[ክቡር ሚኒስትሩ ከአማካሪያቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ጠፍተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት አልጠፋ?
- የት ሄደው ነው?
- በአገር ውስጥ የለህም እንዴ?
- ኧረ አለሁ፡፡
- ቲቪ አትከታተልም?
- ሰሞኑን መብራት ስለሌለ አይቼ አላውቅም፡፡
- አንተ እኮ አፍራሽ መሆንህን አውቃለሁ፡፡
- ምን አደረግኩ?
- መብራት ያለበት ቦታ አትሄድም?
- አይ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን ሆንክ?
- መብራት ጠፍቶብኛል ስል አፍራሽ እያሉኝ እንዴት ልንግባባ እንችላለን?
- ታዲያ ታዳሽ እንድልህ ጠብቀህ ነው?
- ምንድን ነው እሱ?
- የስብሰባችን ፍሬ ነዋ፡፡
- የምን ስብሰባ?
- ሰሞኑን የጠፋሁት ስብሰባ ገብቼ ነው፡፡
- ማለት?
- ለመታደስ ወስነን ነው የወጣነው፡፡
- መታደስ ሲሉ?
- ይኸውልህ አገሪቱ በአጠቃላይ መታደስ አለባት፡፡
- እ…
- ግን ቢያንስ ከራሳችን መጀመር አለብን፡፡
- መታደስ ማለት ምን ማለት ነው?
- ሁሉን ነገር በአዲስ መተካት፡፡
- እሺ፡፡
- እና መታደስ በእኔ ይጀምራል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በአዲስ ሰው ሊቀየሩ ነው እንዴ?
- የለም የለም፡፡
- መታደስ ከእኔ ይጀምራል ሲሉኝ ነዋ፡፡
- እኮ ለምሳሌ የቢሮዬ ቀለም መቀየር አለበት፡፡
- ምን?
- ምንጣፌም መቀየር አለበት፡፡
- ስድስት ወር አልሞላውም እኮ፡፡
- ግን አዲስ አይደለም፡፡
- እ…
- የቢሮዬ ፈርኒቸርም ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር?
- የእኔ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የመሥሪያ ቤቱ መቀየር አለበት፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የገባዎት አልመሰለኝም፡፡
- ምኑ?
- መታደስ ማለት፡፡
- ደግሞ ፖለቲካውን ልታስተምረኝ ነው?
- የተሳሳቱ ስለመሰለኝ ነው፡፡
- አልጨረስኩም እኮ፡፡
- እሺ፡፡
- መኪናዬም የ2017 ሞዴል መሆን አለበት፡፡
- ምን?
- ስልኬም አይፎን 7 ፕላስ ይሁንልኝ፡፡
- ካሉ ምን ይደረጋል?
- ነገርኩህ በተሃድሶ ሁሉም ነገር መታደስ አለበት፡፡
- እርስዎ እንዳሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ስለዚህ ሁሉም ነገር በአዲስ ይለወጥ፡፡
- ጨረታ ይውጣ?
- አያስፈልግም፡፡
- ለምን?
- ሕዝብ ሰልችቶታል፡፡
- ምኑ?
- ቢሮክራሲው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ለምሳ ቤት ገብተው ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]
- ዛሬ ቀጠሮ የለህም እንዴ?
- የምን ቀጠሮ?
- ለምሳ መጣህ ብዬ ነው፡፡
- በቃ ተሰብስበን ጨረስን፡፡
- ለዚያ ነው የመጣኸው?
- መታደስ አለብን፡፡
- ምን?
- በቃ ዋናው መፍትሔ መታደስ ነው፡፡
- ሰውዬ ይኼን እዚያው ስብሰባህ ላይ አውራ፡፡
- አይ ቤተሰባችንም መታደስ አለበት፡፡
- ስማ ልጆቼን ፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ አልፈልግም፡፡
- ምን ነካሽ? ፖለቲካና ሕይወት እኮ የተሳሰሩ ናቸው፡፡
- ነገርኩህ ሰውዬ፡፡
- ለመሆኑ የቤቱን ቀለም አይተሽዋል?
- አዎ ምን ሆነ?
- እስቲ እይው፡፡
- አየሁት እኮ ምንም አልሆነም፡፡
- አዲስ ቀለም መቀባት አለበት፡፡
- ከተቀባ እኮ ስድስት ወር አልሞላውም፡፡
- ነገርኩሽ ይኼ ሶፋ፣ ዳይኒንግ ቴብሉ ምናምን ይቀየር፡፡
- አብደሃል እንዴ?
- ምን ሆንሽ?
- ባለፈው ለሱቅ ፈርኒቸር ሳስጭን እኮ ነው የቤቱ ዕቃ የተገዛው፡፡
- ቢሆንስ?
- ሰባት ወሩ ነው ገና፡፡
- መቀየር አለበት፡፡
- እ…
- ግቢውንስ አይተሽዋል?
- አንደኛውኑ ቤቱ ፈርሶ ይሠራ ለምን አትልም?
- እርሱም ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡
- ምን?
- ቤቱ ለምን…
- ምን?
- ሙሉ ለሙሉ አይታደስም?
- ምን ሆኖ?
- የስብሰባችን ውሳኔ መታደስ አለብን የሚል ነው፡፡
- መቼም አይገባህም አይደል?
- ምኑ?
- ሁሉም ነገር፡፡
- ማለት?
- ይታደስ የተባለው እኮ ሌላ ነገር ነው፡፡
- ማለት?
- ፖሊሲው፣ አሠራሩ፣ ቢሮክራሲው እኮ ነው ይታደስ የተባለው፡፡
- ግን እኛም መታደስ አለብን፡፡
- ከእናንተ የሚታደሰው ዕቃችሁ አይደለማ፡፡
- ታዲያ ምናችን ነው የሚታደሰው?
- አዕምሯችሁ!
[የክቡር ሚኒስትሩ ሾፌር ከፍቶታል]
- ምን ሆነሃል?
- ምን አደረግኩዎት ክቡር ሚኒስትር?
- እኮ ምን ሆንክ?
- እኔ ለእርስዎ ታዛዥ አይደለሁም?
- ምንድን ነው የምታወራው?
- በጠዋት ቢጠሩኝ በሌሊት፣ ቅዳሜ ቢሉ እሑድ እምቢ ብዬ አውቃለሁ?
- ሰውዬ ጤነኛ ነህ?
- እኮ የድሃን ጉሮሮ ዘግተው እንቅልፍ ይወስድዎታል?
- ምንድን ነው የምትቀባጥረው?
- ከሥራ ሊያባርሩኝ መሆኑን ሰማሁ፡፡
- ማን ነው የነገረህ?
- የ2017 ሞዴል መኪና ሊገዙ አይደል?
- አዎ ልገዛ ነው፡፡
- የ2017 ሞዴል መኪና ከሆነ ያለሾፌር እንደሚሄድ የቲቪ ማስታወቂያ አይቻለሁ፡፡
- ኪኪኪ…
- ምን ያስቅዎታል?
- ያለሾፌር የሚሄድ መኪና ቢሆን እኔ መቼ ይገባኛል?
- ምኑ?
- ቴክኖሎጂው!
[ክቡር ሚኒስትሩ በቅርቡ ካሠሩት ሕንፃ ማኔጀር ጋር እያወሩ ነው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ ስንቴ ነው የምነግርህ?
- ምኑን ክቡር ሚኒስትር?
- እዚህ ክቡር ሚኒስትር አትበለኝ አላልኩህም?
- ማን ልበልዎት ታዲያ?
- ክቡር ኢንቨስተር፡፡
- እሺ ክቡር ኢንቨስተር፡፡
- ስማ ሕንፃው መታደስ አለበት፡፡
- አዲስ እኮ ነው፡፡
- በቃ ተሃድሶ ማድረግ እንዳለብን ስለተስማማን፣ በአስቸኳይ ሕንፃው ይታደስ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አትበለኝ አልኩህ እኮ?
- መታደስ ምናምን ሲሉ ረስቼው ነው፡፡
- ስለዚህ ተከራዮቹ የቢሯቸውን ቀለም እንዲቀይሩ ንገራቸው፡፡
- ችግር የለውም፡፡
- የሚፈልጉትን ቀለም መምረጥ ይችላሉ፤ የማቀርበው ግን እኔ ነኝ፡፡
- ከየት?
- ከራሴ ፋብሪካ ነዋ፡፡
- እሺ እንዳሉ፡፡
- ፓርቲሽኖቻቸውን ከፈለጉ በአልሙኒየም፣ ከፈለጉ በፒቪሲ፡፡
- አስተላልፋልሁ ጌታዬ፡፡
- አቅራቢው ግን እኔ ነኝ፡፡
- ከየት?
- ኢምፖርት አደርጋለሁ አይደል እንዴ?
- እሺ፡፡
- ፈርኒቸሮቻቸውንም መምረጥ ይችላሉ፣ አቅራቢው ግን…
- እርስዋ ነዎት!
[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ደወሉላቸው]
- ኧረ ተው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አደረግኩ ደግሞ?
- ይኸው ከተማው ውስጥ የፈርኒቸር ቢሉ የአልሙኒየም ግዥ እያጧጧፉት ነው አሉ፡፡
- ምን ችግር አለው?
- በቃ በአደባባይ አደረጉት?
- በሰጣችሁኝ አቅጣጫ እኮ ነው እየተንቀሳቀስኩ ያለሁት፡፡
- የምን አቅጣጫ?
- የተሃድሶ አቅጣጫ፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- በቃ ቤቴም፣ ቢሮዬም፣ ሕንፃዬም እየታደሱ ናቸው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ለእርስዎ መታደስ አይደለም መፍትሔው?
- እና ምንድን ነው?
- መወገድ!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- ክቡር ሚኒስትር ሰሙ እንዴ?
- ስለምኑ?
- ስለሹም ሽሩ?
- እኔ ሳልሰማ አንተ እንዴት ሰማህ?
- አይ እንዳይሰሙ ተፈልጐ ይሆናላ፡፡
- ማለት?
- ቴክኖክራቶች ሥልጣን ላይ ሊወጡ ነው አሉ፡፡
- ይውጡ ምን ችግር አለው?
- ከዛም ባለፈ ሌላ የሰማሁት ነገር አለ፡፡
- ምን ሰማህ?
- ከዳያስፖራም አገር ለመምራት የሚመጡ አሉ ተብሏል፡፡
- ምን ችግር አለው ታዲያ?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እኛም እንሆናለና፡፡
- ምን?
- ዳያስፖራ!