Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር በክብ ጠረጴዛ እንዲወያዩ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር በክብ ጠረጴዛ እንዲወያዩ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት አገሪቱን ከሚመራው መንግሥት ጋር በክብ ጠረጴዛ እንዲወያዩ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አቀረበ፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥቅምት 12 ቀን እስከ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ያደረገውን መደበኛ ስብሰባ መጠናቀቁን አስመልክተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች አሉን የሚሉ ወገኖች ኢትዮጵያንና ጥቅሞቿን በማይፃረር በሰላማዊ መንገድ ተቀራርቦ በክብ ጠረጴዛ ከመንግሥት ጋር የጋራ ውይይት በማካሄድ ችግሮችን መፍታት አግባብነት አለው፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘውም ይህ የአገር ጉዳይ የጋራና የውስጥ ጉዳይ እንጂ ድንበር ተሻጋሪ እንዳልሆነ፣ በአገሪቱ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግንዛቤን ወስደው የበኩላቸውን ድርሻ መፈጸም ይችሉ ዘንድ የራሳቸው የሆነውን አመለካከት ይዘው አገሪቱን ከሚመራው መንግሥት ጋር በክብ ጠረጴዛ እንዲወያዩ አሳስበዋል፡፡

የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በዓመታዊ መደበኛ ስብሰባው የተመለከተው ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በወቅቱ በተፈጠረው ችግር የሰዎች ሕይወት እየጠፋ መሆኑ፣ ሀብትና ንብረት እየወደመ መታየቱ፣ ከነበሩበትና ከኖሩበት ቦታ የሕዝቦችን ፍልሰት ማስከተሉን፣ በእነዚህም እየታዩ ባሉ ችግሮች ምክንያት በሰላማዊው ኅብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ሥጋት እየሰፈነ መምጣቱንና ልማታዊ ሥራዎችም ሊስተጓጎሉ እንደሚችሉ መገንዘብ ተችሏል ብሏል፡፡

ከዚህ አንፃር ባወጣው መግለጫው መንግሥት እንደ ቤት ኃላፊና ልጆቹን እንደሚያስተዳድር መሪ እንደመሆኑ መጠን በሰከነና በተረጋጋ ሁኔታ ከዜጎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥባቸው፣ ለሕዝቡ የገባውንም ቃል በተግባር አውሎ በሥራ እንዲተረጉም ፓትርያርኩ አሳስበዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ ዕለት ተዕለት ከምታከናውነው መንፈሳዊ አገልግሎት ባልተናነሰ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጀምሮ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መላው ካህናትና አገልጋዮች በዕለተ ሰንበት፣ በማታ ጉባዔ፣ በወርኃዊና በዓመታዊ በዓላት ሁሉ ሕዝበ ክርስቲያኑ በሥነ ምግባር ታንፆ፣ በፈሪኃ እግዚአብሔር በግብረ ገብነት ለአገሩ ሰላምና ለሕዝቡ አንድነት ተባብሮ እንዲቆም የሚያስችል ትምህርት እንዲሰጡ ቅዱስ ሲኖዶስ መወሰኑንም አስታውቀዋል፡፡

ፓትርያርኩ የነገድ፣ የሃይማኖትና የፆታ ልዩነት ሳይኖር ለጋራ ህልውና ልማትና ብልጽግና ተስፋ ሰንቆ እንደሚመጣ የተነገረለት የህዳሴው ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ሁሉም ድጋፍ እንዲያደርግ በመግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሌላ በኩልም ለተዋሕዶ ሃይማኖታቸው ለአገራቸው ልዕልናና ነፃነት በ1928 ዓ.ም. ከአርበኞች ጎን በመሆን ለአገራቸው ነፃነት ጠንክረው እንዲዋጉ ሲያስተምሩ በነበረበት ወቅት፣ በኢጣሊያ ፋሽስታዊ መንግሥት በጎሬ ከተማ በ1929 ዓ.ም. በግፍ በሰማዕትነት የተገደሉት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ሰማዕት ተብለው እንዲጠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በተያያዘ ዜና ከቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በፊት የተካሄደው 35ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ፣ በቀድሞ መንግሥት የተወረሰውና በአራት ኪሎ ከመንበረ ፓትርያርክ አጠገብ የሚገኘው ባለ 12 ፎቅ ሕንፃ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንጡራ ሀብት መሆኑን ማስረጃዎች እያረጋገጡ እያለ መንግሥት እስካሁን አለመመለሱ ሐዘን እንደተሰማው ያመለከተ ሲሆን፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ከኢፌዴሪ የፖለቲካና የፖሊሲ ውሳኔ ሰጪ ሥራ አስፈጻሚ አካላት ጋር በመነጋገር ንብረቱ እንዲመለስ ያደርግ ዘንድ ጠይቋል፡፡

ከዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት የሚገኘውና አሁንም ‹‹ፓትርያርክ ሕንፃ›› (Patriarch Building) በመባል የሚታወቀው ሕንፃ፣ በሁለተኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አማካይነት መታነፁ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...