Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርትኩረት ያጣው የኮንዶሚኒየም ችግር

ትኩረት ያጣው የኮንዶሚኒየም ችግር

ቀን:

በዕድሉ ለማ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 1996 .ም. የከተማዋን ኅብረተሰብ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት በሚል ምክንያት የጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ብዙ የተባለለት ቢሆንም፣ አሁንም ድረስ በርካታ ችግሮች ያልተለዩት ፕሮጀክት ነው፡፡ ከነዋሪው ፍላጎት አንፃር እጅግ አዝጋሚ በሆነ ፍጥነት እየሄደ ያለው የቤት ልማት ፕሮግራም ሥር ነቀል የአሠራር ለውጥ ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ አስተዳደሩ 20/80 የቤት ፕሮግራም ለመጨረሻ ጊዜ ማለትም 11ኛው ዙር ላይ ዕጣ ከወጣ በኋላ፣ ዕድለኛ የሆኑ የቤት ባለቤቶች እያዩት ያሉት መጉላላትና መንከራተት ነው፡፡ የጽሑፉ አቅራቢ 11ኛው ዙር በቦሌ አራብሳ ሳይት ዕድለኛ ስሆን፣ በሐምሌ 2008 .ም. የወጣልኝ ቤት እስካሁን ለመግባት አልታደልኩም፡፡

ይህም በአስተዳደሩ ሥር በሚገኙ የተለያዩ ተጠሪ ሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዝርክርክነትና ግዴለሽነት ነው፡፡ 2007 ዓ.ም. መጋቢት ወር አሥረኛው ዙር ዕጣ ከወጣ በኋላ ቀጣዩ 11ኛው ዙር ከሁለት ወራት በኋላ ይወጣል ተብሎ ተመዝጋቢዎች በጉጉት ስንጠብቅ በመዘግየቱ፣ ይህ ለምን ሆነ ተብለው የተጠየቁት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ፣ለባለ ዕድለኞች 90 በመቶ በላይ ያለቀለት ቤት ለማስረከብ ስላሰብንና መሠረተ ልማቶችን አንድ ላይ አሟልተን ለማስረከብ ስለፈለግን ነው› ብለው ነበር፡፡ ይህ ከተባለ በኋላ በወራት ዕድሜ ውስጥ ይወጣል የተባለው ዕጣ አንድ አመት አራት ወር በላይ ጊዜ ፈጅቶ በሐምሌ 2008 . ቢወጣም፣ አሁንም ለነዋሪዎች መሟላት የሚገባቸው ብዙ ነገሮች አልተሟሉም፡፡ ለዚህም በምሳሌነት በቦሌ አራብሳና በኮዬ ፈጬ ሳይቶች ያለውን ሁኔታ መመልከት በቂ ነው፡፡

በእነዚህ ሳይቶች እስካሁን ድረስ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የለም፡፡ ያለውን ችግር ተቋቁመውና በየጊዜው እየናረ የሚሄደውን የቤት ኪራይ ዋጋ መቋቋም ያልቻሉ ባለዕድለኞች፣ የኤሌክትሪክ መስመር ከፕሮጀክት ቢሮው በገመድ ስበው በማምጣት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ ነዋሪዎች በብዛት እየገቡ ሲሄዱ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በዚህ መንገድ ማግኘት አዳጋች ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕፃናት በሚበዙበት የመኖሪያ አካባቢ ብዛት ያላቸውን የኤሌክትሪክ መስመሮች በእንዲህ ዓይነት መንገድ መዘርጋት ለደኅንነት አሥጊ ነው፡፡

የመጠጥ ውኃ አቅርቦትን በተመለከተ ከፍተኛ ችግር ይስተዋላል፡፡ በኮዬ ፈጬ እስካሁን የውኃ አቅርቦት አልተጀመረም፡፡ በቦሌ አራብሳ የከተማው የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥሪያ ቤት ከደንበኞች ጋር ውል ቢዋዋልም፣ በአሁኑ ወቅት ቆጣሪ አልቆብኛል በማለት ባለ ዕድለኞችን ሦስት ወራት የቀጠሮ ጊዜ በመስጠት እየመለሰ ነው፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ይህን ቀጠሮ ሲሰጡ የነገ ቀጠሮ እንደ ሰጡ ያህል አቅልለው ነው የሚናገሩት፣ ሁኔታው በጣም የሚያበሳጭ ነው፡፡

