Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአራት ቢሊዮን ዶላር ጂኦተርማል ፕሮጀክቶች ስምምነት ተፈረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገሪቱ የመጀመርያ የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ስምምነት እንደሆነ የተነገረለት የኮርቤቲና የቱሉ ሞዬ የ1,000 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ስምምነት፣ ታኅሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት በሸራተን አዲስ ተፈረመ፡፡ የሁለቱ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ አራት ቢሊዮን ዶላር  ነው ተብሏል፡፡

የመጀመርያው የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ስምምነት የተፈረመው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ኮርቤቲ ጂኦተርማል በተባለ የኢንቨስትመንት ኩባንያ ነው፡፡

በምሥራቅ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ከተማ አቅራቢያ ኮርቤቲ በተባለ አካባቢ የሚገነባው የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያ 500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር 1,000 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል በኮርቤቲና ቱሉ ሞዬ ለማመንጨት የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረመው ሬይካቪክ ጂኦተርማል የተባለ የአይስላንድ ኩባንያ፣ ላለፉት አራት ዓመታት ተኩል የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ስምምነት ለመፈራረም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ድርድር ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ሬይካቪክ ጂኦተርማል ፕሮጀክቱን ሁለት ቦታ በመክፈል በኮርቤቲ 500 ሜጋ ዋት፣ በቱሉ ሞዬና ዓባያ 500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ጣቢያዎች ለመገንባት ዕቅድ አቅርቦ ከረዥም ድርድር በኋላ በኢትዮጵያ መንግሥት ተቀባይነት አግኝቷል፡፡

ሬይካቪክ ጂኦተርማል የኮርቤቲን የኃይል ጣቢያ የሚገነባ ኮርቤቲ ጂኦተርማል የተባለ ልዩ የኢንቨስትመንት ኩባንያ በኢትዮጵያ በማቋቋም፣ አይስላንድ ድሪሊንግና በርክሌይ ኢነርጂ የተባሉ ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ኢንቨስትመንት ኩባንያዎችን በሽርክና አብረውት እንዲሠሩ አስገብቷል፡፡ የኃይል ግዥ ስምምነት ሒደቱ በአሜሪካው ፓወር አፍሪካና በአፍሪካ ልማት ባንክ ሲደገፍ ቆይቷል፡፡

ኮርቤቲ ጂኦተርማል የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያውን ገንብቶ ኃይል በማመንጨት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለ25 ዓመታት ለመሸጥ ተስማምቷል፡፡ አንድ ኪሎ ዋት አወር ኤሌክትሪክ በ0.75 ዶላር ለመሸጥ እንደተስማሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከ25 ዓመት በኋላ ኩባንያው ጣቢያውን ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያስተላልፍ ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያው የሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ስምምነት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር)፣ ከኮርቤቲ ጂኦተርማል ተወካዮች ሚስተር ሉካ ቡልጃንና ሚስተር ኤዲ ንጆርግ ጋር ተፈራርመዋል፡፡ በስምምነቱ ላይ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ደበበ ተገኝተዋል፡፡

በተመሳሳይ በቱሉ ሞዬና ዓባያ አካባቢ 500 ሜጋ ዋት የጂኦተርማል ኤሌክትሪክ ኃይል ለማልማት ሬይካቪክ ጂኦተርማል ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል የተሰኘ ኩባንያ በማቋቋም፣ ሜሪዲያን የተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ በሽርክና አብሮት እንዲሠራ አስገብቷል፡፡

የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ይገመታል፡፡ ቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ለ25 ዓመት የሚጸና የኃይል ግዥ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ኩባንያው አንድ ኪሎ ዋት አወር ኤሌክትሪክ በ0.695 ዶላር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ እንደተስማማ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስምምነቱን ወ/ሮ አዜብ ከቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ተወካይ ጉድሙንደር ቶሮድሰን ጋር ተፈራርመዋል፡፡

የጂኦተርማል ፕሮጀክቶቹ ጠንሳሽ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ባለሀብት አቶ ነጂብ አባቢያ የሁለቱን ፕሮጀክቶች በቅርበት ሲከታተሉና አመራር ሲሰጡ ነበር ያሏቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቦርድ ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን (ዶ/ር) አመሥግነዋል፡፡

ወ/ሮ አዜብ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ የማመንጨት አቅም 4,300 ሜጋ ዋት መድረሱን፣ 13,000 ሜጋ ዋት ለማልማት በሒደት ላይ መሆኑን ገልጸው ለዚህም 26 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

ለኢነርጂ ልማት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ አዜብ፣ የተፈረሙት ሁለት የኃይል ግዥ ስምምነቶች በመንግሥት ላይ ያለውን የፋይናንስ ጫና እንደሚያቃልሉ ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች