Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹መንግሥት በሐሳብ ከሚለዩት ጋርም የመነጋገር ልማድ ሊያዳብር ይገባል››

መጋቢ ዘሪሁን ደጉ፣ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ

መጋቢ ዘሪሁን ደጉ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በቲዮሎጂ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በናይሮቢ ፓን አፍሪካን ክርስቲያን ዩኒቨርሲቲ በሊደርሺፕ ሠርተዋል፡፡ በአሜሪካና አውሮፓም የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ በአሁኑ ወቅት በ2003 ዓ.ም. የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ጉባኤው ከሰላም ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች በማስመልከት ምሕረት አስቻለው ከመጋቢ ዘሪሁን ደጉ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባኤው ምንን ዓላማ አድርጐ ተቋቋመ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- 2003 ዓ.ም. ላይ በአምስት ሃይማኖታዊ ተቋማት እንደ ታስክ ፎርስ (ግብረ ኃይል) ሆኖ በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልና መልካም ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ነበር የተቋቋመው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ሰባት (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት፣ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ፣ የኢትዮጵያ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትና የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን) ሃይማኖታዊ ተቋማት ጉባኤ አድጐ በዘጠኙም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ጽሕፈት ቤቶችን ከፍተን በመሥራት ላይ ነን፡፡ በተቋቋመበት ወቅት አልፎ አልፎ በሃይማኖት ተቋማት መካከል የሚታዩ አለመግባባቶችና ውጥረቶችም ነበሩ፡፡ ስለዚህ በዚያ ወቅት የነበረው ዓላማ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የዘለቀው የሃይማኖት መከባበርን ማስቀጠል ነበር፡፡ ከዚያ ዓላማው እየሰፋ ማኅበራዊ ኃላፊነቶች ላይ መሥራት ጀመርን፡፡ አሁን ደግሞ የሰላም ተልዕኮአችን ላይ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ መረጋጋትና ሰላም እንዲሰፍን ጉባኤው ምን ዓይነት ጥረቶችን እያደረገ ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- በሁለት መንገድ እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ የመጀመሪያው የሃይማኖት ተቋማት በተናጥል ስለ ሰላም ስለ አብሮነት ማስተማራቸው ነው፡፡ በጋራ ደግሞ የማስተማሪያ ማኑዋሎች ተዘጋጅተው ተሠራጭተዋል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የአሠልጣኞች ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ የውይይት ባህል እንዲኖር፣ የሕዝብ ጥያቄን መንግሥት እንዲመልስ፣ የሕዝብ ጥያቄዎችም በሰላማዊ መንገድ እንዲቀርቡ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ፈጣንና ሕዝብን እርካታ ሊሰጥ በሚችል መንገድ ጥያቄዎችን እንዲመልስ ውይይቶች ይኖራሉ፡፡ እታች ድረስ ባሉን አደረጃጀቶች ጥያቄ የሚያነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት የማደራደር ሥራም እንጀምራለን፡፡ መተማመንና መግባባት ላይ ይሠራ ዘንድም ራሱን የቻለ ታስክ ፎርስም ተቋቁሟል፡፡  

ሪፖርተር፡- እንቅስቃሴአችሁ ምን ያህል ሰፊ ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው ቢባልም ሁለቱም የሚሠሩት ለሕዝብ ስለሆነ በጋራ የሚሠሩባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን መንግሥትም ይህን ያን አድርጉ ብሎ በሃይማኖት ተቋማት ጣልቃ አይገባም፣ እነሱም እንደዚያው፡፡ በአገር ሰላምና ልማት ላይ በጋራ እንሠራለን፤ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሰላም፣ ልማት የመንግሥት አጀንዳ ብቻ አይደለም፡፡ በተለይም የአገር ሰላም ከምንም በላይ የሃይማኖት ተቋማት ጉዳይ ነው፡፡ የራሳችን መተዳደርያ ደንብ፣ ሌሎች መመርያዎችም አሉን፤ በዚያ መሠረት ነው እንቅስቃሴያችንን የምናደርገው፣ ምንም ዓይነት ተፅዕኖም የለብንም፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅታዊው ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትና ሰላም እንዲሰፍን የምታደርጉት ጥረት ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል? ተቀባይነታችሁስ ምን ድረስ ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- የሃይማኖት አባቶች ወጥተው ስለተናገሩ ወይም በአንድ መግለጫ ነገሮች በአንድ ጊዜ ይለወጣሉ አይባልም፡፡ ተደጋጋሚ ሥራና ጥረቶች ያስፈልጋሉ፡፡ ይህንን እየሔድንበት እየሠራን ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለን ተቀባይነትም ከፍ ያለ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ተሰሚነታችንን የሚጨምረው ደግሞ ገለልተኝነታችን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሥራውን የሚያከናውነው በገለልተኝነት ነው፡፡ ነገር ግን ተሰሚ እንዳንሆን ገለልተኛ አይደሉም ብሎ የሚሠራ የለም አይባልም፡፡ ዋናው እኛ የምንሠራው ለህሊናችን መሆኑ ነው፡፡ ገለልተኛነታችንን ጠብቀን መንግሥትን ይሔ ይሔ ነገር ትክክል አይደለም፣ ሕዝብንም እነዚህ እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢ ናቸው፣ የሚቀርቡበት መንገድም አግባብነት ያለው መሆን አለበት እንላለን፡፡ ጉባኤው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሕዝቦች ዘንድ መተማመን እንዲኖር ባይሠራ ኖሮ የተከሰቱ ችግሮች የከፉ ሊሆኑ ይችሉ ነበር፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎችን ግን እኛ ልንመልስ አንችልም፤ እነዚህ ጥያቄዎች መመለስ ያለባቸው በሕግና በሥርዓት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመንግሥት በኩልስ ያላችሁ ተቀባይነት እንዴት ነው?

መጋቢ ዘሪሁን፡- ባለፉት ስድስት ዓመታት እንደተመለከትነው ተቋማችን ተቀባይነት ያለውና ተፅዕኖ ፈጣሪም ነው፡፡ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በአግባብና በሥርዓት፤ በአፋጣኝም እንዲመልስ ሐሳባችንን ለመንግሥት አቅርበናል፣ ሐሳባችንንም ተቀብሎናል፡፡ መንግሥት በሐሳብ ከሚመስሉት ብቻ ሳይሆን በሐሳብ ከሚለዩት ጋር የመወያየት ልማድ ሊያዳብር ይገባል፡፡  እስካሁን ከመንግሥት ጋር ባደረግነው ውይይት ከመንግሥት ያገኘነው ምላሽ አዎንታዊ ነው፡፡ ስለ አገራቸው ግድ ብሏቸው ጥያቄ የሚያነሱም ሊሆኑ ይችላሉ፣ ሕጋዊነትን ተከትለው የፖለቲካ ወይም ሌላ ጥያቄ ከሚያቀርቡት ጋር የመነጋገር ልማድ ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ብዙ እንደሚሠራ ተስፋ እናደርጋለን፤ የፕሬዚዳንቱ የዚህ ዓመት የፓርላማ መክፈቻ ንግግርም ይህንኑ የሚያመላክት ነው፡፡ ትልቅ ተስፋ ሰጥቶናል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ንግግር ላይ የተገለጹ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚያን ነገሮች ይዘን አስፈጻሚውን አካል እነዚህ እነዚህ ነገሮች የት ደረሱ እያልን እንከታተላለን፡፡ ለሕዝብ ቃል የተገባው አልተፈጸመም ብለን እግር በእግር የማሳሰብ ሥራ እንሠራለን፡፡ እንግዲህ መንግሥት በዚህ በኩል ይሰማናል ብለን እናስባለን፡፡  

ሪፖርተር፡- የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት ነፃ አይደሉም እየተባለ በተደጋጋሚ አስተያየት ይሰጣል፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱ ላይ የሚነሳው የዚህ ዓይነት ጥያቄ እናንተ ላይስ ተፅዕኖ አያሳድርም?

