Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርመሠረታዊ የሐሳብ ገበያችን እንዳይፈርስ

መሠረታዊ የሐሳብ ገበያችን እንዳይፈርስ

ቀን:

ኢትዮጵያ ከራስ አሉላ አባ ነጋ እስከ ራስ ጎበና ዳጬ፣ ከፊታአውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ እስከ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ከራስ መኮንን እስከ አሚር አብዱላሂ፣ ከደጃዝማች ባልቻ ሳፎ እስከ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ወዘተ. ጀብዱ የሠሩ፣ ፍቅርንና አንድነትን ሰብከው ያለፉ ልጆች ባለቤት ነች፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተገነባው በእነዚህ ዓይነት ግለሰቦችና አገር ወዳድ ሰዎች ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ በፅኑ ዓለት ላይ የቆመች አገር ሆናለች፡፡ በቀላሉ የሚፈርስ ማንነት የላትም፡፡ ወደ ነፈሰበት የማትነፍስ፣ ወደ ተዛመመበት የማታጋድል ከብረት በጠጠረ ምሰሶ ላይ የቆመች አገር ነች፡፡፡ ፍቅር ሲሰበክባት የኖረች፣ አብሮ የመኖር ሚስጥር የተገለጠባት አገር፡፡

እዚህ ላይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብርሃም ሊንከን በአንድ ወቅት የተናገሩትን ብጠቅስ ከላይ ያሰፈርኩትን ሐሳብ የበለጠ ያብራራዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ‹‹ለማንም ጥላቻንና ጥልን ሳናሳይ፣ ለሁሉም ፍቅርንና በጎነትን እንግለጽ… (“With malic to ward none, with charity for all”) የሚለውን ንግራቸውና ምክራቸው ‹‹ከተራራው የጌታ እየሱስ ስብከት ቀጥሎ የሰው ልጅ ያደረገው ትልቅ ንግግርና ምክር›› እየተባለ በአሜሪካውያን ዘንድ እስከ ዛሬ ድረስ ይሞካሻል፡፡ ዛሬ አሜሪካ ለደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ለመድረስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል፡፡ በመሪያቸው ስብከት የተማረኩት አሜሪካውያን ጥልንና ፍርኃትን አስወግደው በፍቅርና በአንድነት ገመድ የተሳሰሩ ሕዝቦች ሆነዋል፡፡

ትናንትና የእኛ አያትና ቅድመ አያቶቻችን በፍቅር በመኖራቸው የአክሱምን ሐውልት አነፁ፡፡ የላሊበላን አብያተ ክርስቲያናት ከአንድ የድንጋይ ቋጥኝ ፈለፈሉ፡፡ የፋሲልን ግንብ አቆሙ፡፡ የጀጎልን ግንብ ለታሪክ አኖሩ፡፡ የሼክ ሁሴን ዓሊ መስጊድን አስረከቡ፡፡ ጠላትን በመጣበት እግሩ አባረሩ፡፡

ይህ ባልሆነበት ዘመን ደግሞ በአገራችን የዚህ ተቃራኒ ጉዳይ ተፈጥሮ አልፏል፡፡ ታዋቂው ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ የነበሩት ሙሉጌታ ሉሌ ‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን››› በሚለው መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት፣ ፍቅርና ሰላም ባልተሰበከበት በደርግ ዘመን በተለይም በ1969 ዓ.ም. የዚያድ ባሬ ጦር ኢትዮጵያን እንደወረረና በኦጋዴን ልዩ ልዩ ሥፍራዎች በጋላዲ፣ በጅጅጋ፣ በቀብሪ ደሐር፣ ወዘተ በፀሐይና በንፋስ ስትንገላታ ቀለሟ እየተለወጠ የነበረውን፣ ዳሩ ግን የኢትዮጵያችንን ክብርና ነፃነት የምትገልጸውን ሰንደቅ ዓላማ እያወረዱና እያቃጠሉ የተስፋፊነት ምልክት የሆነውን የሶማሊያ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክን ባለአምስት ኮከብ ሰንደቅ ዓላማ በዚህች አገር አውለብልበዋል፡፡  ምንም እንኳን ይኼ ድርጊት ረጅም ጊዜ የቆየ ባይሆንም፡፡

ፍቅር ከሌለ ትርፉ ሊሆን የሚችለው ይህ ነው፡፡ የደርግ መንግሥት የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብት በመንፈጉ ዜጎች እንደ ንብ መንጋ በአንዴ ጠላትን ለመውጋት አልዘመቱም፡፡ ዘመቻውም የነበረው በግዳጅ ነበር፡፡ ዜጎችም ለተለያዩ አደጋዎች ተጋልጠዋል፣ ታስረዋል፣ ተጨፍጭፈዋል፡፡ የሚሊዮኖች ደም ፈስሷል፡፡ እናት የወለደችውን ልጅ አካለ መጠን ደርሶ የማየት ዕድል አልነበራትም፡፡ እናቶቻችን አንብተዋል፡፡

ይኼ ሁሉ ዘግናኝና አሰቃቂ ድርጊት የተከሰተው መንግሥት ይከተለው የነበረው የአስተዳደር ሥርዓት ፍፁም አምባገነን በመሆኑና ሰብዓዊ መብቶች የተረገጡበት ጊዜ ስለነበር ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ወጣቶች ፈቅደው ሳይሆን ተገደው ወደ ጦር አውድማ ተግዘዋል፡፡ ይህ ያለ ሕዝቡ ፍላጎት ይካሄድ የነበረው ግዳጅ ደግሞ ፍፃሜው ምን እንደሆነ በታሪክ አይተናል፡፡ በወቅቱ በዜጎች መካከል መቃቃርና በዓይነ ቁራኛ መተያየት ነበር፡፡ ወንድም ወንድሙን ገድሏል፡፡ በአንድነት ተቀናጅተን ጠላትን ሳይሆን የራሳችንን ዜጋ ገድለናል፡፡ ይህ የማይፋቅ ቀይ ስህተት ሆኖ በኢትዮጵያ ታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ በወቅቱ ፍቅር አልተሰበከም፡፡ አንድነት አልታወጀም፡፡ ከአገራዊ ጉዳይ ይልቅ የጥቅመኝነትና የሥልጣን ፍላጎቶች ጎልተው ወጡ፡፡ የኅብረተሰቡን ችግር ለማዳመጥ ጆሮ የነበረው መሪ አልነበረም፡፡ በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ተቃውሞዎች በየአቅጣጫው መታየት ጀመሩ፡፡ ተቃውሞውን ወደ አንድነትና የተቀናጀ ትግል ያመጣውና ኢትዮጵያን ከአምባገነኑ ሥርዓት ለማላቀቅ ቆርጦ የተነሳው ግን ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) እየተባለ የሚጠራው ድርጅት ነበር፡፡

ይህንን ግፍና መከራ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ቆርጦ የተነሳው ሕወሓት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ግንባር በመፍጠር ኢሕአዴግ ተብሎ የደርግን ግባተ መሬት አሳካ፡፡ ለአሥራ ሰባት ዓመታት የተጨቆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ጮራ ማየት ጀመረ፡፡ አዲስ አየር ተነፈሰ፡፡ ዜጎች በሠላም ወጥተው በሰላም መግባት ጀመሩ፡፡ የዜጎች ዴሞክራሲዊ እና ሰብዓዊ መብቶች ተረጋገጡ፡፡ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ባጎናጸፈው ድል ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው የመናገርና የፈለጉትን ሃይማኖት የመከተል መብቶች ተረጋገጡላቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ጭቆናን መሸከም የማይችል ሞጋች ኅብረተሰብ፣ መጠነ ሰፊ የተማረና አምራች ኃይል ተፈጠረ፡፡

የጥንቱ ትውልድ አክሱምንና ላሊበላን እንዳቆመ ሁሉ ዛሬም ዓባይ በሕዝቡ ሙሉ ድጋፍ እንዲገደብ እየተንቀሳቀሰ በመሆኑ ኢሕአዴግን ይበል የሚያሰኝ ሥራ ነው፡፡ የገጠሩን አርሶ አደር ተጠቃሚ በማድረግና የእርሻውን ክፍለ ኢኮኖሚ በማዘመን ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር የሚደረገው ጥረት በጣም የሚበረታታ ነው፡፡

ይኼ በእንዲህ እንዳለ ኢሕአዴግ በ25 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ብዙ ያልሠራቸው የቤት ሥራዎች እንዳሉት ግን መካድ አይቻልም፡፡ ዛሬ ላይ የሕዝብ ጥያቄ ሆነው በየአካባቢውና በየአደባባዩ የምንሰማቸው ጉዳዮች ኢሕአዴግ ያላሳካቸው ተብለው በራሱ ልሳን ሳይቀር የሚነሱት ጉዳዮች ዛሬ ለአገራችን ትልቅ ፈተና ሆነዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች እዚህ ላይ መጥቀሱ አንባቢያንን ማሰልቸት ሊሆንብኝ ይችላል ብዬ በመገመቴ አልፌዋለሁ፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች የተነሳ ዛሬ ዛሬ በአገራችን ውስጥ ተቃውሞዎችና ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡ እነዚህ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ከውስጣዊ ሹክሹክታ አልፈው ወደ አደባባይ መውጣት ጀምረዋል፡፡ ፒተር በርገርና ሪቻርድ ጆን ኒሃውስ የተባሉ ሁለት የፖለቲካ ምሁራን ‹‹To Empower People››  በሚለው መጽሐፋቸው ‹‹የሕዝብ ሥልጣን ሲመነምንና ማዕከላዊ ሥልጣን ሲያብጥ መሠረታዊ የሐሳብ ገበያው ይፈርሳል፡፡ በመጨረሻም ሕዝብ ጥያቄውን አንግቦ አደባባይ ይሠለፋል፤›› ይላሉ፡፡

በአገራችን ውስጥ አሁን ላይ እየሆነ ያለው እንግዲህ ይህ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ማበጥ እየታየ ነው (በእነሱ አጠራር ኪራይ ሰብሳቢ አመራር ተፈጥሯል)፡፡ ሕዝቡም ከሹክሹክታና  ከአሉባልታ አልፎ ጥያቄውን ወደ አደባባይ ይዞ ወጥቷል፡፡ እንግዲህ ጨዋታው እዚህ ላይ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መስዋዕትነት የከፈለበት ወቅት ከተሻረና ከችግርና ከኢዴሞክራሲያዊ አሠራሮች ራሱን ማሻሻል ካልቻለ ውጤቱ የዜሮ ድምር ጨዋታ ይሆናል፡፡ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ የሕዝብን ጥያቄ በአፋጣኝ የመመለስ ውስንነት እየታየበት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ የሐሳብ ገበያው ፈርሶ ለአገርም ለዜጋም አደጋ የሆነ ጉዳዮች ብቅብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ መንግሥት የሐሳብ ልዩነትን ሙሉ በሙሉ እንደ ተፈጥሯዊና የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንቢያ ሁነኛ መሣሪያ አድርጎ መውሰድ አልቻለም፡፡

በአገሪቱ የሚታዩ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳዩዋቸው ያሉ ተገቢ ያልሆኑ ሥነ ምግባሮችን በፍቅር ተቀብሎ በፍቅር ማሸነፍ አልቻለም፡፡ እንዲያውም ልማታዊ፣ ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ አክራሪ፣ ወዘተ እያለ የማግለልና ነገሩን የባሰ እያጋነነው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለመሪውም ሆነ ለአገር ትልቅ ኪሳራ አለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ዕርምጃ በአሜሪካ ታሪክ ሳይቀር የከፋ ጉዳት አስከትሎ አልፏል፡፡ በጆማካርቲ (ሪፕብሊካን) ዘመን ዜጎችን በኮሙኒስትነት በመጠርጠርና በአሜሪካ ጥቅም ተፃራሪነት፣ በብሔራዊ ስሜት ጉድለት በመወንጀል መጎተትና እስር ቤት ውስጥ ማጎር የተለመደ ነበር፡፡ ይኼ ድርጊት በአሜሪካ ታሪክ ክፉኛ መስዋትነት አስከፍሏል፡፡ የአሜሪካ ሕዝብና መንግሥትም ከንዲህ ዓይነት አስከፊ ድርጊቶችና ዕርምጃዎች ትልቅ ትምህርት ወስዷል፡፡

የእኛም አገር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ባይባልም በዚህ ስሜት ውስጥ ነው ያለችው፡፡ እነዚህ የተለያዩ ምድብና ስያሜ የምንሰጣቸው ዜጎችም ሆኑ ቡድኖች ምንም እንኳን ድርጊታቸው ለአገር በጎና ጥሩ ነው ባይባልም፣ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲወጡ ፍቅር በመስጠትና በማቅረብ ማሸነፍ አለብን፡፡ መንግሥት የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር በማስፋት ጥልን ሊያሰፉ የሚችሉ ፍረጃዎችንና ምድቦችን መተው አለበት፡፡ ትውልድ ያልፋል፣ ታሪክ ግን አያልፍም፡፡ በዚህ በማያልፍ ታሪክ ደግሞ የማይፋቅ ታሪክ ሠርቶ ማለፍ ጀግንነትና ከዚህ ትውልድና መንግሥት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ውስብስብ የፖለቲካ ችግር ያለበትን ዓባይ እንደደፈርን ሁሉ ልዩነቶች በነፃነት እንዲስተናገዱ ቁርጠኛ መሆን አለብን፡፡ በተለይ መንግሥት በዚህ ላይ ትልቅ ሥራ ሊሠራ ይገባዋል፡፡  

አገራችን አሁን ካለችበት የፖለቲካ አዙሪት ልትወጣ የምትችለው የመንግሥት ቁርጠኛ አቋም ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ጠያቂ ትውልድ እንዳፈራ ሁሉ የቀረፀው ፖሊሲና ስትራቴጂም ፍሬ ማፍራት አለበት፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በፈቀደው ደረጃ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው እንዲከበር ከፍተኛ ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ያኔ ልዩነቶች ይጠባሉ፡፡ ብሔራዊ መግባባቶች ይፈጠራሉ፡፡ ኢትዮጵያም ወደቀደመ ስመ ገናናነቷ ትመለሳለች፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...