀበልም ነገሩት፡፡ ለሁለት ሳምንታት የዘለቀው የኢሜል ምልልሳቸው የውሸት እንደሆነና ምንም ገንዘብ እንደማያገኝ የተገነዘበው ስካመሩ፣ በሁኔታው ተናዶ አቶ ፀጋዬንም ስካም ለማድረግ ማስፈራራት ጀመረ፡፡ ‹‹የጎረቤቴ ኢሜል ላይ ያሉ መረጃዎች ባጠቃላይ ጠፍተው ነበር፡፡ የእኔንም ለማጥፋት ዝቶብኝ ነበር፡፡ ነገር ግን አላደረገውም፤›› ይላሉ፡፡

የአይቲ ኤክስፐርቱ አቶ ፊሊሞን ተክሌ እንደሚሉት፣ ብዙ ሰዎች በግንዛቤ እጥረት ሳቢያ ቅድመ ጥንቃቄ ሲያርጉ አይስተዋልም፡፡ ‹‹በራንሰምዌር መረጃን ኢንክሪፕት አድርጎ በማገት ገንዘብ የሚጠይቁ አሉ፡፡ ሰው የሚያታልል የውሸት ታሪክ በመፍጠር ገንዘብ ስጡን የሚሉም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ዓቀፍ ኔትወርክ ውስጥ እንደመገኘቷ እንደሌሎች አገሮች ሁሉ ኢላማ ልትሆን ትችላለች›› ይላሉ፡፡

በኮምፒውተር የሚደርሱ ጥቃቶች ከግለሰብ ባለፈ እንደ አገርም አስጊ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ጥቃት ፈጻሚ ግለሰቦችንም ተከታትሎ መያዝ ላደጉ አገሮችም ፈታኝ በሆነበት በአሁኑ ወቅት ከግለሰቦች መረጃ ባለፈ እንደ አባይ ግድብ ያሉ አገራዊ ፕሮጀክቶች አደጋ ውስጥ እንዳይወድቁ የሳይበር ወታደሮች አስፈላጊ ናቸው ይላሉ፡፡ ለዚህም የመጀመርያው ዕርምጃ መሆን ያለበት የግለሰቦችን ግንዛቤ ማሳደግ ነው ብለው ያምናሉ፡፡

ከማይታወቁ ሰዎች የሚላኩ ኢሜሎችን አለመክፈት፣ በኢሜል አሳዛኝ መልዕክት ሲደርስ በስሜታዊነት አለመርዳትና ምክንያታዊ ሆኖ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች የሚጎበኟቸው ድረ ገጾችን ትክክለኛነት ማጣራትም አለባቸው፡፡ አንቲማልዌር መጫን እንዲሁም በየጊዜው አፕዴት ማድረግም ያሻል፡፡

እንደ አቶ ፊሊሞን፣ ለወደፊት ኢትዮጵያ ውስጥ የክሬዲት ካርድ ስርዓት ሲዘረጋና የመረጃ ልውውጦች ከአሁኑ የበለጠ ኮምፒውተርን ያማከሉ ሲሆኑ፣ ሁኔታው የበለጠ አስጊ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ኅብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያገኝባቸው መንገዶች መስፋት አለባቸው፡፡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኀንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ ግለሰቦች ራሳቸውን እንዴት መጠበቅ እንደሚችሉ መገንዘብ እንደሚገባቸውም ይገልጻሉ፡፡

ስሜ አይጠቀስ ብሎ አስተያየቱን የሰጠን ሌላ የአይቲ ባለሙያም፣ ተመሳሳይ ሐሳብ አለው፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የበለጠ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑት ኤትኤም ማሽኖች እንደሆኑ ይናገራል፡፡ ከሰዎች የኤቲኤም አካውንት በተጨማሪ ኮምፒውተር ላይ ያሉ መረጃዎቻቸውም ኢላማ ሊደረጉ ይቻላሉ፡፡ ጥቃቱ ሞባይልና ሌሎችም በኢንተርኔት የሚሰሩ ቁሳቁሶች ላይም ይደርሳል፡፡ ‹‹ብዙዎች ፍላሽ የሚጠቀሙት በዘፈቀደ ነው፡፡ ፍላሽ በሚጠቀሙበት ጊዜ ሁሉ በአንቲቫይረስ መጠበቅ አለባቸው፡፡ ግለሰቦችም ይሁኑ ተቋሞች ጠንካራ ኔትወርክ ሴኪዩሪቲ ፋየርዋል (የመረጃ መረብ ደህንነት ጥበቃ) ያስፈልጋቸዋል፤›› ይላል፡፡

