Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልድምፃውያኑ በኮክ ስቱዲዮ

ድምፃውያኑ በኮክ ስቱዲዮ

ቀን:

ኮክ ስቱዲዮ በኮካ ኮላ የሚዘጋጅና የተለያዩ አገሮች ሙዚቀኞች የሚጣመሩበት መድረክ ነው፡፡ ይህ ለዓመታት በበርካታ አገሮች የተከናወነ ሲሆን፣ ዘንድሮ ኢትዮጵያም ተቀላቅላለች፡፡ ኮክ ስቱዲዮ ሙዚቀኞችን በአንድ ስቱዲዮ በማጣመር የየአገራችውን ሙዚቃ እንዲያቀነቅኑ እንዲሁም እርስ በርስም ልምድ እንዲለዋወጡ ዕድሉን ይሰጣል፡፡ ዝግጅቱ በአህጉረ አፍሪካ ኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ በሚል መጠሪያ የሚካሄድ ሲሆን፣ አሁን አራተኛ ዙሩን ይዟል፡፡

ኢትዮጵያንና ሌሎችም የአፍሪካ አገሮችን አካቶ ኬንያ፣ ናይሮቢ ውስጥ ላለፉት ጥቂት ሳምንታት በተቀረፀው የኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ የሙዚቀኞች ጥምረት፣ ኢትዮጵያውያኑ ልጅ ሚካኤል፣ ቤቲ ጂ፣ ኃይሌ ሩትስ፣ ሔኖክ መሓሪና ዳዊት ጽጌ ተሳትፈዋል፡፡ ድምፃውያኑ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ዘፋኞች ጋር የተጣመሩባቸው ኤፒሶዶች (ክፍሎች) ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሣይኛ፣ በስዋሂሊና ፖርቹጊስ ቋንቋዎች ይሰራጫል፡፡

‹‹ዛሬ ይሁን ነገ›› በተሰኘው የመጀመርያ አልበሙ ዕውቅናን ያተረፈው ልጅ ሚካኤል፣ ከታንዛንያውያኑ ያሞቶ ባንድ ሙዚቀኞች ጋር በጥምረት ሠርቷል፡፡ በተጨማሪም ከአሜሪካዊው የግራሚ አዋርድ አሸናፊ ትሬይ ሶንግስ ጋር ተጣምሯል፡፡ የአርኤንድቢና ሂፕ ሃፕ ድምፃዊው ትሬይ ሶንግስ ከኬንያ ከኒያሽንኪ፣ ከታንዛኒያ ቨኔሳ ምዲ፣ ከዩጋንዳ ረማና ሙኩላ፣ ከሞዛምቢክ ነይማ፣ ከኮንጎ ስንጌ ቢናውድ፣ ከናይጄሪያ ፓቶራንኪንድ እና ከጋና ስቶንቦይ ጋርም አቀንቅኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ልጅ ሚካኤል ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የኮክ ስቱዲዮ ቆይታው ብዙ አዳዲስ ነገሮችን የቀሰመበት ነው፡፡ ‹‹በስቱዲዮ ሥራ ከሰዓት አጠቃቀም ጀምሮ ብዙ ነገሮች አውቄበታለሁ፡፡ ሙዚቃው ይሠራ የነበረው በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥራት ነበር፤›› ሲል ቆይታውን ያስታውሳል፡፡ ከያሞቶ ባንድ ጋር ሲጣመር ከሱ ዘፈኖች ‹‹እሹሩሩ›› ከባንዱ ሥራዎች መካከል ደግሞ ‹‹ሴጌሬ›› የተሰኘውን ሙዚቃ ተጫውተዋል፡፡ በስዋሂሊ ቋንቋ የተዜመው የያምቶ ባንድ ዘፈን ከበድ ቢለውም የራሱን ዘፈን ‹‹መከታሽ›› ግጥም ከነሱ ዜማ እያቀላቀለ ዘፍኗል፡፡

እሱና ሌሎቹም ድምፃውያን ከትሬይ ሶንግስ ጋር በሚሠሩበት ወቅት በእንግሊዝኛ ራፕ ማድረግ የመጀመርያ አማራጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ሙዚቃው እንደ ፍላጎታቸው ባለመሆኑ እሱና ሌሎቹም ድምፃውያን በየአገራቸው ቋንቋ ራፕ ለማድረግ ተስማሙ፡፡ ‹‹ትሬይስ ሶንግ ትልቅ ድምፃዊ እንደመሆኑ ተደማጭነቱም ከፍተኛ ነው፡፡ መጀመርያ በእንግሊዝኛ ራፕ እያደረግን ነበር፡፡ ከዛ ግን እኔ በአማርኛ ሌሎቹም ድምፃውያን በየቋንቋቸው ለመሥራት ወሰንን፡፡ በየቋንቋችን እየዘፈንን የተሠራው ሙዚቃ ቆንጆ ስለነበር ሁሉም ድምፃውያን ደስተኛ ሆነዋል፤›› ይላል፡፡ በየቋንቋቸው መዝፈናቸው የባህል ልውውጡን አጉልቶታል፡፡

የኮክ ስቱዲዮ መነሻ ጽንሰ ሐሳብ አገሮችን በሙዚቃና በባህል ማስተሳሰር ነው፡፡ ኮክ ስቱዲዮ አፍሪካም የአህጉሪቷ ድምፃውያን የባህል ልውውጥ በማድረግ እንዲተሳሰሩ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡ የአፍሪካን ድምፃውያን ለማዋሃድ እንደ ኮራ ያሉ አህጉራዊ የሙዚቃ ውድድሮች ጠቀሜታ እንዳላቸው የሙዚቃው ባለሙያዎች ያምናሉ፡፡ ሆኖም ግን አፍሪካውያን ሙዚቀኞች የሚጣመሩባቸው ፌስቲቫሎች ወይም ሌሎች ሙዚቃ ነክ መርሐ ግብሮች ውስን ናቸው፡፡

በተያያዥም የአንድ አፍሪካ አገር ሙዚቃ በተቀረው አህጉር ያለውን ተደማጭነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በበርካታ የአፍሪካ አገሮች የሌሎች አገሮች ድምፃውያንን ሥራዎች የማድመጥ ነገር ይታያል፡፡ የምዕራብ አፍሪካን ሙዚቃ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተደማጭነት ግን አናሳ ነው፡፡ እንደ ኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ ያለ መድረክ የሙዚቀኞች ትስስር ከመፍጠር ባሻገር፣ የየአገሮቹን ሙዚቃ ተደማጭነት ለመጨመር ሊያግዝም ይችላል፡፡

‹‹አብረውን የነበሩት ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸው በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ይደመጡላቸዋል፡፡ የእኛን ሙዘቃ ግን ያን ያህል አያውቁትም፡፡ ከነዚህ ሙዚቀኞች ጋር መሥራቱ ተደማጭነታችንን ይጨምረዋል፤›› ይላል ድምፃዊው፡፡ እንደ ሙላቱ አስታጥቄና መሐሙድ አህመድ ያሉ አንጋፋ ድምፃውያን በዓለም አቀፍ መድረክ ሰፊ ተቀባይነት ቢያገኙም፣  በተመሳሳይ ደረጃ የሚጠቀሱ ወጣት ዘፋኞች ጥቂት ናቸው፡፡

ልጅ ሚካኤል እንደሚለው፣ ድምፃውያን እንዲሁም ሌሎችም የሙዚቃው ዘርፍ ባለሙያዎች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በዓለም መድረክ የሚታወቁ ኢትዮጵያውያን ድምፃውያን ቁጥር የሚጨምርበትና የአገሪቱ ሙዚቃ ተወዳዳሪ የሚሆንበት መንገድ መፈጠር አለበት፡፡ ‹‹ሁላችንም ከባድ የቤት ሥራ አለብን፡፡ ጊዜው የውድድር ስለሆነ ሁሉም ሙዚቀኛ ኃላፊነቱን ወስዶ መጠንከር አለበት፤›› ይላል፡፡

ቤቲ ጂም ተመሳሳይ ሐሳብ አላት፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ሥርጭት ለማስፋት የገንዘብ አቅም ያላቸው ተቋሞች ርብርብ ያስፈልጋል ትላለች፡፡ ‹‹ዘፋኙ ብቻውን ሲሮጥ ብዙም ርቆ አይሄድም፡፡ የሙዚቀኛው ጥረት እንዳለ ሆኖ አቅም ያላቸው ተቋሞች ወደ ዘርፉ ገብተው ብዙ ማገዝ ይችላሉ፤›› ስትል ትናገራለች፡፡

በድምፃዊቷ ገለጻ፣ ከዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች ጋር መወዳደር የሚችሉ ኢትዮጵያውያን ድምፃውያን ብዙ ቢሆኑም፣ የበጀት እጥረት ይፈታተናቸዋል፡፡ እንደ ኮክ ስቱዲዮ ያሉና ሙዚቃ ለመሥራት ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚችሉ ተቋሞች ደግሞ ክፍተቱን ይሸፍናሉ፡፡

በኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ ቆይታዋ እንደ ድምፃዊ ካገኘችው ጥቅም ባሻገር ለአገሪቱ ሙዚቃም አወንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ታምናለች፡፡ ‹‹በቆይታዬ ብዙ ተምሬያለሁ፡፡ ከተለያየ አገር ከተውጣጡ ድምፃውያን ጋር መሥራት ቀላል አይደለም፤›› ትላለች፡፡ ቤቲ ጂ በናይሮቢ የአንድ ሳምንት ቆይታዋ ከሙዚቃ ጎን ለጎን የባህል ልውውጥ ማድረጓንም ትናገራለች፡፡

ስቱዲዮ ውስጥ የተጣመረችው ከካሜሩናውያኑ ኤክስ – ማሌያ ባንድ ጋር ነበር፡፡ ‹‹ማነው ፍፁም›› ከተሰኘው አልበሟ ‹‹የዘንባባ ቀለበት›› የሚለውን ዘፈን ባንዱ ሲያቀነቅን፣ እሷ ደግሞ የነሱን ‹‹ደምባዬ›› የተሰኘ ዘፈን ተጫውታለች፡፡ ፈረንሣይኛ ተናጋሪ መሆኗ ሙዚቃቸውን እንድትረዳ ቢያግዛትም፣ የአገራቸውን ቋንቋ እያስረዷት ሠርታለች፡፡

‹‹ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ነው፤›› እንዲሉ የቋንቋ ልዩነት ሙዚቀኞቹ እንዳይግባቡ አላደረገም፡፡ በተቃራኒው የየአገራቸውን ሙዚቃ በመጫወትና አንዳቸው የሌላውን ዘፈን በመዝፈን ተጣምረዋል፡፡ ይህንን በቴሌቪዥን በሚተላለፉት የኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ ዝግጅቶች እንዲሁም በኮካ ኮላ ድረ ገጽ ላይ ካሉት ምሥሎችና ቪዲዮዎች መረዳት ይቻላል፡፡

‹‹ኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ እንደ ድምፃዊ ራሴን የመዘንኩበት ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ሙዚቃም በአህጉር ደረጃና በዓለምም የመሰማት ዕድልን ያሳድጋል፤›› ትላለች፡፡ ድምፃውያን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀላቀሉ በር ከፋች መሆኑንም ታክላለች፡፡

የኮካ ኮላ ብራንድ ማናጀር ወ/ሪት ትዕግሥት ጌቱ ለሪፖርተር እንደገለጸችው፣ እስከ ዘንድሮ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ በኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ ባትሳተፍም፣ በዚህ ዓመት መጀመሩ ለአገሪቱ ሙዚቃ የጎላ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

‹‹ዓላማችን አገሮችን በሙዚቃ ማስተሳሰር ነው፡፡ መርሐ ግብሩ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ ታሳቢ የምናደርገው ወጣት ታዳሚዎችን እንደመሆኑ በልዩ ልዩ የሙዚቃ  ሥልት የሚሠሩ ወጣት ድምፃውያን ተካተዋል፤›› ትላለች፡፡ የኢትዮጵያው የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ዘወትር እሑድ በ2 ሰዓት በኢቢኤስ ይተላለፋል፡፡ ዝግጀቱ 11 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ድምፃውያን እርስ በርስና ከዓለም አቀፍ ድምፃውያን ጋር የተጣመሩባቸው ክፍሎች ተካተዋል፡፡

‹‹በብዙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ሙዚቃ ስንጠይቅ ዕውቀቱ ውስን ነው፡፡ ይህን ለመቀየር ኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ አንድ መንገድ ይሆናል፡፡ ሙዚቀኞቹ እርስ በርስ የሚተዋወቁበት፣ የሚማማሩበትና የሚተሳሰሩበትም ነው፤›› ትላለች ወ/ሪት ትዕግሥት፡፡

በኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ ሲዝን አራት የተሳፉት 11 አገሮች ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ፣ አይቮሪኮስት፣ ካሜሩን፣ ኮንጎ፣ ጋናና ሴኔጋል ሲካተቱ የዘንድሮው የመጀመርያቸው ነው፡፡ በዝግጅቱ ሙዚቀኞቹ የየራሳቸውን እንዲሁም የሌሎችንም ዘፈን ያቀርባሉ፡፡ በዕውቅ የሙዚቃ ፕሮዲውሰሮች ፕሮዲውስ የሚደረጉ በጥምረት የሚሠሯቸው ሙዚቃዎችም አሏቸው፡፡

የዘንድሮው ኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ 38 አርቲስቶችን ‹‹ዲስከቨር›› በሚል ስያሜ አካቷል፡፡ በዝግጅቱ ድረ ገጽ እንደተመለከተው፣ ወጣትና አንጋፋ ድምፃውያን የሚጣመሩበት መድረክ መፍጠር የታቀደበት ነው፡፡ ዓላማው በዝግጅቱ በቅርቡ ‹‹790›› የተሰኘ አልበም ከባንዱ መሓሪ ብራዘርስ ጋር የለቀቀው ሔኖክ መሓሪ፣ ከናይጄሪያዊቷ ሲንቲያ ሞርጋን ጋር ሠርቷል፡፡ ‹‹ቺጌ›› በተሰኘው የሬጌ አልበሙ የሚታወቀው  ኃይሌ ሩትስ ከጋናዊው ስቶንቦይ ጋር ተጣምሯል፡፡ ከባላገሩ አይዶል አሸናፊው ዳዊት ጽጌ ጋር አብረው ከሠሩ ድምፃውያን ዋጄን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 

 

 

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...