Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎችን የሚገድቡ አሠራሮችን ከለከለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስመጪዎች በሚያቀርቧቸው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች ላይ ይደረጉ የነበሩ ገዳቢ ቅድመ ሁኔታዎች እንዲነሱ የሚያዝ መመርያ አስተላለፈ፡፡

ገዥው ባንክ ከዘጠኝ ወራት በፊት የውጭ ምንዛሪ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ የግልጽነትና የማኔጅመንት ጉድለቶችን የተመለከተ መመርያ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ለሁሉም ባንኮች በጻፈው መመርያ መሠረት ንግድ ባንኮች በሚቀርቡላቸው ደረሰኞችና ፕሮፎርማዎች ላይ የቁጥር ገደብ እንዳያስቀምጡ አዟል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ባንኮች ለውጭ ምንዛሪ ጠያቂዎች ከዚህ ቀደም የሚያደርጉትን የምዝገባ ሒደት በተመለከተም ክልከላ አስቀምጧል፡፡ ይኸውም ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ጠያቂዎች ሲመጡ እንዳይመዘገቡ ከማድረግ እንዲታቀቡና ለተመዝጋቢዎቹም የወረፋ መጠባበቂያ እንዲሰጡ የሚገድባቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ ለባንኮች ያሠራጨው መመርያ ላይ ከሰፈሩት ክልከላዎች መካከል ዋነኛ የተባለው የውጭ ምንዛሪ ለሚጠይቃቸው አስመጪ ሁሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ወይም በባንክ ደንበኝነት እያሉ እንዳያስተናግዱ የሚለው ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ አስመጪዎች የሚፈለግባቸውን የሰነድ ግዴታ እስካሟሉ ድረስ፣ በየትኛውም ባንክ ደንበኛ ወይም የሒሳብ ደብተር እንዲኖራቸው ሳይጠየቁ እንዲስተናገዱ ብሔራዊ ባንክ አዟል፡፡ ‹‹የባንክ ሒሳብ መያዝ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ መቅረብ የለበትም፤›› ያለው ብሔራዊ ባንኩ፣ ከዚህ ቀደም ባወጣው መመርያና  ከባንኮች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ በመመሥረት፣ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች የሚስተናገዱበትን ዝርዝር ረቂቅ መመርያ በየራሳቸው እንዲያሰናዱ ለባንኮች ማስታወቁ፣ የባንኮቹን መመርያዎችም ተመልክቶም ሁሉንም ባንኮች ይመለከታሉ ያላቸውን የጋራ ጉዳዮች በሚመለከት በሰጠው አስተያየት አሥር ‹‹የማሻሻያ  ነጥቦች›› ብሎ የሰየማቸውን መመርያዎች አስተላልፏል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ባወጣው መመርያ መሠረት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ካላቸው ዘርፎች ውጪ የሚቀርቡ የአስመጪዎች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች እንዳመጣጣቸው በቅደም ተከተል እንዲስተናገዱ ማለቱ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ባንኮች ይህ አሠራር ገዳቢ ነው በማለት ትችት ሲያሰሙ ቆይተዋል፡፡ አስመጪዎችም ለአንድ ባንክ ካቀረቡት ጥያቄ በተጨማሪ ወደ ሌሎች በመሄድ ተመሳሳይ ጥያቄ እንዳያቀርቡ ማዘዙን ሲተቹና ለችግር እንደዳረጋቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲስተናገዱ ከተባሉት ውስጥ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያና ሌሎችም የግብርና ግብዓቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የመድኃኒት ምርቶች፣ ፋብሪካዎች የሚያቀርቧቸው የማሽነሪ ግዥዎች፣ መለዋወጫዎች፣ ጥሬ ዕቃዎች፣ ለሕፃናት የሚውሉ አልሚ ምግቦች ግዥ ላይ ለሚቀርቡ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎች ባንኮች ቅድሚያ እንዲሰጡ ማዘዙ ይታወሳል፡፡ ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡ የጭነትና የትራንዚት አገልግሎቶች ክፍያ፣ ብሔራዊ ባንኩ ፈቃድ የሰጣቸው ብድሮች፣ የአቅራቢዎች ብድሮች፣ ወለድ፣ ትርፍ፣ የትርፍ ድርሻ ክፍፍል፣ ለውጭ ሠራተኞች የሚፈጸሙ የደመወዝ ክፍያዎች ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ከተባሉት ውስጥ መመደባቸው አይዘነጋም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች