Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቱሪዝም ዘርፉ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተሰጠው ትርጓሜ ተፅዕኖ አምጥቶብኛል አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለወራት የዘለቀው ተቃውሞ ያስከተለው አመፅ አጠቃላይ የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ አሽመድምዶታል እየተባለ ባለበት ወቅት፣ አመፁን ለመቆጣጠር ያስችላል ተብሎ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተተረጎመበት መንገድ የዘርፉን የገቢ ምንጭ የባሰ ጫና ውስጥ መክተቱን ከዘርፉ ጋር ቁርኝት ያላቸው ባለሀብቶች አስታወቁ፡፡

መንግሥት በበኩሉ በባለሀብቶቹ የተጠቀሰው ችግርና የዘርፉን በተፅዕኖ ሥር መውደቅ እንደሚያምን አስታውቆ፣ በውስጡ የያዛቸውን ድንጋጌዎች በአግባቡ ካለመረዳት ወይም በተሳሳተ መንገድ አጋኖ በመተርጎም የተነሳ እንጂ፣ አዋጁ በዚያ መንገድ ጉዳት የሚያመጣ አልነበረም በማለት ገልጿል፡፡

ረቡዕ ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ በተጠራው የምክክር ስብሰባ እንደተገለጸው፣ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው የሰላም መደፍረስ ክፉኛ ከጎዳቸው ዘርፎች መካከል ቱሪዝም ዋነኛው ነው፡፡ ጥቃቶችን እንዳስተናገደ የተገለጸ ሲሆን፣ ጥቃቱ ደርሶባቸዋል ከተባሉት ውስጥ ለአብነት ስምጥ ሸለቆ አካባቢ ሎጆች ላይ የደረሰው ጉዳት ተነስቷል፡፡

የቱሪስቶች ፍልሰት በተለይ ጎንደር አካባቢ ክፉኛ እንዳስተጓጎለ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ዘርፉ ወደነበረበት እንዲመለስና እንዲያገግም ለማድረግ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደሚደግፉትና አንፃራዊ ለውጥ ለዘርፉ እንዳመጣላቸው ተናግረዋል፡፡ ሆኖም አሁንም ወደነበረበት ለመመለስ ብዙ ሊሠሩ የሚገባቸው የቤት ሥራዎች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡

የአስጎብኚ ድርጅቶች ተወካዮች ተደጋጋሚ የጉዞ ስረዛ እንደሚገጥማቸው ለሚኒስትሯ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፣ ለዚህም የዲፕሎማቶች ከ40 ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ ዕውቅናና ፈቃድ ማግኘት አለባቸው የሚለውን የኮማንድ ፖስቱን የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃ አፈጻጸም መመርያ ክፍል ኤምባሲዎች በአሉታዊ ጎኑ በመተርጎም፣ ወደ አገር ቤት ለጉብኝት ለሚመጡ ቱሪስቶች ተቃራኒ መልዕክት ስለሚያስተላልፉ ነው ተብሏል፡፡

ቱሪስቶችን ዲፕሎማቶች ናችሁ አይደላችሁም የሚሉ ፍተሻዎችና መጉላላቶች በዝተውባቸዋል ሲሉም ለሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡

ባንኮችም ጉዞ ሲሰረዝ ያስገቡትን ገንዘብ የውጭ ምንዛሪ ይፈለጋል እያሉ አለመመለሳቸው ሌላው ችግራችን ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹መንግሥት ለቱሪስቶች ሰላማችን መመለሱንና መጎብኘት እንደሚችሉ ንገሩ ቢለንም፣ የኢንተርኔት መቆራረጥና አለመኖር አሁን አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ለመናገር አላስቻለንም፡፡ በምን ሁኔታ አገራችንን ጎብኙ እንበላቸው?›› ሲሉም አንድ ተሳታፊ ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሯ በኢኮኖሚ ኮማንድ ፖስት ሥር የተቋቋመው የባህልና ቱሪዝም ኮማንድ ፖስት የቤት ሥራውን ለመወጣት ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

በዲፕሎማት የጉዞ ዕቀባ ድንጋጌ በኩል ያለውን የተሳሳተ አተረጓጎም በማስተካከል፣ ከዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ለመወያየት መታቀዱንም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች