Monday, February 26, 2024

የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ግጭት የንፁኃንን ሕይወት እየቀጠፈ ነው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

አህመድ ከድር (ሙሉ ስሙ ተቀይሯል) ተወልዶ ያደገው በኦሮሚያ ክልል ልዩ ስሙ አወዳይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እንደሆነ ይናገራል፡፡ አወዳይ ተወልዶ ያደገበት ከመሆኑም በላይ፣ ትዳር ይዞና ቤተሰብ መሥርቶ የሚኖርበት ከተማ እንደነበር ያስረዳል፡፡ አሁን የአምስትና የስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆቹን ይዞ በአዲስ አበባ ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ውስጥ እየኖረ ነው፡፡ ምክንያቱን ባላወቀው ጉዳይ ያፈራው ንብረቱ ከመቃጠሉ በተጨማሪ፣ በልጆቹ ላይ ሞት ሊያስከትል የሚችል አደጋ ተጋርጦ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ዕድሜ ዘመኑን ያፈራው ንብረት በሙሉ እንደወደመበትና በሰዎች ድጋፍ የቤተሰቦቹንና የራሱን ሕይወት ለመምራት መገደዱንም ይገልጻል፡፡  በመስከረም የመጀመርያው ሳምንት 2010 ዓ.ም. በሶማሌና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ሳቢያ ለችግር መዳረጉን ያስረዳል፡፡ ቤተሰቦቹን ማስተዳደር የማይችልበትና የዕለት ዕርዳታ ለማግኘት እጁን የዘረጋበት ጊዜ ላይ መድረሱንም ይናገራል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በ2010 ዓ.ም. መግቢያ በተቀሰቀሰ ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት ከመዳረጋቸውም ባሻገር፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

ችግሩ በተከሰተ ማግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሁለቱ የክልል አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና አባገዳዎች ጋር አድርገውት በነበረው ስብሰባ፣ ‹‹ግጭቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የፌዴራል መንግሥት ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት አፋጣኝ ዕርምጃዎችን ይወስዳል፤›› ብለው ነበር፡፡ በዚህም የፌዴራል የፀጥታ አካላት ወደ ሥፍራው ተልከው የማረጋጋት ሥራ ሲያከናውኑ እንደቆዩና አጥፊዎችን ለሕግ የማቅረብ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መንቀሳቀሳቸውም ተነግሯል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ለሃይማኖት አባቶች፣ ለአገር ሽማግሌዎችና ለአባ ገዳዎች ሰላም የማስፈን ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገው ነበር፡፡ የአካባቢዎችን ሰላምና ፀጥታ ወደነበረበት ለመመለስ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች በፌዴራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሕዝብን ሰላም የመጠበቅና የማረጋጋት ሥራ እንዲያከናውኑ፣ አካል በማጉደልና የሰው ሕይወት በማጥፋት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማዘዛቸው ይታወሳል፡፡ ግጭቱ በተከሰተባቸው አዋሳኝ አካባቢዎችና የግጭቱ ቀጣናዎች የፌዴራል መንግሥት ማንኛውንም የጦር መሣሪያ ወይም ትጥቅ እንደሚያስፈታ አክለው ገልጸው ነበር፡፡  በሁለቱ ክልሎች ሰብዓዊ መብት በመጣስ የሰው ሕይወት ያጠፉ፣ የፀጥታ ኃይልም ሆነ ማንኛውም አካል በሕግ አግባብ ዕርምጃ እንደሚወሰድበት አስታውቀው ነበር፡፡

በአዋሳኝ አካባቢዎች ግጭት ከተከሰተ በኋላ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች በጋራ መግለጫ ሰጥተው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ በመካከላቸው ተቀምጠው በሰጡት መግለጫ፣ የተፈጠረው ግጭት ሁለቱን ሕዝቦች እንደማይወክል ገልጸው ማውገዛቸው አይረሳም፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳ፣ ከሶማሌ ክልል አቻቸው አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ጋር በመሆን መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ሁለቱ ሕዝቦች የአንድ ኢትዮጵያ አካል ብቻ ሳይሆኑ ዘመናትን የተሻገረ የጋራ እሴትና ትስስር ባለቤት መሆናቸውን በመግለጽ፣ ግጭቱ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ወደ ማረጋጋቱ የመመለስና ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ተናግረው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይህ ሁሉ እየተባለና እየተነገረ ባለበት ጊዜ በሁለቱ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች  ግጭት እንደገና አገርሽቶ ከአንድ ወር በፊት ከሃያ በላይ ዜጎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል፡፡ የተከሰተውን ግጭት ወደነበረበት ለመመለስም መንግሥት እየሠራ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ሰላም እንዲሰፍንና ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳይደርስም ሲባል አጥፊዎችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ ሲከናወን እንደነበር ከሳምንታት በፊት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ገልጸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

መንግሥት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመመለስና በግጭቱ እጃቸው ያለበትን የመለየት ሥራ እያከናወነ መሆኑን እየገለጸ ባለበት ወቅት፣ ደግሞ ሌላ ግጭት ባለፈው ሳምንት ተከስቷል፡፡ ከታኅሳስ 5 ቀን እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሃዊ ጉዲናና ዳሮ ለቡ ወረዳዎች በተከሰቱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል፡፡

የሃዊ ጉዲናና የዳሮ ለቡ ወረዳዎች ከሶማሌ ክልል ጋር እንደማይዋሰኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በርካታ የሶማሌ ክልል ተወላጆች በእነዚህ ወረዳዎች መንደሮችን መሥርተው ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ለረዥም ዓመት አብረው ይኖሩ እንደነበር አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡ አቶ አዲሱ፣ ‹‹ታኅሳስ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሃዊ ጉዲና ወረዳ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ወንድሞቻችን ከሚኖሩባቸው መንደሮች ሰላማዊውን የሶማሌ ወንድሞቻችንን የማይወክሉ ታጣቂዎች ሰላማዊውን ማኅበረሰብ ተገን አድርገው ኢብሳና ታኦ በሚባሉ ቀበሌዎች ላይ ጥቃት መፈጸም ይጀምራሉ፡፡ በሰነዘሩት ጥቃትም በተጠቀሱት ቀበሌዎች 29 የኦሮሞ ተወላጆች ሞተዋል፡፡ ከ300 በላይ መኖሪያ ቤቶችም ከነሙሉ ንብረታቸው ወድመዋል፤›› ብለዋል፡፡

በሃዊ ጉዲና ወረዳ በተፈጸመው ጥቃት ሕይወታቸውን ካጡ ሰዎች መካከል አቶ አህመድ ጠሃ የተባሉ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰብ እንደሚገኙበት አቶ አዲሱ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ዚያድ ጠሃ የተባለ የሟች አቶ አህመድ ጠሃ ወንድም ደግሞ በዳሮ ለቡ ወረዳ ጋዱሉ ቀበሌ ነዋሪ መሆኑን፣ በሃዊ ጉዲና ወረዳ በተፈጠረ ግጭት የወንድሙን አቶ አህመድ ጠሃን ሞት የተረዳው አቶ ዚያድ በከፍተኛ የሐዘን ስሜት በመሆን ግብረ አበሮችን በማስተባበር ሃዊ ጉዲና ወረዳ ላይ ከተፈጠረው ግጭት ጋር ምንም ግንኙነት በሌላቸው የሶማሌ ክልል ተወላጅ ወንድምና እህቶች ላይ ዘግናኝ ዕርምጃ መውሰዱን፣ በደረሰ ሪፖርት መሠረትም የ32 የሶማሌ ክልል ተወላጆች ሕይወት ማለፉን ማረጋገጣቸውን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡  

ከታኅሳስ 5 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሃዊ ጉዲናና ዳሮ ለቡ ወረዳዎች በተቀሰቀሰ ግጭት የ61 ዜጎች ሕይወት ማለፉን አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡ ሪፖርቶቹ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ከፍ እንደሚል ቢጠቁሙም ማረጋገጥ አልተቻም፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው ግጭት ረገብ ያለ መስሎ እንደገና በማገርሸት የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፍ ላይ ነው፡፡ 2010 ዓ.ም. ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት የመስከረሙን ግጭት ሳያካትት የሟቾ ቁጥር ከ80 በላይ ደርሷል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ እንደሆነም መንግሥት በተደጋጋሚ ጊዜ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡ አንዳንድ ሪፖርቶች ቁጥሩን ከ600 ሺሕ በላይ አድርሰውታል፡፡

በሁለቱ ክልሎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ ሰዎችን በሕግ ጥላ ሥር የማዋል ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ሲገለጹ ቆይቷል፡፡ ለአብነት ያህልም በኦሮሚያ ክልልና በፌዴራል መንግሥት አማካይነት ከ80 በላይ በሕግ ጥላ ሥር መዋላቸውን ዶ/ር ነገሪ ጠቁመው ነበር፡፡ በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል መንግሥት ሳይሆን፣ በፌዴራል የፀጥታ አካላት አማካይነት ከሃያ በላይ ዜጎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ከአንድ ወር በፊት ተናግረው ነበር፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለውን ግጭት ለማስቆም የሕዝብ ለሕዝብ ኮንፈረንስ ለማካሄድ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ማካሄድ አልተቻለም፡፡ ምክንያቱ በውል ባይታወቅም መንግሥት ግጭቱን፣ ለማብረድና ዜጎችን ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ የሕዝብ ኮንፈረንስ አካሂዳለሁ ብሎ ቢያቅድም፣ እስካሁን ድረስ ሊሳካ አልቻለም፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው ግጭት ባለመቆሙ የተነሳ፣ በኦሮሚያ ክልል ባሉ የተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች የማስተማር ሥራ ለመቋረጡ አንዱ ምክንያት ሆኖ እየተነገረ ነው፡፡ በአምቦ፣ በመቱ፣ በወለጋ፣ በሐሮማያና በጅማ ዩኒርሲቲዎች የሚማሩ የክልሉ ተማሪዎች ከመውጫ ፈተናው በተጨማሪ፣ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው ግጭት ባለመብረዱ፣ በሚሞቱትና በሚፈናቀሉት ዜጎች ምክንያት ትምህርት እንዲቋረጥ መደረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች፣ በጨለንቆና በዩኒቨርሲቲዎች የተከሰቱትን ችግሮች አስመልክቶ እሑድ ታኅሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው እንደተናገሩት፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት የሚያውኩ ነገሮች ከመታየታቸው ባሻገር፣ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፣ የሕዝብ ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ግጭት ለማብረድ መንግሥት ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው፣ በቅርቡ ግን እንደገና እንዳገረሸና በንፁኃን ዜጎች ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት በማስከተል ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በምዕራብ ሐረርጌ በዳሮ ለቡ ወረዳ በጋድሌ ቀበሌ ለደኅንነታቸው ሲባል በአቅራቢያ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተጠልለው በነበሩ የሶማሌ ተወላጆች የጅምላ ግድያ ተፈጽሞባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም በጨለንቆና ሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች የሞትና የመቁሰል አደጋ አጋጥሟል በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፀጥታ ኃይሎቻችን መንግሥት ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ሰላምን እንዲያረጋግጡ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የጨለንቆን ግጭት ጨምሮ ተልዕኳቸውን እየፈጸሙ ባሉበት ወቅት ያጋጠሙ ክፍተቶች ካሉ አሠራሩን ተከትሎ መንግሥት ያጣራል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩ የሰው ሕይወት ከማጥፋቱና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር፣ በፍጥነት ካልተወገደ እንደ አገር አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ሊጥል እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሁለቱ ክልሎች አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና የሃይማኖት አባቶች ጋር በጽሕፈት ቤታቸው አድርገውት በነበረው ውይይት፣ በሁለቱ ክልሎችና በሌሎች የመረጃ አውታሮች የሚሠራጩ መረጃዎች ሕዝቡን እርስ በርስ የሚያጋጩና በዓይነ ቁራኛ እንዲተያዩ የሚያደርጉ እንዳይሆኑ አሳስበው ነበር፡፡ እሑድ ታኅሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም.  በሰጡት መግለጫም፣ ‹‹ሕዝቡ ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የሚያገኛቸውን መረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥና መረጃዎችን በተለያየ አግባብ ለማጣራት የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡ በመደበኛው የሚዲያ ዘርፍም ሆነ በሌሎች የመረጃ ማሠራጫ ሕግን አክብረው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

መንግሥትና ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ ግጭቶችን መንስዔ በመለየት፣ ችግሩን ከሥር መሠረቱ የሚፈታ ዕርምጃ የሚወስድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ያለው ግጭት እስከ ታኅሳስ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ እንዳልቆመ መረጃዎች ጠቁመው ነበር፡፡ በድጋሚ ለተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያቱ ምን እንደሆነ የተጠየቁት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ የተሟላ መረጃ እንደሌለና ገና በመጣራት ላይ እንዳለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የሶማሌ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ በሪፖርተር የተጠየቁ ቢሆንም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ጥሩነህ ገምታ ማክሰኞ ታኅሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከታኅሳስ 5 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. የተከሰተውን ግጭት በአካል ተገኝተው ባያዩም፣ አባሎችና ደጋፊዎች እዚያ አካባቢ ባለው ግጭት የተነሳ ከባድ አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ ቀድመው እንደ ነገሯቸው ገልጸዋል፡፡

ጉዳቱ ከፍተኛ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጥሩነህ፣ ከ60 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ፣ ቤቶች እንደ ተቃጠሉና ንብረት እንደ ወደመ መረጃ እንደደረሳቸው ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰ ሪፖርት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ ጉዳቱን ያደረሰውን አካል በተመለከተ ሲናገሩም፣ ‹‹ለጊዜው ጉዳቱን ያደረሰው አካል ማን እንደሆነ ከመናገር እንቆጠባለን፤›› ብለዋል፡፡

ለግጭቱ ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮችም አንስተዋል፡፡ ‹‹ለቢዝነስ ኢምፓየራቸው ገቢና ወጪ ትርፍ የሚገኘው በስፋት ከኦሮሚያ አካባቢ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ያንን ገደብ የለሽ ብልፅግናን የሚሹ አካላት ያደረሱት ይሆናል የሚል እምነት አለን፡፡ ከዚያ በተረፈ ደግሞ ኦሮሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሕገ መንግሥቱን ተከትሎ በቁመቱና በስፋቱ ልክ ሁሉም ነገር ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ ይገባኛል ብሎ መጠየቅም ስለጀመረ ነው፡፡ ይህ የሕዝብ ጥያቄ፣ የፍትሐዊነት ጥያቄ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ ያሠጋቸው ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ አሉም፡፡ የሶማሌ ልዩ ጦር ወይም ልዩ ኃይል የሚባለው ነገር ለእኔ አርቲፊሻል ነው፤›› ብለዋል፡፡  

ችግሮቹን ለማስተካከልና ወደ ቀድሞ መልካቸው ለመቀየር ካስፈለገ መንግሥት የመፍትሔ ዕርምጃዎችን መውሰድ አለበት ብለው፣ መንግሥት እንደ መንግሥት የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ መቻል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ የራሱን ቢዝነስ ‹ኢምፓየር› ከማስጠበቅ መውጣት እንዳለበትና የሕዝብን ኢኮኖሚያዊ ፍትሐዊነትን መገንባት እንዳለበት ገልጸው፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል ያሉ ባለሥልጣናት ጠንካራ ቃላትን ከመወርወር ወጥተው በጠንካራ ድርጊት የታጀበ ሥራ ማከናወን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ጠንካራ ቃላት በጠንካራ ድርጊት ካልታጀቡ በስተቀር እውነቱን ለመናገር የትም ሊያደርስ አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ መንግሥት ያለፈውን ታሪክ ከማነብነብ አባዜ ወጥቶ ወቅታዊ ለሆኑ የሕዝብ ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፍትሐዊ የሕዝብ አስተዳደር፣ ከሙሰኝነት የፀዳ መልካም አስተዳደር፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ለሕግ ማቅረብ፣ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ በአገሪቷ ሁሉም ዜጎች የሚሳተፉበት ሥርዓት ይመሥረት ነው የሕዝቡ ጥያቄ፤›› በማለት አቶ ጥሩነህ አስረድተዋል፡፡ ወደኋላ በመመለስና ሕዝብን ይቅርታ በመጠየቅ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ተገቢ ዕርምጃ ሲባል ደግሞ የሕዝብ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ታንክ ያለውን አካልም ቢሆን ማንበርከክ አለበት፡፡ ይህ ከሆነ መፍትሔው ቀላል ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) መሥራችና የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፣ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ከዚህ በፊትም ይከሰቱ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት በሐሳብ እንጂ በተግባር አልተሞከረም፡፡ አሁን በተግባር ታየ፡፡ አይደለም ነባሩን ችግር ሊፈታ ይቅርና አዳዲስ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፤›› ብለዋል፡፡

 በአገሪቱ የነበረው ግጭት መጀመርያ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ልደቱ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚናቸው ሲቀጭጭ ቅራኔው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡ ችግሩ እየሰፋና ዓይነቱ እየተለየ በመምጣት ችግሩ በኢሕአዴግ በራሱ ውስጥ መከሰቱንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ሁሉም ግጭቶች ግን ብሔርን መሠረት ያደረጉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰቱ ላሉ ችግሮች መሠረታዊ ምክንያት ያሏቸውን ጉዳዮች አቶ ልደቱ አውስተዋል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ ጀምሮ በሕግ ደረጃ የተቀመጡት ሕጎች ብሔር ተኮር መሆናቸው የራሱ ችግር አለው፡፡ የአገሪቱ አከላለል ብሔርንና ቋንቋን መሠረት ማድረጉ፣ በአገሪቱ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በብሔር መደራጀት፣ ሕጎች ላይ ያለው በጎ ነገር እንዳለ ሆኖ፣ በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ የዜጎች መብቶች በተግበር አለመዋላቸው ለችግሮቹ በመንስዔነት ተጠቃሽ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታትና በአገሪቱ ሰላማዊ ኑሮ እንዲከሰት ደግሞ የብሔር አደረጃጀት ችግሩ መፈታት እንዳለበት ሲገልጹ፣ ‹‹ብሔርን መሠረት ያደረገ አደረጃጀት በፓርቲዎች ደረጃ መቀየር አለበት፡፡ የጥገኝነትና የሙሰኝነት ችግር መስፋፋቱ ኢኮኖሚያዊ ብቻ አይደለም፡፡ ሙሰኝነትና የኪራይ ሰብሳቢ አመለካከቶች በዚህ ደረጃ ያደጉት የፖለቲካ ሙስና ስላለ ነው፡፡ ይህንን ኢሕአዴግ መፍታት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ዑመር መሐመድ ሰሞኑን የተከሰተውን ግጭት አውግዘውታል፡፡ አቶ አብዲ ለዛሚ ኤፍኤም ሬዲዮ በሰጡት ገለጻ፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት ከቦታው በ80 ኪሎ ሜትር ርቀት የነበረ ሲሆን፣ በፍጥነት ቢንቀሳቀስም በመንገድ ላይ ተደጋጋሚ የተኩስ ምልልስና የመንገድ መዝጋት እየገጠመው ለመድረስ አንድ ሰዓት የሚፈጀው መንገድ ሰባት ሰዓት ፈጅቶበታል፡፡

‹‹የመከላከያ ሠራዊት ከቦታው በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ሃሩሪቲ እንደ ደረሰ በመስጊድ ተጠልለው የነበሩ 53 ሰዎችን ተረክቧል፡፡ ከአካባቢው በተገኘ መረጃ መሠረት የተገደሉ ሰዎች የተወሰዱበትን ቦታ ፍለጋ እንደ ጀመሩና ሁለት የጅምላ መቃብሮች እንዳገኘ ተረድተናል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ጉድጓዶች ተቆፍረው ብዙ ሬሳ እንደተገኘባቸው ለፌዴራል መንግሥት ሪፖርት ተደርጎ በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ የሚመራ የልዑካን ቡድን በሔሊኮፕተር ደርሰው እንዲያዩ ተደርጓል፡፡ ከሚኒስትሩ ጋር ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አብዩ አሰፋና ከኢሕዴድ ጽሕፈት ቤት ተወካይ በሔሊኮፕተር ሄደው ሁኔታውን አይተዋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በቦታው ከነበሩት 62 ሰዎች መካከል የ48 ሰዎች ሬሳ እንደተገኘና ከመቃብር እንደወጣ አቶ አብዲ ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ ባለን መረጃ መሠረት ቶምሳ በተባለ ቀበሌ 24 ሰው፣ ሁለቆ አራት ሰው፣ ቆራቴ 18 ሰው የተገደሉ ሲሆን፣ መከላከያ የታደጋቸው ደግሞ በአሮሪቲ 53 ሰው፣ በሰውራ ቀበሌ 100 ሰው፣ በደሩ ለማ 300 ሰው ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዳሮ ለቡና ሃዊ ዲና ወረዳዎች ውስጥ ኦሮሞ ክልል ውስጥ በሚኖሩ የሶማሌ ክልል ተወላጆችና በኦሮሚያ ተወላጆች መካከል በተፈጠረው ግጭት፣ ከሁለቱም ክልሎች ሰዎች መገደላቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የተገደሉ የኦሮሞም ሆነ የሶማሌ ሕዝቦች የእኛ ሕዝቦች ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን ይገልጻል፡፡ የሶማሌ ክልል ተወላጅ በሆኑ ነዋሪዎች ላይ የተፈጸሙት ነገሮች አፀያፊ በመሆናቸው፣ በየትኛውም መልኩ የኦሮሞን ሕዝብ የማይወክል ድርጊት ነው፡፡ በጣም አሳዝኖናል፡፡ ደጋግመን ለሕዝባችን የምናስተላልፈው በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን የሶማሌም ሆነ በክልላችን ውስጥ የሚኖር ዜጋ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ለእኛ ጥቅም የለውም፡፡ ግን ጥፋት የሚፈጽም አካል ማንም ይሁን ማን መንግሥት ለሕግ አቅርቦ እንዲጠየቅ ማድረግ ግዴታው ስለሆነ እንቅስቃሴው ተጀምሯል፤›› ብለዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሦስት ትልልቅ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ መንግሥት ችግሩን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቢገልጽም፣ በድጋሚ እያገረሸ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ ነው፡፡ የተለያዩ ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸው ቢገለጽም፣ ግጭቱን ሙሉ በሙሉ ማቆም አልተቻለም፡፡ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ለማስቆም እየተፈጠረ ያለውን ችግር በማመን አዳዲስ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመንደፍና ከመላ የአገሪቱ ሕዝብ ጋር ውይይት በማድረግ መፍታት እንደሚገባ፣ የፖለቲካ ተንታኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተናገሩ ናቸው፡፡

 

    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -