በመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923-1967) ዘመን ለአራት አሠርታት በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ከአምባሳደርነት እስከ ሚኒስትርነት፣ ከርዕሰ መምህርነት እስከ መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል፡፡ አቶ አማኑኤል አብርሃም፡፡ በሃያኛው ክፍለ ዘመን ከተነሱት ልዕልናን ከተጎናፀፉ ግንባር ቀደም ኢትዮጵያውያንም አንዱ ነበሩ፡፡
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር በተዘጋጀችበትና በድንበር ትንኮሳ ባስነሳችበት ወቅት፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኢጣሊያ ዓለም አቀፍ ሕግን እየተላለፈችና እየጣሰች መሆኗን ለአውሮፓ መንግሥታት ለማመልከት አዛዥ (ሐኪም) ወርቅነህ እሸቴን (ዶ/ር ማርቲን ቻርልስ) ወደ እንግሊዝ ሲልኩ፣ ሎንዶን ላይ የኢትዮጵያ ሌጋሲዮን ጸሐፊ ሆነው የተመደቡትና ከሰኔ 1927 እስከ ሚያዝያ 1931 ዓ.ም. ድረስ ያገለገሉት አቶ አማኑኤል፣ ንጉሠ ነገሥቱ በስደት በነበሩበት ዘመንና ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በሎንዶን የመንግሥት ጉዳይ ጸሐፊ ተብለው ሠርተዋል፡፡
ድኅረ ፋሺስት ወረራ ከድል በኋላ አፄ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን መንግሥት ዳግም ለማቆም በተለያዩ መስኮች ኢትዮጵያውያንን ሲያሰባስቡ ከሎንዶን የተጠሩት አቶ አማኑኤል አንዱ ናቸው፡፡ በሐምሌ 1935 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ከጥቅምት እስከ ግንቦት 1936 ዓ.ም. በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና ዳይሬክተር ከሆኑ በኋላ፣ ለሦስት ዓመት (ከ1936 እስከ 1939 ዓ.ም.) በሚኒስትር ሥልጣን የትምህርትና ሥነ ጥበብ ዋና ዳይሬክተር በመሆን በአገሪቱ አያሌ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቃል ኪዳን (ቻርተር) በ1937 ዓ.ም. በአሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ላይ በተዘጋጀ ጊዜ ከኢትዮጵያ መልዕክተኞች አንዱ ሆነው የተላኩት አቶ አማኑኤል፣ ከ1940 ዓ.ም. እስከ 1943 ዓ.ም. በኒውዮርክ በተካሄዱት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓቢይ ጉባዔዎች ከተሳተፉት የኢትዮጵያ መልዕክተኞች አንዱ ነበሩ፡፡
የአቶ አማኑኤል ከ82 ዓመታት በፊት በለንደን የኢትዮጵያ ሌጋሲዮን ጸሐፊነት የተጀመረው የዲፕሎማሲ ሥራ ወደ አምባሳደርነት ከፍ ያለው በግንቦት 1941 ዓ.ም. ሲሆን፣ በቅድሚያ በህንድ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን ለአራት ዓመት፣ በተከታታይም ከሰኔ 1944 እስከ ሐምሌ 1947 ዓ.ም. በኢጣሊያ፣ ከታኅሣሥ 1948 እስከ ሰኔ 1951 ዓ.ም. በብሪታኒያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከአሥር ዓመታት የዲፕሎማሲ መልዕክተኛነት በኋላ አዲስ አበባ የተመለሱት አቶ አማኑኤል፣ ቀዳሚው ተግባራቸው ከታኅሣሥ 1952 እስከ የካቲት 1953 ዓ.ም. በሚኒስትር ማዕረግ ‹‹በግርማዊነታቸው ልዩ ካቢኔ›› የፖለቲካ ጉዳይ ዋና ሹም ሆነው መሥራታቸው ነው፡፡
በመቀጠልም በወቅቱ አጠራር የፖስታ፣ ቴሌግራፍና ቴሌፎን ሚኒስትር ከሆኑበት ከየካቲት 1953 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ሚኒስቴሩን በመምራት በዘመናቸው ዘመናዊ የፖስታና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሕንፃዎች ማሠራታቸው፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ቦርድ ሊቀመንበር ሆነው መሥራታቸው ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
ከሚያዝያ 1958 እስከ ኅዳር 1962 ዓ.ም. የመገናኛ ሚኒስትር በመሆን፣ በዚያው ዘመን የምድር ባቡር ኩባንያ አስተዳደር ጉባዔን፣ የሲቪል አቪዬሽን ቦርድን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድን፣ የባህር ክፍልን፣ የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ ቦርድን፣ የየብስ መገናኛ ክፍልን፣ የመንገድ ማመላለሻ አስተዳደርንና የመንገድ ማመላለሻ ቦርድን በበላይነትና በሊቀ መንበርነት መርተዋል፡፡ ከኅዳር 1962 እስከ የካቲት 1966 ዓ.ም. የማዕድን ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ አዲስ የማዕድን አዋጅና ደንብ በማሳወጅ መሥሪያ ቤቱ በፅኑ መሠረት ላይ እንዲቆም አድርገው ለአያሌ ዓመታት በቸልታ ተይዞ የኖረውን የማዕድን ልማት ሥራ በቁም ነገር እንዲያዝና እንዲፋጠን ለማድረግ መድከማቸውን ገጸ ታሪካቸው ያሳያል፡፡
የ1966 ዓ.ም. አብዮት ፍንዳታ ተከትሎ የተቋቋመው ‹‹የጦር ኃይሎች የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ደርግ›› (በኋላ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት) ከሚያዝያ 22 ቀን 1966 እስከ ጥር 19 ቀን 1967 ዓ.ም. ከንጉሠ ነገሥቱ የካቢኔ ሚኒስትሮች ጋር በግዞት ካቆያቸው በኋላ በነፃ ተለቀዋል፡፡
አቶ አማኑኤል ከ1956 ዓ.ም. አንስቶ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ፕሬዚዳንት ሆነው በቤተ ክርስቲያኒቱ ዓቢይ ጉባዔ በተደጋጋሚ በመመረጥ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለ22 ዓመታት ከመምራታቸው በፊት፣ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ረገድ ከ1949 ዓ.ም. አንስቶ መካነ ኢየሱስን በመወከል በተለያዩ የክርስቲያን ኢኩሜኒካል አካላት ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በእነዚሁ ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት አባል የሆኑበት የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት ለአሥር ዓመታት መርተዋል፡፡
አቶ አማኑኤል በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አገልግሎት ላይ በነበሩበት ዘመን የኢትዮጵያ ክብር ኮከብ ኮርዶን ኒሻንና የዳግማዊ ምኒልክ ኮርዶን ኒሻን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ተሸልመዋል፡፡ ከውጭ አገር መንግሥታትም አያሌ ኒሻኖችን ሲቀበሉ፣ በአሜሪካ ፔንሲልቬንያ ከሚገኘው ለንበርግ ኮሌጅ የክብር የሕግ ዶክትሬት ተቀብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በአገሪቱ ሥራዋ የተጀመረበትን 110ኛ ዓመት፣ በአገር ደረጃ የተዋቀረችበትን 50ኛ ዓመት ስታከብር አቶ አማኑኤል ‹‹ተወዳዳሪ ስለሌለው መሪነታቸው›› በሚል በከፍተኛ ትምህርት ተቋሟ መካነ ኢየሱስ ሴሚናሪ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ እንዲሰጣቸው አድርጋለች፡፡
የመንግሥት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎታቸውን ከፈጸሙ በኋላ የሕይወታቸውና የሥራቸው ማስታወሻ እንዲሆን ‹‹የሕይወቴ ትዝታ›› እና “Reminiscences of My Life” የተሰኙ መጻሕፍት በአማርኛና በእንግሊዝኛ አሳትመዋል፡፡
በወለጋ ጠቅላይ ግዛት፣ በቦጂ ወረዳ ከአባታቸው ከአቶ አብርሃም ታቶና ከእናታቸው ከወይዘሮ ቀናቱ ማልሞ መጋቢት 8 ቀን 1905 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ አማኑኤል፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በቦጂ ከርከሮ የስዊድን ወንጌላዊት ሚሲዮን ትምህርት ቤት ገብተው በኦሮሚኛና በአማርኛ ማንበብና መጻፍ ተምረዋል፡፡ ቀጥሎም ደጃዝማች ገብረ እግዚአብሔር ሞሮዳ ነቀምቴ ላይ በከፈቱት ትምህርት ቤት በ1917 ዓ.ም. ለስድስት ወራት ትምህርታቸውን ከቀጠሉ በኋላ፣ ከጥቅምት 1918 እስከ ሰኔ 1923 ዓ.ም. በአዲስ አበባው የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ዘመናዊውን ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
አቶ አማኑኤል አብርሃም ጥር 4 ቀን 1939 ዓ.ም. ወይዘሮ እሌኒ ዓለማየሁን አግብተው ሁለት ሴት ልጆችና ሁለት ወንድ ልጆች ሲወልዱ፣ ሦስት የልጅ ልጆቻቸውንም አይተዋል፡፡
ከ1927 ዓ.ም. ጀምሮ ለ53 ዓመታት አገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን በትጋት ያገለገሉት አቶ አማኑኤል፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ104ኛው ዓመታቸው ላይ ያረፉት ጥቅምት 12 ቀን 2009 ዓ.ም. ነው፡፡
የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ሥርዓተ ቅዳሴ ጥቅምት 17 ቀን አምስት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ መካነ ኢየሱስ ማኅበረ ምዕመናን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ፕሬዚዳንት ቄስ ዶ/ር ዋቅሥዩም ኢዶሳ መሪነት የተከናወነ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብሩም በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡
በሥርዓተ ቀብሩም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ የኦሮሚያ ክልል አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳና የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል፡፡