Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ራያ ቢራ ከአክሲዮን ዝውውር እንዲከፍል የተጠየቀውን ታክስ በመቃወም ለመንግሥት አቤቱታ አቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ሊከፍል እንደሚችል ይገመታል

ቢጂአይ ኢትዮጵያ የራያ ቢራን አክሲዮን ማኅበር ጠቅልሎ ለመግዛት ያቀረበውን ጥያቄ የተቀበሉ ባለአክሲዮኖች፣ የአክሲዮን ዝውውሩ ሕጋዊ ሒደት በአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ በኩል እንዲፈጸም ውክልና ሰጡ፡፡ ከአክሲዮን ዝውውሩ ጋር በተያያዘ ለመንግሥት የሚከፈለው የ30 በመቶ ታክስ ውዝግብ መፍጠሩ ተጠቆመ፡፡

የራያ ቢራ ባለአክሲዮኖች ለማኅበሩ ዳይሬክተሮች ቦርድ የሰጡት ውክልና ይፋ የተደረገው የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ቅዳሜ፣ ታኅሳስ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ነው፡፡ ውሳኔው የተላለፈው የአክሲዮን ድርሻቸውን ለቢጂአይ የሚሸጡ ባለአክሲዮኖች በተናጠል ወደ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በመሄድ የሚፈጽሙትን ስምምነት በጥቅል ማድረጉ እንደሚሻል በመታመኑ፣ ቦርዱ ባለአክሲዮኖችን ወክሎ ሒደቱን እንዲያስፈጽም በማድረግ ሽያጩን ለማፋጠን ይረዳል በማለት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደተዘገበው፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለውን አንድ አክሲዮን በ7425 ብር ለመግዛት ያቀረበው ሐሳብ በራያ ቢራ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖች በመደገፋቸው፣ በዚሁ መሠረት ወደ ሕጋዊ ስምምነቱ እንደሚገቡ ሲጠበቅ ነበር፡፡

ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት ከሆነ፣ የቢጂአይን የግዥ ጥያቄ ያልተቀበሉ  ባለአክሲዮኖች እንዳሉና፣ ድርሻቸውን እንደማይሸጡ የሚገመቱ ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከአሥር በመቶ በታች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይህም ሆኖ የመሸጥ ፍላጎት ያላሳዩ ባለአክሲዮኖች፣ ድርሻቸውን ከነጭራሹ አይሸጡም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል ማለት እንደማይቻል እየተነገረ ነው፡፡

በራያ ቢራ የ42 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ የያዘው ቢጂአይ፣ ከይዞታው ውጭ ያሉትን አክሲዮኖች ሰባት እጥፍ ከፍሎ በመግዛት የመጠቅለል ፍላጐቱን ሲያሳውቅ፣ ድርሻቸውን ለመሸጥ የማይፈልጉ ካሉም እንደያዙ መቆየት የሚችሉበት ዕድል መሰጠቱ ተረጋግጧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከጠቅላላ ጉባዔው በተጓዳኝ የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአክሲዮን ሽያጩ ሲካሄድ ከእያንዳንዱ ሽያጭ ለመንግሥት የሚከፈለው የ30 በመቶ ታክስ አወዛግቧል፡፡

ከአክሲዮን ሽያጩ ለመንግሥት የሚከፈለው የ30 በመቶ ታክስ መከፈል የሚገባው እስካሁን ባለው አሠራር መሠረት፣ የአክሲዮኑ ዋጋና አክሲዮኑ እስካሁን ታስሮ የቆየበት ዋጋ ተቀናንሶ ነው፡፡

በመሆኑም የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ፣ ከአክሲዮን ሽያጩ ለመንግሥት የሚከፈለው የ30 በመቶ ታክስ ታሳቢ የሚደረግበት የገንዘብ መጠን ምን ያህል መሆን አለበት በሚለው ላይ ውዝግብ መፈጠሩ ታውቋል፡፡

ቦርዱ እያንዳንዱ የአክሲዮን ዋጋ ለዓመታት የተቀመጠበትና የትርፍ ክፍያ ያልተፈጸመበት በመሆኑ፣ በባንክ እንኳ ቢቀመጥ ሊያስገኝ ይችል የነበረው ዋጋ ተቀናሽ ሊደረግ ይገባዋል የሚል እምነት አለው፡፡ ለዚሁ ተብሎ የተዘጋጀው መመርያም ይህንኑ እንደሚደግፍ የቦርድ አመራሮቹ ያምናሉ፡፡

ስለጉዳዩ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የአንድ አክሲዮን ዋጋ አንድ ሺሕ ብር ቢሆንና ይህ አንድ ሺሕ ብር ምንም ዓይነት የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ ወይም ዴቪደንድ ሳያስገኝበት ቆይቶ ከሆነ፣ ይኸው ጉዳይ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአክሲዮኖች ዝውውርን በተመለከተ በወጣው መመርያ ውስጥ የተመለከተ በመሆኑ፣ ራያ ቢራ የሚከፈለው የ30 በመቶ ታክስ ላይ ከዚህ አግባብ በመነሳት አለአግባብ ታክስ መክፈል እንደሌለባቸው በመጥቀስ እስከመጨረሻው እንከራከራለን ሲሉ የራያ ቢራ ባለድርሻዎች ገልጸዋል፡፡

የታክስ አከፋፈል ጥያቄው ቀርቦ ቦርዱ እየተራከረበት ሲሆን፣ በጠቅላላ ጉባዔው ወቅትም ከአክሲዮን ሽያጩ ለመንግሥት የሚከፈለው የ30 በመቶ ታክስ ከምን ያህሉ ላይ ታሳቢ ተደርጐ ይከፈል? የሚለው ጥያቄ ውይይት ተደርጐበታል፡፡ የታክስ ክፍያው  ጉዳይ ላይ ቦርዱ የደሰበትን አቋም ለባለአክሲዮኖች ገልጾ፣ ይከፈል ተብሎ በመንግሥት አካላት የተገለጸላቸውን የገንዘብ መጠን በመቃወም ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አቤቱታ ማቅረባቸውን የራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ ባለአክሲዮኖችን ወክሎ እንዲያነጋግርላቸው ባለአክሲዮኖች ለቦርዱ ሥልጣን መስጠታቸውም ተጠቅሷል፡፡ መንግሥት ከአክሲዮን ዝውውሩ እንዲከፈለው የጠየቀው የታክስ መጠን ተፈጻሚ ከሆነ፣ እያንዳንዱን ባለአክሲዮን ማግኘት ከሚኖርበት ገንዘብ ውስጥ ከ10 እስከ 12 በመቶ ሊያሳጣው እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

ስለጉዳዩ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት የራያ ቢራ ቦርድ አባል፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በተመሳሳይ መንገድ የኮካኮላ ባለአክሲዮኖች አክሲዮናቸውን ሲሸጡ የ30 በመቶ ታክስ የከፈሉበት አግባብ እስካሁን በነበረውና መደበኛ አክሲዮናቸው በባንክ ቢቀመጥ ሊስገኝ የሚችለው የወለድ መጠን ወይም የወቅቱ የዋጋ ግሽበት ታሳቢ ተደርጐ መሆኑን በመግለጽ፣ ራያ ቢራ ላይ የቀረበው የታክስ ጥያቄ የተለየ እንዲሆን ለምን እንደተፈለገ ግልጽ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡

ባለሥልጣኑ እስካሁን የሚሠራበትን መመርያ ወደ ጎን በማለት የ30 በመቶ የአክሲዮን ዝውውር ታክስ እንዲከፈለው ያቀረበው ጥያቄ የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ሳይደረግ ነው፡፡ ይህም አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለው አክሲዮን 7425 ብር በመሸጡ ከአክሲዮኑ ዋጋ ውጪ ያለው 6425 ብር ላይ የ30 በመቶ ታክስ ታሳቢ ተደርጎ እንዲከፈል የሚጠይቅ ደብዳቤ ለትግራይ ክልል ገቢዎች ጽሕፈት ቤት ተጽፏል፡፡

የራያ ቢራን ሽያጭ ተከትሎ ለመንግሥት የሚከፈለው የ30 በመቶ ታክስ መከፈል የሚገባው ከምን ያህሉ ገንዘብ ላይ ተሰልቶ እንደሆነ መታወቅ አለበት የሚለው ጥያቄ፣ ያስነሳው ውዝግብ እልባት እንዲያገኝ የራያ ቢራ ቦርድ አመራር ጉዳዩን ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በማቅረብ ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) እንዲያነጋግሯቸው አቤት ማለታቸውንም ሪፖርተር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

በመንግሥት ውሳኔ መሠረት የ30 በመቶው ታክስ ክፍያ የሚፈጸመው በ6425  ብር ላይ ከሆነ፣ ከ4200 በላይ ባለአክሲዮኖች በዚሁ አግባብ እንዲከፍሉ ቢደረግ፣ መንግሥት ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከአክሲዮን ዝውውሩ ያገኛል፡፡

ራያ ቢራ 700 ሺሕ ሔክቶ ሌትር የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ የገነባ ሲሆን፣ ግንባታውን አጠናቅቆ ሥራ ለማስጀመር 1.7 ቢሊዮን ብር ወጪ ጠይቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ ይገመታል፡፡

ቢጂአይ ከራሱ ድርሻ ውጪ ያሉትን አክሲዮኖች ሙሉ በሙሉ ከገዛ ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡     

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች