የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ሕገወጥ መሣሪያዎችን በከፍተኛ ደረጃ በመሰብሰብ ላይ እንደሆነ ተጠቆመ፡፡
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ረቡዕ ጥቅምት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ኮማንድ ፖስቱ ስኬታማ ከሆነባቸው መካከል በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕገወጥ መሣሪያዎችን መሰብሰብ መቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ሕገወጥ መሣሪያዎች መሰብሰባቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕገወጥ መሣሪያዎች አሁንም ያልተሰበሰቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ጊዜያት ውስጥ የተገኙትን ውጤቶች ሲያስረዱም፣ ግጭትንና ብጥብጥን በዋናነት በመላ አገሪቱ መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
‹‹ዜጎች ጥቃት ይደርስብናል ከሚል ሥጋት ተላቀው ወደ ቀድሞው ሕይወታቸው መመለሳቸው ትልቁ ስኬት ነው፤›› ሲሉ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል፡፡ በርካታ ኢንቨስትመንቶችና ፋብሪካዎች ተመልሰው ወደ ሥራ መግባታቸውንም አክለዋል፡፡
በተቃውሞ ወቅት ሰዎችን በመግደልና ንብረት በመቃጠል ወንጀል የፈጸሙ እጃቸውን እየሰጡ መሆናቸውን፣ እንዲሁም በኅብረተሰቡ ጥቆማና በፀጥታ ኃይሎች ጥረት መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ምን ያህል ሰዎች እንደታሰሩ በእርግጠኝነት መናገር ያልቻሉት አቶ ጌታቸው በሕግ የሚጠየቁ እንደሚኖሩ ግን ጠቁመዋል፡፡
አብዛኞቹ የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው እንደሚለቀቁ ገልጸው፣ የተሃድሶ ሥልጠና ምን እንደሆነ እንዲያብራሩ ሲጠየቁ ‹‹ሕገ መንግሥቱን መማርና የሰውነት ማጎልበቻ ሥልጠና ሊወስዱ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