Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየግብፅ ፓርላማ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጉብኝት ላይ የቀረበውን ተቃውሞ ውድቅ አደረገ

የግብፅ ፓርላማ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጉብኝት ላይ የቀረበውን ተቃውሞ ውድቅ አደረገ

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በግብፅ ፓርላማ ተገኝተው ንግግር እንዳያደርጉ የግብፅ ፓርላማ አባላት ያቀረቡትን ተቃውሞ፣ የአገሪቱ ፓርላማ ውድቅ ማድረጉ ተሰማ፡፡

በግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱፈታህ አልሲሲ የተጋበዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚቀጥለው ሳምንት በግብፅ ፓርላማ ተገኝተው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የመንግሥታቸውን አቋምና በሁለቱ አገሮች ግንኙነት ላይ ንግግር እንዲያቀርቡ መጋበዛቸው ይታወቃል፡፡ ይህንን በመቃወም 19  የግብፅ ፓርላማ አባላት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት፣ እንዲሁም በግብፅ ፓርላማ ንግግር እንዲያደርጉ የተያዘውን ፕሮግራም በመቃወም የተቃውሞ ፊርማቸውን ለአፈ ጉባዔው አቅርበው ነበር፡፡

የቀረበውን የተቃውሞ ፊርማ አስመልክቶ የአገሪቱ ፓርላማ ሰሞኑን ሲወያይ፣ የግብፅ ገዥ ፓርቲን የሚደግፉ የፓርላማ አባላት ጥምረት ተቃሞውን ውድቅ ማድረጋቸውን የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በግብፅ ፓርላማ ተገኝተው ንግግር ማድረጋቸው እንደ ዕድል መታየት እንደሚገባው፣ የግብፅ ፓርላማን በአብላጫ ድምፅ የሚወክሉ 350 አባላትን የያዘው ጥምረት አስታውቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በግብፅ ጉብኝታቸው በፓርላማው ተገኝተው ንግግር ሲያደርጉ፣ የዓባይ ውኃ ለግብፅ ሕዝብ ምን ማለት እንደሆነና የኢትዮጵያ ልማትን አስመልክቶ ውይይት ለማድረግ እንደሚጠቅም፣ የጥምረቱ ቃል አቀባይና የፓርላማ አባል ሳላ ሀሽባላህ ተናግረዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት የተቃወሙ የፓርላማ አባላት አጉል ጀግንነትን የሚያንፀባርቁ መሆኑን፣ ይህ ግን ግብፅን እንደማይጠቅም ቃል አቀባዩ መናገራቸው ታውቋል፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የህዳሴውን ግድብ አስመልክቶ የተፈጠረው አለመግባባት በጥልቅ ውይይት መፈታት አለበት ማለታቸውም ተሰምቷል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን የጉብኝት ዕቅድና የፓርላማ ንግግር የግብፅ ፓርላማ አባላት የተቃወሙት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር በመስተጓጎሉና ግድቡ የግብፅን የውኃ ድርሻ ይቀንሳል በሚል መነሻ ነበር፡፡

‹‹የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር የጉብኝት ዕቅድ የምንቃወመው የዓባይ ውኃ ጉዳይ፣ የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት መሠረታዊ አካልና የማይታለፍ ቀይ መስመር በመሆኑ ነው፤›› ሲሉ 19 የፓርላማ አባላት ተቃውሞ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያ የምትገነባውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ ቆይቶ የተሰናከለውን ድርድር አስመልክቶ የአገሪቱ የውኃና መስኖ ሚኒስትር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን በፓርላማ ቀርበው እንዲያስረዱ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በታኅሳስ ወር በግብፅ የሚያደርጉት የሥራ ጉብኝት በፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ጥያቄ መሠረት መሆኑንና እስካሁን የፕሮግራሙ ይዘት አለመቀየሩን ገልጸዋል፡፡

      የህዳሴ ግድቡ የአካባቢ ተፅዕኖና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅን፣ እንዲሁም የሚካሄደው ገለልተኛ ጥናት መሠረት የሚያደርግባቸው መረጃዎችን በተመለከተ ግብፆች ያቀረቡትን መከራከሪያ ኢትዮጵያ አልተቀበለችም፡፡

በግብፅና በሱዳን መካከል የተፈረመው የቅኝት ግዛት ዘመን የውኃ ክፍፍል ስምምነት፣ ኢትዮጵያን የማይመለከት መሆኑን ባለሥልጣኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዓባይ ትብብር ማዕቀፍን ኢትዮጵያና ሌሎች አገሮች ተስማምተው በሕግ አውጪ ተቋሞቻቸው ሕግ አድርገው አፅድቀውና የቅኝ ግዛት ስምምነትን ውድቅ አድርገው ሳለ፣ ... ወደ 1959 የቅኝ ግዛት ስምምነት መመለስ ኢትዮጵያ በቀናነት ለምታደርገው ድርድር ክብር አለመስጠት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርህ መግለጫ ስምምነት እንደሚጣረስም አስረድተዋል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ስምምነት ግብፅ ለመጀመርያ ጊዜ የላይኛው የተፋሰሱ አገሮች ጉልህ ጉዳት ሳያደርሱ፣ ውኃን የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተቀብላ መስማማቷን ባለሥልጣኑ በዋቢነት አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የውኃ ደኅንነት ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ ግብፅ በከፍተኛ የመንግሥት መዋቅር ደረጃ ድርድሩ እንዲቀጥል ከማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሌላት ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ አሁንም አለመግባባቶችን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን በማስታወቅ፣ የግድቡ ግንባታ ግን የሚቆመው ሲጠናቀቅ ብቻ መሆኑን በግልጽ ይፋ አድርገዋል፡፡     

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...