እነሆ መንገድ። ከአያት ወደ ጦር ኃይሎች። ያጠበቁት እየላላ፣ ያላሉት እየጠበቀ፣ በፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ግራ መጋባት የሄድንበትን መንገድ ደግመን ልንሄድበት ባቡር ተሳፍረናል። ቁጭት፣ ሰቀቀን፣ ተስፋ፣ ማጣት፣ ማግኘት፣ ጉትትና ጉጉት የለሽነት በየመልክና አቋሙ ልክ ከሰፈረው ወዘ ብዙ ተሳፋሪ ጋር ተደራርቦ ቆሟል። አንዱ አቀርቅሮ ስልኩን ይጎረጉራል። አንዱ ውልብታውን በመስኮት አነጣጥሮ እንደ ፊልም እያየ ያለበትን ረስቶ አፍንጫው እስኪደማ ይጎረጉረዋል። በዚህ ቀልበ ቢስ የሚጠቋቆሙ ወጣቶች የማያስቀው ሁሉ አሳቀን እያሉ ይንከተከታሉ። ባለተራ ሆኖ የሳቃቸው ቀስት ወደ እሱ እንዳይነጣጠር የሰጋ ርብትብት ደግሞ ምንም ሳይገባው ያጅባቸዋል። ባቡራችን ጥቂት ሳብ ጥቂት ቆም ጨዋታውን ይጫወታል። ወሬ የተከለከለ ይመስል ተሳፋሪው እርስ በእርሱ እየተፋጠጠ ቆይቶ አንገቱን ይደፋና ያቃናል።
በአፍንጫ ጎርጓሪው ቀልበ ቢስነት ተመስጠው ፌሽታ ከፈጠሩት ወጣቶች ፊት ለፊት የተቀመጡ ወይዘሮ አንዴ ጆሯቸውን እየነካከኩ አንዴ ወደ መንጋጋቸው የእርቅ ጣታቸውን ሰደው ስንቅር አኞ እየፈለጉ ነገረ ሥራቸው አልጥም ያላቸውን ወጣቶች ይታዘባሉ። ደራሽ ይወርድና ተረኛው ይገባል። በባቡር ውስጥ የተከለከሉ ነገሮች ዝርዝር በየሚዲያው እንዳሰለቸን የቢራ ማስታወቂያ ሲደጋገምበት የወጣበትን ለማስታወስ ጥቂት የማይባል ሰው ወደ ልቦናው ማስታወሻ ገብቶ የዕለት ዕቅዱን የሚያጠና ይመስላል። “አቦ ይኼ ነገር ምንድነው? ሐበሾች እኮ ነን። እንኳን ነገር ተደጋግሞብን እንዲሁም ጠርጥረን ዱር የምንመነጥር መሆናችንን እያወቁ ምንድነው ጆሯችንን የሚያደነቁሩት?” ይላል አንድ አጭር ደንዳና። አዛውንቷ ፈገግ ብለው እያዩት፣ “አንተስ ብትሆን ስለነገር አዋቂነታችን ለማውራት ምን ይኼን ያህል ጉልበት ያስጨርስሃል? ‘ምሳር ላወቀበት ደን ይመነጥራል፣ አትቀደም ያለው ባይን ይጠረጥራል’ ብለህ ዝም አትልም?” አሉት። “ይቅር ይበሉኝ እማማ። ጨዋታው የመቀደምና ያለመቀደም መሆኑ አልገባኝም ነበር፤” ብሎ እንደ ሽርኩ በዓይኑ ሲጠቅሳቸው እንዳላዩ አለፉት። ሳይገባው የገባው መስሎ የሚታየው በዝቶም ይሆናል እኮ ክልከላና ማስጠንቀቂያው የሚያጨናንቀን!
ባቡራችን ፀሐይ እንደናፈቃት እርጉዝ እባብ እየተጥመለመለ መምዘግዘጉን ቀጥሏል። ወራጅ ወርዶ ሂያጅ ተተክቶ ሲኤምሲን ስንለቅ በባቡሩ ውስጥ ተቀጣጣይ ነገሮች መያዝ የሚለውን ማሳሰቢያ ሳትጨርስ ተናጋሪዋ ፀጥ አለች። ወዲያ እነዚያ ፌዝ የሚቀናቸው ወጣቶች በኅብረት ድምፅ ማሳሰቢያውን ጮክ ብለው ጨረሱት። አንዳንዱ ሳቀ። አንዳንዱ ተናደደ። ወይዘሮዋ ይኼኔ፣ “አቀጣጣይ ሳይኖር የሚቀጣጠል ነገር ይጎዳ መስሏችሁ ነው? ዋናው አቀጣጣዩ ነው፤” ሲሉ፣ “እንዴ እማማ እንደርስዎ አባባል ከሆነ እኮ ባቡሩ ባዶውን ዋለ ማለት ነው፤” አሉ ወጣቶቹ። “አሁንስ ባዶ አይደለም እንዴ?” አሉ በቁጣ። “ምነው እማማ? ይኼን ሁሉ ሰው ዓይንዎ እያየ ምን አበሳጭትዎ ይክዳሉ?” ሲላቸው ያ ደንዳና፣ “ሰውማ አየን። ለአገሩ ለሚጠቀምበት የሕዝብ ንብረት የሚያስብ። የሚያነሳ የሚጥለውን ሌላውን አስቦ የሚሠራ ሰውማ አየን። በማፍረስ ሳይሆን በመገንባት የተካነ፣ በደመ ነፍስ ሳይሆን በምክንያት የሚራመድ ሰው የሞላበትና የጠፋበት ገበያማ ተለየ፤” ብለው ክረምቱን አውሮፓ ልጃቸው ጋ ተቀምጠው ዓይተው ስለመጡት ብዙ ብዙ አወሩ።
“ታዳያ ሁሉም ነገር እኮ ቀስ እያለ ይስተካከላል። ያዩት ላላዩት ሲያሳዩ፣ የተማሩት ላልተማሩት ሲያስተምሩ፣ የተመከሩት የሚመከሩትን ሲመክሩ እኛም በአገራችን አውሮፓዊ እንሆናለን። እርስዎ መመረቅ፣ ጎብዙ አይዟችሁ ማለት ነው ያለብዎት፤” አላቸው። “ወድጄ መስሎህ ነው? ልጄን ዓይኗን ካየኋት ሃያ ዓመት ሆኖኝ እንጂ ምነው ባልሄድኩ እስክል ድረስ ወሽመጤን ቆርጠውታል። ሰው በነገር የሰው ወሽመጥ ይቆርጣል። ሰው በስድብ ለዕለትም ቢሆን የሰው ቀልብ ይገፋል። እንዴት አንድ ሕዝብ በሥራው፣ በጥንቁቅነቱ፣ በአርቆ አሳቢነቱ፣ ለሕግ ባለው ተገዢነት የሰው ወሽመጥ ይቆርጣል? ወይ ዕድሜ?” ብለው በረጅሙ ሲተነፍሱ “ዋናው እሱ አይደል እንዴ?” ብሎ አጠገቤ አንዱ ሽክ አለኝ። ቁም ነገሩን በሹክሹክታ ፌዝና ቧልቱን በድንፋታ የምናወራው ግን ለምን ይሆን?!
ወይዘሮዋ በረደላቸው፣ ንፅፅራቸው ተረሳ ሲባል ደግሞ አንድ በሩ አጠገበ የቆመ ተሳፋሪ ያለኃፍረት ደረቱ እስኪፋቅ አክ ብሎ ጫማው ሥር ተፋ። “እዩልኝ! አንሳት ብየሃለሁ! አንሳት ነው የምልህ!” ብለው ወይዘሮዋ እንደ እብድ ሆኑ። ወትሮም ቋፍ ላይ ናቸው የእሳቸውን መባስ ሲያይ የጉዟችን ኅብረት በሆታ ሳቅ ተናጋ። ነውረኛው ሳይደነግጥ ሳይገረም ‘ምን አጠፋሁ?’ ዓይነት ግራ ቀኝ ያያል። “አንዳንዱ ሰው ግን ጥግ ነገር ሲያይ ለምን እንደሆነ አላውቅም ወይ መትፋት ወይ መሽናት አለበት። ምንድነው ግን ጉዳዩ?” ትላለች አንዷ ጠይም ሎጋ። ወዲህ ነውርን ክብር ስላደረገ አኗኗር ተሳፋሪው ሲነጋገር፣ ከወዲያ በኩል በታላቅ ቁጣና ተግሳጽ ነውረኛው ትፋቱን እንዲያብስ ሶፍት ይወረወርለታል።
“ልምድ እኮ ነው የሚጫወትብን። የሰው ልጅ የልምድ ባሪያ ነው ይባል የለ?” ይላል አንዱ። “የለም ልምድ ዝም ብሎ አይለጠፍብህ። ደረጃውን የጠበቀ መፀዳጃ ቦታ ዓይተህ ሳታድግ ሥነ ሥርዓት ልትማር አትችልም፤” ትላለች ሌላዋ። “ኧረ ተይ እባክሽ። ዋናው ቤት ነው። ለሁሉም ነገር መሠረቱ ቤት ነው። አለቤ ሾው ትዝ ይላችኋል? ልክ ሲጀምር? ሥራ ቦታው እስኪደርስ ድረስ ልብሱን እየለበሰ፣ ጥርሱን እየቦረሸ፣ ፂሙን እየላጨ የሚሄደው መንገድ ላይ ነበር። ለምን? ምክንያቱም ኑሯችን መንገድ ላይ ስለሆነ። የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ነዋሪ ኑሮ እንደዚያ ነው። የዓይን ማዘኗን እየጠረጉ ያሳደጉን ወይ ጎረቤቶቻችን ወይ አስተማሪዎቻችን ናቸው። መስታወት እናውቃለን እንዴ? ለምን? ቤት ሳይኖር መስታወት ስለማይኖር። አበቃ!” ሲላት አንዱ አብዛኛው ተሳፋሪ አንገቱን በመስማማት ነቀነቀ። መጀመሪያ መቀመጫዬን ከዚያ መስታወቴን መሆኑ ነው እንግዲህ!
ጉዟችን ቀጥሏል። ከጎኔ የቆመው ተሳፈሪ፣ “አሁን ይኼንን ሁሉ ትዝታ ከመፈንቀል በአጭሩ ኮንዶሚኒየም ተመዝግቤያለሁ ዕጣ አልወጣልኝም አይልም? እኛን ጨምሮ እስኪ አሁን ጎል መክተት፤” ሲል ሌላ ሰው ሰማው። “ኧረ ዝም በለው እስኪ አሁን ነውርን ተገን አድርጎ ብሶት መዘርገፍ ምን ይባላል?” ብሎ አሽሟጠጠ። “የመንገዱ ፀባይ ነው። ምንም ማድረግ አይቻልም። ይኼ መንገድ እንደሆነ ገና ብዙ ብዙ ያነጋግራል። እንዲያውም እኛ እኮ አንነጋገርም፤” ብላ አንዷ ጨዋታውን ተቀላቀለች። “ኤድያ። ተነጋገርን አልተነጋገርን ደግሞ እኛ። ገና ሀ ብለን ሁ ሳንል በየፊናችን ዱላና እብሪት ሲቀድመን ነው የኖረው። ተጨነቁ ብሏችሁ፤” አለች ሌላዋ። “የለም። እንደዚያማ አይባልም። በአሥር ዓመት አንዴም ቢሆን መነጋገር ጥሩ ነው። ይህቺን ታህል ያኖረን ምን ሆነና? ደህና ዋልክ ደህና አደርሽ መባባላችን አይደለም እንዴ?” ሲላት ከጀርባዋ የሚወዛወዝ ጎልማሳ፣ “እሱማ የእግዜር ሰላምታ ነው። ደግሞ እሱም እስኪከለከል እንተዛዘብ እንዴ? እንዴት ያለ ነገር ነው?” ብላ መለሰችለት።
“ታዲያ የምን ንግግር ነው የናፈቃችሁ?” ጠየቀ ጎልማሳው ግራ ገብቶት። “የአንተ ትብስ የአንቺ ትብስ ነዋ። ‘ይኼው ጥፋትህ እንዲህ ያደረግከው እንደዚህ ቢሆን ነበር መልካም’ ሲባል ‘ነው? ልክ ነው ተቀብያለሁ! ተሳስቻለሁ’ የምንባባልበት ንግግር ነው ያልንህ? አይደለም? ነው?” ብላ ዙሪያ ገባዋን ስትቃኝ ሁሉም ባልሰማ ፊቱን አዞረ። “ዋ እማማ ኢትዮጵያ! እስከ መቼ ፊት ተዙሮ ይሆን ተነባብረን የምናድርብሽ?” ብላ አነባበሮ እንደምትጋግር እጆቿን ወደ ሰማይ ስትዘረጋ አጠገቧ የቆምነው ሽሽት ይዘን ተበታተንን። አንዳንዱ ዘመን ምን መፍራት፣ ምን መድፈር፣ በምን ማፈር፣ በምን መኩራት በቅጡ አላስጠና ይልና ይኼው እንዲህ ለእግዚኦታም ‘አልሰማሁም አላየሁም’ የሚባልበት ይሆናል። በለው!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ጫጫታውና ግርግሩ ጎዳናውን ቀልብ ነስቶት እያየን ባቡራችን የሐዲድ ገደፉ ሞልቶ እስኪያራግፈን አሰፍስፈናል። “አይ አንተ ጎዳና?” አለ አንዱ። “ጎዳናው ምን አደረገን እኛ ነን እንጂ፤” አለው ከአጠገቡ። “እኛ ምን አደረግን? እነሱ ናቸው እንጂ?” አለች ጠይሟ ሎጋ። “እነሱና እኛ አንድ አይደለንም እንዴ?” አሉ አዛውንቱ። “ኧረ ምንድነው የኮድ መዓት? ግልጽ አድርጉት አቦ፤” ብሎ አንድ ወጣት አገጠጠ። “ግልጽ የሆነው እየተድበሰበሰ፣ የተድበሰበሰውና የማይረባ የማይረባው እየገነነ እያየህ ለምን ግልጽ አድርጉት ትለናለህ?” አለ ጎልማሳው። “ታዲያ አትቆጣና፤” ይላል ምኑም ያልተነካው። “ቆይ እኮ ጎዳናችን ምን ሆነ?“ አንዷ አፈጠጠችበት። “ፍርደ ገምድል በዛው እያልኩሽ ነው፣ ነውሩን ክብር ያደረገ በዛ፤” አላት ከአጠገቤ የቆመው። “አልገባኝም?” ስትለው አሁንም ወይዘሮዋ፣ “ይኼ ካልገባሽማ ውኃ በላሽ ልጄ። ዓለምና የተዛባ የፍርድ ሚዟና እንደሆኑ ያሉ፣ የነበሩና ወደፊትም የሚኖሩ ጥንዶች ናቸው። ደህና ነገር የምታወሩ መስሎሽ ነው?” አሉዋት።
ይኼኔ አንድ አዛውንት ድምፃቸውን ጠራርገው፣ “እርግጥ እርስዎ እንዳሉት ሁሉም ያለና የነበረ ነው። ግን አአንዳንድ ነገሮች ወደፊት መሻገር የማይገባቸው ነገሮች አሉ። አለበለዚያ በዚህ ብሂል ትውልድ ከማበላሸት ውጪ ልናንፅ አንችልም። ነውርና ፍትሕ አልባነትን ካልታገልን ሙስናም የመልካም አስተዳደር እጦትም፣ የመደማመጥ ችግርም አብረውን መኖራቸው ነው። እኛም አልቅሰን ልጆቻችንም ሲያለቅሱ መኖራቸው ነው፤” እያሉ አዋዙት። “እና ምን አድርጉ ነው?” ጠይሟ መለሳለስ ስትጀምር፣ “የማይሞገሰውን ባለማሞገስ፣ ክብር የሚገባውን በማክበር፣ ቅድሚያ የሚሰጠውን በመስጠት፣ መደመጥ ያለበትን በማድመጥ፣ መማር ካለብን በመማር፣ መገሰጽ ያለበትን በመገሰጽ፣ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ አለማለፍ። በእግዚኦታና ‘እሱ ይይልህ’ ብሂል ማስተካከል የምንችለውን ነገር አደባብሶ አለማለፍ። ለውጥ ከራሴ ነው። እውነቴን ነው፤” ሲሏት ባቡራችን ቆመ። ጎዳናው ክብርንና ነውርን አሽሞንሙኖ ይታየናል። አፍ ቢኖረው ይኼ መንገድ ያስተማሪ ያለህ! አይልም ትላላችሁ? ለማንኛውም ማለባበስና ማድበስበስ ቢበቃንስ? መልካም ጉዞ!