ግለሰቦች፣ ተቋሞች ወይም አገሮች ሆን ተብሎ ኢላማ የሚደረጉበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ፣ ጥቃቱ በዘፈቀደ የሚሆንበትም ወቅት አለ፡፡ ባለሙያው እንደሚለው፣ ጥንቃቄው በሦስቱም ደረጃ አስፈላጊ ነው፡፡ ሰዎች ለተለያዩ የማኅበረሰብ ድረ ገጾቻቸው የሚሰጡት የይለፍ ቃል የተለያየ መሆን አለበት፡፡ የፋይሎች (ባክ አፕ) መረጃ መያዝም ጥሩ አማራጭ ነው፡፡ ማኅበረሰብ ድረገጽ ላይ በጣም ግላዊ የሆነ መረጃ አለማስፈር እንዲሁም ዋይፋይ በተገኘበት አጋጣሚ ሁሉ አለመጠቀምም ይመከራል፡፡

አይቲ ኒውስ አፍሪካ በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሰረት፣ አፍሪካ ውስጥ በሳይበር ጥቃት አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የኢንሳ የሳይበር ህግና ፖሊሲ ተመራማሪ አቶ ኃለፎም ኃይሉ በአቢሲንያን ሎው ድረገጽ ላይ ያስነበቡት ጥናት፣ የኢትዮጵያ የኢንተርኔት ዝርጋታ ውስን ቢሆንም፣ የፋይናንስና ሌሎችም ዘርፎች ኢንተርኔትን የተመረኮዘ እንቅስቃሴ እየጨመረ መሆኑን ያሳያል፡፡

እንደ ጥናቱ፣ ኢትዮጵያ እንዲሁም ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ከፍተኛ ጥንቃቄ አለማድረጋቸው ለሳይበር ጥቃት አጋልጧቸዋል፡፡ ‹‹የሞባይል መስመርና እንደ ኤቲኤም ያሉ የፋይናንሱ ዘርፍ አገልግሎቶችም ለጥቃቱ ተጋላጭ ናቸው፡፡

አጥኚው ለተለያዩ የግልና የመንግስት ተቋሞችን መጠይቅ በማቅረብ ባገኙት መረጃ መሰረት፣ የኮምፒውተር ቫይረስ፣ የስፓምና የሌሎችም ማልዌሮች ጥቃት በብዛት ይደርሳል፡፡ ብዙ ተቋሞች ጥቃቱን የሚከላከል የባለሙያ ስብስብ የላቸውም፡፡ ጥቃት ሲደርስባቸውም ለሚመለከተው አካል አያሳውቁም፡፡ ‹‹ግለሰቦችም ይሁን ተቋማት የሳይበር ጥቃትን ሪፖርት አያደርጉም፡፡ አንዳንዶች ሪፖርት በማድረግ ለውጥ ይመጣል ብለውም አያስቡም፣ ስለጥቃቱ ሲገልፁ ገጽታቸው የሚበላሽ የሚመስላቸውም አሉ፡፡›› ይላል፡፡

የችግሩን ሥር መስደድና ወንጀለኞቹ አንድ አገር ሆነው የሌላውን አገር ዜጋ ማጥቃታቸውን ከግምት ያስገባው ዓለም አቀፉ ኢንተርፖል፣ የሳይበር ጥቃትን የሚከላከልበት ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ በየአገሩ ላሉ የወንጀሉ መርማሪዎች የየጊዜውን ቴክኖሎጂ ያማከለ ሥልጠና በመስጠትም ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ችግሩን በመከላከል ረገድ፣ በኢትዮጵያ የኮምፒውተር ወንጀልን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ይጠቀሳል፡፡ በአዋጁ ሕገወጥ ጠለፋ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከ10,000 ብር እስከ 50,000 ብር የሚደርስ እንደሚያስቀጣ ተገልጿል፡፡ በኮምፒውተር አማካይነት የሚፈፀሙ የማታለል ወንጀል፣ ማለትም በተጭበረበረ መንገድ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት የኮምፒውተር ዳታን በመለወጥ፣ በማጥፋት ወይም ሌላ ማንኛውንም ጉዳት በማድረስ ሌላ ሰው ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያደረሰ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከ10,000 እስከ 50,000 ብር ይቀጣል ይላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቤተክህነት ባቀረበችው የይግባኝ አቤቱታ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለዕሮብ ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገወጥ ነው በተባለው አዲሱ ሲኖዶስና...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...