Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና መንግሥት በአጭር ጊዜ ከነዋሪዎች ነፃ የተደረገለትን መሬት ሊረከብ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኳታር ንጉሣዊያን ቤተሰቦች እየተጠበቁ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ መልሶ ማልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነዋሪዎች ንክኪ ሙሉ ለሙሉ በፀዳው የቂርቆስ ፈለገ ዮርዳኖስ አካባቢ፣ የቻይና መንግሥት የተፈቀደለትን መሬት ሊረከብ ነው፡፡ በአንፃሩ የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች መሬቱን ለመረከብ ገና አልቀረቡም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ በከንቲባ ድሪባ ኩማ ልዩ ዕገዛ እየተደረገለት፣ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አፍሪካ ኅብረት አካባቢ የሚገኘውን ‹‹ፈለገ ዮርዳኖስ ሳይት›› 17 ሔክታር መሬት ላይ ያረፉ ቤቶችን በማንሳት ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ ከነዋሪዎች ንክኪ ነፃ አድርጓል፡፡

ከ17 ሔክታር አራት ሔክታር የሚሆነው ለቻይና መንግሥት፣ ስድስት ሔክታር መሬት ደግሞ የኳታር ንጉሣውያን ቤተሰቦች ንብረት ለሆነው አዝዲን ሆልዲንግ ግሩፕ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡ ቀሪው ሰባት ሔክታር መሬት አስተዳደሩ በባለቤትነት ለሚያካሂዳቸው ግንባታዎች እንደሚውል ታውቋል፡፡

የቻይና መንግሥት የተፈቀደለትን ቦታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመረከብ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች ያሟላ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ሥር የሚገኘው የመልሶ ማልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቻይና መንግሥት የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን በአብዛኛው አሟልቷል፡፡ ‹‹ስለዚህ በቅርቡ ቦታውን ይረከባል፤›› ሲሉ አቶ ሚሊዮን ገልጸዋል፡፡

የቻይና መንግሥት ይህንን ቦታ የፈለገው በአፍሪካ ያለውን ተልዕኮ ለማስፈጸም ዋና ቢሮውን ለመገንባት ነው፡፡ ‹‹የቻይና ሕዝብ ተልዕኮ ለአፍሪካ ኅብረት›› በሚል ስያሜ የሚገነባው ዋና መሥሪያ ቤት የቦታ ርክክቡ እንደተፈጸመ ግንባታው ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሌላው በዚህ አካባቢ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው የኳታር ግዙፍ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ነው፡፡ ኩባንያው አዝዲን ሆልዲንግ ግሩፕ በተፈቀደለት ስድስት ሔክታር መሬት ላይ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል፣ ሪል ስቴት፣ የገበያ ማዕከልና የመዝናኛ ሥፍራዎችን የመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡

አቶ ሚሊዮን እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ ከኩባንያው ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ ስለነበር ቦታቸውን ለመረከብ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአጠቃላይ በቂርቆስ ፈለገ ዮርዳኖስ አካባቢ በመልሶ ማልማት ከተያዘው 17 ሔክታር መሬት ላይ 1,573 ቤቶች ፈርሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቦታው ከሰው ንክኪ ነፃ ሆኖ ግንባታው እየተጠበቀ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስካሁን በመሀል ከተማ በርካታ የመልሶ ማልማት ፕሮጀክቶችን ቢያካሂድም፣ የፈለገ ዮርዳኖስን ያህል ትኩረት የተሰጠው ፕሮጀክት የለም፡፡

አቶ ሚሊዮን እንዳሉት፣ የፈለገ ዮርዳኖስ ፕሮጀክት በቅንጅት የተሠራና የተነሺዎችን ፍላጎት ያሟላ በመሆኑ እምብዛም ቅሬት አልቀረበበትም፡፡ ለአካባቢው የግል ተነሺዎች ምትክ ቦታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ሰሚት አካባቢ፣ ለቀበሌ ቤት ተነሺዎች ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ቡልቡላ ሳይትና አራብሳ ሳይት የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተሰጥተዋል፡፡ ለአካባቢው ነጋዴዎች ደግሞ የተክለ ሃይማኖት መልሶ ማልማት ቀጣና ከሆነው ሆቴል ዲአፍሪክ አካባቢ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች