የፍቅር ጠበቃ
ፍቅር ጠበቃ አለው፣ ዘብ የሚቆምለት፤
ትዝታው እንዳይሞት፣ የሚሟገትለት፡፡
‹ናፍቆት ትዝታሽን፣ እረስቼዋለሁ፤
መቆዘሜን ትቼ፣ መሳቅ ጀምሬያለሁ፡፡
የፍቅርሽም ኃይል፣ መውደድሽ ግለቱ፤
ዛሬ ተፈጸመ፣ ግብአተ መሬቱ፡፡›
እያልኩኝ ሳቅራራ፣ እያልኩኝ ስፎክር፤
ካንገቴ በጥሼ፣ ያሰርሽልኝን ክር፤
ትዝታሽ ጠፋ ስል፣ ከውስጤ መንምኖ፤
ሽቶሽ አስታወሰኝ፣ ሌላ ሰው ላይ ሆኖ፡፡
- ፍስሃ ተክሉ ‹‹የግዞት ዓለም›› (2008)
* * *
በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የፖሊሱን የእጅ ስልክ ለመስረቅ የሞከረ
በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ገብቶ ቁሳቁስን መስረቅ እምብዛም የተለመደ አይደለም፡፡ በስፍራው ከደኅንነት አካላት በተጨማሪ የደኅንነት ካሜራዎች የሚገጠሙ በመሆናቸው በተለይ በቴክኖሎጂው በበለፀጉ አገሮች ድርጊቱን መፈጸሙ ምናልባትም ቂል ሊያስብል ይችላል፡፡ ቻይናዊው የፈጸመውም ይህንኑ ነው፡፡ ዩፒአይ እንደሚለው፣ የቻይና የፖሊስ ዲፓርትመንት የደኅንነት ካሜራ፣ አንድ ግለሰብ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ገብቶ የፖሊሱን የእጅ ስልክ ለመስረቅ ሲሞክር የቀረጸውን ምስል ይፋ አድርጓል፡፡ ግለሰቡ የፖሊሱን ስልክ ከቻርጀሩ ላይ ሰርቆ ከኪሱ ሲከት፣ በኋላም ከክፍሉ ወጥቶ ሊሄድ ሲል የክፍሉ በር ድንገት ተቆልፎ በማግኘቱ በመደናገጥ የሰረቀውን ስልክ ሶፋ ላይ ሲወረውር ያሳያል፡፡
ግለሰቡ ወደ ፖሊስ ጣቢያው የሄደው፣ ቀጣሪ ድርጅቱን ለመክሰስ እንደነበር ዘገባው ያሳያል፡፡
* * *
የአውስትራሊያ የፓርላማ አባል በመንግሥት መኪና ውሻቸውን በማጓጓዛቸው ይቅርታ ጠየቁ
የአውስትራሊያ የፓርላማ አባልና የኮሬክሽን ሚኒስትር ስቲቭ ኸርበርት፣ ሁለት ውሾቻቸውን መንግሥት በመደበላቸው መኪናና ሾፌር በማጓጓዛቸው ሕዝባቸውን ይቅርታ ጠየቁ፡፡
ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ኸርበርት ፖችና ቴድ የተባሉትን ውሾቻቸውን በሾፌራቸው የላኩት 120 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኘው ቤታቸው ነበር፡፡
ሚስተር ኸርበርት ስህተታቸውን ያመኑ ሲሆን፣ ‹‹በከፍተኛ የፖለቲካ ማዕረግ ላይ መገኘት ከባድ ሥራ ነው፡፡ አንዳንዴ ስህተት እንሠራለን፡፡ እኔ ያደረግሁት ከስህተቱ አንዱን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በታክስ ከፋዩ ገንዘብ የተገዛን መኪናና ለሾፌሩ የሚከፈል ደመወዝን ለግል ጥቅም በማዋላቸው ሚስተር ኸርበርት ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡
ሕዝባቸውን ይቅርታ ጠይቀው ለትራንስፖርት የወጣውን ነዳጅ እከፍላለሁ ቢሉም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ማቲው ጌይ ‹‹ኸርበርት ከሥራ መልቀቅ አለበት፤›› ብለዋል፡፡
* * *
ወጣቷ ዶናልድ ትራምፕን የተቃወመችበት መንገድ
ሰዎች እንዲመሯቸው የማይፈልጉትን ሰው ደብዳቤ በመጻፍ፣ በሚዲያ በመቅረብ፣ በአደባባይ ወይም ፊት ለፊቱ በመናገር ስሜታቸውን እንዲገልጹ የአሜሪካ ምድር የተመቻቸ ነው፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ምርጫ ዕጩ ሆነው የቀረቡትን ትራምፕ የተቃወመች ወጣት ደግሞ ተቃውሞዋን የገለጸችው የእሳቸው ደጋፊዎች ንብረት ናቸው ባለቻቸው 30 መኪኖች ላይ የኦቾሎኒ ቅቤ በመለቅለቅ ነው፡፡ ሃፍንግተን ፖስት እንዳሰፈረው፣ ወጣቷ በምርጫው ውዝግብ ተሰላችታለች፡፡ በተለይም ትራምፕን አትደግፍም፡፡ ተቃውሞዋን ለመግለጽ ብላ በመኪኖቹ ላይ የኦቾሎኒ ቅቤ በመቀባቷ ግን ክስ ተመሥርቶባታል፡፡ የ32 ዓመቷ ክርስቲና ፈርጉሰን፣ የተጠቀመችው የኦቾሎኒ ቅቤ ዝቅተኛ የጨው መጠን ያለው ስለነበር የመኪኖቹን ቀለም እንዳልሰነጣጠቀው ተዘግቧል፡፡
* * *
ካመለጠ ከ36 ዓመት በኋላ የተያዘው እስረኛ
የፔሩ ዜግነት ያለው ጋርሺያ ጐዶስ ከአደንዛዥ ዕፅ ጋር በተያያዘ አሜሪካ ውስጥ 12 ዓመት ተፈርዶበት ወህኒ ቤት የወረደው እ.ኤ.አ. በ1979 ነበር፡፡ ከ36 ዓመታት በፊት ከእስር ቤት ያመለጠው የያኔው ወጣቱ ጋርሺያ ጐዶስ የአሁኑ የ62 ዓመት አዛውንት የተያዙት ታዋቂ በሆነው የመዲናዋ ጐዳና ላይ እየተንጐራደደ እንደነበር የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል፡፡ በወቅቱ ከተፈረደበት ከአንድ ዓመት የእስር ቆይታ በኋላ ያመለጠው ጋርሺያ ጎዶስ ረዥሙን የዕድሜውን ዘመን ያሳለፈው ከፖሊስ በመሸሸግ ነው፡፡ ግለሰቡ ከአሜሪካ ወህኒ ቤት አምልጦ መቼ ፔሩ ውስጥ እንደገባ የፔሩ ፖሊስ ያለው ነገር የለም፡፡ ግለሰቡ በተገኘበት እንዲያዝ ዓለም አቀፍ የእስር ማዘዣ ወጥቶበት ነበር፡፡ ፔሩ ላለፉት አሥርት የኮኬይን ንጥረ ነገር የሆነውን ኮካ በማምረት ቀዳሚ ከሚባሉ አገሮች መካከል መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