Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የአይቲ ኢንዱስትሪ በዓለም መሪ ሆኖ ሳለ በአገራችን ግን እንደ ዝቅተኛ ኢንዱስትሪ ይቆጠራል!››

 አቶ ተከስተብርሃን ሀብቱ፣ የሳይበርሶፍት ዋና ሥራ አስኪያጅ

 ሳይበርሶፍት ባለፉት 19 ዓመታት ለተለያዩ ተቋሞች ልዩ ልዩ ሲስተሞችን የሠራ የአይቲ (ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ተቋም ነው፡፡ የመንግሥትና የግል ተቋሞች በዲጂታል ሲስተም የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻልም የድርሻቸውን እየሰጡ ነው፡፡ የፍትሕ፣ የትምህርትና የጤና ተቋሞችን ጨምሮ የ702 ድርጅቶችን ሲስተም አልምተዋል፡፡ በተቋሙ እንቅስቃሴ ዙሪያ የሳይበርሶፍት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተከስተብርሃን ሀብቱን ምሕረተሥላሴ መኰንን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ሳይበርሶፍት አመሠራረት ቢገልጹልን?

አቶ ተከስተብርሃን፡- ሳይበርሶፍት የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1998 ነው፡፡ ያቋቋምነው ስድስት ሆነን ነው፡፡ እኔ የማኔጀመንት፣ ሌሎቹ የኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ፣ ሒሳብና ፊዚክስ ሙያ ስብስብ ነን፡፡ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል ወይም “አይቲ ሀብ” ማድረግ ይቻላል በሚል እሳቤ ነው የተቋቋመው፡፡ ራዕያችን ለአገራችን በነፍስ ወከፍ ደረጃ የሚያስፈልገው አይቲ መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በነፍስ ወከፍ ደረጃ የሚያስፈልገው አይቲ ነው ሲሉ ምን ማለት ነው?

አቶ ተከስተብርሃን፡- አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ኢንዱስትሪውም ሆነ ዕውቀቱ ሁሉ በአይቲ የሚንሸራሸር መሆን አለበት፡፡ ከአይቲ በፊት ከነበሩ ቴክኖሎጂዎች የተለየ ነው፡፡ በፊት የነበረው “ሎው ኦፍ ዲሚኒሺንግ ሪተርንስ” የሚተገበርበት ሲሆን፣ አይቲ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ “ሎው ኦፍ ኢንክሪዚንግ ሪተርን” ይተገበራል፡፡ ማለትም የአይቲ  ሀብትን ሁሉ ሰው ጋ ባደረስነው ወይም በበተነው ቁጥር ዋጋው እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በቀድሞው እሳቤ ግን አንድ ነገር አንድ ቦታ ከተጠቀምንበት ሌላ ቦታ ልናገኘው አንችልም ነበር፡፡ በሁለቱ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ ስለዚህም አይቲ አገራችን ያሳድጋል፡፡ አይቲ ከሁሉም ቴክኖሎጂ ቁልፍ ነው፡፡ አይቲ ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን ሁሉ አልፎ የመጣ ትልቁ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በዘመነ አይቲ ኢንዱስትሪ በሌላ ኢንዱስትሪ ብቻ በመሰማራት ተወዳዳሪ መሆንና ማደግ አይቻልም፡፡ ለራሳችን፣ ለቤተሰቦቻችን፣ ለሕዝባችን፣ ለመንግሥታችንና ለአገራችን ቁልፍ የሆነው አይቲ ወይም የመረጃ ቴክኖሎጂ ነው ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይዛችሁ ከተነሳችሁ ዓላማ አንፃር ማለትም ዘመኑ የአይቲ መሆኑን በመገንዘብ ረገድ ኅብረተሰቡ እንደጠበቃችሁት ምላሽ ሰጥቷችኋል?

አቶ ተከስተብርሃን፡- እኛ እየወደቅንም እየተነሳንም ሐሳባችንን በተግባር ለማዋል ጥረናል፡፡ ጠቅላላ ኃይላችንን አውለንበታል፡፡ ምን ያህል ግንዛቤ አለ የሚለው ፍርዱ የኅብረተሰቡ ነው፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ሕዝባችንና መንግሥታችን ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ አንፃር እጅግ የተዋጣለት ውጤት አግኝተናል፡፡ ሳይበርሶፍት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ትልቁ የሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ድርጅት ነው፡፡ ይኼንን የሚያስብለኝ ለ702 ድርጅቶች የተዋጣለት ሥራ ሠርቶ ማስረከቡ ነው፡፡ ይኼንን ስናደርግ ተከፍሎን ሳይሆን፣ ድርጅቱ እየከሰረም በመሥራትና በሠራተኞቹ ተነሳሽነት ነው፡፡ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል የመሠረት ሥራ ሠርተናል፡፡ አንዳንዶቹ ውጤቶቻችን በዓለም ደረጃ እንደ ወርልድ ባንክ ያሉ ድርጅቶች የጻፉላቸው ናቸው፡፡ ከሲንጋፖር የመጡ ባለሙያዎች እንደዚህ ዓይነት ሥራ አልተሠራም ብለው ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ ከስምንት ዓመት በፊት የአገራችንን የጡረታ ክፍያ ሠርተናል፡፡ በዓመት ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ይከፍላል፡፡ ይኼንን ሶፍትዌር የሠራነው በ800,000 ብር ነው፡፡ ውጪ አገር ብንሄድ 80 ሚሊዮን ያህል ያስከፍላል፡፡ በፍትሕ ሥርዓት የኮርት ኬዝ ማኔጅመንት ሲስተምን ሠርተናል፡፡ ኋላ ቀር የሚባለው የፍትሕ ሥርዓቱ ሲሆን፣ ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ አውቶሜት አድርገነዋል፡፡ በ387 ፍርድ ቤቶች ማለትም ገጠር ያሉትም ሳይቀሩ እየሠሩበት ነው፡፡ ሲንግል ሬጅስትሬሽን ኤንድ ቫይታል ስታትስቲክስን ለአፍሪካ በሚሆን ደረጃ ብንሠራውም፣ በኛ አገር ለመተግበር ዕድል አላገኘንም፡፡ በትግራይ ለሰባት ወረዳዎች እንዲሠሩበት በነፃ ብንሰጥም ህንዶች እንዲሠሩበት ተደርጓል፡፡ ትልቁ ሥራችን ኢንተርፕራይዝ ሪሶርስ ፕላኒንግ ወይም ኢራፒ ነው፡፡  ይኼ በአንድ ቋት የአንድ ድርጅትን ሥራዎች በአጠቃላይ መሥራት የሚያስችል ነው፡፡ ሲስተሙ የፋይናንስ፣ የሰው ኃይል (ሒውማን ሪሶርስ) እና ሌሎችም የተቋሙን መረጃዎች የያዘ ነው፡፡ ኢራፒን የምንሸጠው በርካሽ ዋጋ ነው፡፡ እኛ ድሮ ሠርተን የጨረስነውን፣ የውጭ ድርጅት አምጥተው 20 ሚሊዮን ዶላር ከፍለው የሚያሠሩ እናያለን፡፡ ውጪ የሚያስኬድ ነገር የለም፡፡ እንዴት 100 ሚሊዮን ሕዝብ ይዞ ጭንቅላት የለንም ብሎ ጭንቅላት ሁኑልን ብሎ ወደ ውጪ ገበያ ይወጣል? ጭንቀት ባይኖር እንኳን እዚሁ መፈጠር አለበት፡፡ ተልዕኳችንን ይኼንን በተግባር ማዋል ነውና የፋንታችንን ሠርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የአይቲ ዘርፍ ባለሙያዎች ከሚያነሷቸው ችግሮች አንዱ ለአገር ውስጥ ተቋሞች ዕድል አለመሰጠቱና ሁሌ ለውጭ ድርጅርቶች ቅድሚያ የመስጠት ነገር ነው፡፡ ይኼ ምን ያህል ሥራችሁን ፈታኝ አድርጎታል?

አቶ ተከስተብርሃን፡- እጅግ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ሁሉም ሰው ጥናት ሳይሠራ እዚህ አገር ተቋም የለም ብሎ ይደመድማል፡፡ ከባለሥልጣን ጀምሮ ያለው አመለካከት ይኼ ነው፡፡ እኛንም እንዳናድግ አድርጎናል፡፡ ቴክኖሎጂው አገራችን ውስጥ እንዳያድግም አድርጎታል፡፡ የአይቲ ኢንዱስትሪ በዓለም መሪ ሆኖ ሳለ በአገራችን ግን እንደ ዝቅተኛ ኢንዱስትሪ ይቆጠራል፡፡ በዚህ በኩል ብዙ ጽሑፎች አዘጋጅተን አቅርበናል፡፡ የፖሊሲ አቅጣጫዎች አርቅቀን ቢሆን የምንለውን አቅርበናል፡፡ መፈጸም የእኛ ድርሻ ስላልሆነ መፈጸም አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡- በፖሊሲ ረገድ የሚጠቁሟቸውን ነጥቦች ቢያብራሩልን?

አቶ ተከስተብርሃን፡- ለምሳሌ አንዱ የግዢ ፖሊሲ ነው፡፡ አገር ውስጥ እንደማይሠራ ሳይረጋገጥ ውጪ መሄድ የለበትም፡፡ በግንባታ ዘርፍ በደረጃ ጨረታ እንደሚያወጣ በአይቲ ዘርፍም ጨረታ ሲወጣ በደረጃ መሆን አለበት፡፡ ለማይሆን ተቋም ሥራው ተሰጥቶ ሲበላሽ፣ እኛ አገር መሥራት አይችሉም ከሚል ድምዳሜ ይደርሳል፡፡ ችግሩ ለሚችሉት አለመስጠቱ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ የሶፍትዌር ኢንዱስትሪ ውጤቶች የሚሰጣቸውን ቦታ ማየትም ያስፈልጋል፡፡ የአማዞን፣ የጉግል፣ የፌስቡክና የኡበርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ በትሪሊየን የሚቆጠር ሀብት ያላቸው የዓለም ሀብታሞች ናቸው፡፡ በእኛ ተቋም የ702 ድርጅቶች ሲሰተም ተሠርተዋል፡፡ 18 ኢንተለክችዋል ፕሮፐርቲ ራይት ያላቸው የብቻችን ውጤቶች አሉ፡፡ በእኛ አገር ግን ይኼ ዋጋ አይሰጠውም፡፡ እንደ ካፒታልም አይታይም፡፡ ሌላው ጥያቄ ለምን ዘርፉ እንደ ኢንዱስትሪ አይታይም የሚለው ነው፡፡ ለምን እንዳደጉ አገሮች አይሆንም? እኛ አገር እንደ ኢንዱስትሪ የሚታየው ትልልቅ ማሽን ያለው ፋብሪካ ብቻ ነው፡፡ እኛ ግን የምናመጣው ፋብሪካውን ሳይሆን ጭንቅላት ነው፡፡ ኅብረተሰቡን ጭንቅላት ሞልቶታል፡፡ ልንጠቀምበት ይገባል፡፡ እንዴት ጭንቅላት የለንም ብለን ገበያ እንወጣለን? እንዴት ራሳችንን በቅኝ ቅርስ ኅሊና (ኮሎናይዝድ ሜንታል ሞዴል) እናያለን? እንዴት ራሳችንን እናገላለን? በሚል እየታገልን ነው፡፡ በእርግጥ የፖለቲካ ድርጅት አይደለንም፡፡ በዚሁ ሚዲያ እንደምናደርገው ከመተንፈስ በስተቀር ሌላ መድረክ የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተ ስለተዘጋጀው የፍትሕ መረጃ ሥርዓትና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ ቢያስረዱን?

አቶ ተከስተብርሃን፡- የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ምን መምሰል አለበት የሚለው በአገራችንና በውጭ የፍትሕ አዋቂዎች ተጠናና በ1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራም ተቀረፀ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ሁለንተናዊ የፍትሕ ሥርዓት ነው በሚል ተቀርጿል፡፡ ሥራው መሠራት ያለበት ሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚውንና ሕግ ተግባሪው በሁለተንተናዊ መንገድ በመካከላቸው መረጃ እየተንሸራሸረ ነው፡፡ ከዝቅተኛ ቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ያሉትን የሚያስተሳስር የተቀናጀ የፍትሕ መረጃ ሥርዓት መቀረፅ አለበት ተብሎ ተጠና፡፡ ሥራው በተግባር እንዲውል ጨረታ ሲወጣ፣ እኛ ከአንድ የውጭ ድርጅት ጋር በአንድነት ተጫረትን፡፡ በአንድነት የሠራነው በ86 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ወስዷል፡፡ የመጀመርያው ክፍል የጥናት ሥራ ሲሆን፣ 64 ሺሕ ገጽ ጥናት ቀርቧል፡፡ አጋራችን ብዙ ብር ቢወስድም የሠራነው ብቻችንን ነበር፡፡ ያኔ የሠራው 60 በመቶ የተሠራ ሲሆን፣ አሁን ዌብቤዝድ በሆነ ሁኔታ 70 በመቶውን ሠርተነዋል፡፡ የሠራው ኢንተሌክችዋል ፕሮፐርቲ ራይቲ ያለንም እኛ ነን፡፡ ጥናቱን ብንጨርሰውም፣ ሥራው በተግባር ከሚውልበት የጨረታ ሒደት ተገለናል፡፡ ለምን እንደተገለልን እኔም ሠራተኞቹም አልገባንም፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምን ተገለላችሁ?

አቶ ተከስተብርሃን፡- ይኼንን እኛ መመለስ አንችልም፡፡ የሚመለከታቸው መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እኛ ምንጊዜም ከማንም በቀለጠፈና ዋጋው በቀነሰ መንገድ ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ የሠራነው በሁሉም የአገር ውስጥ ቋንቋ ነው፡፡ እስከ 4,000 ወረዳዎች ድረስና በየዞኑ፣ በየክልሉና በፌዴራል ቢሮዎች ጥናቱ ተሠርቷል፡፡ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የምናውቀውና መረጃው ያለን እኛ ነን፡፡ ከውጭ መጥቶ የሚሠራ ድርጅት እንዴት በአገር ውስጥ ቋንቋ ሊያቀርብ ይችላል? የመጀመሪያውን ደረጃ ማለትም አውቶሜሽኑ ሊሠራ የሚችልበትን ቴክኒካል ሥራ አጠናቀናል፡፡ ቀጣዩን ሥራ የሚመመራው ይኼ ነው፡፡ ቀጣዩ ደረጃ ሶፍትዌር ዴቨሎፕ ማድረግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣዩን ደረጃ ወደ ሌላ ተቋም መውሰዱ ያስኬዳል?

አቶ ተከስተብርሃን፡- በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ አይቻልም፡፡ ነገር ግን እኛ አናዝበትም፡፡ የውጭ ተቋም አምጥቶ ለማሠራት፣ የውጭው ድርጅት ምን ያህል እዚህ ያለውን ፍላጎት ያውቀዋል? የሚለው አለ፡፡ እዚህ ሳይሞክሩ የውጭ ድርጅት እንደመጣባቸው ሌሎች ፕሮጀክቶች ሊበላሽ ይችላል፡፡ እዚህ ያለነው መሞከር አለብን፡፡ የአገር ውስጥ ሰው ተቀጥሮ፣ በአገር ውስጥ ገንዘብ እናስከፍላለን፡፡ የውጭ ምንዛሪም ማዳን ይቻላል፡፡ አሁን በፍትሕ መረጃ ሥርዓት ውስጥ 578ቱ የሚሠሩት በእኛ ነው፡፡ በኮርት ኬዝ ማኔጅመንት ሲስተም 387 ፍርድ ቤቶችና በጀስቲስ ኢንፎርሜሽን ሲስተም በደቡብ ክልል 170 የፍትሕ ቢሮዎች ይሠራሉ፡፡ በፕሮስኪውሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተም አዲስ አበባና ድሬዳዋ ይገለገላሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ከሥራዎቻችሁ መካከል ትራፊክ አክሲደንት ክሪሚናል ኤንድ ሎው ብሪቺንግ ሲስተምና ፎረንሲክ አውቶሪኮርድ ሲስተም በምን መንገድ በተግባር አገልግሎት ይሰጣሉ?

አቶ ተከስተብርሃን፡- የትራፊኩን የሠራነው ሶማሌ ክልል በተደረገ ጥናት ነው፡፡ በትራፊክ ሥርዓት ያጠፉ ሰዎች የሚቀጡበት መንገድ ነው፡፡ በሞባይል ወይም በአይፓድ ሊሠራ ይችላል፡፡ የአጥፊው ሪኮርድ ተይዞ የሚቀጣበትና የሚከፍልበት ሒደት ነው፡፡ የፎረንሲክን ሲስተም የሠራነው ለምኒልክ ሆስፒታል ነው፡፡ አንድ ሰው ሲሞት፣ ስኬለታል ሪሜኒንግ የሚታይበት፣ ሜዲኮ ሌጋል ሪፖርት የሚቀርብበትና ሌሎችም አገልግሎቶች የሚሰጥ ነው፡፡ የፎረንሲክ ሐኪሞች ድሮ በመዝገብ የሚሠሩትን በዲጂታል የሚያግዝ ነው፡፡ ይኼንን ከሠራንላቸው ቆይቷል፡፡ ተመልሰው መጥተው አያውቁም፡፡ ቢመጡ አፕግሬድ እናደርግላቸዋለን፡፡ 

ሪፖርተር፡- የምትሠሩላቸው የመንግሥትም ይሁን የግል ተቋሞች ሲስተሙን በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ እያዋሉት መሆኑን ትከታተላላችሁ? እንደ ምሳሌ የብሔራዊ ቤተ መዛግብትና  ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) የሪከርድስ አርካይቭ ኤንድ ላይብረሪ ማኔጅመንት ሲስተምን ይጠቀሙበታል?

አቶ ተከስተብርሃን፡- ወመዘክር እየተጠቀመበት ነው፡፡ እኛ ካስተላለፍን በኋላ ሥራችንን እንጨርሳለን፡፡ እንደ ደንቡ በየዓመቱ እንድንረዳቸው የሰፖርት ኤንድ ሜንተናንስ ኮንትራት መግባት አለባቸው፡፡ ካልገቡ መቀጣት አለባቸው፡፡ የድርጅቱን ንብረት እንደማጥፋት ነው፡፡ በጀት ካላደረጉ እኛ ጋ አይመጡም፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ቦታ ክፍተት ቢኖርም፣ አብዛኞቹ ይሠራሉ፡፡ ውጭ አገር አንድ ሥራ ከተሠራ በኋላ ሁልጊዜ ቀጣይነት ያለው ገቢ የሚገኘው ከሰፖርትና ሜንተናንስ (የጥገና አገልግሎት) ነው፡፡ እኛን እየጎዳን ያለው የምንሠራላቸው ተቋሞች በሙሉ ተመልሰው አለመምጣታቸው ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች በሙሉ ሰፖርትና ሜንተናንስ አልገቡም፡፡ ከዓመታት በፊት በሠራንላቸው ሲስተም የሚሠሩ አሉ፡፡ አፕግሬድ እንድናደርግላቸው መምጣት አለባቸው፡፡ በእኛ አገር ሶትፍትዌር ሲገዛ እንደ ወንበርና ጠረጴዛ ነው፡፡ አንዴ ከተገዛ ምንም ሳይደረግለት ለዘለዓለም ይኖራል፡፡ ሶፍትዌር ግን ተከታታይ እንክብካቤ የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እያንዳንዱ ተገልጋይ በጀት መያዝ አለበት፡፡ በአሁን ጊዜ በዓለም ትልቁ ሀብት ዲጂታል ሀብት ነው፡፡ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት የራሱን መረጃ በእንክብካቤ መያዝ አለበት፡፡ ሆኖም የሪከርድ አርካይቨ (ስነዳ) ኋላ ቀርና ቆሻሻ መጣያ የሚመስል ነው፡፡ ይኼንን አቶሜት አድርገነዋል፡፡ ለዚህ ሀብት እንክብካቤ የማያደርግ ተቋም ኃላፊነቱን አልተወጣም፡፡ ሌሎች ሶፍትዌሮችንም እየተንከባከበ ሁልጊዜ እንዲሠሩ ያላደረገ የሕዝብና መንግሥትን ሀብት እያባከነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ዘርፉን እየተቀላቀሉ ያሉ ወጣት የአይቲ ባለሙያዎች ቁጥር መጨመር ምንን ያመላክታል ይላሉ?

አቶ ተከስተብርሃን፡ መብዛታቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በፖሊሲና በአተገባበር ደረጃም ለቢዝነሱ የተመቸ ግልጽ የሆነና አይቲ መሪ ኢንዱስትሪ እንደሆነ የሚገልጽ ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ አይቲ የጨርቃ ጨርቅ ወይም ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ተከታይ አይደለም፡፡ አይቲ የውጭ ምንዛሪ አምጡ አይልም፡፡ ጭንቅላታችሁን አሠሩ የሚል ነው፡፡ የእኛ ሕዝብ ደግሞ የቅኝ ቅርሰ ኅሊና ያለው ሳይሆን አምራች ቅርሰ ኅሊና ያለው እንደሆነ እናምናለን፡፡ እነዚህ ልጆች በሺዎች የሚቆጠሩ ከግልም ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ናቸው፡፡ ወደኛም ይመጣሉ፡፡ እኛ ካልተሳካልን ግን እነሱ በምን ተአምር ስኬታማ ይሆናሉ፡፡ ለአንድ ሰው ኮምፒውተር ስለተሰጠ ወይም አይቲ ፓርክ ውስጥ ስላስገባነው ብቻ ውጤታማ ይሆናል? ለእኔ አይታየኝም፡፡ ስለዚህ ሥራው እንደየሁኔታው ከጀማሪ አንስቶ በየደረጃው እንደየችሎታው ተመጥኖ በአገር ውስጥ ተቋሞች መሠራት አለበት፡፡ የአገራችን የአይቲ ሥራ በሚሊዮኖች ሆነንም አንጨርሰውም፡፡ ለሁሉም የሚሆን ቦታ አለ፡፡ በችሎታ ደግሞ ከጥሩ ዩኒቨርሲቲ ተመርጠው የሚመጡት ከእኛ ተርፈው ለሌላ አገርም እየሆኑ ነው፡፡ ከእኔ ድርጅት እንኳን ወደ አሜሪካ 113 ሠራተኞች ሄደው እስከ 170 ሺሕ ዶላር በዓመት ያገኛሉ፡፡ ከውጭ የሚመጣ ድርጅት ለሥራ የሚያስከፍለው ያን ያህል ነው፡፡ ታዲያ ለምን የራሳችንን እንንቃለን? አገር ውስጥ ችሎታ እያለ ለምን ለውጭ ድርጅት ይሰጣል?

                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                   

 

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ውጭ የሠራችኋቸው ሥራዎች አሉ?

አቶ ተከስተብርሃን፡- ከአንድ የአሜሪካ ድርጅት ጋር የሬል ትራኪንግ ሲስተም ለመሥራት እየተነጋገርን ነበር፡፡ የመረጃ ቴክኖሎጂ ግንኙነቱ ጥሩ ስላልነበረ ሳይሳካ ቀረ፡፡ እዚ አገር የሚሠሩ ሆነው በውጭ አገር ድርጅት (ኢቲኦ) ተቀጥረን የሠራናቸው አሉ፡፡ ለምሳሌ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ኢትዮጵያ ዶት ትራቨል ዌብሳይት ሠርተናል፡፡ ሥራውን ግን ያገኘነው እዚህ ሳይሆን የአየርላንድ ድርጅት ቀጥሮን ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ የሚሠራውን በውጭ ድርጅት ካልተሰጠን አናገኝም፡፡ አንድ የቤልጂየም ኩባንያ የአይቲ ኮንትሮል ሲስተም አሠርቶናል፡፡ የእንግሊዝ አገር ኩባንያ ኮንተንት ማኔጅመንት አሠርቶናል፡፡ ከሁሉም የሚበልጠው በአገራችን የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ የውጭ አገር ድርጅት የሚያሠራን በብዛት በአገራችን ስንሠራ ነው፡፡ የእኛው ሰው ያላመነንን ለምን ሌላው እንዲያምነን እንጠብቃለን? እኔ የሚገርመኝ እዚህ አገር አንድ ነገር ሳይደረግ ኤክስፖርት ሲባል ነው፡፡ ጀማሪ ሆኖ እንዴት ከዓለም ጋር መወዳደር ይቻላል፡፡ እዚህ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል  ለምሳሌ በፍትሕ መረጃ ሥርዓቱ አፍሪካን ማጥለቅለቅ ይቻላል፡፡ ሌሎች አገሮች ሲስተሙ የላቸውም፡፡ የውጭ ድርጅቶች ሥራ የሚፈጥሩት ገንዘብ እየሰጡና እየረዱ ነው፡፡ በእኛ አገር ይኼን መሰል ዝግጅት የለም፡፡ ከኪሳችን አውጥተን እንድንሠራ ነው የሚደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- መነሻችሁ የነበረው ‹‹ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአይቲ ማዕከል የማድረግ ዓላማን›› ምን ያህል አሳክተናል ብለው ያምናሉ?

አቶ ተከስተብርሃን፡በእኛ በኩል አሳክተናል ብለን እናምናለን፡፡ 702 ድርጅት ቀላል አይደለም፡፡ ወርልድ ባንክ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሠራው የኮርት ማኔጅመንት ሲስተም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጻጸር የላቀ መሆኑን ገልጿል፡፡ ኖቫቲክ ስፓይደር ዶት ኦርግ ስለ ሳይበርሶፍት ጽፏል፡፡ አይሲሲ ፎር ዴቨሎፕመንት እ.ኤ.አ. 2004 በስዊዘርላንድ ሲካሄድ ጋብዘውን ነበር፡፡ ትልቅ የአይቲ መንደር ያላቸው ሲሆን፣ እኛም ተካተናል፡፡ ከማይክሮሶፍት፣ ኤችፒ፣ ኖኪያና ሌሎችም ትልልቅ ድርጅቶች ጋር ስለ ሳይበርሶፍትም ተጽፏል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ለግል ተቋሞች ፕሮጀክቶች ከመስጠት ወደ ኋላ  ከሚልባቸው ምክንያቶች አንዱ ከደኅንነት ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው የሚባል ነገር አለ፡፡ ይኼ በሥራችሁ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

አቶ ተከስተብርሃን፡- እንደዚህ ዓይነት የመንግሥት ፖሊሲ አላውቅም፡፡ ከሆነም የተሳሳተ ነው፡፡ መንግሥት ሕዝቡ ደኅንነት አይጠብቅም ካለ ችግር አለ፡፡ መንግሥት የሠራው ብዙ ነው፡፡ ሁሉንም መሥራት ግን አይችልም፡፡ ‹ሁሉንም እሠራለሁ የሚል ቢኖር ይምጣና ምንም አይደለህም እለዋለሁ› የሚባል ነገር አለ፡፡ መንግሥት ሁሉንም መሆን አይችልም፡፡ ደኅንነትን መጠበቅ ያለ ኅብረተሰብ መንግሥት ብቻውን አይችለውም፡፡ እኛ ሳይከፈለን 18 ሚሊዮን ብር ካወጣንና ለኅብረተሰባችን ከተነሳሳን የአገራችንን ደኅንነት፣ መጠበቅ እንችላለን፡፡ አገርን አሳልፎ የሚሰጥ በመንግሥት ውስጥም፣ በግል ውስጥም፣ በኅብረተሰቡ ውስጥም ሊኖር ይችላል፡፡ ችግር የሚፈጥሩ ጥቂቶች ስለሆኑ እነሱን መለየት ያስፈልጋል፡፡ ዘርፉ አግላይ ሳይሆን አሳታፊ መሆን አለበት፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግዴታን መሠረት ያደረገ የጤና መድኅን ሥርዓት

የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍና የማኅበራዊ ጤና መድኅን ሥርዓቶችን መሠረት አድርጎም ይሠራል፡፡ የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን ሥርዓት በኢመደበኛ...

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...