Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርአቶ ልደቱ አያሌውን ‹‹ባንዳ›› እያስባላቸው ያለው ጉዳይ ምን ይሆን?

አቶ ልደቱ አያሌውን ‹‹ባንዳ›› እያስባላቸው ያለው ጉዳይ ምን ይሆን?

ቀን:

ባሳለፈው ሳምንት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አዘጋጅነት ተዘጋጀ የተባለ አንድ የውይይት መድረክ ስለመካሄዱ ብዙዎቻችን የሰማን ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳን ውይይቱን በቀጥታ በመገናኛ ብዙኃን ለመከታተል ባንታደልም፣ ኢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከውይይቱ ክፍል ያስፈልጋችኋል ያሉትን ቆንጥረው አሰምተውናል፡፡ በእኔ በኩል የውይይቱ ዓላማ እንዲሁም መነሻና መድረሻ ምን እንደሆነ በግልጽ ባይገባኝም፣ ውይይቱ መካሄዱ በራሱ የሚነቀፍ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሁትም የውይይቱን ዓላማ እንደመጠይቅ ይዤ ወይም ይዘቱን ለመዳሰስ ፈልጌ ሳይሆን (ይህን ውይይቱ ላይ የተገኙቱ ሙሉ መረጃ ይኖራቸው ይሆናልና ቢያደርጉት መልካም ነው) በውይይቱ ላይ ጽሑፍ አቅራቢ ከነበሩት አራት ግለሰቦች መካከል አንዱ በሆኑት የኢዴፓ መሥራችና የቀድሞ ሊቀመንበር በነበሩት አቶ ልደቱ አያሌው ሐሳብና በዚሁ ዙሪያ የተሰጡ አስተያየቶችን ላለፉት 11 ዓመታት ከከረምንበት ብዥታ ጋር ማሰላሰል በመፈለጌ ነው፡፡

በቅድሚያ ለአንባቢዎች ማሳወቅ የምፈልገው እኔ አቶ ልደቱን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፖለቲካው መድረክ ከማውቃቸው ውጪ ምንም ዓይነት ግላዊ ግንኙነት የሌለኝ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም የዚች አገር የፖለቲካ ጉዞ እንደሚያሳስበው አንድ ዜጋ ላለፉት 11 ዓመታት በብዙዎች ሲሰነዘሩ በሰማናቸውና በአሁን ወቅትም እየተነሱ ባሉ ሐሳቦች ላይ ብቻ የበኩሌን ለመሰንዘር ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ተነሳሳሁ፡፡ አቶ ልደቱ በምርጫ 1997 ዓ.ም. ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቀባይነት አግኝተው የነበሩ መሪ መሆናቸው በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በቅርበት ስንከታተል የነበርንና አብዛኛው በምርጫው የተሳተፈ ሕዝብም የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡ ይፋ የሆነውን የምርጫ ውጤት ተከትሎ በተፈጠረ የሐሳብ ልዩነት ነገሮች ከመቅጽበት መቀያየራቸውንም እንዲሁ እናስታውሳለን፡፡ ግለሰቡ በወቅቱ የቅንጅቱን መዋሃድና ፓርላማ መግባት በተመለከቱ አከራካሪ ሐሳቦች ላይ አራመዱት በተባለው አቋም በብዙ ሲወገዙ ሰምተናል፡፡ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ትኩሳት እንዴትና ለምን የሚሉ የምክንያታዊነት ጥያቄዎችን ወደ ጎን የገፋ በመሆኑ፣ ሒደቱ በአጠቃላይ ኢሕአዴግ በሠራው ታሪካዊ ስህተት በአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ ያስከተለው የኋልዮሽ ጉዞ እንደተጠበቀ ሆኖ በሒደቱ ተሳታፊ የነበሩ ፖለቲከኞች ለአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ሊያበረክቱ የሚገባቸውን አስተዋጽኦ የገደበና ፖለቲካችን የአሉባልታ ቁራኛ እንዲሆን ያደረገ መሆኑም የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ ታሪካዊ ስህተት ዛሬም ከ11 ዓመታት በኋላም ሲደገም ማየት ደግሞ ህሊናን ያሳምማል፡፡ መቼም ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለፖለቲካ፣ ለዴሞክራሲና ለመሰል ጉዳዮች ያለው አመለካከት በጊዜ ሒደት እንደሚያድግ እንዲሁም በመረጃ መዛባት ለስህተት የተጋለጡ አስተሳሰቦች ውለው ሲያድሩ እየጠሩ እንደሚመጡ እሙን ነው፡፡ ግን እየሆነ ያለው ከዚህ በተቃራኒ ይመስላል፡፡

ወደተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ በቅርቡ በተካሄደው ውይይት አቶ ልደቱ በሁለት ፈርጅ የሚታዩ ሐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ (እኔ በሰማሁት ልክ ማለቴ ነው)፡፡ በአንድ በኩል የኢሕአዴግን ደካማ ጎኖች አንድ ሁለት ብለው ቆጥረው ሲያስቀምጡ፣ በሌላ በኩል ጥንካሬዎቹ ያሉዋቸውንም ከመዘርዘር አልታቀቡም፡፡ ይህን ንግግራቸውን ተከትሎም በርካታ ትችቶች በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ወጥተው ተመልክቻለሁ፡፡ ትችቶቹም እንደ 1997ቱ ሁሉ ግለሰቡን በባንዳነት፣ በአድርባይነትና በውሸታምነት የሚፈርጁ ሲሆኑ፣ በአብዛኞቹ የትችቶቹ ሰንዛሪዎች ደግሞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት እንታገላለን የሚሉ በባህር ማዶ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሆናቸውን ስመለከት፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አእምሮዬ በጥያቄዎች ሊሞላ ግድ ሆነ፡፡ ማንኛውም ምክንያታዊና ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው ሰው በዚህ ወቅት ለመሆኑ የግለሰቡ ስህተት ምን ይሆን? ተሳስተውስ ቢሆን የተሳሳቱበትን ሐሳብ ከመሞገት ይልቅ እነዚህ ከምዕራብያውያን የዕውቀትና የዴሞክራሲ ማዕድ ተቋድሰናል የሚሉ ወገኖቻችን ስለምን ስድብን መረጡ? ደግሞስ ኢሕአዴግን የሚቃወሙበት የሐሳብ ነፃነትን አለማክበር ችግር እነሱን እንዴት እንደተጸናወታቸው አለማስተዋላቸው ስለምን ይሆን? እውነት እነሱ ለአገራችን ይበጃል ብለው የሚያራምዱት የትጥቅ ትግል ለእነሱ ትክክል እንደመሰላቸው ሁሉ ሌላው ይበጃል ብሎ የሚያራምደው ሰላማዊ ብሎም ምክንያታዊ የፖለቲካ ትግል ለእርሱ ትክክል እንደሆነ ማሰብ ስለምን ተሳናቸው? ዛሬ ሥልጣን ሳይዙ በስድብና በማሸማቀቅ እየጣሱት ያለውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ነገ ሥልጣን ቢይዙ እንዴት አድርገው ሊያከብሩት ይችላሉ? ወይስ ይልቁኑ ከኢሕአዴግ የባሱ የራሳቸውን ሐሳብ ብቻ የሚጭኑ፣ ሌሎችን የሚያሳድዱ አምባ ገነኖች ይሆኑ ይሆን? የሚሉትን ጥያቄዎች ለማንሳት የሚገደድ ይመስለኛል፡፡

እዚህ ጋ በአቶ ልደቱም ሆነ በማንኛውም ግለሰብ የሚነሱ ሐሳቦችን መንቀፍ ወይም መቃወም ትክክል አይደለም እያልኩ እንዳልሆነ ለአንባቢዎች በትህትና ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን እሳቸው ከሌሎቹ በተለየ የፓርላማ እንግባ ሐሳብ ስላቀረቡ ወይም ኢሕአዴግ ትክክል ሠርቷል ብለው ያመኑበትን ጉዳይ ስለተናገሩ፣ የመቻቻልን (ቢያንስ ቢያንስ በአንድ መድረክ ላይ ቁጭ ብሎ የመነጋገርን) ፖለቲካ ስላራመዱ ባንዳ ናቸው ወይም የኢሕአዴግ ሰላይ ናቸው የሚል ታፔላ መለጠፍ ፍጹም ፀረ ዴሞክራሲያዊ መሆን ነው፡፡ ማንኛውም የአቶ ልደቱ አቋም ትክክል አይደለም ብሎ የሚያስብ ሰው በወቅቱ ፓርላማ መግባት ስህተት መሆኑን በምክንያት ከማስረዳት ባለፈ የጥላቻ፣ የቂምና የስድብ ቃላትን በሕዝቡ ውስጥ መዝራት አገራዊ ኃላፊነት ይሰማኛል ከሚል ሰው የሚጠበቅ አይደለም፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስም ሰው ወደ ስድቡና አሉባልታ የሚሄደው የራሱን ሐሳብ በጨዋ ደንብ በሰዎች ውስጥ የማስረጽ አቅም ሲያንሰው ነው፡፡ ይህ ደግሞ መሸነፍ እንጂ ማሸነፍ ሊሆን አይችልም፡፡ በተመሳሳይ እኔ እስከማውቀው በአሁን ወቅት በውጭ አገሮች ሆነው በማኅበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ፖለቲካን ከሚሰብኩ ግለሰቦች በላይ አቶ ልደቱ ለዚች አገር ዴሞክራሲ ግንባታ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ ኢ ሰብዓዊ በሆነ መልኩ በኢሕአዴግ ካድሬዎች ተሰቃይተዋል፡፡ ሆኖም በዙሪያቸው ከነበሩ ሰዎች የተለየ ሐሳብ ስላነሱ ብቻ ብሎም የሰከነ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ስላራመዱ ብቻ በሕዝብ ዘንድ እንዲጠሉ የሚያደርግ የአሉባልታ ዘመቻ መክፈት በተለይም የ1997 አስተማሪ ክስተትን ካሳለፈፍን 11 ዓመታት በኋላም በዚሁ አዙሪት ውስጥ መውደቅ ሰልጥኛለሁ፤ ሐሳብንም በሠለጠነ መንገድ አስተናግዳለሁ ከሚል ልሂቅ፣ ተራማጅ፣ ለነፃነት ታጋይ ወይም ሌላ ተመሳሳይ ስያሜን ካነገበ አካል የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ሆኖ ከተገኘም የኋላ ቀርነት መገለጫ ብቻ ሆኖ ከሚቀር በስተቀር ሌላ ካባ የሚያጎናጽፍ አይሆንም፡፡

በአሁን ወቅት በአገራችን እየታየ ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ኢሕአዴግ ለዓመታት በላይ በላይ ሲደርታቸው የከረማቸው ችግሮች ውጤቶች እንደሆኑ ባምንም፤ እየጠፋ ላለው የሰው ሕይወትና ንብረት ተጠያቂው ኢሕአዴግ ስለመሆኑ ጽኑ እምነት ቢኖረኝም፣ በአገራችን ለውጥ ለማምጣት የተሻለው መንገድ ግን ይኼ ነው የሚል አቋም የለኝም፡፡ እነዚህ ችግሮች ከኢሕአዴግ አብራክ የተወለዱ ይሁኑ እንጂ የፖለቲካ ባህላችን ማደጎም መሆናቸውን መካድ የለብንም፡፡ በተቃውሞ ጎራ ውስጥ ያለን ሰዎች ጥላቻን በዘራን ቁጥር ስህተትን በስህተት ለማረም ከመድከማችን ውጪ ምንም ጠብ የሚል ነገር አይኖረም፡፡ ከኢሕአዴግ ሰዎች ጋር በመድረክ ተገናኝቶ በሐሳብ ተከራክሮ ተጨባብጦ መለያየት ለጽንፈኛ ሰዎች  የኢሕአዴግ ቡችላ መሆን ከሆነ እነርሱ በሚኖሩባት አሜሪካ የሚያዩትን ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ምን ሊሉት ይሆን? እዚህ ጋ ኢሕአዴግ እንደዚህ ዓይነቱን ሰላማዊ ትግል የማስተናገድ ፍላጎት ወይም ቅንነት አለው እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ሆኖም ኢሕአዴግ ሰላማዊ ትግሉን አዳጋች በሚያደርግባቸው ሁኔታዎች ሁሉ የሚፈጽማቸውን ስህተቶችና የሚያደርሳቸውን ጭቆናዎች ለሕዝብ እያጋለጡ በሒደት ከሕዝቡ ጋር እንዲፋታ ማድረግ ምናልባትም የትጥቅ ትግል ከማድረግ የበለጠ አስተዋይነት፣ ታጋሽነትና አርቆ አሳቢነትን እንደሚጠይቅ ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ የአፍሪካችን ብሎም የኢትዮጵያችን የዴሞክራሲ ዳዴና የምዕራብያውያን የዴሞክራሲ እምርታም ቀዳሚ ሚስጥር ይህ ስለመሆኑ በፊታችን ያፈጠጠ እውነታ ነው፡፡

እናም ሁላችንም በዚህ የንጹኃን ዜጎች ሕይወት እየጠፋ ባለበት ፈታኝ ወቅት ኢሕአዴግን ፊት ለፊት ለመሞገት ለውይይት የተቀመጡትን አቶ ልደቱን ለምን የትግሉ አካል አድርገን ለመውሰድ ተናነቀን የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይኖርብናል፡፡ በጥላቻ መንገድ እየሄዱ ያሉ ወገኖቻችንን በወንድማማችነት ልንተናነጽ ወደምንችልበት ጎዳና ልንመራቸው ይገባል፡፡ ይህን ማድረግ ያለብንም ለአቶ ልደቱ አያሌው ጥብቅና ለመቆም ሳይሆን እንዲህ ዓይነቱን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች የማሸማቀቅ ከፖለቲካው እንዲርቁ ባደረግን ቁጥር የፖለቲካው መድረክ ካለስድብ የማይሞቅ፣ ካለጥላቻ የማይደምቅ፣ ሲብስም ካለመገዳደል የማይሰምር የሚመስላቸውን ሰዎች እያበራከትን መሄዳችን እርግጥ ስለሚሆን ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ ለጊዜው የሞቀንና ስሜታችንን የኮረኮረልን ቢመስለንም፣ የበርካታ ንፁኃን ዜጎችን ሕይወት እንደሚቀጥፍና ዛሬ ጥላቻንና መጠፋፋትን የሚሰብኩ ሰዎችንም ጭምር ይዞ እንደሚጠፋ ታሪክ በሚገባ የሚያስረዳን ይመስለኛል፡፡

(በኤልያስ ፍቅሩ፣ ከአዲስ አበባ)     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...