መጋቢ ዘሪሁን፡- የአባል የሃይማኖት ተቋማት ነፃነት ተጠብቆ ነው በጉባኤው አማካይነት የጋራ ጉዳዮች ላይ በአንድ ላይ የሚሠሩት፡፡ እነሱ የእኛ አለቆች እንጂ እኛ የእነሱ አለቆች አይደለንም፡፡ ስለዚህ የሃይማኖት ተቋማቱ በተናጥል በሚወስዷቸው ዕርምጃዎችና የሚያደርጉት ውሳኔ ነፃ ናቸው፡፡ ጉባኤውም ጣልቃ አይገባም፡፡ ነገር ግን የዚህ ጉባኤም ነፀብራቅ ናቸው፡፡ ስለዚህም የሃይማኖት ተቋማቱ ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ እንዳይወድቅ ሁልጊዜ ይሠራል፡፡ ለምሳሌ ወደ ታች እየተወረደ ሲመጣ ገለልተኛ ያለመሆን ነገር ሊስተዋል ይችላል፡፡ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች ገለልተኛ የማያስብል አቋም ሊያንፀባርቁ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የሃይማኖት ተቋሙ አቋም ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፡፡ እዚህ ላይ መገናኛ ብዙኃን በብዙ መልኩ ችግር ሲሆኑ ታይቷል፡፡ የሃይማኖት አባቶች ያላሉትን ነገር ከተነገረበት ዐውድ ውጭ የሚፈልጉትን ነጥሎ የማውጣት ነገርም አለ፡፡ ይህ ሕዝብ ጋ ሲደርስ የሃይማኖት አባቶች ወይም ተቋማት ገለልተኛ አይደሉም ያስብላል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት አቋም ከመንግሥት ጋር ሲመሳሰል ገለልተኛ አይደሉም፣ ከሌላው ወገን ጋር ሲመሳሰል ደግሞ ሌላ ናቸው ይባላል፡፡ ዋናው ነገር አገራችን ሰላም መሆን አለባት፣ የውስጥ ሰላማችን መረጋገጥ አለበት የሚለው ነው፡፡ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት በምንም መንገድ መጥፋት የለበትም፣ ከየትኛውም ወገን ቢሆን ንብረትም የመሠረተ ልማት አውታሮችም መውደም የለባቸውም፡፡ እነዚህ ነገሮች ላይ በመግባባት አንድ ዓይነት አቋም ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ግጭቶች ከመፈጠራቸው በፊት የምትንቀሳቀሱበት ዕድል አለ?

መጋቢ ዘሪሁን፡- በዚህ ረገድ ውይይትን ነው የምናበረታታው፡፡ የሰላም ነገር የሚታወቀው የውይይት ባህል ሲኖር ነው፡፡ ለምሳሌ ጎንደር ወልቃይት ላይ መጀመሪያ ጥያቄ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እንዲወያዩ መድረክ አዘጋጅተን ነበር፡፡ በእርግጥ መድረኩን ለብቻችን ሳይሆን ከመንግሥት ጋር ነበር ያዘጋጀነው፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመሠረተ ልማት ተደራሽነት የሚፈልገው የግብርና ትራንስፎርሜሽን

የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ተቋም አርሶ አደሩን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን የማሳደግ ዓላማ ይዞ የተመሠረተ ነው፡፡ ተቋሙ የግብርናውን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ጥናቶችን...

‹‹በአሁኑ ሰዓት እየፈተነን ያለው እንደ ልብ ተንቀሳቅሰን መሥራት አለመቻላችን ነው›› አቶ ልዑል ሰገድ መኮንንን፣ አይሲዳ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር

አይሲዳ አገር በቀል የዕርዳታ ድርጅት በኤችአይቪ ሥርጭት ቁጥጥር ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ወዲህ ራሱን እንደ አዲስ አዋቅሮ በተለይ ለሰው ሠራሽና ለተፈጥሮ አደጋዎች ምላሽ...

‹‹ማንም ያለ ምክንያት አልተፈጠረምና ዜጎች እንዳይባክኑ እንሠራለን›› አቶ አብዱልፈታህ ሁሴን፣ የብሬክስሩ ትሬዲንግ ሥራ አስፈጻሚ

ብሬክስሩ ትሬዲንግ ‹ባለራዕይ፣ ቅን፣ ጤናማና ባለፀጋ ትውልድን ለመፍጠር የሚል ዓላማን ሰንቆ ቅን በተሰኘና አሥራ ስድስት አባላት ባሉት ቡድን ከአራት ዓመት በፊት የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡...