ግንባታ በስፋት እየተካሔደባት ባለው አዲስ አበባ ከግንባታ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ የግንባታዎች መወጣጫ (ስካፎልዲንግ) በብረት መሆን ሲገባው በእንጨት እየሆነና በአግባቡ ባለመሠራት የግንባታ ሠራተኞች ላይ በተለያየ መልኩ ጉዳት ሲደርስ ይስተዋላል፡፡ የራስ መከላከያ ሔልሜትን ጨምሮ የሥራ ላይ አደጋ መከላከያ ቁሳቁሶች ሳይሟሉላቸው ሠራተኞች ሲሠሩ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ግንባታዎች በአግባቡ መሸፈን ሲኖርባቸው ባለመሸፈናቸው ከውኃና ከአርማታ ፍንጥርጣሪ ባለፈ ከላይ የሚወርዱ ድንጋይና ሌሎች ቁሳቁሶች ግንባታዎቹ በሚካሔዱበት ሥር በሚተላለፉ እግረኞች ላይ ጉዳት የሚያደርሱበት አጋጣሚም ጥቂት አይደለም፡፡ በግንባታዎች በአግባቡ አለመሸፈን ከላይ የሚወርዱ ቁሳቁሶች እግረኞች ላይ ብቻም ሳይሆን ተሽከርካሪዎች ላይ ጭምር ጉዳት እያደረሱ ነው፡፡ የግንባታዎች ሰፊ የመንገድ ክፍል ይዞ መታጠርም ለእግረኛም ለተሽከርካሪም ችግር ስለመሆናቸው የተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ምስክር ናቸው፡፡