Friday, July 12, 2024

በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም የሕገ መንግሥቱ የበላይነት መቀጠል አለበት!

አገራችን ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ናት፡፡ በዚህም ሳቢያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን አግኝቷል፡፡ የዚህ ሁሉ መሠረት ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ በደግ ዘመንም ሆነ በክፉ ጊዜ፣ በጦርነትም ሆነ በሰላም ወቅት፣ በመደናበርም ሆነ በድንገተኛ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የሚገዛንና የምንገዛውም በሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አገሪቱን አደጋ ውስጥ የሚከት አጋጣሚ በመፈጠሩና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል አስገዳጅ ሁኔታ ማጋጠሙን በማስታወቅ፣ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል፡፡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦም ፀድቋል፡፡ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ተቋቁሟል፡፡ ቦርዱም በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ክንውኑ ሁሉ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እየተካሄደ ነው፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ሥራም በአዋጁ አፈጻጸም ወቅት የታሰሩ ሰዎችን ስም ዝርዝርና የታሠሩበትን ምክንያት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግ፣ በአፈጻጸም ወቅት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ኢሰብዓዊ እንዳይሆኑ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ነው፡፡ ሌሎችም ግዴታዎች አሉበት፡፡ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ሆነ፣ ሁልጊዜም ሕገ መንግሥቱ የበላይ ገዥ መሆን አለበት፡፡ ከተራ ዜጋ ጀምሮ ዝቅተኛና መካከለኛ ሹማምንት፣ ከፍተኛ ሥልጣን የጨበጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተለያዩ የሥልጣን አካላት፣ ከመንግሥት በተፃራሪ የቆሙ ተቃዋሚ ኃይሎችም ሆኑ ማንም ከሕግ የበታች መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱን የማስከበርና ተገዥ የመሆን ኃላፊነት በሁሉም ወገን ላይ የተጣለ ግዴታ ነው፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሥርም ሆነ በመደበኛው ሕይወት ውስጥ ለሕግ የበላይነት መገዛት የሚጠቅመው ሥርዓት ያለው መንግሥታዊ ቅርጽ ለመፍጠርና ዴሞክራሲን ለመገንባት ነው፡፡

በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻልና በአገር ላይ ያንዣበበ አደጋ አጋጥሞ አገርን አስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ ሲፈጠር፣ መንግሥትም የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን ሲያገኝ፣ ዋናው ዓላማና ግብ አገርና ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እንዲያገኙ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ሕዝብ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶቹን የሚጎናፀፍበትንና ዕለት ተዕለትም መብቶቹን የሚያጣጥምበት ጤናማ ሁኔታ እንዲፈጠርለትና አደጋዎችን ለማስወገድ መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ቀውጢ ጊዜም ቢሆን የሁሉም ነገር የበላይ አሁንም ሕገ መንግሥቱ መሆን አለበት፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ተሁኖም የአስቸኳይና የድንገተኛ ሁኔታዎች ሥልጣን የተሰጠው መንግሥት፣ የሕግ አስከባሪ አካላትንና አባላትን ነቅቶ የመጠበቅና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ ምክንያቱም መርማሪ ቦርዱ ኢሰብዓዊ የእስረኛ አያያዝ አለ ብሎ ሲያምን በገለልተኝነትና በታማኝነት ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ ማስተካከያ እንዲደረግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐሳብ ያቀርባልና፡፡

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን የሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ የሚጠበቁ መብቶችና ነፃነቶች አሉ፡፡ ለምሳሌም መላ አገሪቱን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባና መንግሥትንም የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣንና ኃላፊነት የሚሰጥ፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለና በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማያስችል ችግር ተፈጥሯል ወይ የሚል ጥያቄ ሲቀርብ፣ መጠየቁ ራሱ የጠላት ወይም የክፉ ሰው ጥያቄ ተብሎ መደምደም የለበትም፡፡ ምክንያቱም በአንፃራዊ ሁኔታ ሰላም የሆኑ በርካታ ሥፍራዎች አሉና፡፡ የአደጋውን መንስዔና መፍትሔ በተመለከተ ችግሩ በሚገባ ታውቋል? ትክክለኛው መድኃኒትስ ተገኝቷል? ብሎ መጠየቅም ለምንገኝበት ሁኔታ ከሚፈቀደው መብት፣ ነፃነትና ውይይት በላይ አይደለም፡፡ አማራጭና ተጨማሪ መፍትሔዎችን ለመፈለግ ይረዳል እንጂ፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለመንግሥት የተሰጠው ሥልጣን በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ለሕግና ለፀጥታ አስከባሪዎች የተሰጠውም ሥልጣን የዚያኑ ያህል ነው፡፡ የመርማሪ ቦርዱን ብርታትና ፅናት የሚፈታተኑም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለዘህም ነው የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት መቼም ቢሆን መረሳት የሌለበት፡፡

በተጨማሪም ተፈጻሚነት የላቸውም የተባሉ ሕጎች ስፋት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት የሚወሰዱ ዕርምጃዎችና የማይፈቀዱ ተግባራት፣ ኮማንድ ፖስቱ ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃ አፈጻጸም መመርያ ውስጥ የተከለከሉ ተግባራት፣ ለትርጉም የሚጋለጡና ለዘፈቀደ ዕርምጃ የሚያመቻቹ ክፍተቶች፣ ሕግ አስከባሪው የሕግ ተገዥውን በተለጠጠ ሥልጣን እንዳያጠቃ፣ ወዘተ. ሥጋቶች ሲኖሩ የመርማሪ ቦርዱን ትጋትና ንቁነት ይጠይቃሉ፡፡ ለመንግሥትም ሆነ ለፀጥታ አስከባሪዎች የተሰጠው ሥልጣን ብርቱ ክትትልና ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 (5፣6) መሠረት የተቋቋመው መርማሪ ቦርድ በዚህ ረገድ አደራና ሥልጣን አለው፡፡ የሕገ መንግሥቱን ሥልጣን ነቅቶ መጠበቅ አለበት፡፡ ሕገ መንግሥቱ በተለያዩ አንቀጾች የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብትን፣ ኢሰብዓዊ አያያዝን፣ የተያዙ፣ የተከሰሱና በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎችን መብት፣ በሰብዕና ላይ የሚፈጸም ወንጀል፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅና የመሳሰሉትን የያዘ ነው፡፡ ሁሌም ገዥ የሚሆነው እሱ ነው፡፡

ሥራውን በይፋ የጀመረው መርማሪ ቦርድ በተለይ በአንቀጽ 93(6)(ሀ) የተደነገገውን ሲፈጽም፣ ይህ ሥልጣኑ በሕገ መንግሥቱ የመሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ምዕራፍ ውስጥ የተደነገጉትን ማስከበር ግብ እንዳለው፣ የሕገ መንግሥቱ የበላይነት ድንጋጌ (አንቀጽ 9) መከበር፣ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ አካል መሆናቸው፣ በሕገ መንግሥቱ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋት ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ በሚሉት መገዛት አለበት፡፡ በተለይ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(6)(ሀ) የተገለጸው የአንድ ወር ጊዜ ብርቱ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ሰውን መሰወር በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሰው ልጆች ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል ያደረገች አገር፣ ለእነዚህ ወንጀሎች ደግሞ ክስ በይርጋ በማገድ ይቅርታና ምሕረት የከለከለች አገር፣ ቤርሙዳ የሚባሉ እስር ቤቶችና ደርግን የመሰለ መንግሥት ያየች አገር፣ በዚህ ዘመን የታሰሩ ሰዎችን አድራሻና ምክንያት ለአንድ ወር ያህል ሲቆይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግ ይመረጣል፡፡ ለዚህም ነው በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታም ውስጥ ሕገ መንግሥቱ የበላይነት መቀጠል ያለበት!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...

የታመቀ ስሜት!

የዛሬ ጉዞ ከመርካቶ በዮሐንስ ወደ አዲሱ ገበያ ነው፡፡ ታክሲ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...

ልዩነትን ይዞ ለዘለቄታዊ ሰላምና ጥቅም መተባበር አያቅትም!

መሰንበቻውን በአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች ተጫውተው ያለፉ ዝነኛ የአፍሪካ እግር ኳስ ከዋክብት በኢትዮጵያ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ዝነኞቹ ንዋንኮ ካኑ፣ ዳንኤል አሞካቺ፣ ታሪቡ ዌስት፣ ካማራና መሰሎቻቸው...