እነዚህን ነገሮች እንዴት ቀድሞ ማሰብ አይቻልም? ለምን በኅብረተሰቡ ላይ ይቀለዳል? አብዛኛው ኅብረተሰብ እኮ ከየትም ተበድሮ የቅድሚያ ክፍያውን የከፈለውና ለዕድሳት ብሎ ገንዘብ የሚያወጣው፣ በቶሎ ገብቶ ከኪራይ ብዝበዛ ነፃ እሆናለሁ ብሎ በማሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ቤቶቹ ለነዋሪዎች ዝግጁ ባለመሆናቸው ባለ ዕድለኞች ለሚኖሩበት ቤት የቤት ኪራይ፣ ለባንክ ደግሞ የኮንዶሚኒየሙን ወርኃዊ ክፍያ ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡ አንዱ ክፍያ ለሚያንገዳግደው አብዛኛው ባለ ዕድለኛ ሁለት ቦታ እንዲከፍል ማድረግ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው፡፡

ሌላው አስቸጋሪ ጉዳይ የቤቶቹ ጥራት መጓደል ነው፡፡ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቼ አስገነባኋቸው ለሚላቸው ቤቶች ክፍያ የሚፈጽመው የጥራት ደረጃቸውን ሳያረጋግጥ ነው? አብዛኞቹ ቤቶች በተለይ የመጨረሻ ወለል ላይ የሚገኙ ቤቶች ከፍተኛ የጥራት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ በርና መስኮቶች በአግባቡ አይገጠሙም፣ የአብዛኞቹ ቤቶች ጣራዎች ያፈሳሉ፣ ወለሎችና ግድግዳዎች ይሰነጠቃሉ፣ የመወጣጫ ደረጃዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁና ተሠርተው ያላለቁ ናቸው፡፡ በቦሌ አራብሳ ሳይት ብዛት ያላቸው ባለ ሰባት ወለል ሕንፃዎች የሚገኙ ቢሆንም ሊፍት አልተገጠመላቸውም፡፡ በዚህ ሁኔታ ሕፃናት፣ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች እንዴት በየቀኑ እነዚህን ደረጃዎች ሲወጡ ይውላሉ?

 መንግሥት ከአራት ወለል በላይ ላላቸው ሕንፃዎች በአስገዳጅነት ሊፍት እንዲገጥሙ ያዛል፡፡ የራሱ ሲሆን ግን ለምን ያወጣውን ሕግ ለማክበር ይሳነዋል? ብዙ የግዴለሽነት ሥራዎች ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለማስተካከል ባለ ዕድለኞች ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት ግድ ይሆንባቸዋል፡፡ ይህን ማድረግ ሲያቅታቸው ቤቱን አቅም ላለው ግለሰብ መሸጥን ይመርጣሉ፡፡ በእነዚህ ሳይቶችም እየታየ ያለው ይህ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ አስተዳደሩ አልሞ የተነሳው ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት ማድረግ የሚለው ሐሳብ ከከሸፈ ውሎ አድሯል፡፡

በሳይቶቹ የሚገኙ ለንግድ አገልግሎት ተብለው የተገነቡ ቤቶች እስካሁን ጨረታ ወጥቶባቸው ሽያጭ ስላልተከናወነ፣ ነዋሪዎች መሠረታዊ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎችን በአቅራቢያቸው ለማግኘት ባለመቻላቸው ለተጨማሪ ወጪና እንግልት እየተዳረጉ በጣም እየተቸገሩ ነው፡፡ የጨረታው ሒደት እስካሁን ማለቅ ነበረበት፡፡ አስተዳደሩ ግን ተኝቶበታል፡፡

የትራንስፖርት አቅርቦትን በተመለከተ አዳዲስ ወደሚገነቡ የጋራ መኖሪያ መንደሮች የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የራሳቸውን ታሪፍ ተግባራዊ ሲያደርጉ፣ የከተማው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለምን ይሆን ዓይቶ እንዳላየ የሚያልፈው? ለምሳሌ ከአያት አደባባይ እስከ ቦሌ አራብሳ ያለው ርቀት አምስት ኪሎ ሜትር አይበልጥም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ባወጣው ታሪፍ መሠረት ሁለት ብር 70 ሳንቲም መከፈል ሲኖርበት፣ ታክሲዎች እያስከፈሉ ያሉት ግን አምስት ብር ነው፡፡ አሁን በሚገባ ካልታረመ ነዋሪዎች ሲገቡም ይህ ታሪፍ እንዳይቀጥል ያሠጋል፡፡ ስለዚህ የሚመለከተው የትራንስፖርት ተቋም ይህን ሁኔታ ሊያስተካክል ይገባዋል፡፡

በመጨረሻም መንግሥት ሊመሠገን የሚገባው በእነዚህ ሳይቶች በመንገድ መሠረተ ልማት ያከናወነውን ሥራን በተመለከተ ነው፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁና ሰፋፊ መንገዶችን ነዋሪዎች ከመግባታቸው በፊት ማሠራቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የከተማው አስተዳደር ከላይ በጥቆማ የቀረቡትንና ነዋሪዎችን በከፍተኛ ሁኔታ እያማረሩ የሚገኙ ችግሮችን በአስቸኳይ በመፍታት፣ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ እንደሚያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

    ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

                                                 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...