አነጋጋሪ አጀንዳዎችን በማንሳት የሚዲያውንና የማኅበረሰቡን ቀልብ በመሳብ የሚታወቁት አወዛጋቢው የአሜሪካ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ፣ ሰሞኑን ያነጣጠሩት በአሜሪካ በሚገኙ ሚዲያዎችና ቅድመ ምርጫን በሚተነብዩ ተቋማት ላይ ነው፡፡
የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሊከናወን ሁለት ሳምንት በቀረበት በአሁኑ ወቅት የምረጡኝ ቅስቀሳ እያካሄዱ የሚገኙት ትራምፕ፣ በሴንት ኦገስቲንና በፍሎሪዳ በነበራቸው ዘመቻ፣ ሚዲያውና የቅድመ ምርጫ ትንበያ ተቋማት ዘራፊዎችና እምነተ ቢሶች ናቸው ብለዋል፡፡
ሁለቱም ተቋማት በተበለሻሸ የአሠራር ሥርዓት ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው ያሉት ትራምፕ፣ ሚዲያውም ሆነ የቅድመ ምርጫ ትንበያ ተቋማት የትራምፕን ዕጩነት እያጣጣሉ ናቸው ብለዋል፡፡ የቅድመ ምርጫ ትንበያ ተቋማት ለዴሞክራቷ ክሊንተን የተጭበረበረ የአብላጫ ድምፅ በመስጠት የመራጩን ቀልብ ለመሳብ እየሠሩ ነው ሲሉም ኮንነዋል፡፡
ዴሞክራቶቹ በቅድመ ምርጫ ትንበያ ከሪፐብሊካኖቹ የተሻለ ድምፅ አገኙ የሚባለው የትራምፕ አጀንዳ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመፍጠር እንደሆነ፣ ሪፐብሊካኑ በትዊተራቸው ማስፈራቸውን ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡
‹‹እናሸንፋለን›› ያሉት ትራምፕ፣ ከሐምሌ 2016 ጀምሮ በገለልተኛ አካል የተሠሩ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች በክሊንተን ውጤት ላይ ለውጥ እንዳላሳዩና ባሉበት እንደቀጠሉ ተናግረዋል፡፡
ትራምፕ በቅድመ ምርጫ ትንበያ ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን በሚዲያው ላይም የሰላ ነቀፋ ሰንዝረዋል፡፡ ‹‹ፕሬሱ የዘራፊዎችና የእምነተ ቢሶች ስብስብ ነው፤›› በማለት ሚዲያዎች ‹‹እምነተ ቢስ›› ከሚሏቸው ሒላሪ ክሊንተን በባሰ በሙስና የተዘፈቁ ናቸው ብለዋል፡፡
ሚዲያው የራሱን የበላይነትና ፍላጐት የሚያስጠብቁ ሐሳቦችን ብቻ የሚያንሸራሽር፣ የሚፈልጋቸውን ምሁራን ሐሳቦች ብቻ የሚቀበል፣ የሚሞግቱትን ደግሞ የማያስተናግድና ወገንተኛም ነው ብለዋል፡፡
ሚዲያውን በደፈናው ያብጠለጠሉት ትራምፕ ሚዲያውን ለግል ዓላማቸው ማስፈጸሚያ የሚያጭበረብሩትን በማስጠንቀቅ፣ ‹‹ሚዲያው የሰዎችን አቅም፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚና በአጠቃላይም አገሪቱን በበላይነት ተቆጣጥሯል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹እኔ ትልልቅ ጉዳዮች ኖረውኝ ያልተዘገቡበት ጊዜ አለ፤›› ሲሉም ሚዲያው ፍትሐዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህንን በተናገሩበት ዕለትም የራሳቸውን የሚዲያ ኢንተርፕራይዝ አቋቁመዋል፡፡ በፌስቡክ የሚታገዘው ሚዲያም ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ትራምፕ የሚኖራቸውን የምረጡኝ ዘመቻ ምሽት ላይ በቀጥታ የሚያስተላልፍ ነው ተብሏል፡፡ ‹‹ትራምፕ ቲቪ›› በመባል እየተሠራጨ በሚገኘው ፕሮግራምም የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ማኔጀር ኬልያኒ ኮንዌይ ቃለ ምልልስ፣ ትራምፕን የተመለከቱ ዜናዎች፣ በማስታወቂያ የታጀቡ የትራምፕ እንቅስቃሴዎች እየተላለፉበት ነው፡፡
በሚዲያው ላይ እምነት ማጣታቸውን ያስታወቁት ትራምፕ፣ ሚዲያው እሳቸውን ለማስጠላት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሲሉ በየምሽቱ በፌስቡክ የሚተላለፈውን የምሽት ቀጥታ ሥርጭት የቲቪ ፕሮግራም ጀምረዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፣ ሚዲያዎች በእሳቸው ላይ ሸፍጥ እየሠሩ ነው፡፡ ሴቶችን አማለዋል በማለት የሚነዙት ዜናም ያልተገባ ነው፡፡ በተለይ ኒውዮርክ ታይምስ የሁለት ሴቶችን ታሪክ ይዞ የወጣው ዘገባ እሳቸውን ሆን ብሎ ለማንቋሸሽ የተቀነባበረ ሸፍጥ ነው ብለዋል፡፡
በኒውዮርክ ታይምስ ትልቁ ባለድርሻ ካርሎስ ስሊም ሜክሲኳዊ መሆኑን በመግለጽም፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ከሒላሪ ክሊንተንና ከክሊንተን ኢኒሼቲቭ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኒውዮርክ ታይምስ ሪፖርተሮች ጋዜጠኞች አይደሉም፡፡ የካርሎስ ስሊምና የሒላሪ ክሊንተን የቅስቀሳ አጋሮች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
ትራምፕ የሴት ነጋዴዋን ጄሲካ ሊድስ በአንድ አውሮፕላን በተሳፈሩበት ወቅት አማልለዋል ተብሎ የተዘገበውንም፣ ‹‹እመኑኝ እሷ እኮ የምታምር አይደለችም፡፡ የእኔ የመጀመሪያ ምርጫም አይደለችም፡፡ ዘገባው ላይ እንደተጻፈው አላደረግኩም፤›› ብለው ከሁለት ሳምንት በፊት ተናግረው ነበር፡፡
ትራምፕ ሴቶችን አላማለልኩም ይበሉ እንጂ፣ የፊልም ተዋናይዋ ጀሲካ ድራክን ጨምሮ 11 ያህል ሴቶች በትራምፕ መጐንተላቸውን ተናግረዋል፡፡
ሚዲያዎች ሆን ብለው የተቀነባበረ የማጥላላት ዘመቻ እንደጀመሩባቸው የሚናገሩት ትራምፕ፣ ሰዎችን ያላግባብ የሚያብጠለጥሉ ሚዲያዎችን ለመቅጣት ዕቅድ እንዳላቸውም መቀመጫውን ማያሚ ላደረገው ደብሊው ኤፍኦአር ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል፡፡
ብሪታንያ የውሸት መረጃ ያተመ ወይም በብሮድካስት ሚዲያው ያሠራጨ ጣቢያን ለመቅጣት ያላትን ዓይነት ሕግ እንደሚቀርፁም አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በኢንግላንድ አንድ ሚዲያ ውሸት ካሠራጨ ሰዎች ሊከሱት ይችላሉ፡፡ የእኛ ፕሬስ ግን የፈለገውን ይናገራል፣ እየተናገረም ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡
የፕሬስ ነፃነት አቀንቃኝ ነኝ የሚሉት ትራምፕ የአገራቸው ሚዲያዎች ሆን ብለው ሰዎችን ለመጉዳት ስህተት እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በራሴ ስለደረሰ ብዬ አይደለም የምናገረው፡፡ ማንኛውንም ሰው ወክዬ ነው፡፡ እንደማምነው በሚዲያው ያላግባብ የሚጐዳ ሰው ሚዲያውን መክሰስ የሚችልበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰዎች በሚዲያ የውሸት ዘገባ ከተሠራጨባቸው መክሰስ የሚችሉበት አሠራር ቢኖርም፣ ትራምፕ ግን በአገሪቱ የላላ አሠራር እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ሚዲያዎች ለሠሩት ስህተትና ስም ማጥፋት ለሕዝቡ በሚደርስ መንገድ ይቅርታ እንዲጠይቁ አያስገድድም ሲሉም መንግሥትን ይወቅሳሉ፡፡
በስደተኞችና በሙስሊሞች ጉዳይ ዓለምን ላለፈው አንድ ዓመት ያነጋገሩት ትራምፕ፣ በተለያዩ ማዲያዎች በነበራቸው ሽፋን በአብዛኛው በአሉታዊ ጐናቸው ሲተቹ ከርመዋል፡፡ የተቀናቃኛቸው ሒላሪ ክሊንተን የኢሜይል ሸፍጥ የአንድ ሰሞን ወግ ሆኖ ያለፈ ሲሆን፣ የትራምፕ ጉዳይ ግን አሁንም የሚዲያው መነጋገሪያ ነው፡፡ እሳቸው እንደሚሉትም፣ ሚዲያው ወገንተኛ ሆኖ እሳቸውን የሚያጥላላ ዘገባ እያሠራጨ ነው፡፡ ሴቶችን ያማልሉ ነበር መባል ከጀመረበት አንድ ወር ወዲህ እንኳን 11 ሴቶች በየሚዲያው እየቀረቡ በትራምፕ መጐንተላቸውን ተናግረዋል፡፡ አሜሪካ ጥቅምት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ፕሬዚዳንቷን የምትመርጥ ሲሆን፣ ቢቢሲ ጥቅምት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ባሰፈረው የቅድመ ምርጫ ትንበያ መሠረት ሒላሪ ክሊንተን 50 በመቶ፣ ትራምፕ ደግሞ 44 በመቶ ላይ ይገኛሉ፡፡ ትራምፕ ግን እነዚህን ትንበያዎች አይቀበሏቸውም፡፡ ተንባዮቹም ነፃና ፍትሐዊ ናቸው ብለው አያምኑም፡፡ እሳቸውን ለማጣጣል ሲሉም ትንበያውን እንደሚያጭበረብሩ ከወራት በፊት ጀምሮ ሲናገሩ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በአሜሪካ አሁን ያለው ሥርዓት ደካማ፣ ሙሰኛና የተፍረከረከ በመሆኑ እሱን ለማስተካከልና ጠንካራ አሜሪካን ለመፍጠር እንደሚሠሩ፣ በዚህም አሸናፊ እንደሚሆኑ እየገለጹ ነው፡፡ ምርጫውም ትክክለኛና ያልተጭበረበረ የሚሆነው እሳቸው ሲመረጡ ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው፡፡