- የአክሲዮን ገበያ ቢቋቋም 200 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማመንጨት እንደሚቻል ተጠቆመ
ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም በመለየት ብሔራዊ የአክሲዮን ገበያ (Stock Market) አለማቋቋሟ፣ በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ የፋይናንስ ባለሙያዎች አስታወቁ፡፡
ማክሰኞ ታኅሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ በተከፈተው ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ የፋይናንስ ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ ባለመቋቋሙ ምክንያት ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የሚያስፈልግ ካፒታል ማመንጨት አለመቻሉን፣ በዚህም አገሪቱን ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እያሳጣት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የዋይኤችኤም ኮንሰልቲንግ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል አፄ ምኒልክ የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ለመገንባት የሚያስፈልገው 40 ሚሊዮን የፈረንሳይ ፍራንክ ስላልነበራቸው፣ በፈረንሳይ አክሲዮን ሸጠው ለ100 ዓመታት ያገለገለ ፕሮጀክት ማሳካታቸውን፣ የመጀመርያው አቢሲኒያ ባንክ አክሲዮን በ1909 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በኒውዮርክ፣ በፓሪስ፣ በለንደንና በቪየና መሸጡን፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አዲስ አበባ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቄራዎች ድርጅት፣ ቦትሊንግ ካምፓኒ ኦፍ ኢትዮጵያ፣ ኢንዶ ኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ፣ ኤችቪኤ የስኳር ፋብሪካና የመሳሰሉት ኩባንያዎች አክሲዮን በአክሲዮን ገበያ መልክ ሲሸጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁንም በርካታ ባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና ሌሎች ከፋይናንስ ውጪ ያሉ ኩባንያዎች አክሲዮን እየሸጡ ቢሆንም፣ የተቀናጀ የአክሲዮን ገበያ አለመመሥረቱ በርካታ የኢኮኖሚ ጉዳቶች እያስከተለ እንደሆነ አቶ ያሬድ ተናግረዋል፡፡ ባለአክሲዮኖች በቀላሉ አክሲዮን የሚገዙበት፣ የሚሸጡበትና የሚያስተላልፉበት ሥርዓት ባለመዘርጋቱ ዜጎች አክሲዮን እንዲገዙ እንደማያበረታታ የገለጹት አቶ ያሬድ፣ የፋይናንስ ዘርፉ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ቢሆንም ሌሎች አክሲዮን ኩባንያዎች በአግባቡ ቁጥጥርና ክትትል ስለማይደረግባቸው በየጊዜው ሲከስሩ፣ ከገበያ ሲወጡና ከባለአክሲዮኖች ጋር ንትርክና ክስ ውስጥ ሲገቡ እንደሚስተዋል ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የአክሲዮን ገበያን ከካዝና ቁማር ጋር የማመሳሰል የተሳሳተ አመለካከት መኖሩን ገልጸው፣ ይህ በአፋጣኝ ሊለወጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 80 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው አክሲዮኖች መሸጣቸው ተገልጿል፡፡
የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ ዋና ሊቀመንበር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እ.ኤ.አ. በ2001 እርሳቸውና ሌሎች የፋይናንስ ባለሙያዎች የአዲስ አበባ የአክሲዮን ገበያ ለማቋቋም ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ሰፊ ጥናት ማጥናታቸውን ገልጸው፣ የአክሲዮን ገበያውን ለማቋቋም ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በመንግሥት ትዕዛዝ መቋረጡን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ጥናቱ የተካሄደባቸው ሦስት ወፍራም ጥራዞች አሁንም ቢሮዬ መደርደሪያ ላይ ይገኛሉ፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹በወቅቱ በጥናቱ ላይ መንግሥትን አለማሳተፋችን ስህተት ነበር፤›› ብለዋል፡፡
በወቅቱ የነበሩት የገንዘብ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ለአክሲዮን ገበያ ዝግጁ አይደለችም ብለው በጻፉት ደብዳቤ የአክሲዮን ገበያ ምሥረታ ሒደት እንደተቋረጠ ያስታወሱት አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹ያኔ ቸኩለን ሊሆን ይችላል፡፡ አገሪቱ ዝግጁ አልነበረችም፡፡ አሁን ግን የአክሲዮን ገበያ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመመሥረት ትክክለኛው ወቅት ላይ እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ዘመዴነህ የአክሲዮን ገበያ ቢቋቋም በርካታ ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ባለሀብት እንደሚሆኑ፣ ከፍተኛ የልማትና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በራስ አቅም መገንባት እንደሚቻልና ሰፊ የሥራ ዕድል ለወጣቱ መፍጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
‹‹በአንድ በኩል በርካታ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ይዘው ተቀምጠዋል ወይም ዝም ብለው ሕንፃና የገበያ ማዕከል ይገነባሉ፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ሕንፃዎች እየተገነቡ ተከራይም ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ በሌላ በኩል አዋጭና ለአገር ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ፕሮጀክቶች ዕቅዶች ይዘው ካፒታል ያጡ የሥራ ፈጣሪዎች አሉ፤›› ያሉት አቶ ዘመዴነህ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ዩሮ ቦንድ በውጭ ገበያ በመሸጥ ላይ መሆኑን ገልጸው ፖሊሲ አውጪዎች የአክሲዮን ገበያ ምሥረታን ጉዳይ ሊያጤኑት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
አቶ ዘመዴነህ በድርጅታቸው ባደረጉት ጥናት የአክሲዮን ገበያ ቢቋቋም በአራት ዓመታት ውስጥ 200 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማመንጨት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ ይህ አገሪቱ እያስመዘገበችው ላለው ፈጣን ዕድገት ትልቅ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ የጉባዔው አወያይ የነበሩት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ አፄ ምኒልክ በ1909 ዓ.ም. በአሜሪካ የምድር ባቡር ኩባንያዎች ላይ አክሲዮን ይገዙ እንደነበር የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ጽሑፍ ጠቅሰው በማስረዳት፣ እ.ኤ.አ. በ2001 ከአቶ ዘመዴነህና ከሌሎች የፋይናንስ ባለሙያዎች ጋር የአዲስ አበባ የአክሲዮን ገበያ ምሥረታ ምክር ቤት አባል በመሆን በአክሲዮን ገበያ ምሥረታ ላይ በርካታ ጥናቶችና ውይይቶች ላይ ተካፋይ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹ከ16 ዓመታት በኋላ አሁንም ስለአክሲዮን ገበያ ምሥረታ መነጋገራችን በጣም ያሳዝነኛል፤›› ያሉት አቶ ኢየሱስ ወርቅ፣ ‹‹ፖሊሲ አውጪዎች ሐሳባችንን ሊያዳምጡን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
አክለውም፣ ‹‹ፖሊሲ አውጪዎች ውሳኔ ለመወሰን የፍርኃት ቆፈን ሸብቦ ይዟቸዋል፤›› ብለዋል፡፡
ሁለተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ አይ ካፒታል አፍሪካ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጂማ ዩኒቨርሲቲና ከመንግሥት ከፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የተሰናዳ በፋይናንስ ዘርፍ ያሉ ዕድሎችና ፈተናዎች ላይ የሚመክር መድረክ ነው፡፡