Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከዲፕሎማቶቻችን ዶላር ይፈለጋል

በኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት ፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ስለመመዝገቡ በአኃዝ ተደግፈው የቀረቡ መረጃዎች ከመንግሥት ብቻ የተሰሙ አይደሉም፡፡ የዕድገቱ መጠን የተባለውን ያህል ሳይሆን ይህንን ያህል ነው በሚል አኃዛዊ ልዩነቶች ካልኖሩ በስተቀር፣ የመንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ውጭ ያሉና የተለያዩ አገሮችን ኢኮኖሚያዊ ጠባይ እየለኩ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቁ ተቋማት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት መስክረዋል፡፡ እንዲያውም ዕድገቱ ፈጣን ስለመሆኑ በሪፖርቶቻቸው ውስጥ አካትተዋል፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ነገም ቀጣይ ስለመሆኑ የመንግሥት እምነት ነው፡፡ በአንፃሩ ለቀጣዩ ዕድገት መሰላል ይሆናሉ የተባሉ አንዳንድ ዕቅዶች ደግሞ የልብ እያደረሱ አለመሆናቸው ሲታይ፣ ዕድገቱ በታሰበው መጠን ልክ ላይሆን ይችላል የሚል ብዥታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡

ለምሳሌ እንደ ሰሞኑ ዓይነት ያልታሰበ ግጭት ሲፈጠር ደግሞ ኢኮኖሚው መንገጫገጩ አይቀርም፡፡ አንዳንድ የወደሙ ወይም ለጊዜውም ቢሆን ሥራቸው የተስተጓጐለባቸው ተቋማት ለታሰበው ዕድገት የራሳቸው ሚና እንደሚኖራቸው ታሳቢ ተደርጐ ነው፡፡ ነገር ግን ባጋጠማቸው ችግር ያስገኛሉ የተባለው ውጤት ሲቀር ይብዛም ይነስም ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን መጫናቸው አይቀርም፡፡ በድምር ሲታይም በአኃዝ የሚቀርበውን ቁጥር መሸራረፋቸው አይቀርም፡፡ ይህንኑ ተከትሎ አገር ሰላም መሆኑን በጥንቃቄ የሚመለከቱ የውጭ ኩባንያዎችም ቢሆኑ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንታቸው ምርጫ በማድረግ የጀመሩትን ጉዞ ለጊዜው ቆም ማድረጋቸውም ሌላው ተፅዕኖ ነው፡፡ አገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገቱ ሲሰላ እንዲህ ዓይነት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ያስገኙልናል ተብሎ በመሆኑ የወደፊቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መጠን ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይታመናል፡፡

ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ዓይነተኛ ሚና ይኖራቸዋል ከሚባሉ ዘርፎች አንዱ የሆነው ቱሪዝም ቢሆንም፣ ከወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ምን ያህል እንደተጐዳ ካሰላንም አጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጠረው ጫና ይታወቃል፡፡  

እንዲህ ያሉ ተፅዕኖዎች ሌሎች ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያሳረፈው ተፅዕኖ ሲደማመር ችግሩ እንዲህ በቀላል የሚታይ አይሆንም፡፡ ስለዚህ ይህንን መንገራገጭ ወደ ቦታው ለመመለስ የሚጠይቀው መስዋዕትነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ኮሽ ባለ ቁጥር ሊታጣ የሚችለውን የውጭ ምንዛሪ በሌላ ለመተካት የሚያስችል አቅም ሊኖር የሚገባ ስለመሆኑም ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ሌላውን ነገር ሁሉ ትተን ለአገራዊ ዕድገቱ ዓይነተኛ መገለጫ ከሆኑ ክንውኖች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ዋነኛ ምንጭ ደግሞ የወጪ ንግድ ነው፡፡ ዛሬም ቡና፣ ቆዳና ሌጦ፣ አበባ እየተባለ ነገም የኢትዮጵያን ዕድገት ለማስቀጠል ከባድ ይሆናል፡፡ አማራጮች መስፋት አለባቸው፡፡ በእርግጥ ምንም እሴት ያልተጨመረባቸውን የወጪ ንግድ ምርቶችን ከመላክ እሴት ታክሎባቸው የሚላኩ ምርቶች እንዲበራከቱ ለማድረግ ውጥን አለ፡፡ ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ወይም የወጪ ንግድን ታሳቢ ያደረጉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ውስጥ ስለመገባቱም ይታወቃል፡፡ ይህንን ከግብ ለማድረስ ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ላይሆን ይችላል፡፡ ከፓርኮቹ ግንባታ ባሻገር ዘላቂ ገበያ ያስፈልጋል፡፡ ያመረቱትን መሸጥ ደግሞ ትልቁ ግብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የዓለምን ገበያ ለማግኘት ጠንካራ የገበያ ሥራ ይፈልጋል፡፡

አሁን ባሉት የወጪ ንግድ ምርቶችን በብዛት በጥራትና ልኮ መገኘት ይችል የነበረውን ያህል ያለመገኘቱ ለምንድነው ሲባል፣ አሁንም አሰልቺ ምክንያቶች የሚደረደሩበት ሆኖ የሚቀጥል ከሆነም የተቀመጠን ግብ ለማሳካት ከባድ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡ ስለዚህ ወጪ ንግዱ እንዲሰፋ ራሱን የቻለ ገበያ አፈላላጊ ተቋም መፈጠር ግድ የሚል ነው፡፡

የእስካሁን የወጪ ንግዱ ማዳረሻ ቦታዎችን ለማስፋት ሲሠራበት የነበረው መንገድ ደካማ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ተቀባዮቻችን ቀድሞ የምናውቃቸው ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የምትልከውን ምርት ሊገዙ የሚችሉ አገሮች ዘመናዊ ንግድ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ምርቶቻችን የሚሸምቱት አገሮች እነዚሁ ብቻ ሆነው እስከ መቼ ይቀጥላሉ? አሁንም ያሉትን አማራጮች ሁሉ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ አንዱ መንገድ ኤምባሲዎቻችን ናቸው፡፡

የአገሪቱ የውጭ ገበያ መዳረሻ አገሮች ምነው ውስን ሆኑ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ሁሌም የማስበው ኤንባሲዎቻችንን ነው፡፡ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ከ100 ያላነሱ ኤምባሲዎች አሉዋት፡፡ እንደኔ እንደኔ የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ለማሳደግ ይህ ትልቅ ዕድል ነው ቢሆንም፣ አዳዲስ ገበያ እንዲፈጠር ለማድረግ የእነዚህ ኤምባሲዎች አስተዋጽኦ የሚጠበቅባቸውን ያህል በተግባር የታየ አይመስልም፡፡

የንግድ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚነግረን ደግሞ ከኢትዮጵያ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚገዙት ወይም ምርታችንን በዶላር የሚለውጡት አገሮች 20 አይሞሉም፡፡ ይህ ደግሞ ኤምባሲዎቻችን የሚገኙባቸው አገሮች ውስጥ ምርቶቻችንን የሚገዙ ደንበኞች ማፍራት ያለመቻላችን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ እንዲያውም ሥልጣን ቢኖረኝ እያንዳንዱን ኤምባሲ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ዕድገት ምን አስተዋጽኦ አደረገ በሚል በግምገማ አፋጥጥ ነበር፡፡ የአምባሳደር ሹመት ለማስቀጠል መሠረታዊ ጉዳዩ በተቀመጠበት አገር ሆኖ ለኢትዮጵያ ገበያ ምን አዲስ ነገር ፈጠረ? ምን አስገኘ? ኢትዮጵያን ምን ያህል ሸጠ? በሚል ምዘና ኃላፊነታቸውን ለመቀጠል አለመቀጠላቸው አንድ መመዘኛ በተደረገ ነበር፡፡ እንዲያው ግን ኤምባሲዎቻችን ቢያንስ በተሾሙበት አገር ሲቆዩ የኢትዮጵያን ቡናና አበባን በማስተዋወቅ ከምን ያህል ኩባንያዎች ጋር ተገናኙ? እኔ አይመስለኝም፤ ቢሆንማ ኖሮ ለውጡን እናይ ነበር፡፡

እውነት እንነጋገር ከተባለ የኤምባሲዎቻችን ከአገር ኢኮኖሚ ጠቀሜታ አንፃር ያስገኙት ውጤት ምንድነው? በእርግጥ ሁሉንም በአንድ መደቆስ ባያስፈልግም፣ ኤምባሲዎቻችን ባሉባቸው አገሮች የአገሪቱን ምርት የሚረከብ ደንበኛ ለማፍራት በተጨባጭ ያደረጉት ጥረት ምንድነው?

መቼም ባሉበት አገር ትንሽም ሀብት ያለው ኩባንያ አይጠፋምና አባብለው ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ብታደርግ ትጠቀማለህ ብለው፣ ጉዳዩን በመከታተል የሠሩ ስንት ኤምባሲዎች ናቸው?

የኢትዮጵያ ባንዲራ የሚውለበለብባቸው ያማሩ ኤንባሲዎቻችን የሚገኙበት አገሮች ውስጥ ያሉት ዜጎች ለእግራቸው መጫሚያ የአገር ውስጥ ጫማዎችን ሳይፈለጉ ቀርተው ነውን? በየትኛውም የዓለም ክፍል ቡና ይጠጣልና የኢትዮጵያ ቡና ከሌሎች የላቀ ስለመሆኑ በመግለጽ የአገሬው ቡና ጠጪ የኢትዮጵያን ቡና እንዲጠጣና የኢትዮጵያን ጫማ እንዲሞክሩ ያደረጉ የኤምባሲዎቻችን የንግድ አታሼዎች አሉ? ካሉ ዕውቅና ሰጥተን ለሌሎች ምሳሌ ቢሆኑ  ምን አለ? ስለዚህ ለወጪ ንግዱን ለማሳደግ ብሎም የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት የኤምባሲዎቻችን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉት አስተዋጽኦ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ከወጪ ንግድ ከተሰማሩ ተቋማትና ገበያ በማፈላለግ የሚታወቁ ባለሙያዎችን በማካተት ገበያ አፈላላጊ ተቋም ቢፈጠርና ኤምባሲዎቻችንም ተግባራቸው ከዚሁ ወሳኝ ጉዳይ ጋር የተቆራኘ ቢሆን የወጪ ንግዱ ገበያ መዳረሻዎች በተስፋፉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢውም ባደገ ነበር፡፡ ዲፕሎማቶቻችን ይህንን ታሪክ ይቀይሩ፡፡ ዋነኛ የሥራቸው መመዘኛቸውም ይኸው ቢሆን ለውጥ አይኖር ይሆን?    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት