ይህ ነው የሚባል ገቢ የላቸውም፡፡ ለትምህርት ቤት እንኳ የሚከፍሉት አጥተው ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ከቀሩ ሰነባብተዋል፡፡ አስቤዛም ይቸግራቸዋል፡፡ በደህናው ጊዜ የሚያውቋቸው ወዳጆቻቸው ሕፃናቱ እንዳይራቡ ዳቦ ገዝተው ይሰጧቸዋል፡፡ ያልለመደባቸው የሰው እጅ ማየት ሞት ሆኖባቸዋል፡፡ ነገር ግን ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ የሚበሉት እስኪጠፋ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በችግር የተቆራመዱት አቶ አረቦ አህመድ ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ኑሯቸው ሙሉ የሚባል ዓይነት ነበር፡፡
ባለትዳርና የልጆች አባት የሆኑት አቶ አረቦ የመጡት ከሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ ነው፡፡ በደራ የእህል ነጋዴ ስለነበሩ ኑሯቸውም የሞላ ነበር፡፡ በኑሯቸው ደስተኛ የነበሩ ቢሆንም የባለቤታቸው የልብ ሕመም ግን ዕረፍት ይነሳቸው ጀመር፡፡ ለሕክምና በየጊዜው ወደ አዲስ አበባ መመላለሱም ያሰለቻቸው ነበር፡፡ ለሕክምናው ቀረብ ለማለትሲሉም ቤት ንብረታቸውን ሸጠው ሱሉልታ ቤት ሠርተው መኖር ጀመሩ፡፡ ቤት ሠርተው በተረፋቸው ገንዘብ ላይ ከባንክ መጠነኛ ብድር በመውሰድ የ2012 ሞዴል የሆነ ደረጃ 1 ታታ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ ገዙ፡፡
‹‹መኪናውን የገዛሁት ከሰው ላይ በ1.2 ሚሊዮን ብር ነው፡፡›› የሚሉት አቶ አረቦ በየወሩ 15,000 ብር የባንክ ብድር የመክፈል ግዴታ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ከየት አምጥቼ እከፍላለሁ የሚል ሥጋት አላደረባቸውም፡፡ ከመኪናው የሚገኘው ገቢ የባንክ ብድሩን እንደሚመልስ፣ ቤተሰባቸውን ቀጥ አድርጐ እንደሚያስተዳድርም ተማምነው ነበር፡፡ በእርግጥም ይቻላቸው ነበር፡፡ በመካከል ግን ያልጠበቁት ዱብ ዕዳ ገጠማቸው፡፡
ማክሰኞ መስከረም 24 ቀን የጅማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አድርሶ በመመለስ ላይ የነበረው የአቶ አረቦ አውቶቢስ ሰበታ አካባቢ እንደደረሰ አደጋ አጋጠመው፡፡ በዕለቱ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የነበሩ በአቶ አረቦና ሌሎች በመስመሩ ላይ ይሠሩ በነበሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ፈጸሙ፡፡ ጥቂት የማይባሉ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች በድንጋይ ተመትተው መስታወታቸው ሲረግፍ ሦስቱ ደግሞ በእሳት ጋዩ፡፡ ብዙ ይጠበቅበት የነበረው የአቶ አረቦ አውቶቢስ የአደጋው ሰለባ ሆነ፡፡ ‹‹መኪናው ከተገዛ ገና ወር አልሆነውም፡፡ ያለብኝን የባንክ ብድርም ገና ከፍዬ አልጨረስኩኝም፡፡ ባዶ እጄን ቀረሁኝ፡፡ ሌላ ምንም ዓይነት ገቢ የለንም፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር ሜዳላይ ወድቀናል›› በማለት በተስፋ መቁረጥ ስሜት ያሉበትን ሁኔታ ገልጸዋል፡፡
አጋጣሚው በባለንብረቶቹ ላይ ብቻ ሳይሆን በረዳቶች እና በአሽከርካሪዎች ላይም ከፍተኛ የሆነ ድንጋጤ ፈጥሮ ነበር፡፡ በተለይም ድርጊቱ ሲፈጸም በቦታው በነበሩት ላይ የፈጠረው ጭንቀት በቀላሉ የሚጠፋ አልነበረም፡፡
ከ18 ዓመታቸው ጀምሮ በአሽከርካሪነት ሥራ የቆዩት አቶ ሙሉጌታ አድሃኖም በቦታው ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ በወር 4,500 ብር እየተከፈላቸው የሚያሽከረክሩትን ደረጃ አንድ አገር አቋራጭ አውቶቢስ ይዘው ሰበታ ሲደርሱ ያልጠበቁት እንዳጋጠማቸው ሲገልጹ ‹‹ተከታትለን ሰበታ የደረስነው 4 መኪኖች ነበርን፡፡ እንደደረስን በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ቁሙ ቁሙ የሚል ምልክት አሳዩን፡፡ እንደተባልነው መኪኖቹን አቁመን ሁኔታውን ለማጣራት ሾፌሮች ብቻ ወረድን፡፡ ቀድመውን በደረሱ መኪኖች ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የነበሩ ወጣቶች ድንጋይ እየወረወሩ ነበር፡፡ በተመለከትነው ነገር በጣም ተደናገጥን፡፡ ወደኋላ እንዳንመለስ ብዙ መኪኖች ከኋላ ነበሩ፡፡ ወደፊትም ወደኋላም መሄድ አልቻልንም፡፡ ከዚያ ሆ! ብለው ወደኛ መጡ፡፡ ተሳፋሪዎችን አስወረዱና ዕቃ ማወራረድ ጀመሩ፡፡ በድንጋይ መስታወቱን መደብደብ ጀመሩ፡፡ በስተመጨረሻም ነዳጅ አምጥተው መኪናውን አቃጠሉት፡፡ ኡኡ ብዬ አለቀስኩኝ›› በማለት እንደ ፊልም መስሎ የሚታያቸውን የማይረሱትን አጋጣሚ ይገልጻሉ፡፡
አጋጣሚው ክፉኛ አስደንግጧቸው ነበርና ዳግም ወደ ሥራ ለመመለስ ፍላጐት አልነበራቸውም፡፡ ይሁንና የቤተሰብ ኃላፊ በመሆናቸው የሚጠበቅባቸውን ለማሟላት ሲሉ ከወር በኋላ ወደ ሥራ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹እኔ የሚያሳዝነኝ የመኪናው ባለቤት ነው፡፡ አደጋው የደረሰው ደግሞ ባለቤቱ ወልዳ አራስ ቤት ባለችበት ወቅት በመሆኑ ችግሩ እጥፍ ድርብ ነው›› ሲሉ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሙሉጌታ ያሉ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች አጋጣሚው ድንጋጤ ቢፈጥርባቸውም ግርግሩ ከተረጋጋ በኋላ ወደየሥራቸው ተመልሰዋል፡፡ እንደ አቶ አረቦ ያሉ ባለንብረቶችን ደግሞ የማይወጡት መከራ ውስጥ ከቷቸው አልፏል፡፡ ባለንብረቶቹ አደጋው በመድረሱ እና ሥራ መሥራት ባለመቻላቸው ከፍለው ያልጨረሱት የባንክ ብድር፣ የልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ፣ የአስቤዛ ወጪ ሌላም የማይወጡት ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡
አቶ ታከለ ኃይሌ ይባላሉ፡፡ ባለትዳርና የልጆች አባት ናቸው፡፡ የሚተዳደሩት በሜካኒክነት ሙያና በ1.5 ሚሊዮን ብር ከገዙት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢስ በሚገኝ ገቢ ነው፡፡ አብዛኛው ወጪያቸውን የሚሸፍኑት ከመኪናው በሚገኝ ገቢ ነበር፡፡ አሁን ግን ገቢው ተቋርጧል፡፡ አውቶቢሱ በደረሰበት የመቃጠል አደጋ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ ከተገዛ 2 ዓመት ከ4 ወራት አስቆጥሯል፡፡ ከመኪናው በወር ከሚገኘው ገቢ ላይ 17,675 ብር ለባንክ ብድር ይከፍሉ እንደነበረ፣ 5,000 ብር ለሾፌር ደመወዝ እንደሚከፍሉ እጃቸው ላይ የሚቀረው ቢበዛ 10,000 ብር እንደሆነ፣ ከዚያ ላይ 6,000 ብር ለቤት ኪራይ እንደሚከፍሉ፣ ተናግረዋል፡፡
‹‹3 ሕፃናት ልጆች አሉኝ፡፡ ለወተትና ለዳይፐር መግዣ የሚወጣው ወጪ ቀላል አይደለም›› የሚሉት አቶ ታከለ ብዙ ቀዳዳዎችን ይሸፍኑበት የነበረው ከዚሁ መኪና ገቢ በመሆኑና፣ እሱም በመቋረጡ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ይናገራሉ፡፡ ያለባቸውን የባንክ ዕዳ መክፈል አልቻሉም፡፡ ባልከፈሉ ቁጥር የሚኖረው የወለድ መጠን ከፍተኛ ስለሚሆን ብዙ ተጨንቀው ነበር፡፡ ‹‹ያለብኝን የባንክ ብድር ጓደኛዬ እንዲከፍልልኝ አድርጌያለሁ፡፡ ይህንን ያደረኩት በየወሩ ይወልድ የነበረውን 5,000 ብር ለማስቀረት ብዬ ነው፡፡ ገንዘብ ሳገኝ እከፍለዋለሁ›› በማለት አውቶቢሱ በመቃጠሉ የደረሰባቸውን ተደራራቢ ችግር ይናገራሉ፡፡
በተፈጥሮ አደጋ፣ በጦርነትና በመሳሰሉት በንብረትና በሕይወት ላይ ለሚደርሱ አደጋዎች የኢንሹራንስ ዋስትና አለመኖር ሁኔታውን ፈታኝ አድርጐታል፡፡ ምናልባት ከመንግሥት የምናገኘው ዕርዳታ ቢኖር በሚል ተስፋ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በመዘዋወር አቤቱታ እያቀረቡ እንደሚገኙ አቶ ታከለ ገልጸዋል፡፡
የአስጎብኚ ድርጅት ተሽከርካሪዎችም የጉዳቱ ሰለባ መሆናቸው ተሰምቷል፡፡ የአክሲዮን ማኅበር ይዞታ በሆኑ አገር አቋራጭ አውቶቢሶችም ላይ ተመሳሳይ ጉዳት ደርሷል፡፡
የዓባይ ደረጃ 1 አገር አቋራጭ አውቶቢስ የቦርድ ሰብሳቢና የጐልደን ባስ አክሲዮን ማኅበር ምክትል የቦርድ ሰብሳቢው አቶ መለስ ክህሽን እንደሚሉት፣ በወቅቱ ከሚዛን በመነሳት ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበረ አንድ ጐልደን ባስ ቱሉ ቦሎ ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ በነበሩ ሰዎች ተቃጥሏል፡፡ መኪናው 3 ሚሊዮን 150,000 ብር የተገዛ ሲሆን፣ ያልተከፈለ የባንክ ዕዳ አለበት፡፡ ሌሎች የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶችም በድንጋይ ተደብድበው መስታወታቸው ተሰባብሯል፡፡
በዓለም ደረጃ 1 ከፍተኛ አገር አቋራጭ አውቶቢስ ባለንብረቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጁ አቶ ገንዘብ አስማማውም እንደዚሁ በተፈጠረው ችግር ድርጅቶች ለኪሳራ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በማኅበሩ ሥር የሚገኙ ሁለት ደረጃ አንድ ታታ አውቶቢሶች መቃጠላቸውን፣ የአንዱ መኪና ዋጋ ከ1.5 ሚሊዮን ብር እስከ 1.9 ሚሊዮን ብር እንደሆነ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆን ያልተከፈለ የባንክ ብድር እንደነበረባቸውም ተናግረዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ወለጋ ሲዳሞና ሌሎችም መስመሮች ላይ ሲሠሩ በነበሩ 12 1ኛ ደረጃ አውቶቢሶች የፊት፣ የኋላ እና የጎን መስታወቶች ተሰባብረዋል፡፡ የፊት መስታወት አገር ውስጥ የማይገኝ መሆኑ፣ የአንዱ ዋጋም እስከ 100,000 ብር የሚደርስ በመሆኑ ተሽከርካሪዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ጥገና አድርጐ ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ አስቸጋሪ አድርጐታል፡፡ በድርጅቱ ሥር በሚገኙ አውቶቢሶች ላይ በአማካይ ከ200,000 እስከ 300,000 ብር የሚገመት ኪሣራ አድርሷል፡፡
የተለያዩ ጥያቄዎችን አንግቦ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በቀላሉ አልተረጋጋም ነበር፡፡ በግርግሩ የሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ መንገዶች ተዘግተዋል፣ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች በእሳት ጋይተዋል፣ ተሰባብረዋል፡፡ በወቅቱ መንገዶች ተዘጋግተው ስለነበር ወደተለያዩ ክልሎች መሔድ የነበረባቸው የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትራንስፖርት አጥተው ተቸግረውም ነበር፡፡
ዘመድ ለመጠየቅ ከሚኖሩባቸው ከተሞች ወደ አዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ወጥተው የነበሩም፣ በነበረው የትራንስፖርት ችግር በፈለጉት ጊዜ መመለስ ሳይችሉ ቀርተው ብዙ ተጉላልተዋል፡፡
የ15 ዓመቱ ቢኒያም ሰለሞን (ስሙ ተቀይሯል) ከሚኖርበት ጅማ ወደ አዳማ የሔደው እህቱን ለመጠየቅ ነበር፡፡ የአሥረኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ ክረምቱን ያሳለፈው አዳማ እህቱ ጋር ነበር፡፡ የዕረፍት ጊዜውን ጨርሶ ትምህርት ቤት ሲከፈት ወደ ጅማ ለመሔድ ተነሣ፡፡ ነገር ግን አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ወደ ጅማ የሚሔድበት የትራንስፖርት አገልግሎት ማግኘት አልቻለም፡፡
‹‹አውቶቢስ ተራ ብሔድ መኪናዎች አልነበሩም፡፡ ጭር ብሎ ነበር፡፡ የማደርገውን ነገር ባጣ እዚያው ሆኜ ማጠያየቅ ጀመርኩኝ፡፡ አንዳንድ መኪናዎች አቋራጭ መንገዶችን ተጠቅመው እንደሚሠሩ፣ ነገር ግን በመደበኛ ታሪፍ የሚከፈለው 106 ብር እንደማይበቃ፣ 450 ብር እንደሚጠይቁ፣ ለዚያውም ደግሞ በቀላሉ እንደማይገኙ ነገሩኝ›› የሚለው ቢኒያም አማራጭ በማጣቱ ወደ አዳማ ለመመለስ ተገድዶ እንደነበር ይናገራል፡፡
ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መንቀሳቀስ ለነበረባቸው የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሠራተኞችም ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር፡፡ የእነሱም ተሽከርካሪዎች የጥቃት ሰለባ ሆነው ነበር፡፡
ጥቂት የማይባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ይህ ነው የሚባል እጥረት ባይፈጥርም ሁኔታው በባለንብረቶች ላይም ሆነ በረዳቶችና ሾፌሮች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ሥጋት አሳድሮ ስለነበር ብዙዎች አገልግሎት ለመስጠት አይደፈሩም ነበር፡፡ ይህም ችግሩ ጐልቶ እንዲታይ አድርጐታል፡፡
በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ተስፋዬ በላቸው እንደሚሉት፣ በአገሪቱ ከሰላም ባስ ውጪ 1,500 የሚሆኑ አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቢሶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል 58 በሚሆኑ ላይ ቀላልና ከባድ አደጋ ደርሷል፡፡ የስፖኪዮ፣ የፊትና የኋላ መስታወት መሰባበር እና በሦስት ተሽከርካሪዎች ላይ የመቃጠል አደጋ ደርሷል፡፡ ነገር ግን እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ የደረሰው ጉዳት የትራንስፖርት ዕጥረት የሚያስከትል አይደለም፡፡
‹‹በአውቶቢሶቹ ላይ የደረሰው አደጋ በሌሎች ላይ ፍርኃት አሳድሮ ነበር፡፡ ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ ግን ሁሉም ተስተካክሏል፡፡ ከተቃጠሉት ውጪ ያሉት ቀላል የሆነ የመስታወት መሰባበር ያጋጠማቸው አውቶቢሶች ተጠግነው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡›› ሲሉ ከሞላ ጐደል ሁኔታዎች ወደነበሩበት እንደተመለሱ ተናግረዋል፡፡ በተሽከርካሪዎች ላይ በደረሰ አደጋ ለተፈጠረው ኪሣራ መንግሥት ሊያደርጋቸው ስለሚገቡ ነገሮች ምክረ ሐሳብ በማቅረብ የመፍትሔ አፈላላጊነት ተግባራቸውን እንደሚወጡ አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡ ይህ ምናልባትም ተስፋቸው ድንገት እልም ላለባቸው እንደ አቶ አረቦ የብርሃን ጭላንጭል ሊሆን ይችላል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ነገሮች የተረጋጉ ቢሆንም አሽከርካሪዎች ከሥጋት አለመላቀቃቸውን፣ ተደብቀው በተሽከርካሪዎች ድንጋይ የሚወረውሩ አልፎ አልፎ አሁንም እንዳሉ የሚናገሩም አልጠፉም፡፡