Thursday, July 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየኤኤንሲ አዲሱ መሪ ሲሪል ራማፎሳ

የኤኤንሲ አዲሱ መሪ ሲሪል ራማፎሳ

ቀን:

የደቡብ አፍሪካ አውራ ፓርቲ ‹‹አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ›› (ኤኤንሲ) በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ክፍፍል ወደ አንድ ያመጣሉ የተባሉትን ሲሪል ራማፎሳ መሪ አድርጎ መርጧል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የሚመራውን ኤኤንሲ የሚረከቡት ባለሀብቱ ራማፎሳ፣ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስናም ያስተነፍሳሉ ተብሎ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ አገሪቱም እ.ኤ.አ. በ2019 ለምታደርገው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም  ራማፎሳ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ ሆኖም በፓርቲው ውስጥ ክፍፍል ሊፈጠር ይችላል ተብሏል፡፡

በፓርቲው ውስጥ ይበልጥ ክፍፍል ይፈጥራል ተብሎ የተሠጋው በእሳቸውና በቀድሞዋ የካቢኔ ሚኒስትርና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የቀድሞ ባለቤት ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ መካከል የነበረው የአንገት ለአንገት ፉክክር ነው፡፡ ሚስተር ራማፎሳ በምርጫው በ179 የድምፅ ብልጫ ከድላሚኒ ዙማ ልቀው እንዳሸነፉ ሲታወቅ፣ ዙማ ራማፎሳን በማቀፍ ነበር መልካም ምኞታቸውን የገለጹት፡፡ ነገር ግን የነጭ የበላይነት በደቡብ አፍሪካ አልረገበም የሚሉት ዙማ፣ ለባለሀብቶች ትኩረት እሰጣለሁ ለሚሉት ራማፎሳ እጅ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ሐሳባቸውን ለማሳካት ደግሞ ኤኤንሲን ከደጋፊዎቻቸው ጋር በመሆን መክፈል አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡

የኤኤንሲ አዲሱ መሪ ሲሪል ራማፎሳ

 

ራማፎሳና ድላሚኒ ዙማን ምን ይለያቸዋል?

      የ65 ዓመቱ ራማፎሳ በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና በመቃወምና የንግዱን ማኅበረሰብ በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡ የፓርቲያቸውን መንበር ለመቆናጠጥ ባደረጉት ቅስቀሳም አጀንዳ አድርገው ያወሱት፣ በአገሪቱ ያለውን ሙስና እንደሚዋጉና የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ለጥቂት ሳምንታት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ በኤኤንሲ የሚወሰን መሆኑን ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2017 የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዙማን በሙስና፣ በማጭበርበርና በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ሊጠየቁ እንደሚገባ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

የ68 ዓመቷ ድላሚኒ ዙማ አጀንዳቸው በነጮች አብዝቶ የተያዘውን የንግድ ምኅዳር ማመጣጠን ነው፡፡ በቀድሞ ባለቤታቸው ፕሬዚዳንት ዙማ ድጋፍ ይደረግላቸዋል የተባሉት ዙማ፣ በአገሪቱ አሁንም ድረስ የጥቁሮች እኩልነት እንዳልተረጋገጠ ገልጸው፣ በምርጫው ቢያሸንፉ ይህንን ለመቀየር ቃል ገብተው እንደነበር ቢቢሲ አስፍሯል፡፡ ሆኖም የራማፎሳ ማሸነፍ በደቡብ አፍሪካ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ሆነው ለማገልገልና የነጮችን የበላይነት ለማስከን ያለሙትን ዙማ ትልም አስቀርቷል፡፡

የፕሬዚዳንት ዙማ የወደፊት ዕጣ ምን ይሆን?

በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ አገሪቱ እ.ኤ.አ. የ2019 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እስክታከናውን በሥልጣናቸው መቆየት አለባቸው፡፡ ሆኖም የፓርቲው መሪ ሆነው የተመረጡት ራማፎሳ፣ ኤኤንሲ ጃኮብ ዙማ ፕሬዚዳንት ሆነው ይቀጥሉ አይቀጥሉ በሚለው ላይ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ያደርጉ ይሆናል፡፡ ፕሬዚዳንት ዙማ እንዲነሱ ከተወሰነም ራማፎሳ በዙማ ዙሪያ ያሉትን ወሳኝ የሥልጣን ቦታዎች ለማጥራት ዕድል ያገኛሉ፡፡

የኤኤንሲ አዲሱ መሪ ሲሪል ራማፎሳ

 

የራማፎሳ ማሸነፍ ለደቡብ አፍሪካ ምኗ ነው?

እ.ኤ.አ. በ1952 በደቡብ አፍሪካ ሶዌቶ ጆሃንስበርግ የተወለዱት ሲሪል ራማፎሳ ሁሌም ግንባር ቀደም እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ በፀረ አፓርታይድ አቋማቸው እ.ኤ.አ. ከ1974 እስከ 1976 በእስር የቆዩት እኝህ ሰው፣ በ1997 ሙሉ ለሙሉ ወደ ንግዱ መግባታቸው በደቡብ አፍሪካ አሉ ከሚባሉ ሀብታሞች ተርታ አሠልፏቸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አሁን ደግሞ የገዥው ፓርቲ ፓርቲ ኤኤንሲ መሪ የሆኑት ራማፎሳ፣ በአብዛኞቹ ግዛቶች ድጋፍ ሲያገኙ ይስተዋላል፡፡ በተለይ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት እንደ መሆናቸው፣ ማኅበረሰቡ እንደ ወራሽ ያያቸዋል፡፡ ይህም ቃል የገቡትን ለማሳካት ዕድል ይከፍትላቸዋል፡፡

የራማፎሳ የኤኤንሲ መሪ ሆነው መመረጥ ለደጋፊዎቻቸውም ዕፎይታን ሰጥቷል፡፡ ቢቢሲ እንደሚለው፣ የኤኤንሲ መሪ ለመሆን በፓርቲው ውስጥ የነበረው ሽኩቻ ከባድ ነበር፡፡ በሸፍጥ የተሞላ ነው ሲባልም ከርሟል፡፡ ማስፈራራትና ጉቦኝነትም ተጠናውቶት ነበር፡፡

ላለፉት አምስት ዓመታት የፕሬዚዳንት ዙማ ምክትል ሆነው ቢያገለግሉም፣ የዙማን አካሄድ የማያስቀጥሉ ዕጩ አድርገው ራሳቸውን ይገልጹታል፡፡ በርቱዕ አንደበታቸውም በአገሪቱ የተንሰራፋውን ሙስና እንደሚዋጉ፣ ሙስናም አገርን ከመክዳት ጋር እንደሚመጣጠን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህም ንግግራቸው በብዙዎች ዘንድ የተወሰደው፣ በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች የሚጠረጠሩትን ጃኮብ ዙማ ለማጥቃት አልመው እንዳደረጉት ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ባለሀብቶችና ደረጃ አውጪ ኤጀንሲዎችም የሲሪል ራማፎሳን ማሸነፍ በአዎንታ ዓይተውታል፡፡ እየዋዠቀ ያለው የደቡብ አፍሪካ ገንዘብና ኢኮኖሚ በአጭር ጊዜ ሊረጋጋና ሊያድግ እንደሚችልም እምነት አሳድረዋል፡፡

ውጤታማ ነጋዴ የሚባሉት የኤኤንሲ ተመራጭ መሪ ራማፎሳ በአገሪቱ ድህነት የወለደውን ልዩነት ለማጥበብም ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃ ዕቅድ የነደፉ ናቸው፡፡ በዚህም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላቸው፡፡ ሆኖም የኤኤንሲ ህልውና ላይ አደጋ መጋረጡም ይሰማል፡፡

ሮይተርስ እንዳሰፈረው፣ በራማፎሳና በድላሚኒ ዙማ መካከል ያለው የሥልጣን ሽኩቻ በፓርቲው በውስጥ መከፋፈል ፈጥሯል፡፡ ይህም ፓርቲው ፖሊሲዎችን ለማውጣትና ተቀባይነት ለማግኘት ደንቃራ ይሆንበታል ነው የሚባለው፡፡ ይህ ደግሞ እ.ኤ.አ. የ2019 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሳይከናወን ፓርቲው እንዲሰነጠቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚለውን አጉልቶታል፡፡

የኤኤንሲ አዲሱ መሪ ሲሪል ራማፎሳ

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት 

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...