Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ምሳሌ

ትኩስ ፅሁፎች

  1. ካያያዝ ይቀደዳል ካነጋገር ይፈረዳል፤
  2. ባፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ፤
  3. ዓሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፤ የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል፤
  4. ደባ ራሱን፤ ስለት ድጕሱን፤
  5. የአባት ዕዳ ለልጅ፤ የአፍንጫ እድፍ ለእጅ፤
  6.  ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ፤
  • ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደቂርቆስ ‹‹የአማርኛ ሰዋስው›› (1948)

******

ሰምና ወርቅ

ወላድ ኢትዮጵያ ለልጆቿ ብላ

እጅግ ሳይጥሩባት ሳይዘሩዋት አብቅላ

ስንዴውን ጠብቃ እንክርዳዱን ነቅላ

ስትመግበን አየን በፀሐይ አብስላ

ምሳሌ ዘር ሀገራችን

ንፁህ ዝናም መንግሥታችን

  • ዮፍታሔ ንጉሤ

*****

ደወል ለበደል

አፄ ዮሐንስ ጻድቁ የጎንደሩ፣ የተበደለ ደሃ አቤት አቤት ሲል ሰምተው ለኔ ለፍጡሩ እንደ ፈጣሪ አቤት መባል አይገባኝም ሲሉ የተበደለ ደሃ በደሉን የሚያሰማበት ደወል ሰቀሉ፡፡ አንድ ቀን የደወል ድምጥ ቢሰማ ምን የተበደለ ይሆን ጠይቁ ብለው ሰው ቢሰጹ ሰው የለ አህያ ነው አሏቸው፡፡ እሱም ተበድሎ ይሆናል አምጡ ብለው ቢያዩት ጭሬ እየበላው የደማውን ገጣባውን አዩ፡፡ ከፈረሶቻቸው ጋር አስቀልበው ሲድን ለባለቤቱ መልሰው ሰጡ ይባላል፡፡

ከንቲባ ገብሩ ‹‹ያማርኛ ሰዋስው መሪ፡፡›› (1915)

******

እንዲህ ነው!

ልብ ለልብ የተራራቁ ሰዎች በቅን ልቡና ጨዋታ ሲጫዋወቱ አንዱ የተናገረውን አንደኛው በብዙ ዓይነት መጥፎ መንገድ ከመተርጎም ብዛት የሚያቀያይም አሽሙር ያገኝበታል፡፡ ቅን መንገድ የሚከተሉ የተማመኑ ሰዎች ግን የተባረኩ ናቸው፡፡

***

ጥቂት ሽቱ የፈሰሰበት ቦታ በአፈሩ ላይ እስከ ብዙ ጊዜ ድረስ መልካም መዓዛ ይገኝበታል፡፡ ትልቅ ሙያ ያለው ሰው ሲፈጠርም እንዲሁ እንኳንስ በሕይወቱ ሳለ ከሞተም በኋላ ቢሆን የተወለደባትን አገር ሲያመሰግናትና ሲያስከብራት ይኖራል፡፡

***

ጠላት የለኝ ጠብም አልወድም ብሎ የዕለት ተግባሩን በሰላም እየሠራ ከቤቱ አርፎ የሚቀመጥ ሰው ሰላምን የሚያገኝ ቢሆን ኖሮ እጅግ መልካም ነበር፡፡ ግን ክፋቱ ያለምክንያት ጠብ ያለህ ዳቦ እያሉ እቤቱ ድረስ መጥተው ሰው ሰውን የሚበጠብጡ ሰዎች በዓለም ላይ ስለሞሉ ሰው ያለጠባዩ ታጥቆና ለጠብ ተሰናድቶ መቀመጥ ግዴታ ሆኖበታል፡፡

*******

በግልጥ ከታወቀው ጠላት ይልቅ ወዳጅ እየመሰለ የጠላትነት ሥራ የሚሠራ ሰው በጣም እንደሚጎዳና ሳይታወቅበት እንደሚያጠፋ የታወቀ ነው፡፡ አንድ ሊቅ ሲናገር አምላኬ ሆይ እኔ በዙሪያዬ ያሉት ጠላቶች እንዳያጠፉኝ ስታገል አንተ ደግሞ አደራህን ከወዳጆቼ ሰውረኝ አለ ይባላል፡፡

ከበደ ሚካኤል ‹‹የዕውቀት ብልጭታ››

******

‹‹የሀገራችንን ገመና የሚያውቁት መሰለኝ››

‹‹ደስ ያለህ ትመስላለህሳ!›› አለው ሰውየው ተላላኪው ማፍቀሯን ለመግለጽ ወኔ እንደከዳት ዓይናፋር ልጃገረድ እየተሽኮረመመ፡፡

‹‹ትንሽ ሎተሪ ቀንቶኝ ነበር››

‹‹ዕድለኛ ነህ ጃል ለመሆኑ ምን ያህል ነበር?

ተላላኪው ጥቂት ካመነታ በኋላ ‹‹አንድ መቶ ሴዲ ነው›› አለ፡፡

‹‹ብዙ አይደለማ!›› ሰውዬው እየሳቀ፡፡

‹‹ብዙ እንዳልሆነ አውቃለሁ ግን ብዙ ሰው እንደሚያስቸግረኝ ወይም እጅ እጄን እንደሚያይ ደግሞ እገምታለሁ››

‹‹እሱ ሳይታለም የተፈታ ነው››

‹‹እሱ እንኳ ማንም ሊያውቅ አይችልም››

‹‹እንዴት? ትኬቱን በቅጽል ስም ነበር እንዴ የቆረጥኸው?››

ደስታህን ያዝልቅልህ አለው ሰውየው፡፡

‹‹አመሰግናለሁ ደስታዬ ግን ከስጋት ነፃ አይደለም አለ ተላላኪው ፊቱን ኮስኩሶ፡፡

‹‹መተተኛ ምናምን?››

‹‹አይ ነገሩ ወዲህ ነው የሀገራችንን ገመና የሚያውቁት መሰለኝ››

‹‹አዎን እንጂ እንዴታ!››

‹‹ሁሉም ሰው የጋና ሎተሪ ውስጡን ለቄስ ነው ይላል››

‹‹ስጋትህ ገንዘቤን አላገኝ ይሆናል የሚል መሰለኝ››

‹‹እንዴታ! ጌታዬ አምና ከአምስት መቶ ሴዲ በላይ ወጥቶላቸው እስካሁን ድረስ ቀይ ሳንቲም ያላሸተቱ ደንበኞች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡››

‹‹ለፖሊስ ወይም ለፍትሕ አካላት አላመለከቱም ነበር?››

‹‹ያሾፋሉ መሰለኝ›› አለ ተላላኪው በምሬት ቅላፄ

‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› አሉ ለፖሊስ ማመልከት ማለት እኮ ለበለጠ ወጭ መዳረግ ማለት ነው?››

‹‹አሁን ታዲያ ምን ተሻለ?››

‹‹እዚያው ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ውስጥ ከዕጣዬ ውስጥ የተወሰነውን ጎርሶ ቀሪው የሚያስለቅቅልኝ ባለሥልጣን አላጣም የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ ከማለቱ ፊቱ የተቃጠለ ቅጠል መሰለ፡፡

‹‹የአንድን የመንግሥት ባለሥልጣን በጉቦ ቅሌት ማስገኘት አይሆንብህም›› አለው ሰውየው በስላቅ፡፡

‹‹ጌታዬ ምን ነካብኝ ምድሪቱ’ኮ ጋና ናት ይህን ለርስዎ መንገር ለቀባሪ ማርዳት ነው›› እያለ ከቢሮው ለመውጣት ተነሳ፡፡

  • መላክነህ መንግሥቱ ‹‹አልነጋም ገና ነው››

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች