Sunday, February 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የዓረቦን ገቢ አሰባሰበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጠለፋ ዋስትና ሰጪ ኩባንያ በመሆን የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ፣ በመጀመርያው የሒሳብ ዓመት ሪፖርቱ ከ519 ሚሊዮን ብር በላይ ዓረቦን ማሰባሰቡንና 82 ሚሊዮን ብር የጉዳት ካሳ መክፈሉን አስታወቀ፡፡ በመጀመርያው ዓመት የሥራ ክንውኑ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ አስመዝግቧል፡፡

የአክሲዮን ኩባንያው የ2009 ዓ.ም. አፈጻጸሙን ማክሰኞ፣ ታኅሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም.  ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ይፋ ባደረገው መሠረት፣ ከአጠቃላይ የመድን ሽፋንና ከሕይወት ነክ የመድን ሽፋን ዘርፎች 519.5 ሚሊዮን ብር አግኝቷል፡፡

ከተገኘው ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ ውስጥ 194 ሚሊዮን ብር ከአስገዳጅ ጠለፋ መድን ውል የተገኘ ሲሆን፣ 321.8 ሚሊዮን ብር ወይም 62 በመቶው ገቢ የተገኘው ከአስገዳጅ ቀጥታ የመድን ውል ነው፡፡ የተቀረው 3.7 ሚሊዮን ብር ወይም ከጠቅላላው የዓረቦን ገቢ አንድ በመቶ ድርሻ ያለው ገቢ ለግዙፍ የአደጋ ሥጋቶች ከሚሰጥ የጠለፋ መድን ውል ነው፡፡

ከዓረቦን ገቢው ውስጥ ከአጠቃላይ መድን ሽፋን የተገኘው 502 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ሕይወት ነክ ከሆነው የመድን ዘርፍ ደግሞ 17 ሚሊዮን ብር እንደተገኘ ተጠቅሷል፡፡ የኩባንያው ቦርድ ሰበሳቢ አቶ ኃይለ ሚካኤል ኩምሳ እንደገለጹት፣ ኩባንያው በ2009 ዓ.ም. 82.2 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ ከዚህ ውስጥ የአስገዳጅ ጠለፋ መድን ድርሻ 16.2 ሚሊዮን ብር ሲይዝ፣ ለአስገዳጅ ቀጥታ መድን ዘርፍ የተከፈለው ካሳ ደግሞ 66 ሚሊዮን ብር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢው እንደጠቀሱት፣ በ2009 ዓ.ም. 60.9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ኪሳራ የተመዘገበው ኩባንያው የመጠባበቂያ ገንዘብ እንዲይዝ በመደረጉ ነው፡፡ ኩባንያው በመጀመርያው የሥራ ዘመኑ የ270 ሚሊዮን ብር መጠባበቂያ ተቀማጭ ገንዘብ እንዲይዝ መደረጉ ታውቋል፡፡

 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጠለፋ መድን አሠራርን በተመለከተ ባስቀመጠው  መመርያ መሠረት፣ ማንኛውም መድን ሰጭ፣ ከሚሰጠው የመድን ሽፋን ውስጥ አምስት በመቶውን ለኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ እንዲሰጥ ግዴታ መጣሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ የተገኘው ገቢም ከኩባንያው ዓመታዊ ገቢ የአንበሳውን ድርሻ ማለትም ከ62 በመቶ በላይ ይዟል፡፡ በመመርያው መሠረት ግዴታው ፀንቶ የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ በመሆኑ፣ የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ ኩባንያው ላይ የሚፈጠረውን የዓረቦን ገቢ ክፍተት ለመሙላት ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንዳለበት የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው፣ ኩባንያው በዚህ መስክ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን በበለጠ ዕቅዶች ማዘጋጀቱን አስታውቀዋል፡፡

ኩባንያው ባዘጋጀው የስትራቴጂ ዕቅድ ሰነድ ውስጥ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ፣ በጊዜ ገደብ የተቀመጠውን ከእያንዳንዱ ውል የሚገኝ አስገዳጅ ገቢ የሚተኩ ሥራዎችን አፈላልጎ መሥራት የሚጠቀሰው ነው፡፡ ድርጅቱን በታዋቂ ዓለም አቀፍ ደረጃ መዳቢ ኩባንያዎች የማስገምገም ሥራ፣ በአገር ውስጥ የጠለፋ መድን ድርሻን የማሳደግ ሥራዎችን የመሥራትና ኩባንያውን በዓለም አቀፍ መድረኮች በማስተዋወቅ ድንበር ዘለል የጠለፋ መድን ሽፋኖችን መስጠት ከሚንቀሳቀስባቸው ሥራዎች መካከል ስለመሆናቸው ተገልጿል፡፡

ኩባንያው ከተሰጠው ኃላፊነት አንፃር ገበያውን ከኢትዮጵያ ውጭ በማስፋት መሥራትን የሚመለከት በመሆኑ፣ ይህንኑ ለማድረግ በመጀመርያው የሥራ ዘመኑ ያደረጋቸው ሙከራዎች ባይሳኩም፣ ወደፊት በዚሁ መስክ እንደሚንቀሳቀስ የቦርድ ሰብሳቢው ጠቁመዋል፡፡

ኩባንያው በአንድ ዓመት ውስጥ ስላከናወናቸው ተግባራት ተጨማሪ መረጃ የሰጡት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ የወንድወሰን ይታይ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ ሲቋቋም ዋነኛ ዓላማ አድርጎ የተነሳው የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ለውጭ የጠለፋ ዋስትና ሰጪዎች በውጭ ምንዛሪ የሚያወጡትን ወጪ መቀነስ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ የጠለፋ ኩባንያው ከመቋቋሙ በፊት የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየዓመቱ ለጠለፋ ዋስትና የሚያወጡት ወጪ በዓመት ከሚሰበስቡት ዓረቦን እስከ 30 በመቶውን ይወስዳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኩባንያው ከምሥረታ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሲጠቀምበት የነበረውን ስያሜ ለመቀየር ያቀበረውን ሐሳብ ጠቅላላ ጉባዔው ተቀብሎታል፡፡ በዚሁ መሠረት ‹‹የኢትዮጵያ ሪኢንሹራንስ ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር›› የሚለው መጠሪያ ‹‹የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ አክሲዮን ማኅበር›› በሚል ስያሜ እንዲለወጥ ተወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ አክሲዮን ማኅበርን ሰባት ባንኮች፣ 17 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ 80 ግለሰቦችና አንድ የሠራተኞች ማኅበር የአክሲዮን ባለድርሻ ሆነው ያቋቋሙት ኩባንያ ነው፡፡ የኩባንያው አጠቃላይ የተፈረመ ካፒታል 997.3  ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ኩባንያው ሥራ የጀመረው ከአንድ ዓመት በፊት መሆኑም ይታወቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች