Sunday, May 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የተሿሚዎች ብቃት አሳማኝ ይሁን!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ለፌዴራል መንግሥት ካቢኔ አባልነት የሚቀርቡለትን ተሿሚዎች በቅርቡ ያፀድቃል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ እነዚህ አዳዲስ ተሿሚዎችም ሆኑ በሥራ ላይ ያሉት ለሹመት ሲታጩ በትምህርት ዝግጅታቸው የተመሰከረላቸው፣ የዳበረ የሥራ ልምድና ከፍተኛ የሆነ የሥነ ምግባር ባለቤት እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም የፓርቲ አባልነትና ታማኝነትን ያስቀድም የነበረው አሠራር ያሳደረው ተፅዕኖ ያደረሰው ጉዳት ይታወቃል፡፡ አገራቸውን ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑና ለሹመት የሚመጥን ብቃት ያላቸው ዜጎች እየተገፉ፣ ጥቅማቸውን ብቻ የሚያነፈንፉ አስመሳዮችና አድርባዮች መድረኩን ሲቆጣጠሩት ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፓርቲ አባልነት ውጪ ያሉ ዜጎችም ለኃላፊነት እንደሚታጩ በመንግሥት በይፋ በመነገሩ፣ ከወዲሁ ብቃት ያላቸው ዜጎች ይፈለጉ፡፡ የተሿሚዎችም ብቃት በሕዝቡ ዘንድ አመኔታ ያግኝ፡፡

በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልል ለተለያዩ ኃላፊነቶች የሚሾሙ ሰዎች ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ ከራስ ጥቅም ይልቅ አገርን የሚያስቀድሙ፣ የተሻለ የትምህርት ዝግጅት፣ የዳበረ የሥራ ልምድ፣ ምሥጉን የሆነ ሥነ ምግባርና በኅብረተሰቡ ውስጥ ከበሬታን ያተረፉ መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉት በሙስና የተዘፈቁ፣ ግዴለሾች፣ ሕዝብን የሚያማርሩ፣ በሥልጣን የሚባልጉ፣ ከወሬ በስተቀር ችሎታ የሌላቸው፣ አድሎአዊና የተበላሸ ሰብዕና ባለቤቶች ናቸው፡፡ በእነሱ የተነሳ በሚገባ የተዘጋጁ ዕቅዶች ግባቸውን አይመቱም፡፡ ከተጨባጭ ሁኔታዎች የሚነሱ ዕቅዶችን ማዘጋጀት አይችሉም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ይደፈጥጣሉ፡፡ ሕገወጥነት የበላይነት እንዲይዝ ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ በየቦታው ጩኸትና ምሬት ይሰማል፡፡ ተቃውሞ ይጋጋላል፡፡ ግጭት ይቀሰቀሳል፡፡ ሰዎች ይሞታሉ፡፡ ለጉዳት ይዳረጋሉ፡፡ የደሃ አገር ንብረት ይወድማል፡፡ የሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ይናጋል፡፡ የአገር ህልውና አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ተፈጥሮ ለነበረው ቀውስ በመንስዔነት ሲጠቀሱ የነበሩት የመልካም አስተዳደር መጥፋት፣ የፍትሕ መጓደል፣ የሙስና መስፋፋት፣ የሕገወጥነት መብዛት፣ የፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራት መበራከት፣ ወዘተ. ብቃት በሌላቸው ተሿሚዎች ምክንያት ነው ቢባል የተጋነነ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስብሰባ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በተመለከተ የተሠራው ጥናት እንደጠቆመው፣ የሕዝቡን ምሬት ያበዙ ጉዳዮች በየደረጃው ባሉ ሹማምንት ይፈጸሙ የነበሩ አጥፊ ተግባራት ናቸው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሕዝብና የመንግሥት መሆኑ የተረጋገጠለት መሬት የደላሎችና የአጋሮቻቸው የመንግሥት ሹማምንት መጫወቻ የሆነው ተጠያቂነት በመጥፋቱ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ተጠያቂነትም እንዳለ ተደንግጎ ሳለ፣ ብቃት አልባ ሹማምንት ግን የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንደፈለጉ ሲጫወቱበት ነበር፡፡ ሕዝብ ከመንግሥት ጋር እንዲቆራረጥ ያደረጉ ተሿሚዎች ተወግደው፣ የሕዝብ ኃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሾሙ መደረግ አለበት ሲባል ያጋጠሙ ችግሮችን ዋቢ በማድረግ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላለፉት 15 ዓመታት ያደረገውን ጉዞ በመገምገም ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› እንደሚያደርግ ቃል ከገባ ሰነባብቷል፡፡ ምንም እንኳ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ባገረሸው ሁከት ምክንያት በሰው ሕይወትና በአገር ሀብት ላይ በደረሰው ጥፋት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅም፣ የመታደሱና ለውጥ የማምጣቱ እንቅስቃሴ እንደማይገታ ተስፋ ይደረጋል፡፡ አገሪቱ ሰላም እንድትሆን፣ የሕዝቡ ደኅንነት እንዲጠበቅና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው መሠረት እንዲጣል ሲፈለግ፣ ተወደደም ተጠላም የአገሪቱ ጉዳይ የሚያገባቸው ዜጎች አገሪቱ ከገባችበት ችግር ውስጥ እንድትወጣ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባቸው፡፡ ከውጥረት ወደ ተሻለ ሰላማዊና አሳታፊ ምኅዳር መመለስ የሚቻለው ለአገራቸው አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ወገኖችም ለሹመት ሲታጩ ነው፡፡ ለሹመት የሚታጩ ዜጎችም ከምንም ነገር በላይ ታሳቢ ማድረግ ያለባቸው መተኪያ የሌላትን አገራቸውንና ወገናቸውን ነው፡፡ በመሆኑም ዳር ሆኖ ታዛቢ ከመሆን ይልቅ መሀል ገብቶ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ማመንታት የለባቸውም፡፡ ለአገር ህልውናም ይበጃል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ አዲሱን ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ቃል በገቡት መሠረት ለአገር የሚጠቅሙ ብቁ ዜጎችን በፋኖስ ጭምር መፈለግ አለባቸው፡፡ በሚኒስትርነት ቦታ የሚታጩ ሹማምንት ከፖለቲካ ተሿሚነት ባልተናነሰ በሕዝብ ዘንድ አመኔታ ያተረፉ ባለሙያዎችም መሆን አለባቸው፡፡ አገራቸውን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎችም ሆነ በአገር ውስጥ የሚወክሉ በመሆናቸው ለዘመኑ አስተሳሰብ የሚመጥኑ፣ ከዓለምና ከአገር ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ጠቃሚ የፖሊሲ ሐሳቦችን የሚያመነጩ፣ ስትራቴጂዎችን የሚቀርፁ፣ በተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ መወሰን የሚችሉ፣ ስህተትን በሌላ ስህተት የማያርሙ፣ ሙስናን በተግባር የሚፀየፉ፣ በመርህ የሚያምኑ፣ የማይዋሹ፣ ከአልኮልና ከመሳሰሉ ሱሶች የፀዱ፣ ራሳቸውን አስከብረው አገር የሚያስከብሩ፣ ወዘተ. ሊሆኑ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ በራስ የመተማመን መንፈሳቸው የዳበረና ለማንኛውም ዓይነት መረጃ ቅርብ የሆኑ ንቁና ብቁ ተሿሚዎች ናቸው አገሪቷ የሚያስፈልጓት፡፡ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሚባሉትን መርሆዎች ጠንቅቀው የተረዱ ተሿሚዎች ናቸው አገሪቷን ከቀውስ  ወስጥ አውጥተው ወደሚፈለገው ከፍታ የሚያደርሱት፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን ነው በሻማ ብርሃን ጭምር መፈለግ የሚገባው፡፡

በአገር ላይ የሚያላግጡ፣ ሕዝብን የሚያስለቅሱ፣ ከግልና ከቡድን ጥቅማቸው ውጪ ምንም የማይታያቸው፣ በዘረፋ አገር እያደኸዩ ራሳቸውንና ቢጤዎቻቸውን የሚያከብሩ፣ የአገርና የሕዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ሲገባ የሚያደፍጡ፣ ከዕውቀቱም፣ ከልምዱም ሆነ ከሥነ ምግባሩ የሌሉበት ብኩኖች ለአገር አይጠቅሙም፡፡ ኢትዮጵያችን ቀን ከሌሊት እንቅልፍ አጥቶ የሚያገለግላት እንጂ፣ በአድርባይነትና በአስመሳይነት ካባ ውስጥ ተደብቆ የሚቀልድባት ወስላታ አያስፈልጋትም፡፡ ሕዝብ ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡ አገርን ችግር ውስጥ የሚከታትን ዘራፊና ወሬኛም እንዲሁ፡፡ ዘመኑ ሥልጣኔ ጣራ የነካበት እንደመሆኑ፣ ሕዝቡም በዚያ የውኃ ልክ መጠን ብቃት ያላቸው ተሿሚዎች እንዲኖሩ ይፈልጋል፡፡ ሕዝብን ማሳመን የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ በከፍተኛ ችሎታና በሥነ ምግባር የሚመሩትን ተሿሚዎች ሲጠብቅ፣ መንግሥት ደግሞ ለሕዝብ ፍላጎት ተገዢ በመሆን ኃላፊነቱን ይወጣ፡፡ የሕዝብ እርካታና አመኔታ የሚገኘው በዚህ አጋጣሚ ጭምር ነው፡፡ በመሆኑም የተሿሚዎች ብቃት አሳማኝ ይሁን!           

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...