Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሥራ መጀመሩን ይፋ ያደርገው መርማሪ ቦርድ ከአስፈጻሚው የሚሞከር ተፅዕኖ አያሠጋኝም አለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የፓርቲ አባልነታችን ለኢሕአዴግ ጥብቅና አያስቆመንም›› የፓርላማው ወኪል አባላት

‹‹ሥራችንን የምናከናውነው ኢሕአዴግን ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን እያሰብን ነው›› የፍትሕ ዘርፍ ወኪል አባላት

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማስፈጸም ሒደት በኮማንድ ፖስቱና በሌሎች የሕግ አስፈጻሚ አካላት ሊከሰት የሚችል የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመከታተልና ዕርምጃ ለማስወሰድ የተቋቋመው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ፣ ሥራውን በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ከአስፈጻሚው አካል የሚሞከር ተፅዕኖም አያሠጋኝም አለ፡፡

በማጣራት ሥራ ወቅት በኮማንድ ፖስት አማካይነት የማስፈጸም ሥራውን ከሚያከናውነው የመንግሥት አካል፣ መርማሪ ቦርዱ ነፃነትና ገለልተኝነት ላይ ተፅዕኖ  ሊያሳድር የሚችል ሥጋት ሊኖር አይችልም በማለት የቦርዱ አባላት ገልጸዋል፡፡

ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. የቦርዱን በይፋ ሥራ መጀመር ለማብሰር የቦርዱ ዋና ሰብሳቢና አባላት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመከላከያ አዳራሽ  የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ በዕለቱም የቦርዱ አባላት በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሱ ዋና ዋና ተግባራትና ኃላፊነቶችን ዋቢ በማድረግ፣ ቦርዱ ሊተገብራቸው የተዘጋጀበትን የትግበራ ዕቅድ በመዘርዘርም አስረድተዋል፡፡

በዕቅድ ትግበራው ወቅት በክትትልና በቁጥጥር ሥራዎች ከሰብዓዊ መብት አያያዝና ከመብት ጥሰቶች ጋር ሊኖሩ የሚችሉ ክስተቶችን በግልጽ ለይቶ በማውጣት፣ ተጠሪ ለሆኑለት ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ገልጸዋል፡፡ ከምክር ቤቱ በተጨማሪ መርማሪ ቦርዱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠሪ መሆኑን ያስረዱት ሰብሳቢው፣ በኮማንድ ፖስቱ በኩል ሊከሰት የሚችል ኢሰብአዊ አያያዝን አጋልጦ የእርምት ዕርምጃ ማስወሰድ በሕገ መንግሥቱ ለቦርዱ የተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

ከቦርዱ ዋና ዋና ተግባራት ውስጥ ከአዋጁ ድንጋጌዎች መተላለፍ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ግለሰቦችን ዝርዝር፣ ማንነትና የታሰሩባቸውን ሥፍራዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል፡፡

ሙሉ በሙሉ በኢሕአዴግና በአጋር ፓርቲዎች ከተወከለው ምክር ቤትም ሆነ ከፍትሕ ተቋማት የተሾሙ አባላት የተዋቀረው መርማሪ ቦርድ፣ በሥራ አስፈጻሚው በኩል ሊታይ የሚችል የሰብዓዊ መብት ጥሰትን መርምሮ ለማጋለጥ ምን ያህል ገለልተኛና ተዓማኒነት ሊኖረው እንደሚችል፣ ነፃና ግልጽ የሆነ ሪፖርት ለማቅረብም ከአስፈጻሚው አካል ተፅዕኖ ሊያጋጥመው ይችል እንደሆነ ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡፡

ለጥያቄው ምላሽ ለመስጠት ቅድሚያውን የወሰዱት የቦርዱ ሰብሳቢ፣ ‹‹ቦርዱ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አባላቱም ከምክር ቤቱ የተውጣጡ ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት ቀድሞውንም የምክር ቤት አባል ያደረጋቸው የፓርቲው አባላትነታቸው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ለፓርቲያቸው ፖሊሲና ስትራቴጂ ተገዥ ቢሆኑም፣ በአፈጻጸም ላይ በሚታዩ ችግሮች ልዩነት ለማሳየት አይከለክላቸውም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአፈጻጸም በምናደርገው እንቅስቃሴ ተፅዕኖ ሊመጣ አይቻልም፡፡ ሥራችንን በነፃነት እንደምንሠራ ሊታወቅ ይገባል፤›› ሲሉም አቶ ታደሰ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የምክር ቤት ወኪል በመሆን የተሾሙት ወ/ሮ ገነት ታደሰ በበኩላቸው፣ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ የቦርዱ አባላት የኢሕአዴግ አባል ስለሆንን ብቻ ለመንግሥት ጥብቅና አንቆምም፤›› በማለት ቦርዱ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ስለሆነ የገለልተኝነት ጥያቄ ሊነሳ እንደማይችል ጠቁመዋል፡፡

ከፍትሕ ዘርፍ ተወክለው የተሾሙት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛው አቶ ክፍለጽዮን ማሞ በበኩላቸው፣ ‹‹ሥራችንን የምናከናውነው ኢሕአዴግን እያሰብን ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን እያሰብን ነው፤›› በማለት በቦርዱ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ እንደማያስነሳና በተፅዕኖ ሥር ሊወድቅ እንደማይችልም ገልጸዋል፡፡

ዋና መሥሪያ ቤቱን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ከፍቶ ሥራ መጀመሩን ይፋ ያደረገው መርማሪ ቦርዱ፣ በቅርቡም ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በተለያዩ የክልል ከተሞች እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡

ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች ከኮማንድ ፖስቱ አፈጻጸም እንቅስቃሴ ጋር ተያይዘው እንደሚከፈቱ ያስታወቁት የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ፣ በሁሉም ሥፍራዎች የኮሚቴ አባላቱን በማሰማራት ቦርዱ የክትትልና የቁጥጥር ተግባር እንደሚያከናውን ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ የሚገኙ ሪፖርቶችን ለምክር ቤቱ በማቅረብ፣ ዕርምት ያስፈልጋቸዋል ባላቸው ጉዳዮች ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብ ዕርምጃ የማስወሰድ ሥራ እንደሚኖርም ገልጸዋል፡፡

ኅብረተሰቡም ከመብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ጥቆማ ካለው ቦርዱ በሩ ክፍት መሆኑንም አሳውቋል፡፡ ለማንኛውም የጥቆማ አገልግሎት ኅብረተሰቡ በስልክ ቁጥር 0111-544641 እና በፋክስ ቁጥር 0111-545926 መጠቀም እንደሚችልም ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች