Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ46 በላይ ቀበሌዎች በመሠረተ ልማት ዕጦት እየተፈተኑ ነው

በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ46 በላይ ቀበሌዎች በመሠረተ ልማት ዕጦት እየተፈተኑ ነው

ቀን:

በአማራ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን በሸበል በረንታ እና በዮፍታሔ ንጉሤ ወረዳዎች የሚገኙት ከ46 በላይ ቀበሌዎች ነዋሪዎች በመሠረተ ልማት ዕጦት መቸገራቸውን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ እነዚህ ቀበሌዎች ጤፍን ጨምሮ ከሰባት ዓይነት በላይ ሰብል አምራች ሲሆኑ፣ ምርታቸውን ለገበያው ለማውጣትም የመንገድ ችግር ቀስፎ ይዟቸዋል፡፡

አቶ አሰፋ ጫኔ በወይኒ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ ናቸው፡፡ ከበጋ ውጪ ወደ እነሱ መንደር ትራንስፖርት እንደማይገባ፣ መብራትም እንደሌለና ከከተማ ተስቦ እርሻው መሀል ገብቶ ለወፍ ማደሪያ ሆኖ እንደቀረ ይናገራሉ፡፡

በቀበሌዎቹ ከሚገኘው እነማይ ወደ ውስጥ የሚያስገባውን 18 ኪሎ ሜትር የገጠር ጠጠር መንገድ 22 የገጠርና ሦስት የከተማ ቀበሌዎች ይጠቀሙታል፡፡ የመንገዱ ግራና ቀኝ ደግሞ የጤፍ ምርት ደርቶበት ይታያል፡፡

የተጓዝንበት መኪና እያዘገመ ቢሄድም፣ መንገዱ ጥርስን ከማንገጫገጭ አላረፈም፡፡ ይኼ ወጣ ገባ መንገድ ለመኪናም ብቻ ሳይሆን ለእግረኛም አስቸጋሪ ነው፡፡ ገበሬዎቹ ሰብሎቹን ከማሳው ወደ ዋና መንገዱም ሆነ ወደ መውቂያ ለመውሰድ በጋማ ከብት፣ በጋሪና በሰው ኃይል ከማሸከም ውጪ እምብዛም አማራጭ የላቸውም፡፡ የመንገዱ ርዝመት ታሪፍ ስምንት ብር ቢሆንም፣ የትራንስፖርት ዕጦት በመኖሩ እስከ 20 ብር ለመክፈልም ይገደዳሉ፡፡

ለሕክምና አምቡላንስ ቢቀርብ እንኳን በፍጥነት ሕክምና ለማድረስ አዳጋች እንደሆነ ለመረዳት አዋቂ መሆንን አያሻም፡፡ የተዘናፈሉት ሰብሎች ደርሰዋልና እየታጨዱ ወደ ጎተራ እየገቡ ሲሆን፣ ወደ ገበያ ለማውጣት የትራንስፖርት ችግር በመኖሩ ባለበት ቦታ ደላሎችና ነጋዴዎች ዋጋውን በመቀነስ ይገዛሉ፡፡

የታዋቂው ደራሲና ባለቅኔ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ትውልድ ቦታ ዕድሜ ጠገብ ብትሆንም፣ ዛሬም ከቀይ አፈር መንገድና ካረጁ መንደሮቿ ልትላቀቅ አልቻለችም፡፡ በወረዳዋ 21 የገጠርና የከተማ ቀበሌዎች ሲኖሩ፣ ከፍተኛ የስንዴ ምርትና ብዙ የቱሪስት መስህብ አላት፡፡ የመንገድ ዕጦት ግን ያላትን ደጅ እንዳታወጣ እንዳደረጋት የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ፡፡

አቶ አብርሃም አለልኝ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ ኅብረተሰቡ ያነሳቸው ጥያቄዎች በሙሉ ትክክል መሆናቸውን በመግለጽ፣ ቀበሌ ከቀበሌ የሚገናኙ መንገዶች ግን ደረጃቸው ይለያይ እንጂ መገንባታቸውን ሆኖም የማሻሻልና የማሳደግ ሥራ እንደሚቀር ተናግረዋል፡፡

አንዳንዶቹ አካባቢዎች አመቺ ባለመሆናቸው ክልሉ ለመሥራት አቅዶ አለመሠራታቸውን፣  የመንገዶቹ ጉዳይ ከዞኑ በላይ መሆኑን፣ ይሁንና የክልሉን ፕሬዚዳንት ጋብዞ ከማሳየት ባለፈም ሁኔታዎችን ለማሻሻል እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በመብራት በኩልም፣ የመሥሪያ ቤቱም ችግር መኖሩንና የተገዙት መስመሮች ትራንስፎርመር ኬብሎች፣ ሲኒዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆናቸው ችግሩን እንዳባባሱት አክለዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ አቅም ስለሌለውም የተበላሸውን መስመር ለመጠገን መኪና ካልተዘጋጀ መተው መጠገን እንደማይችሉ የገለጹት አቶ አብርሃም፣ ከዞኑ ከፍተኛ ምርት የሚቀርብ ቢሆንም፣ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት እሴት ጨምሮ ለመሸጥ እንዳልተቻለ፣ ምርቱንም ወደ ገበያ ለመውሰድ ትራንስፖርት እንደ ልብ ባለመገኘቱ በርካሽ እንደሚሸጡ፣ አንዳንዴም ቶሎ መቅረብ የሚገባቸው ምርቶች ባለመቅረባቸው እንደሚበላሹ ጠቅሰዋል፡፡

በአማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ዞን በአጠቃላይ በ17 የገጠር ወረዳዎችና በአራት የከተማ አስተዳደሮች የተከፋፈለ ነው፡፡ ካሉት ወረዳዎችም አሥር በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በገጠርና በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ከአሥር ዓመት በፊት በተካሄደው የሕዝብ ቆጠራ 2.5 ሚሊዮን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 85 ከመቶው አርሶ አደር ነው፡፡ የአካባቢው ዋና ምርትም ጤፍ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...